አዛውንቱ በየቢሮ መንከራተት እንዳሰለቻቸው የፊታቸው የድካም ገጽታ ይናገራል። በድካም የዛለው ጉልበታቸው ይንቀጠቀጣል። የአይናቸው ብሌን ደብዝዞ ደም ለብሷል። አይኖቻቸው እምባ እንዳያፈሱ የድካም ዓይናር ገድቧቸዋል። ብዙ ተንከራተው መፍትሔ ስላጡ ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በመምጣት ለዓመታት ሲንከራተቱ መኖራቸውን ሕዝብ እንዲያውቅላቸው አስበው መገኘታቸውን በመግለፅ ተበደልኩ ያሉትን እንዲህ ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የአቤቱታው ፍሬ ነገር
አቶ ገበየሁ ወልደሰንበት አሁን ስማቸውን በፍርድ ቤት ቀይረው አቶ ጉራቻ ሰንበቶ ቆሪቻ ተብለዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ውሃ ክፍል ተብሎ ይጠራ በነበረው ተቋም፤ በመቀጠል በቀድሞ አጠራር በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አገልግለዋል። ከዚያም ከ1987 ዓ.ም እስከ 1994 ዓ.ም ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ አገልግሎት የሰጡ ቢሆንም፤ ተገቢውን የጡረታ አበል ሳያገኙ 11 ዓመታትን እንዳሳለፉ ይገልፃሉ።
በ1994 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅቱ በዞን 4 ፋይናንስ ቢሮ በቋሚ የመንግሥት ሠራተኝነት ሲያገለግሉ አንድ ደብዳቤ ደረሳቸው። ደብዳቤው በግንቦት 2 ቀን 1994 ዓ.ም የተፃፈ ሲሆን፤ ‹‹በጡረታ ልትሰናበት በመሆኑ የመንግሥት ንብረት አስረክብ፤ ያልተጠቀምክበትን የዓመት ዕረፍት ተጠቀም::›› የሚል ነበር።
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ ይህ ከሥራቸው በጡረታ እንዲገለሉ የሚያመላክተው ደብዳቤ ጊዜውን የጠበቀ አልነበረም። ይህ ድርጊት የተፈፀመባቸው በወቅቱ ከነበረው የመስሪያ ቤቱ አስተዳደር ጋር አለመግባባት በመፈጠሩ እንጂ ዕድሜያቸው ደርሶ፤ ወይም ‹‹ጡረታ መውጣት እፈልጋለሁ›› ብለው በመጠየቃቸው አልነበረም። ስለዚህ የጡረታ መውጫ ደብዳቤ ስለተሰጣቸው ተቃወሙ።
ይህን ተከትሎ የጡረታ ጊዜዎ በመድረሱ ያልተጠቀሙበትን የዓመት ፍቃድ እንዲጠቀሙ እና ሥራዎትን እንዲያስረክቡ በሚል በድጋሚ ተጠየቁ። እርሳቸው በበኩላቸው የጡረታ መውጫ ጊዜያቸው እንዳልደረሰ የተቀጠሩበት ዘመንን በመግለጽ ተከራከሩ። አቶ ጉራቻ ባቀረቡት ሰነድ ላይ እንደተመላከተው በተቋሙ ቅጥር ሲያካሂዱ በሚያዝያ 11 ቀን 1968 ዓ.ም በሞሉት የሕይወት ታሪክ ፎርም መሠረት ግንቦት 30 ቀን 1994 ዓ.ም የጡረታ መውጫ ጊዜያቸው መሆኑን በመጥቀስ ‹‹ ጡረታ መውጣት አለብህ›› በማለት ደጋግሞ አሳሰባቸው።
አቶ ጉራቻ ግን በጡረታ ከሥራ መገለል በሚለው ሃሳብ ላይ በፍፁም አልተስማሙም። ተቋሙ በበኩሉ ‹‹ጡረታ መውጣት ግዴታዎት ነው›› ብሎ ወደ ቢሮ እንዳይገቡ ከለከለ። በወቅቱ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዞን 4 ፋይናንስ ጽሕፈት ቤት በጽሑፍ አቤቱታ አቀረቡ፡፡
ለዞን 4 ፋይናንስ ጽሕፈት ቤት የቀረበው አቤቱታ
