የአራዳ ቋንቋ የሚጠቀሙ ወጣቶች አብዝተው “ኧረ ላሽ ላሽ” ሲሉ ይሰማል።ያልተመቻቸው አልያም ሲነገር ያልወደዱትን ጉዳይ ይቅርብኝ ለማለት ሲፈልጉ የሚጠቀሙት ነው።እኔም በመንገዴ ላይ በገጠመኝ ጉዳይ “ኧረ ላሽ” ማለት አማረኝ፡፡
ትክክለኛ ባልሆነ ጉዳይ ላይ አቋም ይዘን ስንሞግት፤ በተሳሳተ መንገድ እየተጓዝን “የእኔ ነው ፍፁም ልክ፤ ያንተ ወይም ያንቺ ግን ፍፁም ስህተት ነው” ማለታችን አልበዛም? የእኔ ነኝ ልክ ፍፁም አባዜያችን የሚላቀቀን መቼ ይሆን! በዚህ መንገድ የሚጓዝ ስንቱን ታዘብነው? እኛስ በመንገዱ ተመላልሰን በስንቱ ትዝብት ውስጥ ወድቀን ይሆን?
እውነታውን አብጠርጥራችሁ የምታውቁትን ነገር፣ ግን ይህ እውነት አልያም ትክክል የሆነ ጉዳይ በሌሎች ስለ ጉዳዩ በማያውቁ አልያም የጉዳዩን እውነታ በቅጡ ባልተረዱ ሰዎች በተሳሳተ መልኩ ሲገልፅ ገጥሟችሁ ያውቃል? “እንዴታ በደንብ እንጂ!” ትሉኝ ይሆናል።ምክንያቱም ዛሬ ላይ የምንታዘበው ጉዳይ በዝቷል።አላፊ አግዳሚው ከትክክለኝነት ይልቅ መሳሳቱ በበዛበት ዛሬ ላይ ቆመን ይህ አዲስ ሊሆንብን አይችልም።ሰው እንዴት እውነት ያልሆነን ነገር እውነት ነው ብሎ ተከራክሮ ለማሳመን ይሟገታል?
እውቀታችን ውስን፣ የምናካልለውም በጣም ጥቂቱን ቦታ ሆኖ ሳለ ሁሉን አዋቂ ነኝ ብሎ መጀነን በእውነቱ ለትዝብት ይዳርጋል።ሰው ሁሉን ሊያውቅና ሁሉም ነገር ላይ እውቀት ሊኖረው ፈፅሞ አይችልም።አንተ በሰዎች ጤና ጉዳይ ላይ እስፔሻሊስት ብትሆን እቤትህ ያለ ቧንቧ ቢፈነዳ አልያም ቢበላሽ ቧንቧ ሰሪው ጋር ለመደወል ስልክህን ማውጣትህ አይቀርም፡፡
አንቺ የጠራ የሂሳብ እውቀት ቢኖርሽ አንድ ቀን በስራሽ የሆነ እንከን ተፈጥሮ የሚያስጠይቅሽ ጉዳይ ቢፈጠር የህግ እውቀት ያለው ሰው ማማከርሽ አይቀርም።እናም አንዱ ጋር ያለው ሌላው ጋር ይጎላል፤ ሌላኛው ጋር የጎደለው ደግሞ አንተ ወይም አንቺ ጋር ተሟልቶ ይገኛል።ስለዚህም ምሉዑነት ያለው ሰው ፈፅሞ ሊኖር አይችልም፡፡
ጉዳዮችን ሁሉ የምንረዳበት አልያም የምናይበት መንገድ ሁሌም ጥሩ ሊሆን አይችልም። አብዛኛውን ጊዜ እኛ እውነት የሚመስለንና፤ ሀቅ ነው ብለን የምንከራከርበት ጉዳይ በትክክለኛ ቁመናው ትክክል ላይሆን ይችላል።ታዲያ እኛ እውነት ነው ብለን በጉዳዩ ላይ ማመናችን ሳይሆን ስህተቱ፤ ያንን የተሳሳትንበትን ጉዳይ ትክክለኝነቱ መለየት አለመቻላችን አልያም ደግሞ ትክክለኛ ማስረጃ ላይ ተመርኩዘን አለመቀበላችን ነው።
ከዚህ በላይ ስህተት ደግሞ በእኛ አተያይ ትክክል ነው ወይም አይደለም ያልነው ጉዳይ ላይ በይነን ሽንጣችን ገትረን “በፍፁም! ይሄ ነው እውነትና ትክክለኛው መንገድ” ብለን ለሌሎች ለማስረዳት መሞከራችን ነው።እንዴት እርግጠኛ ያልሆንበት ጉዳይ ለሌሎች ለማብራራትና ለመግለፅ ተዳፈርን?
