ግብርና ለሰው ፍጡር ሁሉ ህልውና ነው። ህልውና ይሆን ዘንድ ግን ሂደቱም ሆነ አሠራሩ የዋዛ አይደለም። ሁላችንም እንደምናውቀው እጅግ ከባድና በገበሬው ላይ የወደቀ ኃላፊነት ነው።
ይህ በአርሶ አደሩ ትከሻ ላይ የወደቀ ኃላፊነት እንደኛ ላሉ አገራት ሁሉ ነገራቸው ሲሆን፤ በተለይም ኢኮኖሚውን ቀጥ አድርጎ የያዘው መሆኑ በራሱ ማስረጃ ነውና ስለ አተገባበሩ ማውራት ተገቢነቱ አጠያያቂ አይሆንም። እርግጥ ነው፣ ይህንን ከባድ ማህበራዊና አገራዊ ኃላፊነትን የተሸከመው ገበሬ የዋዛ አይደለም። የዋዛ አለመሆኑ ማሳያው ደግሞ የዋዛ ያልሆነውን ተግባር የሚያከናውነው የዋዛ ባልሆነ ቴክኒክና ታክቲኮች መሆኑ ነው፤ እሱም በደቦ ሥርዓት።
ካህሳይ ገብረእግዚአብሔር ከ«ባህላዊ ማህበራት» ዐቢይ ምድብ ስር የሚያካትቱት ደቦ – በግብርና ሥራ ጊዜ ተሰባስቦ እርዳታን መለዋወጥ («እገሌ የእኽል አጨዳ ደቦ አለበት» እንደሚባለው ማለት ነው)፤ ብዙ ሰው ተሰብስቦ ለአንድ ሰው የሚሠራበት የኅብረት ሥራ፣ ደቦ የተወጣላቸው (ሥራው በደቦ የሚሠራላቸው) ሰዎች ድግስ እየደገሱ ተሳታፊውን እያበሉ፣ እያጠጡ የሚከናወን ተግባር ነው።
ቃሉ ከኦሮሚኛ የሆነው ደቦ በተለያዩ ተዛማጅ ስያሜዎችም የሚታወቅ ነው፤ ጂጊ፣ ወንፈል … እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። ደቦ «ወንፈል» ማለት ነው። ወንፈል ደግሞ ፍችው «አንድነት የሚታይበት የህብረት ሥራ ማህበር» ማለት መሆኑ ነው በስፋት የሚታወቀው። («ወንፈል»ን መዝገበ ቃላቱ ሲፈታው «ርስ በርሱ አንድ ቀን ላንዱ አንድ ቀን ለሌላው እየ ተወናፈሉ በማኅበር፣ በአንድነት፣ በተራ በተራ መሥራት ወንፈል ይባላል።» በማለት ሲሆን፤ በእንግሊዝኛውም communal labor, agricultural activity conducted by assisting one another በማለት ያስቀምጠዋል።)
ደቦ በአንድና ሁለት የአገራችን ክፍሎች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ስሙና ስያሜው ይለያይ እንጂ በሁሉም የአገራችን ክፍሎች ተግባራዊ ሲደረግ የኖረና እየተደረገም ያለ ማህበረ-ባህላዊ እሴት ነው፤ ይህ ካህሳይ በ«ባህላዊ ክርስቲያናዊ ትውፊት በኢትዮጵያ» መጽሐፋቸው ያረጋገጡት፤ በትግራይ «ወፈራ» መባሉን በማሳያነት የጠቀሱለት በኅብረት የመሥራት ዘዴ ነው። ይህ ማለት፣ ደቦ፣ ጂጊ ወይም ወንፈል በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል በጋራና በመተባበር ሥራ የሚሠራበት ባህላዊ ሥርዓት ነው።
ሰዎች፣ በተለይም በግብርናው ዘርፍ በእርሻ፣ በዘር፣ በአረም፣ በአጨዳና በውቂያ ወቅት የአካባቢው ኅብረተሰብ ጉልበቱን (ከነመሣሪያው) በማዋጣት ደቦ የጠራውን ሰው ይረዳል። ለምሳሌ፣ ለግለሰቡ ገበሬ ረዥም ጊዜ ሊወስድበት የሚችለውን የግብርና ሥራ (ለምሳሌ አጨዳ) በርካታ ሰዎች በአንድ ቀን ያጠናቅቁለታል ማለት ነው። በአንድ ሰው ጉልበት ብቻ ለማቃለል የማይችልን የግብርና ሥራ በተባበረ ክንድና በጣም በአጠረ ጊዜ የማጠናቀቂያ አገር በቀል የአሠራር ሥርዓት ነው።