‹‹የተወለድኩት ሰኔ 16 ቀን 1940 ዓ.ም መሆኑን ለረዥም ጊዜ በማህደሬ ተያይዟል። ይህ በመሆኑም ጡረታ እንድወጣ የተሰጠኝ ደብዳቤ ሆን ተብሎ እኔን የግል አመልካችን ለመበደል ታስቦ የተደረገ እንጂ የጡረታ መውጪያ ጊዜዬ ገና ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ደብዳቤ ሳይደርሰኝ የደመወዝ መቁረጥ፤ በማይመለከተኝ ስብሰባ ላይ አልተገኘህም በሚል የደመወዝ ቅጣት ተወስኖብኝ ተግባራዊ ተደርጎብኛል።
አለቆቼ ከእነርሱ ጋር አለመተባበሬን እያስወሩ በሕጋዊነት ሽፋን ጊዜን እና ሁኔታን ተገን በማድረግ ግፍ እና በደል በመፈፀም መብቴን እና የሥራ ነፃነቴን ገድበውብኛል። ስለዚህ መብቴም ይከበር፤ የተቆረጠብኝ ገንዘብ ይመለስልኝ፤ የተሰጠኝ የጡረታ ውጣ ደብዳቤም ይሰረዝልኝ፡፡›› ሲሉ አቤቱታ ማቅረባቸውን ለዝግጅት ክፍሉ ያቀረቡት ሰነድ ያብራራል።
እንደ አቶ ጉራቻ ገለፃ፤ አቤቱታ ቢያቀርቡም ተገቢውን ምላሽ የሚሰጣቸው አካል አላገኙም። ስለዚህ ሕግ ይፈፀማል፤ ፍርድ አገኛለሁ ብለው በማመናቸው ጉዳያቸውን ይዘው ፍርድ ቤት ቀረቡ። ከጊዜው አስተዳደር ጋር የነበረውን አለመግባባት በሚመለከት፤ ይፈፀምባቸው የነበረውን በደል እና ግፍ እንዲሁም ደመወዝ እስከ መቁረጥ የደረሰ በደል እንደነበረባቸው አመልክተው፤ መስከረም 7 ቀን 1995 ዓ.ም ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መናገሻ ምድብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ቢሮን ከሰሱ።
በ1995 ዓ.ም ያቀረቡት ክስ ጭብጥ
ተቋሙ ማለትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዞን 4 ፋይናንስ ጽሕፈት ቢሮ በወቅቱ 641 ብር ከ92 ሳንቲም ያለአግባብ ከደሞዛቸው የቆረጠ መሆኑን በመጥቀስ፤ ፍርድ ቤቱ ገንዘቡን እንዲያስመልስላቸው ጠየቁ። ጨምረውም ‹‹ጡረታ ወጥተሃል፤›› በሚል የሠራተኞች የሰዓት ፊርማ ላይ ቢፈርሙም ከሥራ እንደሌሉ ተቆጥሮ የተሰረዘ መሆኑን፤ ይህንንም የተሰረዘውን የሰዓት ፊርማ በማየት ማረጋገጥ እንደሚቻል በመጠቆም፤ የጡረታ መውጫ ጊዜያቸው አለመድረሱን በማመላከት ክስ አቀረቡ። ሆኖም ተቋሙን መርታት አልቻሉም።
እርሳቸው እንደሚገልፁት፤ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በትክክል መብታቸውን ባላገናዘበ መልኩ ውሳኔ አስተላለፈ። በዚህ ምክንያት ጡረታቸውንም ደሞዛቸውንም ሳይቀበሉ ተቋሙ ጋር እየተመላለሱ ሲንገላቱ ቆዩ። አቶ ጉራቻ ቀድሞ ጡረታ መውጣት የለብኝም እና ሌሎችም የአስተዳደር በደል ደርሶብኛል የሚሉ ጉዳዮችን በማካተት ተቋሙን ሲከሱ የቆዩት የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ላይ ብቻ አልነበረም፤ በመቀጠል ለከፍተኛ ፍርድ ቤት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዞን 4 ፋይናንስ ጽሕፈት ቤትን በድጋሚ ይግባኝ በማቅረብ ከስሰዋል። ሆኖም ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትን ውሳኔ አፅንቶት ነበር።
