‹‹ሊነጋ ሲል ይጨላልማል›› የምትል አንድ አባባል አለች። እውነት ነው ንጋት ላይ ይጨልማል። ኧረ ደረቅ ጨለማ ብቻም አይደል ! ብርድም አለ፤ ከፍተኛ ቅዝቃዜ። ሆኖም ግን ብዙ ሰዓት አይዘልቅም። ጨለማው እየገፈፈ፣ ብርዱም እየለቀቀ ፣ ጤዛውም እየረገፈ ይሄዳል። ውርጩ ቀለል እያለ የአእዋፋት ጫጫታ አየሩን ይሞላል፤ የወፎቹ ዝማሬ ንጋትን ያበስራል። በመጋረጃው ጀርባ በመስኮቱ ጭላንጭል ሲያይ ያንቀላፋው ሰውነት ይነቃቃል። ምክንያቱ ብርሀኑን ማየቱ ነዋ ።
ያኔ ታዲያ በእንቅልፍ ጭፍግግ ያለው ሰውነትም እየተፍታታ፣ ፊትም ይፈካል። በቀዝቃዛው ሰማይ ላይ በምሥራቁ ክፍል ፍንጥቅ ብላ የወጣችውን የፀሐይ ጮራ ላየ ተስፋው ይለመልማል።… በንጋት ውስጥ ብዙ ነገር አለ። ብዙ ሥራ ይሠራል መልካም… መልካም…። ብርሀናማው አየር ተስፋ ብቻ ሳይሆን ብዙ ራዕይ ያሰንቃል። ለዓላማ በዓላማ ያሠራል። ምቹ አየር ካለ፣ ምቹ ስፍራ ከተገኘ፣ ተስፋ ያደረገ ሁሉ ተስፋው አብቦና አፍርቶ ያየዋል። ለሁሉም ግን የሚያስፈልገው ቀን ነው ፤ ብርሀኑ ከዳር ዳር የሚያበራ ቀን፤ ቀኑን ቆጥሮ ጠንከር ብሎ ተስፋውን ወደ ፍሬ መለወጥ የሚችል ቆራጥና ቆፍጣና።
ዛሬ በትግራይ ያለው ሁኔታ ይህን ይመስላል። የትግራይ ሕዝብ ንጋት ላይ ነው። የደበዘዘው ተስፋ አሁን መነቃቃት ይጀምራል፤ ተስፋ የቆረጠው ሕዝብ የተስፋ ጭላንጭል ማየትና ማለም ይቀጥላል። የነገዋን ፀሐይ ለማየት የደመነውን ፊቱን በሀሴት ለመቀየር ጊዜው ተቃርቧል። ጭለማው ዛሬ ላይ ወደ ሰሜን እያዘቀዘቀ ይገኛል። የጭለማው ጊዜ በብርሀን ሊተካ ወጋገን ላይ ቆሟል።
የትግራይ ሕዝብ ጨለማ ውስጥ የገባው ዛሬ አይደለም። የትግራይ ሕዝብ ድቅድቅ ጨለማ የገባው አሸባሪው ትህነግ የሰሜን እዝ ሰራዊት ላይ ጥቃት የፈጸመ ዕለት ነው። ብርድ አይንካህ ወገኔ፤ ዝናብና ፀሐይ አይፈራረቅብህ ወንድሜ ብሎ ቤቱን ሲሠራ፣ አይራብህ አይጥማህ ብቻህን አትድከም ብሎ አብሮት ማሳ ለማሳ ሲያጭድና ሲከምር፤ አንበጣ ሲያባርር፤ የውሀ ጉድጓድ ሲቆፍር ኖሮ የተከዳ ዕለት ነው።
የድህነት ማባረሪያው፣ የክፋት ማሰሪያው ትምህርት ቤት ነው ብሎ በገዛ ገንዘቡ ትምህርት ቤት ሲገነባለት የኖረው የመከላከያ ሰራዊት ላይ አሸባሪው ቡድን ቃታ የጎተተ ቀን ነው የትግራይ ሕዝብ ጨለማ የገባው። በላዩ ላይ ጭካኔ በሞላ ሁኔታ ሲኖትራክ የተነዳበት ጊዜ ነው። ልብሱን አስወልቆ ራቁትን በረሀ ለበረሀ የበተነው ጊዜ፤ የአገሩ ሰንደቅ ያረፈበትን የመከላከያ ሰራዊት ልብስ ሜዳ ለሜዳ የጎተተ ጊዜ ነው። ያኔ ነው የኢትዮጵያን ክብር አዋረድኩ ብሎ ክብሩን ያወረደው። ያኔ… ያኔ ነው አሸባሪው ትህነግ የትግራይን ሕዝብ ጨለማ ውስጥ ያስገባው። የመከላከያ ሰራዊትን እጅ አመድ አፋሽ ፤ ልፋቱን ከንቱ ያደረገበት ውለታ ቢሱ ትህነግ የከዳው ዕለት ነው የትግራይን ሕዝብ ጨለማ ውስጥ የጣለው።