ግብርና ላይ አተኮርን እንጂ ከእርሻ ሥራ ውጪም ለሌሎች ተግባራት ለምሳሌ ቤት መሥራት፣ ለቀብርና ለሰርግ … ወዘተ ድንኳን ለመደኮንና የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን ደቦ ሊጠራ ይችላል። ይህ በተለይ በአማራ ክልል አካባቢ በስፋት የሚሠራበት አሠራር (የኅብረት ሥራ) ነው።
በደቦ የሚሳተፉ ሰዎች እንደየ አካባቢው ሁኔታ የሚለያዩ ሲሆን፣ አንዱን አካባቢ በደቦ ሥራው የሚሠራለት ሰው ወገኖች (ዘመዶች) ሲሆኑ፣ አብዛኞቹ አካባቢዎች ግን የአካባቢው ሰውና ሙያው ያለው ሁሉ የሚሳተፍበት ተግባር ነው።
ዝቅ ብለን የምንጠቅሰው ምንጫችን እንደሚያመለክተው ደቦ እንደ ዕድርና እንደ ዕቁብ በተወሰኑ ቋሚ አባላት አይመሠረትም፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ወዳጅነትና ቀረቤታ ወይም ዝምድናና አግባብ ያላቸው ሰዎች አንድን በርከት ያለ የጉልበት ኃይል የሚጠይቅ ተግባር ለአንድ የማኅበረሰቡ አባል በጋራ የሚያከናውኑበት ተቋም ነው፡፡ በማኅበረሰብ አባላት መካከል ካለው መጠቃቀም አንፃር ደቦ ልዩ ልዩ መልኮችና አፈጻጸሞች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ ዋና ዋናዎቹ መገለጫዎች፣ ደቦ እንደ ጉልበትና አገልግሎት ልውውጥ እንዲሁም እንደ ማኅበራዊ የጉልበት ድጋፍ አሰጣጥ ሥርዓት የሚኖረው ጠቀሜታዎች ናቸው፡፡ ደቦም ሆነ ወንፈል ወይም ጂጊ በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች እንደ መኖሩ ሁሉ በአማራም የሚዘወተርና በችግር ፈቺነቱ ታምኖበት ለዘመናት ሲሠራበት የቆየ የኅብረት አሠራር ነው።
ከክልሉ በተለያዩ ጊዜ የወጡ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከአማራ ሕዝብ የሥራ እሴቶች መካከል አንዱ ደቦ ነው። አርሶ አደሮች በአንድነት የሚረዳዱበትና የሚደጋገፉበት የመተጋገዝና መረዳዳት ባህል፤ ሥራን በጋራ የማከናወን ሂደት ነው። እንደየ አካባቢው ደቦ፣ ወንፈል፣ ወንበራ፣ ጅጌ እየተባለም ይጠራል። ሥራው በአረም፣ በእርሻ፣ በአጨዳ፣ በውቂያ፣ በቤት ሥራ፣ በእርከን ሥራ . . . ወዘተ የሚከወን ሲሆን፤ በሥራው ጊዜም ቀረርቶ(ሽለላ)፣ ፉከራ፣ የልጃገረዶች ዘፈን ይቀርባል፤ በስነቃል እና ዘፈን ታጅበው የደቦ፣ ወንፈል፣ ወንበራ እና ጂጊ (ጂጌ የሚሉም አሉ) ሥራቸውን ይከውናሉ።
አንድ የቦረና ሳይንት ነዋሪ እንደገለፁት በቦረና ሳይንት አማራ አንድ ጉብል ከታጨለት በኋላ ከሰርጉ በፊት አዝመራ ከደረሰ ባልንጀሮቹን በማሰባሰብ «የአምቻ አጨዳ አስተጫጭዱኝ» በማለት ይዞ ሄዶ የአማቾቹን ማሳ ያሳጭዳል። ሲጨርሱም ወደ ቤት ይጋበዛሉ፤ ይበላል ይጠጣል … ሆታውም ይቀልጣል።