አቶ ጉራቻ አላቆሙም ‹‹ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ መብቴን በትክክል ያላገናዘበ ነው፡፡›› በማለት፤ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቀረቡ። በዚህ ጊዜ በታህሳስ 2 ቀን 2004 ዓ.ም ለእርሳቸው ተወሰነላቸው። ከተወሰነላቸው በኋላ ግን አፈፃፀም እየተካሄደ እያለ ፍርዱን የሰጠው ፍርድ ቤት እራሱ አንድ አመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የሰጠው ፍርድ በማገዱ፤ ደረጃውን ጠብቀው በይግባኝ እንዳያንቀሳቅሱ ያገዳቸው መሆኑን አስታውሰዋል።
ከዓመታት በኋላ ይሠሩበት የነበረው ተቋም ማለትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዞን 4 ፋይናንስ ጽሕፈት ቤት ወደ ሌላ ቦታ ተዘዋወረ። ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ለአራዳ ክፍለ ከተማ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት ማመልከቻ አስገቡ።
በ2003 ዓ.ም የቀረበ ማመልከቻ
አቶ ጉራቻ ባቀረቡት ሰነድ በ2003 ዓ.ም ለአራዳ ክፍለ ከተማ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት ማመልከቻ አቅርበዋል። ማመልከቻው የደረሰባቸውን በደል የሚዘረዝር እና ካሳ እንዲከፈላቸው የሚጠይቅ ነበር። በጽሕፈት ቤቱ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ከወረዳ 8 ማዘጋጃ ቤት በዝውውር መምጣታቸውንና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ ግንቦት ወር 1994 ዓ.ም ድረስ በቅንነትና በታማኝነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ያብራራል። ነገር ግን ዞን 4 የፋይናንስ ቢሮ ባልታወቀ ምክንያት ከሥራቸው አግዶ ማመልከቻውን እስካቀረቡበት ቀን ድረስ ለዘጠኝ ዓመታት በመንከራተት ላይ እንደሚገኙ እና ጡረታም ሆነ ደሞዝ እያገኙ አለመሆኑን ይገልፃል፡፡
ይህንን ከፍተኛ በደልና ችግር ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ያመለከቱ ቢሆንም ማመልከቻውን እስካቀረቡበት ቀን ድረስ አንዳችም መፍትሔ እንዳላገኙ የሚያስረዳ ነበር። በመሆኑም መሥሪያ ቤቱን ባገለገሉበት ጊዜ ማግኘት የነበረባቸውን የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ታስበው እንዲከፈላቸው፤ ከመሥሪያ ቤቱ ባልታወቀ ምክንያት ያለአንዳች የፍርድ ቤት ውሳኔ በመባረራቸው በሕጉ መሠረት የሞራል ካሳ እንዲከፈላቸው እና ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ማመልከቻው እስከቀረበበት ዕለት ድረስ ሊከፈላቸው የሚገባው የወር ደመወዝ ታስቦ እንዲከፈለቸው የጽሑፍ ማመልከቻ በማቅረብ ጠየቁ። ሆኖም በዚህ ጊዜም ተገቢውን ምላሽ አላገኙም። ስለዚህ ወደ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አመሩ።
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ምርመራና ውሳኔ
