የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት /የምድርም የአየርም / ለአገር ክብር የሚዋደቅ፣ ለሉአላዊነት የሚዘምት ሰራዊት ነው። ራሱን መስዋዕት በማድረግ ኢትዮጵያ ጸንታ እንድትቆም ያደረገ፣ አሁንም ቢሆን ለሕገ መንግሥት እንዲሁም ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ መከበር እየተዋደቀ የሚገኝ ነው።
በሕዝባዊነቱ የማይታማ፤ በተሰማራባቸው የግዳጅ ቀጣናዎች ጀብዱዎችን በመፈጸም ታሪክ የሚዘክረው ሰራዊት ነው። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ረሃብ እና ጥማት ሳይበግረው ረጅም ኪሎሜትሮችን በእግሩ እየተጓዘ የኢትዮጵያን የጽናት ታሪክ በወርቃማ ቀለም ያስመዘገበ፤ እያስመዘገበ ያለ ሰራዊት ነው ።
ለውጡን ተከትሎ ‹‹ሰራዊት አገር እንጂ ብሔር የለውም›› በሚል መርህ በጠንካራ ሕዝባዊነት ላይ በመመስረት የተሰጠውን እና የሚሰጠውን ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮ እየተወጣ የሚገኝ፤ ኢትዮጵያዊ መልክ ያለው ሙያውን የሚያከብር ጠንካራ ሰራዊት ነው። ለዚህ ደግሞ ከፍ ያለ ምስጋናና እውቅና ሊቸረው ይገባል።
አሸባሪው እና ከሀዲው ትህነግ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ዘግናኝ ጥቃት ፈጥኖ እራሱን አደራጅቶ በመቀልበስ አገርንና ሕዝብን ከጥፋት መታደግ የቻለ፤ በዚህም የአገርና ሕዝብ ኩራትነቱን በተጨባጭ ያረጋገጠ ጀግና ሰራዊት ነው።
የአስተሳሰብ መሠረቱ የሆነው ሕዝባዊነቱን በየትኛውም ሁኔታ ለድርድር የማያስቀምጥ፤ ይህንን ባህሪውን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶችን መሻገር በሚያስችል ስብእና የገነባ፤ በዚህም የማይታማ ልበ ሰፊ፤ በከፍተኛ ዲሲፕሊን የተገነባ ሰራዊት ነው።
ስለ አገሩ ሉአላዊነትና ከዚህ ለሚመነጨው ክብሩ ጥልቅ ዋጋ ከሚሰጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ የወጣው፣ አገር ችግር ላይ ወድቃለች ሲባል ጨርቄን ማቅን ሳይል ለአገሩ ክብር እና ሉዓላዊነት በጀግንነት የሚዋደቅ የኢትዮጵያዊነት ምልክት! የአገር መለያ አርማ ነው። ለዚህ ሰራዊት አባላት ከፍያለ ክብር ይገባቸዋል። ሞተው ኢትዮጵያን ስላጸኑ፤ ደማቸውን አፍስሰው ሕዝብን ነፃ ስላወጡ ለእነዚህ ጀግኖች እጅ እንነሳለን!።
ሰራዊቱ ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዜ አሸባሪው ትህነግ በአገርና በሕዝብ ላይ የከፈታቸውን የእብሪት ጦርነቶች በመመከት ፤ በታላቅ ጀግንነት የቡድኑን ከንቱ ህልም ወደ ቅዥት በመለወጥ የአገር መመኪያነቱን በተግባር አስመስክሯል።
ኢትዮጵያን እንደ ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ የመን ለመበታተን በውስጥ በውጭ ኃይሎችና በውስጥ ባንዳዎች የተሸረቡ አደገኛ ሴራዎችን በብዙ መስዋእትነት በመቀልበስ የሕገመንግሥቱ ዘብ መሆኑን በመስዋእትነቱ አስመስክሯል።
ዛሬም የትግራይን ሕዝብ ከአሸባሪ ትህነግ የግፍ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት በታላቅ ተጋድሎ ላይ ይገኛል። ይህ ከሕዝባዊነቱ የሚመነጨው ነፃ የማውጣት መስዋእትነት ጉዞ በቀጣይ በትግራይ ሕዝብ ዘንድ ሊፈጥር የሚችለው እፎይታ በታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ሊያገኝ እንደሚችል ይታመናል። የዓባይ ግድብን ጨምሮ ሌሎች የተገነቡና በግንባታ ላይ የሚገኙ ታላላቅ ፕሮጀክቶችንም ከማንኛውም ጥቃት በአስተማማኝ መልኩ በመጠበቅ ልማት እንዲረጋገጥ ያስቻለ ሰራዊት ነው።
በውስጥና በውጭ የነበረውን ከፍተኛ ጫና በመመከት ኢትዮጵያን እንደ አገር ማስቀጠል ችሏል። የሰራዊቱ የግዳጅ አፈጻጸሙ፤ ምኞቱ፣ ፍላጎቱ፣ ግቡም አገርን የማስቀጠል ዓላማ ያነገበ በዚህም ሕዝባዊነቱን ማስመስከር የቻለ ነው።
ሰራዊቱ በወታደራዊ ዲሲፕሊን በእውቀት ክህሎትና ቴክኖሎጂ እራሱን በተሻለ መልኩ አደራጅቶ የትኛውንም ዓይነት ጠላት ሊመክት የሚችል ቁመና ተላብሷል፣ በጠንካራ ሥነ ልቦ የተገነባም በመሆኑ የግዳጅ አፈጻተሙ ከትናንት ዛሬ፤ ከዛሬ ነገ አስተማማኝ እየሆነ በሚሄድበት የጥንካሬ ጎዳና ላይ ነው።
ሰራዊቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቅበት ጉዳይ አንዱ በስነ ምግባሩ ነው። ቀደም ባለው ዘመን በኮሪያ እና ኮንጎ በቅርቡም በሩዋንዳ፣ በሱዳን፣ በሶማሊያ—ወዘተ የተሰጠውን የሰላም ማስከበር ግዳጅ ባግባቡ የተወጣ፣ በዚህም መልካም ስም ያተረፈ ነው። በሕዝብ ፊትም ሰንደቅ ዓላማ ይዞ ስለአገሩ ዘብ ለመቆም ቃል የገባ ለአገሩ፣ ለሕዝቡ እንዲሁም ለሕገ መንግሥቱ ተጠሪ ሆኖ እየሠራ ያለ ነው። በቃሉ ተፈትኖ ፀንቶ መቆም የቻለ ሰራዊት ነው።
ሰራዊቱ ሕዝባዊም ነው። ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ ጤና ተቋም እና ትምህርት ቤቶችን በየአካባቢው የሚገነባ። በእርሻ ወቅትም አርሶ አደሩን የሚያግዝ፣ በዚህም ሕዝባዊነቱን በተጨባጭ ያረጋገጠና እያረጋገጠ ያለ ሰራዊት ነው። ለዚህ ሰራዊት እና ለአባላቱ ከፍያለ ክብር ይገባቸዋል።
የትኛውንም የአገርና የሕዝብ ጠላት ሊመክት የሚችል ቁመና የተላበሰ እና ኢትዮጵያውያንን ያኮራ ሰራዊት ነው። ሕዝብን ነን የማውጣት ተልዕኮውን በድል እየተወጣ የሚገኝ፣ ራሱ እየሞተ ወገኑን ያዳነ፣ አገር እንድትቀጥል እያደረገ የሚገኝ ነው። ለዚህ ጀግና ሰራዊት ክብር ሰጥተናል፣ እጅ ነስተናል።
ሜሎዲ ከኳስ ሜዳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2015