ካህሳይ ገብረእግዚአብሔርም ሆኑ ሌሎች እንደሚስማሙበትና እንዳሰፈሩትም የደቦ አስፈላጊነት፣ ጠቀሜታው … ምርታማነትን (ውጤታማነትን) መጨመር፣ ጊዜን መቆጠብ፣ ማህበራዊ ሕይወትን ማጠናከር፣ የሥራ ላይ ድብርትንና ድካምን ማስወገድ …፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሥራን በወቅቱ ማድረስ ነው። «በወቅቱ …» ሲባል፣ ለምሳሌ ሰብል ሳይሰበሰብ ዝናብ ቢመጣ ሊያበላሸው ስለሚችል ያ ችግር ከመድረሱ በፊት ሰብል እንዲሰበሰብ ማድረግ ማስቻሉ ነው። ይህ ደግሞ ከላይ እንዳልነው፣ በግብርናው ዘርፍ የሞትና ሽረት ጉዳይ ስለሆነ ደቦን እጅጉን ተፈላጊ ያደርገዋል።
አስቀድመን «ደቦ በዘመናዊ አጠራሩ ኅብረት ሥራ ማለት» ነው ብለን ነበር። ኅብረት ሥራ ማለት («ዓለም ፊቷን ወደ ኅብረት ሥራ ማህበራት አዙራለች» በሚል ርእስ ለንባብ የበቃ ጽሑፍ እንደሚያሳየው) ደግሞ፤ የኅብረት ሥራ ማህበራት በጋራ ትብብር ላይ በመመሥረት ያለ ምንም (ጾታ፣ ሃይማኖት …) ሳይለዩ አባሎቻቸውን አንድ ላይ በማቀፍ በዴሞክራሲያዊ መርህ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ሲሆኑ፣ በአንድ በኩል ትርፋማነትን እያራመዱ በሌላ በኩል ደግሞ ሰብአዊነትን የሚያራምድ አደረጃጀት ያላቸው ተቋማት ናቸው።
ማህበራቱ የአባሎቻቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያና ባህላዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚንቀሳቀሱም ጭምር ናቸው። (ይህ በበኩሉ የአገራችንን የኅብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ አዋጅ ቁጥር 985/2009ን ያስታውሰናል።) ከአንድ አመት በፊት ሪፖርተር ጋዜጣ «አገር በቀሉ ደቦ» በሚል ርእስ ስር ባሰፈረው ጽሑፍ «በገጠር የሚዘወተሩና የተለመዱ፣ የተጻፈ ደንብና መመሪያ ሳይኖራቸው በጋራ ስምምነትና በመረዳዳት ላይ የተመሠረቱ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፋይዳ ካላቸው ማኅበራት ወይም ተቋማት አንዱ ደቦ ወይም ወንፈል ነው፡፡ ወንፈል ወይም ደቦ አገር በቀልና ነባር የኅብረት ሥራ ማኅበር ነው፡፡» ማለቱንም እዚህ መጥቀሱ ተገቢ ነው።
እንደ ተመለከትናቸው መረጃዎች ከሆነ የኅብረት ሥራ ማህበራት ሰላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን የሚረዱ ማህበራዊ ድርጅቶችም ናቸው። በመሆኑም የእርሻ የኅብረት ሥራ ማህበራት የኅብረተሰቡን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥና ረሀብን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት የጎላ ድርሻ እንዳላቸው አሁን ዓለም ያመነ ይመስላል። […] የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መወሰድ ካለባቸው እርምጃዎች መካከል በእርሻ የኅብረት ሥራ ማህበራትና በሌሎች የገጠር ተቋማት ላይ ትኩረት በማድረግ የመዋዕለ ንዋይ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያሻም ተመራማሪዎቹ ይመክራሉ። ከዚህ አኳያ ስንመለከተው ደቦም ሆነ ወንፈል ወይም ጂጊ፣ በተለይ ከግብርናው ዘርፍ ውጤታማነትና የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት አኳያ፣ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ማለት ነው።