አቶ ጉራቻ ሰንበቶ ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ላቀረቡት አቤቱታ ሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም ምላሽ ሰጠ። መዝገቡ ተመርምሮ በተሰጠው ውሳኔ ላይ እንደተብራራው፤ ያሰናበታቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዞን 4 ፋይናንስ ጽሕፈት ቤት ከአራዳ ክፍለ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት ወደ ጉለሌ ክፍለ ከተማ የተዘዋወረ መሆኑን እና ለጊዜው ስለአቶ ጉራቻ ቅጥር፣ ስንብት እና ሌሎች ማስረጃዎችን ማግኘት አልተቻለም። አራዳ ክፍለ ከተማም በጊዜው ግለሰቡ በክፍለ ከተማው ተቀጥረው ስለመስራታቸው የሚገልፅ ማስረጃ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ያላገኘ መሆኑን በጽሑፍ አሳውቋል።
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በመቀጠል ለአዲስ አበባ ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲም አቶ ጉራቻ ሰንበቶ በመስሪያ ቤቱ የጡረታ ዝርዝር ላይ ተመዝግበው ያሉ መሆናቸውን አስመልክቶ ጥያቄ አቅርቧል። ሆኖም የአዲስ አበባ ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ መጋቢት 3 ቀን 2004 ዓ.ም ለሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አቶ ጉራቻ የጡረታ መለያ ቁጥራቸውን ካላቀረቡ እንደማያውቃቸው ምላሽ ሰጥቷል።
ተቋሙ በመቀጠል ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ኢኮኖሚና ልማት ቢሮ አቶ ጉራቻን በተመለከተ ‹‹ለምን ተሰናበቱ? እንዲሁም ሊከፈላቸው የሚገቡ ክፍያዎች ለምን ተቋረጡ? ›› የሚሉ ጥያቄዎችን አቀረበ። የፋይናንስ ኢኮኖሚና ልማት ቢሮም በሰጠው ምላሽ፤ አቶ ጉራቻ በሞሉት የሕይወት ታሪክ ፎርም መሠረት ጡረታ የሚወጡት ከግንቦት 30 ቀን 1994 ዓ.ም ቀጥሎ መሆኑን አውቀው የጡ-28ን ፎርም እንዲሞሉ ደብዳቤ እንዲደርሳቸው መደረጉን የተሰጣቸውን ደብዳቤ ፎቶ ኮፒ አያይዞ ያቀረበ መሆኑን እንባ ጠባቂ ተቋም ለአቶ ጉራቻ በሰጠው የጽሑፍ ምላሽ ላይ ተመላክቷል።
በተጨማሪ በመስከረም 14 ቀን 1995 ዓ.ም አቶ ጉራቻ ጡ-28 ፎርም ሞልተው ጡረታቸውን እንዲጠቀሙ ተጠይቀው፤ ሊቀርቡ ፈቃደኛ ያልሆኑ መሆናቸውን በመግለፅ፤ በተጨማሪ ባለ25 ነጥብ የተለያዩ መጠይቆችን የያዘ በክልል 14 መስተዳድር የመንግሥት ሠራተኞች የሕይወት ታሪክ መመዝገቢያ ላይ ሰኔ 6 ቀን 1987 በፊርማቸው አረጋግጠው የሞሉትን ቅፅ በማያያዝ የጡረታ መውጫ ቀኑን በግልፅ በሚያመላክት መልኩ ለሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሞሉትን ቅፅ ኮፒ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ኢኮኖሚና ልማት ቢሮ ለሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ማቅረቡን አስመልክቶም እንባ ጠባቂ ለአቶ ጉራቻ አስታውቋል።
