የተለያዩ ጥናቶችን ስናገላብጥ ለአየር ንብረት ለውጥ መዛባት ሰው ሰራሽ ምክንያቶች በርካታ ሆነው እናገኛቸዋለን። ከሁሉም የከፋው ግን የደን ጭፍጨፋው ጉዳይ ነው። እ.ኤ.አ በ2003 በተደረገ የአለም ባንክ ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ ከጠቅላላ የኃይል ፍጆታችን ውስጥ ኤሌትሪክ 1 ከመቶ፤ ነዳጅ (ማለትም ቤንዚል፤ ናፍታ፤ ቡታጋዝ) 7 ከመቶ፤ እንጨትና የመሳሰሉት 92 ከመቶውን ይሸፍናሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ባደረገው ጥናት መሠረት ኢትዮጵያ ከዓለም በከፍተኛ የከሠል ምርት ከሚታወቁ ሶስት ሀገሮች አንዱዋ ስትሆን ቀዳሚዎቹ ሁለቱ ብራዚልና ናይጄሪያ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ከሚመረተው የእንጨት ከሠል ምርት የ8 በመቶ ድርሻ ስትይዝ፤ ብራዚል 11 ከመቶ ናይጄሪያ ደግሞ 8 ከመቶ ያመርታሉ፡፡ በዚሁ መረጃ መሠረት እ.ኤ.አ ከ1993-2002 ባሉት 10 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ከ32 ሚሊዮን ቶን በላይ ከሠል እንደተመረተ ተመልክቷል:: ይህም በዓመት 3.2 ሚሊዮን ቶን መሆኑ ነው:: ይህን ወደ ተጨፈጨፉት ዛፎች መንዝሮ ለሚያስብ ሰው ምን እየተደረገ እንደሆነ በሚገባ ይረዳል።
በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተሰራ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ጉዳዩ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህን የምንለውም “አዲስ አበባ ዛፍ እየነቀለች ፎቅ መትከሉን በዚሁ ከቀጠለችበት የዛሬ 50 አመት የምትተነፍሰው አየር የላትም” የሚለውን የጥናት ግኝት ይዘን ነው።
ይህም ሆኖ በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ተከትሎ ችግሩን ለመቋቋም በተቻለ አቅም ሁሉ እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙት አገራት መካከል ኢትዮጵያ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። በአገሪቱ ካሉ መንግስታዊ ተቋማት ባሻገር ሌሎች፤ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጀምሮ እስከ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪ ግለሰቦች ድረስ በጉዳዩ ዙሪያ በከፍተኛ ደረጃ ሲንቀሳቀሱ ይታያል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዘርፉ በመሰማራትና ከፍተኛ ስራዎችን በመስራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ከወዲሁ ለመቀነስ እየተረባረቡ ያሉ ባለ ድርሻ አካላት ያሉ ሲሆን ከነዚህም መካከል የእምነት ተቋማት ይገኙበታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በ1964 ዓ.ም ያቋቋመችውና በርካታ አገራዊ ስራዎችን እያከናውነ የሚገኘው ተራድኦ ኮሚሽን ተጠቃሽ ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ላለፉት 47 አመታት በምግብ ዋስትና፣ በመልሶ መቋቋም፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በጤና፣ በንፁህ ውሀ አቅርቦት፣ በስደተኞችና ስደት ተመላሾች እና ሌሎች በርካታ ተግባራትን ሲያከናውንና ማህበራዊ ኃለፊነትን ሲወጣ የቆየ፤ በተለይ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በቤተ-ክርስቲያን ደን ልማት (Church forests) እና የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች ላይ በሰፊው አቅዶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ተግባር ምክንያትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በኃላፊነት እንዲንቀሳቀሱ ግንዛቤ የማስጨበጥና ደኖችን የመንከባከብ ተግባር እንዲያከናውኑ መደረጉና ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ከኮሚሽኑ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው የመንግስትና አጋዥ አካላት ጋር በመሆን በሚያካሂዳቸው ቅንጅታዊ ተግባራትም በ19 አቢያተ ቤተክርስቲያናት እና ገዳማት የሚገኙ ጥብቅ ደኖችን በመንከባከብና የስነ-ምህዳር ጤናማነት እንዲጠበቅ በመስራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ለዚህም የኖርዌይ መንግስት፣ በአዲስ አበባ የኖርዌይ ኢምባሲ፣ የኖርዌይ ቤተ-ክርስቲያን ተራድኦ (NCA)፣ የኖርዌይ አለም አቀፍ የአየር ንብረት እና ደኖች ትብብር (NICFI)፣ የጀርመን መንግስት እና ሌሎችም የቅርብ አጋሮቹ መሆናቸውን ከኮሚሽኑ የወጣው ሰነድ ያመለክታል። በተለይ ከኖርዌይ መንግስት ጋር ኖቬምበር 16 ቀን 2018 በተደረገው ለሶስት ተከታታይ ዓመታት (2018 – 2021) ዓመታት ደኖችን የማልማት ስምምነት መሰረት የተሰራውና እየተሰራ ያለው ደን የማልማት ተግባር ቀላል ሆኖ አልተገኘም።
መጋቢት 26 ቀን 2011 ዓ.ም ኮሚሽኑ ከኖርዌይ መንግስት ጋር በመተባበር ባዘጋጀውና በኖርዌይ አምባሳደር የሚመራ ልኡክ፣ በኖርዌይ አለም አቀፍ የአየር ንብረት እና ደኖች ትብብር ኃላፊ የሚመራ የባለሙያዎች ቡድን፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙበት፤ ከአዲስ አበባ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው መናገሻ መድሀኒ አለም እና ማሪያም ጥብቅ ደን (ወይም “መናገሻ ሱባ ደን”) ጉብኝት በተከናወነበት ወቅት መገንዘብ እንደተቻለው ኮሚሽኑ በከፍተኛ ደረጃ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል።
ለመናገሻ ጥብቅ ደን ጎብኚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር ዶክተር አግደው ረዴ እንደተናገሩት ጉዳዩ አለምን እያሳሰበ ያለ ከመሆኑ አኳያ ከፍተኛ ርብርብን የሚጠይቅ እንደመሆኑ ሁሉም አካላት ችግሩን ለመቅረፍ መረባረብ አለበት። ከተራድኦ ኮሚሽኑ ጎን የቆሙና ለዚህ ደን ልማት አስፈላጊውን የእውቀትና የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉም ሊመሰገኑ ይገባል።
የኖርዌይ አምባሳደር ሚስ ሜሬቴ ሉንዴሞ ባደረጉት ንግግራቸው እንደገለፁት ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ይህም የሁለቱ አገራት ታሪካዊና መልካም ግንኙነት ውጤት ነው።
የኖርዌይ አለም አቀፍ የአየር ንብረት እና ደኖች ስራ አስኪያጅ ሚስተር አንድሪያስም ከአምባሳደሯ ሀሳብ ጋር የሚስማሙ ሲሆን “በውብ ተፈጥሮነቷ የታደለችን ኢትዮጵያ በዚህ መልኩ [እንደ የመናገሻ ደን አያያዝ ማለታቸው ነው] መያዝ፣ መጠበቅ፣ ማልማት፣ መልሶ እንዲያገግም ማድረግ እና የተፈጥሮ አየር መዛባትን መቋቋም የሁሉም ኃላፊነት መሆን ይገባዋል። ሁሉም የእምነት ተቋማትም ይህን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል” ሲሉም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ለመቋቋም መደረግ ስላለበት ጉዳይ አሳስበዋል።