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም (FAO) 23ኛውን የዓለም የምግብ ቀን ሲያከብር መሪ ቃሉን «የእርሻ ኅብረት ሥራ ማህበራት ዓለምን የመመገቢያ ቁልፍ ዘዴዎች» (Agricultural Cooperatives key to feeding the world) የሚለውን ማድረጉም ያለ ምክንያት አይደለምና ደቦ በተለይ ለግብርናው ዘርፍ ወሳኝ ማህበራዊ እሴት ነው ማለት ነው።
ደቦን ወንዶች መሬታቸውን ለማረስ፣ ለመዝራት፣ ቤት ለመሥራት፣ አጥር ለማጠር፣ ሰብል ለማረም …..፤ ሴቶች ጥጥ ለመፍተል፣ ቤት ሲሠራ ውኃ ለመቅዳት፣ የማኅበር፣ የሰንበቴ የሠርግ ድግስ ለመደገስ …. ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ጋር በመሆን ለስኬታማነት ይጠቀሙበታል፡፡
ደቦ እንደ ተቋማት መጠሪያ፣ ማንነት መለያ
ከላይ የተመለከትነው የደቦ ትርጓሜና ፋይዳ በመሠረታዊነት የሚቀመጥ፤ በችግር ፈቺ ሚናውም የሚታይ ሲሆን፤ በሌሎች ዘርፎችም እየገባ ለሌላ ፋይዳ እንደሚውልም ታሳቢ ማድረጉ ተገቢ ነው። በመሆኑም፣ ይህ አምዳችን «አገርኛ» እንደ መሆኑ መጠን አገራዊ የሆኑ ነገሮችን ያበረታታልና ደቦ በሌሎች ዘርፎችም ውስጥ በመግባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ሊያመለክት ይፈልጋል።
ዛሬ ዛሬ በአገራችን በአብዛኛው ለንግድም ሆነ ሌላ የሚሰጡ ስያሜዎች ዲቃላ ቢሆኑም፤ አልፎ አልፎም ቢሆን አገራዊ ስያሜን በመስጠት አገር በቀል ተቋማቱን ፍፁም አገር በቀል የማድረግ ሥራን እየሠሩ ያሉ ወገኖች አሉ። ይህ ደግሞ ሊያስመሰግናቸው የሚገባ ትልቅ ተግባርና እሴትን የማስቀጠል እንቅስቃሴ ነውና እዚህ ሊጠቀሱ የግድ ይሆናል።
መጠሪያቸውን፣ ልክ እንደዚህ ገጽ አምድ «አገርኛ» ያደረጉ ተቋማትም (አገር በቀል የሆኑ) እንደዚሁ ደቦን መለያቸው አድርገውት እንመለከታለን። ደቦን መጠሪያቸው ካደረጉት ተቋማት መካከል፤
«ደቦ» (ከደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ሥራዎች አንዱ)፤ «ደቦ» (የአማርኛ እትም መጽሐፍ በ60 ነባር እና አዳዲስ ጸሐፍት የተጻፈ – ስብስብ)፤ ደቦ ማይክሮ ፋይናንስ ኢንስቲትዩሽን አክስዮን ማኅበር፤ ደቦ ማይክሮ ፋይናንስ፤ ደቦ የእርዳታ ማህበር፤ «ደቦ» (የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮቪድ-19 በሽታ ስርጭትን ለመከላከል የሚያግዝ «ደቦ» የተሰኘ የሰዎች ንክኪ መለያ የአንድሮይድ ስልክ መተግበሪያ ይፋ ማድረጉን አስታወቀ። የሚለውን ዜና ያስታውሷል።)፤ ደቦ (ውቤ በረሀ አካባቢ ያለ ምግብ ቤት)፤ ደቦ መተግበርያ (የኢንተርኔት አፕ)፤ ደቦ ኢንጂነሪግን (Debo Engineering) (በኢትዮጵያ የእፅዋትን በሽታ በተንቀሳቃሽ ስልክ በመጠቀም መለየት የሚያስችል መተግበሪያ፣ በ4 ቋንቋዎች እና በድምጽ እገዛ የሠራ አገር በቀል ድርጅት) እና የመሳሰሉት ይገኙበታል።