ሌሎችም በጥቅምት 13 ቀን 1989 የተሰጣቸውን የሥራ ምደባ እና በ1994 ዓ.ም የደመወዝ ማስተካከያ የተደረገላቸው መሆኑን የሚያመላክቱ የተለያዩ ማስረጃዎችን ከፋይላቸው ላይ ኮፒ በማድረግ ማግኘት የቻለ መሆኑን የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አመልክቷል። የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ምርመራውን ሲያጠቃልል አቶ ጉራቻ ‹‹መብቴን ለማስከበር ተገቢውን ማስረጃ አላገኘሁም›› ለሚለው ጥያቄያቸው ተቋሙ ባደረገው ማጣራት ተጠሪው ተቋም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ መሆኑን አረጋግጧል።
ነገር ግን መስሪያ ቤቱ በደል አድርሶብኛል በሚል ለቀረበው አቤቱታ አንድ ሠራተኛ የጡረታ ዕድሜው ለጡረታ ሲደርስ ጡረታ እንዲወጣ ሠራተኛው እና መስሪያ ቤቱ በጣምራ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። በመሆኑም መስሪያ ቤቱ አቶ ጉራቻ ለጡረታ ዝግጅት እንዲያደርጉ በደብዳቤ ማሳወቁን ከፋይል ላይ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፤ ይህም ተቋሙ ግዴታውን እንደተወጣ ያመለክታል ሲል ገልፆ ውሳኔ አስተላልፏል።
በውሳኔውም አቶ ጉራቻ ማግኘት አልቻልኩም ያሏቸውን ሰነዶች ተቋሙ በማፈላለግ ያገኛቸውን ማስረጃዎች ኮፒ መውሰድ እና ያገለገሉበትን መስሪያ ቤት በመጠየቅ የጡረታ እና ሌሎችንም አለኝ የሚሉትን መብት መጠየቅ ይችላሉ ሲል ገልጿል። በሌላ በኩል ቀጣሪ መስሪያ ቤቱ የጡረታ መውጫ ጊዜውን በደብዳቤ በቅድሚያ ማሳወቁ አስተዳደራዊ በደል አድርሷል ለማለት የማያስችል መሆኑን በማሳወቅ መዝገቡን ዘግቷል።
የጡረታ ልውጣ ጥያቄ
አቶ ጉራቻ ወደ ላይ ወደታች ሲሉ እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ የጡረታ አበል ሳይከፈላቸው ለ11 ዓመት ቆዩ። በኋላም የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በሰጣቸው ማስረጃ ላይ ተመስርተው ወደ ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በመሔድ የጡረታ ጥያቄ አቀረቡ። ተቋሙ በበኩሉ አቶ ጉራቻን የተመለከቱ አስፈላጊ መረጃዎች ማለትም ይከፈላቸው የነበረ የደመወዝ ዝርዝር፣ ሲቀጠሩ የሞሉት የሕይወት ታሪክ ፎርም፣ ሥራ ካቋረጡበት ጊዜ ጀምሮ የጡረታ መብታቸውን ያልተቀበሉበት ምክንያት በጽሑፍ እንዲቀርብ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ኢኮኖሚና ልማት ቢሮን ጠየቀ፡፡
በመጨረሻም ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ አቶ ጉራቻ የጡረታ መብታቸው ተፈቅዶ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በየወሩ የጡረታ አበል ማግኘት ጀመሩ። በመቀጠል
ላለፉት ጊዜያት ማለትም ከ1994 ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም ያልተከፈላቸው የጡረታ አበል እንዲከፈላቸው ጥያቄ አቀረቡ።
ያልተከፈለ የጡረታ አበል ጥያቄ