ተራድኦ ኮሚሽኑ 109 ሚሊዮን 790ሺህ 92 ብር በጀትን በመመደብ 19 ቤተክርስቲያናትና ገዳማት የሚገኙበትን አካባቢ ደን በማልማት ላይ ሲሆን በዚህም 103ሺህ 363 ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል። ከነዚህ አንዱ በሆነው መናገሻ ጥብቅ ደንም በተለያየ ደረጃ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት መኖሩን እራሳቸው ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት የ45 አመቱ ጎልማሳ መሪ ጌታ ማንደፍሮ ሲሳይ “የደኑ ጥቅም ብዙ ነው። እኛም በችግኝ ተከላ እየተሳተፍንና እየተጠቀምን ነው። የተራድኦ ኮሚሽኑ የደን አያያዝ በጣም ጥሩ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው የመጣው። ሌላው ጥቅሙ እርካታ ነው፤ ሌላው ጋ ድርቅና ረሀብ፣ የዝናብ እጥረት ሲባል እኛን ይህ አያውቀንም። ሁል ጊዜ ዝናብ አለ።” በማለት ሽቅብ ጥቅጥቅ ወዳለውና 2906 ሜትር ከፍታ ላይ ወደተገማሸረው ደን በፈገግታ እየተመለከቱ የደኑን ማህበራዊ፣ ስነ- ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ነግረውናል። ያሉትም ምንም ሳይዛነፍ እውነት ሆኖም ተመልከተነዋል። መሪ ጌታ ከኛ ውስን ጥያቄ አንፃር ይህን ብቻ ይበሉ እንጂ ስለ ደኑና ፋይዳው ሲያወጉን ቢውሉና ሲያወጉን ቢያድሩ የሚጠግቡ አይመስሉም።
መሪ ጌታ ማንደፍሮ ሲሳይ ያስተላለፉትን ጠንከር ያለ መልዕክት ግን ሳይጠቅሱ ማለፍ አይቻልም። መልእክታቸውም “ዛፍ ህይወት ነው፤ ዛፍ አይቆረጥም፤ በየቦታው፣ በያገሩ ያለ ሰው ሁሉ ይህንን አውቆ ዛፍ ከመቁረጥ መቆጠብ አለበት።” የሚል መሆኑን ስንጠቅስ የመናገሻ ጥብቅ ደንን እንደ አይኑ ብሌን የሚጠብቀው የአካባቢውን ህብረተሰብ የሚወክል ሆኖ በማግኘታችንም ጭምር ነው።
እማ ሆይ ወለተ ስላሴ ወልደ ሚካኤል ይባላሉ። በገዳሙ ከአስር አመት በላይ ቆይተዋል። ስሜታቸውን፣ ከደኑ ጋር ያላቸውን መንፈሳዊና ስነልቦናዊ ግንኙነት፤ የተፈጥሮን ውብ ስጦታና ፀጋ እንዲህ ሲሉ ነበር የገለፁልን።
“ወደ እዚህ ከመምጣቴ በፊት ይህን የመሰለ ፅድት ያለ፣ ያማረ፣ ጫካ አይቼ አላውቅም። የትም ቢሄዱ መልሶ ነው ፍቅሩ የሚያመጣው። እዚህ ደርሰው የሄዱ ሁሉ ተመልሰው ሳይመጡ አይቀሩም። ለመንፈስም፣ ለጤናም . . . በጣም ጥሩ ነው። የታመመ ሁሉ ይፈውሳል፣ የዛፎቹ ቁመና፣ አሰላለፍ፣ ንፅህናው፣ ከህመም ሁሉ ያድናል። ንፁህ አየሩ ለጤና ተስማሚ በመሆኑ ህመም የሚባል የለም። ሁሉም ቦታ፣ ሁሉም አካባቢ እንደዚህ አይነት ያማረ ጫካ ቢኖረን በጣም ደስ ይላል።”
በመጨረሻም የአየር ንብረት ዝበት የአለማችን ቁልፉ ችግር እየሆነ ከመጣ ቆይቷል። ችግሩን ለመቅረፍም አለም አቀፍ ርብርብ ማስፈለጉም ከበቂ በላይ ተብሏል። በመሆኑም ልክ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሁሉ፤ ሌሎች የእምነትም ሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የበኩላቸውን ኃላፊነት ቢወጡ የአካባቢ ጥበቃው ጉዳይ ወደ ነበረበተ የማይመለስበት ምንም ምክንያት አይኖርምና ቢታሰብበት መልካም ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 /2011
ግርማ መንግሥቴ