የሰው ልጅ ወደዚህች ምድር ሲመጣ በተሰጠው ዕድሜና ጸጋ የራሱን ሂደት ተሻግሮ እንደሚያልፍ ዕሙን ነው ። በሕጻንነት ዕድሜው በወላጆቹ ዕቅፍ ሆኖ ከእሳትና ውሀው ይጠበቃል ። መሰናክልን ከዕንቅፋቶች አልፎም በታማኝ እጆች ስር እንደሆነ የማንነቱን ነፍስ ያውቃል።
ሕጻንነቱን ተሻግሮ ራሱን በወግ መለየት ሲጀምር ደግሞ ቀጣዩን የወጣትነት ዕድሜ ሊይዝ መንደርደሩ አይቀሬ ነው ። ይህ ዕድሜ እሳትና ውሀን በእኩል የሚያውቅበት፣ የቀጣይ ሕይወቱን ሚዛን የሚያስተካክልበት የሩጫ ዘመኑ ይሆናል።
በዚህ የወጣትነት እርከኑ ስለነገው የመኖር ህልሙን ይቀርፃል፣ ሰርቶ ደክሞ የማደርን ጥቅም ይለያል፣ ትዳር መስርቶ ቤተሰብ የሚመራበትን እውነት በተግባር ይከውናል። ይህን ዕድሜ በወጉ ለተጠቀሙት ደግሞ ከትናንትና ይበደሩበታል፣ የዛሬውን ይኖሩበታል፤ ስለነገም ጥብቅ መሰረት ይጥሉበታል።
ወጣትነት አልፎ ጉልምስና ሲጀምር ይህ ሰው በአካል ብቻ ሳይሆን በዕውቀት ጭምር ይበስላል። ከወጣትነቱ ያተረፈውን ዕድሜና ተሞክሮ አጋምዶ የተሻለ ዓለምን ሊፈጥር ቀጥ ባለው መስመር ሊያልፍ ይተጋል። ልጅነቱን ከወጣትነት ያጣመረበት ልምዱ በዚህ ዕድሜው በአብዛኛው ውጤቱን መልካም ያደርገዋል።
የጉልምስና ዘመን ተጠናቆ ቀጣዩ ምዕራፍ ሲተካ የሰው ልጅ አካል በዕድሜ ሸክም ይደክማል ፣ ዓይኖች በወጉ ሊያዩ ፣ ጆሮዎች በቅጡ ሊያዳምጡ ይሳናቸዋል፣ አዕምሮ እንደትናንቱ ላይሆን ከፍጥነቱ ይገደባል። እርጅና ወገብን እንዲሁም እግርን ይዞ አቅም ጉልበትን ይፈትናል።
የትናንቱ ብርታት ውስጥ አካልን ሲክድ ጤንነት በእጅጉ ይፈተናል ። ይህ ጊዜ በሕይወት ዑደት ጊዜን ጠብቆ ከማንነት ሲደርስ የዕድሜ ጠገብነት፣ የአረጋውያንነት ጸጋ ከነችግሩ ይወረሳል፣ ከነውበት ሞገሱ ከድካም ፣ ከጤና ማጣት ጥግ ያደርሳል። በዚህ ጊዜ ተመልካች ዓይኖች ፣ አጋዥና ደጋፊ እጆች ሊኖሩ ግድ ነው።
ብዙዎች ደጋግመን እንደምንለው የአረጋዊነት፣ የእርጅና ዘመን ዕድሜ ጸጋና በረከት ነው። በዕድሜ ማምሻ ላይ ቆሞ መገኘት ያለፉት ዓመታት የሕይወት አሻራዎች ማድመቅና ማስመሰከር ይሆናል። ይህን እውነት ጨምሮ በአረጋዊነት ዕድሜ በርካታ እሴቶችን ማትረፍ፣ ማትረፍረፍ ይቻላል።
የአረጋዊነት ዕድሜ ጸጋና በረከት የመሆኑን ያህል ለበርካቶች መከራና ችግር ሆኖ የሚያልፍበት አጋጣሚም ይስተዋላል። አፍሪካን በመሰሉ አህጉራት በዚህ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አረጋውያን ያለጧሪና ደጋፊ ተንገላተው የማለፋቸው እውነት አዲስ አይደለም። ወደሀገራችን መለስ ስንል ጥቂት የማይባሉ የዕድሜ ባለጸጎች በመደገፊያ፣ በመጦሪያ ዕድሜያቸው ለችግር ተዳርገው የሰው እጅ ሲናፍቁ ማስተዋል ብርቅ አይደለም።