አቶ ጉራቻ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የጡረታ አበላቸውን በየወሩ መውሰድ ቢጀምሩም ለ11 ዓመታት ሳይከፈላቸው የቆየው ገንዘብ እንዲከፈላቸው ጠየቁ። ይህን ለ11 ዓመታት መከበር ያለበት የጡረታ መብትን ጨምረው ሌሎችም በተመሳሳይ መልኩ በደል ደርሶብኛል ያሉባቸውን ጉዳዮች አካተው በግንቦት 7 ቀን 2010 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማመልከቻ አስገቡ። በመቀጠል ነሐሴ 22 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ማመልከቻ አቀረቡ። በመጨረሻም በታህሳስ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ለኢፌዴሪ የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ለአዲስ አበባ ሪጅን ጽሕፈት ቤት ጥያቄውን አቀረቡ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዞን 4 ፋይናንስ ጽሕፈት ቤት ውስጥ በቋሚ ሠራተኝነት በማገልገል ላይ እያሉ ከመስሪያ ቤቱ አስተዳደር ጋር ባለመግባባታቸው ያለፍላጎታቸው በጡረታ እንዲገለሉ መደረጉን አስታውሰው፤ ሆኖም እስከ 2005 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ምንም ዓይነት ጡረታ ሳያገኙ በችግር የቆዩ በመሆኑ መመሪያው የሚፈቅድላቸውን ሊያገኙ ይገባቸው የነበረው የጡረታ አበል እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርቡ። ነገር ግን ‹‹ከማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲም›› ተገቢውን ምላሽ አላገኘሁም በማለት ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መጡ። የዝግጅት ክፍሉ በቅድሚያ ጉዳዩን ለመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ አዲስ አበባ ሪጅን ጽሕፈት ቤት አምርቷል።
የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ምላሽ
የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ አዲስ አበባ ሪጅን ፅሕፈት ቤት የአበል ውሳኔና ክፍያ ባለሞያ አቶ ሰብስቤ ኃይለማርያም እንደሚናገሩት፤ ፋይላቸውን አይተው እንዳረጋገጡት የጡረታ አበል የተወሰነላቸው በመሆኑ በመረጡት ባንክ በየወሩ የጡረታ አበሉ እየተከፈላቸው ነው።
የዝግጅት ክፍሉ ‹‹አቶ ጉራቻ በ1994 ዓ.ም ጡረታ የመውጫ ዝግጅት አድርጉ የሚል ደብዳቤ ሲደርሳቸው፤ እርሳቸው ጡረታ መውጫ ዕድሜዬ ገና ነው ብለው ቅሬታ አቅርበው ነበር። እናንተ ጋር ባለው መረጃ መሠረት የጡረታ መውጫ ጊዜያቸው ደርሶ ነበር? » በሚል ላቀረበው ጥያቄ አቶ ሰብስቤ በሰጡት ምላሽ፤ በጡረታ አዋጅ ቁጥር 345/95ም ሆነ በተሻሻለው በጡረታ አዋጅ ቁጥር 714/2003 መሠረት አንድ ሠራተኛ የመጦሪያ ዕድሜው 60 ዓመት ነው። እርሳቸው ደግሞ መጋቢት 11 ቀን 1959 ዓ.ም ላይ በሞሉት የሕይወት ታሪክ ፎርም መሠረት ጥር 18 ቀን 1936 ዓ.ም መወለዳቸውን ያሳያል። ስለዚህ ጡረታ መውጫ ጊዜያቸው 1996 ዓ.ም ላይ 60 ዓመት ሲሆናቸው ነበር።
ኤጀንሲው እንደሚያውቀው ግን፤ እርሳቸው በፍቃዳቸው ጡረታ የመውጣት ጥያቄ ያቀረቡት 2004 ዓ.ም ነው። ኤጀንሲው ደግሞ በመመሪያ መሠረት ተቀጥረው ለነበሩበት መስሪያ ቤት ከተቀጠሩበት 1957 ዓ.ም እስከ 1996 ዓ.ም ማገልገላቸውን በቅፅ 2 ፎርም ተሞልቶ እንዲላክ ጠይቋል። ዕድሜያቸው ከሞላ በኋላ ካገለገሉም ከዕድሜ ጣሪያ በላይ የከፈሉት የጡረታ መዋጮ ተመላሽ ይደረግላቸዋል ብሎ እንደነበር አቶ ሰብስቤ ያስረዳሉ።