አሸባሪው ትህነግ እኮ የትግራይን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የመላውን ሕዝብ ሰላም ያደፈረሰው፣አንድነቱን ለማናጋት የሞከረው፤ ኢኮኖሚውን ያንገዳገደው ዛሬ አይደለም። አገር አፈርሳለሁ ብሎ ሲደሰኩር፤ የአማራና የአፋር ሕዝብን ሲወርና ሲጨፈጭፍ ነው። በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ሲፈጽም፣ በጅምላ መቃብር ሲያዳፍን፤ ከሕፃን እስከ አዛውንት ሲደፍርና የሀገርን ባህልና ታሪክ ሲያጎድፍ፤ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ቆሞ የባንዳነት ተግባሩን ሲከውን ነው። ተላላኪነቱን ተቀብሎ አገር የከዳ ጊዜ ነው።
የትግራይን ሕዝብ ከሌላው እህት ወንድም ወገኑ ሊነጥለው ፤ ‹‹የትግራይ መንግሥት አቋቁማለሁ፤ ምርጫ በራሳችን፤ በሕገ መንግሥቱ አንተዳደርም›› ብሎ ጡንቻ እንለካካ ያለጊዜ ነው። ያኔ ነው ጨለማ ውስጥ የከተተው የትግራይን ሕዝብ።
‹‹አማራ ጠላትህ ነው››፤ ‹‹ሂሳብ እናወራርዳለን›› ብሎ ሲደሰኩር ተጋብቶ፤ ተዋልዶ በፍቅር የኖረውን ሕዝብ እርስ በእርሱ ሲያባላው ከርሟል። ግን እኮ በዚህ ሰበካው ሕዝብን ከሕዝብ አባላ እንጂ አሁን አሁን ደግሞ ትርክቱን ወደ መዋጥ እየገባም ነበር። አማራ ወንድም ነው፤ አማራ እህት ናት፤ ከአንተ ከአንቺ ጸብ የለንም እያለ ሊሰብከም ሞክሯል።‹‹የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ›› የምትል አንድ አባባል አለች አይደል የትህነግ ቅጥፈት፣ ፕሮፓጋንዳ እና ትርክት ያቺን አባባል እንዳስታውሳት አስታውሼም እንድከትባት ገፋፋኝ።
የትግራይ ሕዝብ በመሠረተ ልማቶቹ እንዳይጠቀም ኤሌክትሪክ እንዳያገኝ፣ የገንዘብ ዝውውር እንዳይኖረው፣ የመገናኛ አውታሮች እንዳይሠሩ መሠረተ ልማቶችን ሲበጣጥሳቸው፣ ሲንድና ሲያፈርሳቸው፤ ሲዘርፍና ሲያወድማቸው ያኔ ነው የትግራይ ሕዝብ ጨለማ የገባው። በጠላቱ በትህነግ ሴራ ሲሠራበት። እንዲራብና እንዲጠማ ያለዳኛ ሲፈረድበት፤ ያኔ ነው የትግራይ ሕዝብ በድቅድቁ ጨለማ የወደቀው።
አሸባሪው ትህነግ በወሬው ‹‹የቆምኩት ለአንተ ነው ፤ ነፃነትህን ላስከብር ነው›› የሚለውን የትግራይ ሕዝብን ያሰቃየውና አይበድሉ በደል ሲበድለው የቆየው አሁን ብቻ አይደለም። በ1977 ዓ.ም የትግል ወቅት በሚለው ሰዓትም የትግራይ ሕዝብ በረሀብና ችግር ሲፈተን ትህነግ ለሕዝቡ የቀረበን ሰብአዊ እርዳታ እየቸበቸበ የመሣሪያ መግዣ ሲያውለው ነበር።
ይህን የትግራይ ሕዝብ ጥንቅቅ አድርጎ ያውቀዋል። በወቅቱ ታጋይ የነበሩት በየአደባባዩ መስክረዋል። ዓለም አቀፍ ተቋማት ማረጋገጣቸውን አሳውቀዋል። ይሄ ከስህተቱ የማይማር የሰዎች ችግር ደስታው፤ የሰው ኀዘን ዳንሱ የሆነ ቡድን ግን አሁንም እየሠራ ያለው ዳግም ጥፋት ነው። አሁንም ከዚሁ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቱ ሳይማር ድጋሚ ይሄንኑ በተግባር አሳይቷል።