ከዚህ የምንረዳው የ«ደቦ» ማህበራዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ … ፋይዳዎች ቀላል አለመሆናቸውን ብቻ ሳይሆን ህብረት፣ አንድነት፣ መተጋገዝ፣ መተባበር … ምን ያህል አስፈላጊ እንደ ሆነ ነው። (በነገራችን ላይ እንዲህ ዓይነት፣ ቱባ ባህላዊ እሴትን የሚያስተዋውቅ፣ ለትውልድ የሚያስተላልፍ፣ ወደ ፊት የሚያስቀጥል … አስተሳሰብን መሠረት አድርገው ለድርጅታቸው፣ ለአካባቢዎቻቸውም ይሁን ተቋማት ስያሜን የሚሰጡ አካላትን ልናደንቅ፣ ልናመሰግናቸውም ይገባልና ሌሎችም የእነሱምን አርአያ ልንከተል ይገባል የሚል ማሳሰብያን ጣል ብናደርግ ከአምዳችን አኳያ ተገቢ ነው እንላለን።
ደቦ/ጂጊን ከሃይማኖት አኳያ
ከላይ ከተቋማት ስያሜ አኳያ እንደተመለከትነው ሁሉ፣ ከሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች አኳያም የሚኖረው ፋይዳና ሚና ቀላል እንደማይሆን መገመት ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ምክንያታችን የሚከተለው ነው።
ደቦ ማለት «ጂጊ» ነው ካልን ጂጊን በሃይማኖትም ተገቢውን ስፍራ ይዞ የምናገኘው ሲሆን፤ ለዚህም በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ያለውን ቁርአን አቀራር ሥርዓት፣ ማለትም «ጂጊ ቁርአን»ን (ቁርአን በተናጠል ሕብረት) መመልከት ይቻላል። (ለምሳሌ የበድሬ ሐሪማን «ሕብረት ቁርአን» መንዙማ ከዩቲዩብ በማውረድ መመልከት ይቻላል።)
(እዚህ ላይ የአንድ «ቃል»፣ ከዛም በዘለለ መልኩ የአንድ «ጽንሰ ሀሳብ» (እዚህ ጋ «ጂጊ»ን እንደ ቃል ሳይሆን እንደ ጽንሰ ሀሳብ መጠቀማችንን ልብ ይሏል) በተለያዩ አውዶችና ሰብአዊ አገልግሎቶች ውስጥ ሲገኝ የእነዛን ተቋማት የጋራ ማንነት የሚያመለክት መሆኑን በቅንፍ አስቀምጦ፣ ለሌላ ጥናት አመቻችቶ ማለፍ ተገቢ በመሆኑ አድርገነዋል።)
በአጠቃላይ፣ ደቦ እንደ አንድ ዘመናዊ የኅብረት ሥራ ማህበር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት (ግብርናው) ነውና ልንንከባከበው ይገባል። ከቱባ ማህበረ ባህላዊ እሴቶቻችን፣ ትውፊቶቻችን … አንዱ ነውና ሳይበረዝና ሳይከለስ ለትውልድ ሊተላለፍ ይገባል። የስነልሳን ምሁሩ ፕሮፌሰር ባዬ ይማም «የእኛ የኢትዮጵያውያን አንድነት መገለጫዎች ሦስት ሲሆኑ እነሱም ስነ ልሳናዊ፣ ባህላዊና ስነልቦናዊ ናቸው» እንዳሉት ሁሉ፣ «ደቦ»ንና ሌሎችንም በተለያዩ ዘርፎች (ከላይ በሃይማኖትና ተቋማት ዘርፎች እንዳየነው ማለት ነው) በመመልከት የአንድነታችንን መሠረት ማጥበቅ ያስፈልጋል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2015