በዚሁ ሳምንት የገጠመኝና ለዚሁ መነሻ ሀሳቤ ማሳያ የሚሆነኝን አንድ ትዝብቴን ላንሳ።ከስራ መልስ ወደቤት እየሄድኩኝ ነው፤ ጉዞዬ ደግሞ የፐብሊክ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ባዘጋጀው የመንግስት ሰራተኞችን ጠዋትና ማታ በሚያመላልሰው ሰርቪስ ውስጥ።በራሴ ጉዳይ ጭልጥ ብዬ በሀሳብ ከሄድኩበት አንድ ከፍ ያለ ድምፅ ወደነበርኩበት መለሰኝ።ከተቀመጥኩበት ወንበር ፊት ለፊት ባለ መቀመጫ ላይ ድምጿን ከፍ አድርጋ የምታወራ ወጣት ሴት ንግግር ባይፈልጉም ትኩረትን ይስባል፡፡
በእርግጥ የልጅቷ ጮክ ብሎ ማውራት እዚያ ሰርቪስ ውስጥ የተለመደ ነው።ነገር ግን ልጅቷ አብዛኛውን ጊዜ የምታነሳቸውና የምትሰጣቸው አስተያየቶች የተቃኑ አይደሉም ብዬ ወደመደምደም ስለደረስኩ አብዝቼ አልሰማትም።መጀመሪያ አካባቢ ሀሳቦቿ ሁሉ የምታየውን ነገር ሁሉ ትችት ስታበዛ ትክክል ብትሆንስ ብዬ በእሷ መንገድ ለማየትም የሞከርኩበት ጊዜም ነበር።ነገር ግን ትክክል ያልሆነ ትክክለኛ ነኝ ባይ መሆኗን ስረዳ ተውኩት።
አንዳንዴ ልጅቷ የምታነሳው ሀሳብ ተገቢ አለመሆኑንና ምክንያታዊ ትሆን ዘንድ ልሞግታት እፈልግና መልሼ እተወዋለሁ።ምን አልባት ሰው ያነሳው ሀሳብ ትክክልም ባይሆን ሲቃወሙት አይወድም አይደል! እኔም ሀሳቧን በመቃረኔ ቅሬታ እንዳይፈጠርባት ሰግቼ ዝም ብዬ ደጋግሜ አልፌያታለሁ፡፡
ዛሬ ግን ማለፍ ከበደኝ።ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች አንስታ ተችታና አጣጥላ አልፋ ሶስተኛውን ስትጀምር በሶስተኛው ጉዳይ ላይ የራሴን ሀሳብ ለመሰንዘር ተዘጋጀሁ።ልጅቱ እያነሳች የነበረውና እየተቸችው የነበረው የዘንድሮ 12 ክፍል ተፈታኞች የአፈታተን ሁኔታ ላይ ነበር።ትለዋለች፤ እኛም እንሰማለን።ተማሪዎቹን ሆን ብለው ለመጣል አስበው ነው፤ እንዴት ከተማረበት ትምህርት ቤት ተነጥሎ፣ ስልክ እንዳይጠቀም ተከልክሎና ከፍተኛ ቁጥጥር ተደርጎበት ይፈተናል ተማሪው? ከስር ጀምሮ አይቆጣጠሩም ነበር? አሁን ከዚህ ፈተና ወድቆ የት እንዲደርስ ነው፤ አጨናንቀው የሚፈትኗቸው…. ትላለች።