ለትግራይ ሕዝብ የመጣን ሰብአዊ እርዳታና መድኃኒት ለሕዝቡ ሳይሆን ለወታደራዊ አገልግሎት ሲያውል በአደባባይ ታይቷል። መጋዘን እየዘረፈ የሕፃናትን አልሚ ምግብ ለወታደሩ ቀለብ አድርጎታል። እርዳታ ለሕዝቡ እንዳይዳረስ ሰብአዊ እርዳታ ይዘው የገቡ መኪኖችን የጦር መሣሪያ መጓጓዣ ሲያደርግና ነዳጅ ሲዘርፍ ዓለምአቀፉ ተቋማትና መገናኛ ብዙኃን ጭምር አጋልጠውታል።
ቅጥፈትና ስርቆት መለያው የሆነው አሸባሪው ቡድን ይሄን ብቻ ግን አይደለም በትግራይ ሕዝብ ላይ የፈጸመው በደል፤ ገና ነገ የሚሰሙ ዛሬ የተደበቁ ግፎች ሁሉ እንደሚኖሩ ይታሰባል። የታሰረው እና የታፈነው ትግራይዋይ ሲነጋለት በደሉን ፀሐይ ያሞቀዋል። ይሄ እንደሚሆን እንጠብቃለን። ምክንያቱም አመላካች ነገሮች ተሰደው የመጡት፤ ክደውና ተማርከው የገቡት ሁሉ እየተናገሩና እየመሰከሩ ያሉት ይሄንኑ ኢ-ሰብአዊ ባህሪውን ነው። ለውትድርና በግድ የመለመለውን ያለ ዕድሜው ለጥይት የዳረገው ሕፃንና ወጣት ሰውነቱ ባይጠና አእምሮው አልቀበል ሲለው ወደኋላው ሲመለስ የሚጠይቀው የትህነግ ጥይት ነው።
ወደፊት ተማገድ እንጂ ወደኋላ እንዳትዞር የሁልጊዜም ማስፈራሪያ ነው። ይህን ያልፈጸመ ለሌሎች መቀጣጫ መሆኑ አይቀሬ ነው። እናም ሕፃን ወጣቱ ሁሉ ከፊት ከኋላ ጥይት ሆኖ ተቀባዩ እናቶች ያለ ጧሪና ቀባሪ እንዲቀሩ ተገደዋል። ያ ሁሉ የረገፈ ወጣት የት ገባ ብሎ ይደሰኩር ይሆን? መቼም እንደጥቂቶቹ ልጆች የእነሱም አውሮፓና አሜሪካ ለትምህርት ሄደው እንደማይሆን ልጆቻቸው ለጥይት ሲሳይ የሆኑባቸው እናቶች ልቡና ያውቀዋል። እነሱ ያለቀሱት ፤ ያረረና የተኮማተረ አንጀታቸውን በመቀነት ያጠበቁት ያኔ ነው፤ ያኔ ትህነግ ከስልጣን ተባሮ መቀሌ ሲከትም፤ላወጣው ሕገ መንግሥት አልገዛም ብሎ ሲፎክር ነው። ቀጥሎ ለስልጣኔ ማስመለሻ ልጆቻችሁን ለጥይት ገብሩ እንደሚላቸው ከኖረው ባህሪው ያውቁታል። አውቀው ችለውታል፣ መቼ ይሆን ከጫንቃችን መውረጃው ነበር ህልማቸው።
አሁንም ግን የትግራይ ሕዝብ ስቃይ አልበቃም፤ ከችግሩ ተላቆ ገና ነፃ አልወጣም። አሁንም በትህነግ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ተታሎ እንዲሁም ተገዶ ልጁን ዓላማ ለሌለው ጦርነት የዳረገው ብዙ ሰው ነው። በመማሪያ ዕድሜያቸው ለማያምኑበት ጦርነት ተገደው የገቡ በሞት የጥይት እራት የሆኑ ሕፃናትና ወጣቶች ብዙ ናቸው። እናት አንጀቷን አስራ ተቸግራና ተሰቃይታ ያሳደገቻቸውን ሴት ወንድ ሳትል ልጆቿን አሳልፋ የጥይት ማብረጃ፤ ለአፈር ለግሳለች። ዛሬ ልጆቼ ያሳልፉልኛል፤ ይደግፉኛል የሚል ተስፋ የላትም። ይሄ ሁሉ በትህነግ የማያባራ ሴራ የተፈጸመ ግፍ ነው።
በችግርና በጦርነት ከሚሰቃየውና ከሚሞተው የትግራይ ሕዝብ ጎን ለጎን ሕፃናት ትምህርት እንዳይማሩ ሆነዋል። ሮጠውና ቦርቀው፤ ፊደል በመጨበጫ እድሜያቸው ጉልበታቸውን ታቅፈው ቆዝመው እንዲቀመጡ ተገደዋል። ‹‹ነፃ እናወጣችኋለን›› ፕሮፓጋንዳ የዕለት ምግባቸው ሆኖ ቆይቷል። የትግራይ ሕዝብ አስከፊ የሆኑ በደሎች ሁሉ ቀምሷል። ተስፋቸው ጨለማ፣ ኑሮው ስቃይ ሆኖ ከርሟል፤ አሁን ግን ይሄ አስከፊ ዘመን የሚቋጭበት ዳር ድንበር ላይ ደርሷል።