ጥቂት የማይባሉ አረጋውያን ረጅሙን ዘመን በሥራና ቤተሰብን በማስተዳደር ድካም አልፈው አካላቸው ሲደክም፣ ጤናቸው ሲጎድል አስታዋሽ፣ አልባሽ አጉራሽ አጥተው ለእንግልት ይዳረጋሉ። ትናንት አገር ወገናቸውን ያገለገሉበት አቅምና ጉልበት ከአጠገባቸው ሲርቅ ውለታቸውን የሚያስብ ፈጥኖ ደራሽ አጋዥ ከጥጋቸው አይገኝም። አብዛኞቹ ከዕድሜያቸው ጫፍ ሆነው የልጅ ልጆቻውን እንዲያሳድጉ ይገደዳሉ። ይህኔ እፎይታ የሚሻው ትካሻቸው ዳግም በሸክም ጎብጦ፣ በዕድሜና ሥራ ብዛት የጠወለገ ውስጠቸው ዘወትር ያለዕረፍት ይናውዛል።
በዚህ አጋጣሚ አብዛኞቹ አረጋውያን የመኖራቸውን፣ የእስትንፋቸውን መርዘም ፈጽሞ አይሹትም። የዕለት ሞታቸውን ይመኛሉ። በክብር የተራመዱትን ያለፈውን መንገድ ትዝታ አድርገው የቆሙበትን ሕይወት ይረግማሉ። ከዕድሜ መግፋት ጎን የሚከሰት ጤና ማጣት ለእነሱ የዘወትር ህመም ነውና የሕይወት ትግላቸውን ያብሰዋል። በዚህ ወቅት አረጋውያኑ አስታወሽ ወገን፣ ጧሪ ደጋፊ ከሌላቸው ሕይወታቸው የጨለማ ጉዞ ይሆናል።
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ በሀገራችን ከስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ አረጋውያን ይገኛሉ። ከእነዚህ አረጋውያን መካከልም በርካቶቹ ለማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ ናቸው ። ከአረጋውያኑ መካከል ጥቂት የማይባሉት የማህበራዊ ዋስትና መድህን የሌላቸውና ጧሪና ተንከባካቢ ያጡ ናቸውም። እነዚህ ወገኖች ካለባቸው የኢኮኖሚ ችግር ሳቢያ የህክምና ደጃፍን የማያውቁ በመሆናቸው ጤናቸው በህመም የተፈነ ይሆናል።
በዘመነ ኮሮና አረጋውያን በበሽታና በርሀብ ሲፈተኑ ቆይተዋል። በርካቶች በመገለልና ራስን በመጠበቅ መስመር ላይ በነበሩበት አጋጣሚም ጧሪና ደጋፊ አጥተዋል። አስታዋሽም አልነበራቸውም። በአሁኑ ጊዜም በሀገራችን በተከሰተው የኑሮ ውድነት የተነሳ ብዘዎቹ በእጅጉ እየተጎዱ ነው። ኑሯቸውን የሚመጥን ገቢና ኢኮኖሚያቸውን የሚደግፍ አቅም በማጣታቸው በርካቶች ሕይወታቸውን የሚገፉት የሌሎችን እጅ በማየት ሆኗል።
የብዙዎቹ አረጋውያን ሕይወት ከእጅ ወደአፍ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጥቂት የማይባሉት እጃቸውን ለልመና ዘርግተው የሰዎችን ምንዳ ይናፍቃሉ። ለእነዚህ ምስኪኖች እምብዛም የበረቱ ክንዶች፣ የነቁ ዓይኖች ያለመኖራቸው እውነትም በርካቶችን ከቤት ወደ ጎዳና እንዲወጡ አስገድዷል።