ልጅቷ ቀጥላለች፤ ምንም ተቀባይነት የሌለው የፈተና ስርዓት ነው።የምታወራው ድምፅዋን ከፍ አድርጋና ሀሳቧንም ድምድም አድርጋ ነው የምታወራው።ተማሪውን ማጨናነቃቸው ልክ አይደለም በሚል ልክ ያልሆነ ምልከታዋን አከታትላ ትገልፃለች።በተለይ አጠገቧ የተቀመጠ ወጣት ‹‹አዎ! አዎ›› እያለ ማገዙ ደግሞ እኔ ሀሳብ እንድሰጥ ገፋፋኝ፡፡
እኔም ሀሳቤን መስጠት ጀመርኩ። ነገር በምሳሌ ቢሆን ይገባልና አንድ ምሳሌ አንስቼ ማውራት ጀመርኩ።እህት ሁለት ታናናሽ ወንድሞች ይኑሩሽና እነዚህ ታናናሽ ወንድሞችሽ የዘንድሮ ተፈታኝ ነበሩ እንበል።አይበለውና እናትሽ ደግሞ ቤት ታመው ከተኙ አመታት አልፏቸዋል።ወንድሞችሽ ተምረው ሐኪም ሆነው እናትሽን እንዲያክሙልሽ ፈለግሽ እንበል፤ ነገር ግን አንዱ ጎበዝ ሌላኛው ደግሞ ሰነፍ ነው። እንደ አጋጣሚ ሁለቱም የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ናቸው ።የትኛው እንዲያልፍና ትምህርቱን በጥሩ ውጤት ተከታትሎ ጨርሶ እናትሽ እንዲያክማቸው ትፈልጊያለሽ? ብዬ ጠየኳት።መልስዋ ቀላል ነበር። “እንዴ ጎበዙ ነዋ ምን ይጠየቃል” ነበር፡፡
አየሽ እህቴ! አሁን ኢትዮጵያም እያደረገች ያለችው መሰል የሆነ በትክክልና በተገቢው መንገድ የሚጓዝ የነገ በሽታዋንም በጠራ እውቀትና ትክክለኛ ውሳኔ የሚያክማትን በመለየት ላይ ናት።አንቺ ጋር ጥሩ እንዲያድግ ፈልገሽ ወደ አገር ሲሰፋና አገር መልካም የሆነ እርምጃ ስትወስድ ስለምን ቅር ትሰኛለሽ፤ ተማሪዎቹ በትክክል ተለይተውና በተጣራ መልኩ ቢያልፉ አገር ከመጠቀሟ ውጪ ምን ይፈጠራል! ብየ ጥያቄም አስተያየትም ሰነዘርኩ።
ልጅቷ ሙግቷን አላቋረጠችም።ደጋግማ የምትለው አይ ልክ አይደለም የሚለውን ቃል ነው።ብዙ አወራን፤ ነገር ግን እኔ መውረጃዬ ደርሶ ነበርና ከዚያ በላይ ቀጥዬ ላሳምናት አልቻልኩም።በእርግጥ ልጅቷም ልክ አይደለም እንጂ ልክ ነው፤ የምትለው አንዲትም ጉዳይ ያለ አልመስል እስኪል ድረስ ተቺ ናት።
አንዳንዴ በየመንገዱ የምንታዘባቸውን ጉዳዮች በተለያየ መነፅር እንመለከታቸው ይሆናል።ነገር ግን እውነት ላይ ያልተመሰረተና መሰረተ ቢስ የሆነ ምክንያት ይዞ እኔ ልክ ነኝ ማለት ያስተዛዝባል።ተጨባጭ ያልሆነ መረጃ ወደ እውነት የማያቀርብ ምክንያት ማቅረብ ግን ደስ አይልም፡፡እንዲህ አይነቱን ነው “ላሽ ላሽ” ማለት የሚገባው።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16 / 2015