ነገር ግን እርሳቸው መብታቸውን እየጠየቁ ስላለው ዓመታት ሲያገለግሉበት የነበረው ተቋም ምላሽ አልሰጠም። አሁንም እዚያ ሲያገለግሉ ከነበረና ከጡረታ መውጫ ዕድሜያቸው በላይ ጡረታ ተቆርጦባቸው ከሆነ ተመላሽ ይደረግላቸዋል ብሏል፡፡
እንደአቶ ሰብስቤ ገለፃ፤ በጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም የ11 ዓመት ጡረታ ታስቦላቸው እንዲከፈላቸው ጥያቄ አቅርበው ቅሬታቸው በኮሚቴ እና በባለሞያ ታይቷል። ስለዚህ የተሰጠው ውሳኔ እስከ 1996 ዓ.ም የነበረው አገልግሎት ተይዞ በወቅቱ 294 የጡረታ አበል ይከፈላቸው ነበር፤ በኋላ ተሻሽሎና ደመወዛቸው ተሰልቶ ጡረታ 1258 ብር ሲያገኙ ነበር። አሁን ደግሞ ከመስከረም ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ባለው ማሻሻያ መሠረት 2258 ይከፈላቸዋል።
ኤጀንሲው አቶ ጉራቻን በሚመለከት ደብዳቤ በመፃፍ ሲቀጠሩ የሞሉት ፎርም፤ የደመወዝ ዝርዝር ከመጠየቅ በተጨማሪ ለ11 ዓመታት ጡረታ ያልተቀበሉበትን ምክንያት እንዲገለፅ ሲል ጠይቋል። ማድረግ የሚችለው ይህንን ብቻ ነው። የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የተሰጠው ስልጣን አንድ አሰሪ መስሪያ ቤት በገባው ውል መሠረት በዲሲፕሊንም ሆነ በብቃት ማነስ ወይም በተደጋጋሚ ሥራ ላይ ባለመገኘትና በሌሎችም በልዩ ልዩ ምክንያቶች ሠራተኛውን ጡረታ ውጣ ማለት ይችላል። አቶ ጉራቻ ግን ጡረታ ውጡ ሲባሉ የማያምኑበት ከሆነ ለሰብአዊ መብት ወይም ለሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ማቅረብ ነበረባቸው። በኤጀንሲው በኩል ግን እርሳቸው ቅሬታውን እንዳቀረቡ ተቋሙን በደብዳቤ ጠይቆላቸው ምላሽ መስጠት የነበረበት ቀጣሪ መስሪያ ቤቱ ምላሽ አልሰጠም።
አቶ ጉራቻ ለመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ጥያቄ አቅርበዋል። ኤጀንሲውም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፤ ያቀረቡት የግለሰቡን መብት ለማስጠበቅ እንደነበር አቶ ሰብስቤ ይናገራሉ፤ በማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በኩል አንድ ተገልጋይ ቅሬታ ካለው በጽሕፈት ቤቱ በሦስት ኮሚቴ ታይቶ በተሰጠው ውሳኔ ካልረኩ እንደገና ይግባኝ ማለት ይችላል። አቶ ጉራቻም ይግባኝ ብለው በሕጉ መሠረት ታይቶላቸዋል። የቀረባቸውና 11 ዓመት ሙሉ ሊከፈለኝ ይገባል የሚሉትን ማድረግ የሚቻለው አሰሪው መስሪያ ቤት በእነዚህ ጊዜያት እያሠራቸው ከነበረ እና የጡረታ ከተቀነሰ የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ይከፍላል። ከዚህ ውጪ አሁንም ካልረኩ እርሳቸው በድጋሚ ቅሬታ ማቅረብ ይችላሉ ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ኤጀንሲው ለጡረታ ከደረሱበት ዕድሜ ጀምሮ ያልከፈለውን መክፈል የለበትም? በሚል ላቀረበው ጥያቄ ባለሞያው በሰጡት ምላሽ ላይ እንደገለፁት፤ በአቶ ጉራቻ ፋይል ጥር 18 ቀን በ1936 መወለዳቸው ተሞልቷል። በማህበራዊ ዋስትና ሕግ መሠረት አንድ ሠራተኛ የጡረታው ቀን የሚሰላው በመጀመሪያ በሞላው የሕይወት ታሪክ ነው። ሌላ ቦታ ላይ 1939 ዓ.ም ብለው ሞልተዋል። ሌላም ቀን በሌላ ተቋም የተለየ አድርገው ቢሞሉም የሚያዘው የመጀመሪያው ነው።