የአረጋውያን ዘረፈ ብዙ ችግሮች ዛሬ ላይ ከተለያዩ ስፍራዎች እንዲውሉ አድርጓል። የአብዛኞቹ ሕይወት በአንዳንድ በጎ ፈቃደኛ ወገኖች መስራችነት በተቋቋሙ ማዕከላት ጥላ ስር የተወሰነ ነው። እነዚህ ማዕከላት አረጋውያኑን በስነልቦና፣ በአካልና በኢኮኖሚ ጭምር ያግዛሉ፤ ጫናዎቻቸውንም ለማቅለል ይጥራሉ።
በእነዚህ ድርጅቶች ስር የሚገኙ የዕድሜ ባለጸጎች ፊት ለፊት ከሚታየው ገጽታቸው ባሻገር ያልተነበበው በጎ ማንነታቸው እንደተሸፈነ በሞት ይሸኛሉ። እነዚህ አረጋውያን ጥቂት የማይባሉት የእድሜ ዘመናቸውን ለሀገርና ወገናቸው ያዋሉ፣ ዕውቀትና ችሎታቸውን ለነበሩበት ትውልድ ያካፈሉ፣ድንቅ ዜጎች ናቸው።
እነኝህ ታላላቅ ሰዎች በዕድሜያቸው ማምሻ እርጅና ከህመም በፈተናቸው ጊዜ ትናንቱን የሀገር ባለውለታነታቸው ይዘነጋል። በመከበሪያና መመስገኛ ዕድሜያቸውም ተመጦ እንደሚጣል ሸንኮራ ይሆናሉ። አብዛኞቻችን እነሱን በታላቅነታቸው ከማክበር ይልቅ ፈጽሞ እንተዋቸዋለን። የህብረተሰቡ አንዱ አካል መሆናቸውን ረስተን ትኩረታችን በራሳችን ኑሮና ሕይወት ላይ ብቻ ይሆናል። የትውልድ ቅብብሎሽን ዕውን የሚያደርጉ አረጋውያን ክብርና ሞገስ እንደሚያሻቸው ቢታመንም ትኩረት የመነፈጉ እውነት የጉዳዩን ባለቤቶች ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።
በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ስፍራዎች የተከፈቱ የምገባ ማዕከላት በልተው ለማያድሩ በርካታ ወገኖች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። የማዕከላቱ መከፈት በተለይ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አቅመ ደካማ አረጋውያን ተስፋን አጭሯል።
በየዓመቱ በሀገራችን አረጋውያንን ምክንያት በማደረግ የምስጋና መርሀግብር ሲካሄድ ቆይቷል። በየዓመቱ በተለያዩ መሪ ቃሎች በሚከበረው የአረጋውያን ቀንም የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶች በማድረስ ትኩረት ሁሉ ለሀገር ባለውለታዎቹ አረጋውያን እንዲሆን ጥረት ተደርጓል።
ዘንድሮ በጥቅምት ወር የመጀመሪያው ሳምንት የተከበረው 31ኛው የአረጋውያን ቀንም ‹‹ የአረጋውያን ኢትዮጵያዊነት አሻራ፣ ለትውልድ አደራ›› የሚል መልዕክትን አንግቧል። ዕለቱን በማክበር መርሀግብሩ ላይ የአረጋውያንን እግር የማጠብ ስነስርዓት የተካሄደ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተው በዕለቱ ባለውለታ ለሆኑ አረጋውያን ምስጋና ተችሯል። እኛም እንዲህ እንላለን። ‹‹ አክብሮትና ምስጋና ሁሉ ለአረጋውያን ይሁን›› ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2015