‹‹ነፃ አወጣሀለሁ›› የሚለውን ነፃ ያልወጣ ቡድን በቃህ የሚሉበት ወቅት ላይ ደርሰዋል። ለራሱ ከሴራ ፖለቲካ ነፃ ያልወጣ ነፃ አውጪ በአንድ ቤተሰብ የተሰባሰበ ነፃ አውጪ ነፃ እንዲያወጣው የትግራይን ሕዝብ የሚያሰቃይ የስም ነፃ አውጪ መሆኑን አሁን መረዳት የሚቻልበት ወቅት ላይ ደርሷል። ነፃ የሚያወጣው የአንድ ቤተሰብ አባላትን በስልጣን ላይ እያስመረቁ በፌስቡክ ምርቃት የሚጠሩትን አካል መሆኑን በትክክል መገንዘብ ችሏል።
አሁን ነፃ የሚያወጣው የአራት ኪሎ ስልጣኑን ለማስመለስ አማልዱኝ፣ እርዱኝና ድረሱልኝ የሚለውን አካል መሆኑን አውቋል። እስካሁንም ሆነ ወደፊት ለሕዝቡ እንዳልቆመ ከድርጊቱ ለማወቅ ችሏል። አሁን የትግራይ ሕዝብ መካሪ አይሻውም። ችግር መክሮታል። አታላይ አያታልለውም፤ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የት እንዳደረሰው የተነገረና የተሞላው ሁሉ ከአገሩና ከወገኑ የሚያለያየው እንጂ የሚያፋቅረው እንዳልሆነ በተጨባጭ አረጋግጧል። ከኢትዮጵያዊ ወገኑ ተጋብቶና ተዋልዶ የኖረ ወንድሙ መሆኑን አሁንም በስደቱ ወቅት አይቶታል። ማነህ አንተ ማነሽ ብሎ ፊቱን ያዞረና የተበቀለው የለም፤ ምክንያቱም ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ጸብ የለውም። ይልቅስ ወገኔ ብሎ አቅፎታል፤ ቆርሶ አጉርሶታል። ጉሮሮውን በውሀ አርጥቦ ማረፊያ ሆኖታል። ኢትዮጵያዊ ይሄ ነውና።
ጥቂቶች ለስልጣናቸው፣ የሰረቁት ሀብት እንዳይወረስ የትግራይ ሕዝብ እንደ ትናንቱ ሁሉ ሊደልሉት ይከጅላሉ። ዛሬ የሚሞኝና በሀሰት ልምጭ የሚነዳ ሕዝብ አይደለም። ቆሞ ያስባል፤ አስቦ ይራመዳል። ተራምዶም መብቱን ያስከብራል። ከትህነግ የኢ- ሰብአዊ ድርጊት ራሱን ነፃ ያወጣል። ለዚህ ደግሞ አሁን ጊዜው ደርሷል። ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል እሚባልበት ደረጃ ላይ ይገኛል። የወፎቹን ድምጽ ሰምቶ ለማጣጣም፤ አጣጥሞ ብርሀኑን ሊያይ በብርሀኑም ሊመላለስ ጊዜው ደርሷል።
ሊነጋ ሲል እንደሚንጫጩት አእዋፋት ሁሉ ለትግራይ ሕዝብም ሊነጋለት ሲል ጫጫታው በዝቷል። ከዚህም ከዚያም ጩኸቱ ደርቷል። ሆኖም እውነቱን ከሀሰት፤ ከሀዲውን ከእውነተኛው መለየት የሚችለው መከራውን የቀመሰው ሕዝብ ነው። በቆየበት የመከራ ጊዜ ይሄንን ለመለየት ይችላል። አስከፊ የጨለማ ዓመታት በቅቶት በብርሀማው ዘመን እንዲተካ አሁንም የትግራይ ሕዝብ ከሀሰተኛው ፕሮፓጋንዳ መባነን አለበት። አሁን የንጋቱ ደውል ተደውሏል፤ የወፎቹን ጫጫታ ማድመጥ ትቶ የተኛውም ይንቃ። በብርሀኑን ይመላለስ። አበቃን !።
አዶኒስ (ከሲኤምሲ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2015