ተቋሙ አሰሪው መስሪያ ቤቱ በሚልከው ዝርዝር መሠረት ማለትም ደመወዛቸውን እና የሕይወት ታሪካቸውን ገልፆ የጡረታ አበሉን ይከፍላል፤ እንጂ ይህ ሳይሟላ ጡረታ የሚከፍልበት ሁኔታ የለም በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
በተጨማሪ የዝግጅት ክፍሉ አንድ ሠራተኛ ጡረታ መውጣት እያለበት ጡረታ ካልወጣ ወይም አሰሪ መስሪያ ቤቱ ጡረታ መውጣት እንዳለበት ካላሳወቅ እናንተ ጥያቄ አታቀርቡም? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ አንድ ሠራተኛ ጡረታ የሚወጣው ዕድሜው ሲደርስ ተቋሙ ጡረታ እንዲወጣ ሲጠይቅ ወይም 55 ዓመት ከሞላው እና 25 ዓመት ካገለገለ ሠራተኛው ራሱ ጥያቄ ካቀረበ አሊያም ከላይ እንደተገለፀው በተለያዩ ምክንያቶች አሰሪ መስሪያ ቤቱ ሠራተኛው ጡረታ እንዲወጣ ጥያቄ ካቀረበ ብቻ ጡረታ እንዲወጣ ፈቅዶ ክፍያውን ይፈፅማል እንጂ ከዚህ ውጪ ሌላ አሠራር የለም ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ኢኮኖሚና ልማት ቢሮ
ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ኢኮኖሚና ልማት ቢሮ አቶ ጉራቻ ሰንበቶ (አቶ ገበየሁ ወ/ሰንበት) በተቋሙ ስለመስራታቸው፤ በሞሉት የሕይወት ታሪክ ፎርም መሠረት ጡረታ የሚወጡት መቼ እንደነበር እና ለምን ከግንቦት 30 ቀን 1994 ዓ.ም ጀምረው የጡ-28ን ፎርም እንዲሞሉና ለጡረታ ዝግጅት እንዲያደርጉ ደብዳቤ እንዲደርሳቸው ተደረገ? በማለት ጥያቄ ለማቅረብ አቅደን ቢሯቸው ድረስ ሔደናል።
በተጨማሪ በጊዜው ባለ 25 ነጥብ የተለያዩ መጠይቆችን የያዘ በክልል 14 መስተዳድር የመንግሥት ሠራተኞች የሕይወት ታሪክ መመዝገቢያ ቅፅ የተሞላው እና በፊርማቸው የተረጋገጠው ፎርም ላይ እንደገለፁት፤ የተወለዱት መቼ ነው? የሚል እና የ11 ዓመት የጡረታ አበላቸው ለምን አልተከፈላቸውም? ለዚህ ኃላፊነቱን የሚወስደው ማን ነው? እናንተ በ1994 ዕድሜያቸው ደርሷል ብትሉም የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የአዲስ አበባ ሪጅን ደግሞ ቀድመው በሞሉት የሕይወት ታሪክ መሠረት ዕድሜያቸው የሚደርሰው በ1996 ዓ.ም መሆኑ ከፋይላቸው ጋር ተያይዟል ብሏል። እናንተ ከምትሉት ጋር እንዴት ተለያየ? ስንል ለጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲሰጡን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ኢኮኖሚና ልማት ቢሮ ሁለት ጊዜ በአካል ሔደን ጥያቄ አቅርበናል።
ነገር ግን ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። ሆኖም ፋይሉን ፈልገው ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን፤ በአቶ ጉራቻ ( በአቶ ገበየሁ) ጉዳይ ላይ ምላሻቸውን ከሰጡን ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16 / 2015