የ12ኛ ክፍል ፈተና ተጠናቅቋል:: በብዙ ድራማ ታጅቦ የተካሄደው ፈተና መጠናቀቁ ትልቅ እፎይታ
ነው:: በእኔ ግምት የዘንድሮው ፈተና አንድ ትልቅ ሙከራ ነበር:: በዚህ የፈተና ሂደት ብዙ ጭንብሎች ተገፍፈዋል:: ፈተናን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ የሚጠቀሙ ኃይሎች ክንዳቸው ተሰብሯል:: ኩረጃን ተማምነው ሳያጠኑ የሚከርሙ ተማሪዎች ከአሁን ወዲያ ይህ አይነት እድል እንደሌላቸው አውቀውታል:: በሙስና ተማሪዎቻቸው ተኮራርጀው ውጤት ሰቅለው እንዲያልፉ ያደርጉ የነበሩ ትምህርት ቤቶች አሁን ከእውነታው ጋር ሊጋፈጡ ጊዜያቸው ደርሷል:: ብቻ ግሩም ሙከራ ነበር:: በቀጣይ አመትም እንደሚደገም ተስፋ አለኝ::
የዛሬው ትዝብቴ የሚያተኩረው ግን በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ ነው:: እሱም በግል ትምህርት ቤቶች የተስፋፋው የውጤት ግሽበት ላይ ነው:: መቼም የግል ትምህርት ቤት ጉዳይ ብዙ ነው:: የዋጋቸው ሰማይ መንካት፤ የተማሪዎች የስነ ምግባር ጉዳይ፤ የትምህርት ቤቶቹ የግብዓት ጉዳይ ወዘተ ብዙ ነገር ያነጋግራል:: የሆነ ሆኖ ሐምሌ በመጣ ቁጥር ዋጋቸውን የሚሰቅሉት እነዚህ የግል ትምህርት ቤቶች ለወላጅ የክፍያውን ዋጋ የሚመልሱለት በከፈለው ልክ በልጁ ላይ እውቀት በመጫን ሳይሆን ማርክ በመቆለል ነው::
እኔ በማውቀው ድሮ ድሮ ሁሉም ተማሪ ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግበው እንደ ስእል እና ስፖርት ባሉ ብዙም ከባድ ባልሆኑ እና ለልጅ በሚስማሙ የትምህርት አይነቶች ነበር:: እኔ ራሴ ሁሌም ከዘጠና በላይ የማገኘው በነዚህ የትምህርት ዘርፎች ላይ ነበር:: በሌሎቹ ላይ ግን ትክክለኛ አቅሜ ፍንትው ብሎ ይታያል:: ለምሳሌ ያህል ሂሳብ የሚባል ትምህርት ብዙም የማይገባኝ የነበረ ሲሆን እስከማስታውሰው በሂሳብ ትምህርት ያስመዘገብኩት በጣም ከፍተኛ ውጤት 70 አካባቢ ነበር::
የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ነገሩ በተቃራኒው ነው:: ሂሳብ የማይወደው ተማሪ በሂሳብ 97 አግኝቶ ታገኘዋለህ፤ ሳይንስ ጭራሽ የማይሰርጸው ልጅ በሳይንስ 99 ነው ያገኘው ይባላል፤ ቋንቋ የሚቸገረው ልጅ በቋንቋ ዋነኛ ተፎካካሪ ሆኖ ይታያል:: ብቻ ማርኩ እንደ ዘንድሮ ገበያ ላይ የተንጠለጠለ ነው:: ልጆቹ እንግዲህ እንዲህ የጋሸበ ማርክ ሲሰበስቡ ኖረው ነው ብሔራዊ ፈተና ላይ የሚቀመጡት እና ባልለመዱት ስርአት የሚመዘኑት::
የትምህርት ዋነኛው ተልእኮ ለተማሪው የመሞከር እና የመሳሳት እድልን መስጠቱ ነው:: አሁን አሁን እኮ ልጆቹ ጭራሽ እንዳይሳሳቱ እየተደረጉ ነው የሚማሩት:: መምህሩ የሚያወጣላቸው ጥያቄ ለመልሱ የተቃረበ ነው:: ፈታኙ አጠገባቸው ቆሞ እንዳይሳሳቱ የሞራልም የእውቀትም ድጋፍ ያደርግላቸዋል:: ራሳቸውን ችለው እንዲሰሩ እና ውጤት እንዲያመጡ እድል አይሰጣቸውም:: ትምህርት ቤቶች ይህን ከመጠን ያለፈ ድጋፍ የሚያደርጉት ተማሪው ውጤቱ ዝቅ ካለ እነሱን ስለሚወቅስ እና ገበያ ስለሚቀዘቅዝባቸው ነው:: ወላጅ ይህን የጋሸበ ውጤት የሚቀበለው የከፈለው ገንዘብ እና የደከመው ድካም ውጤት ያመጣ መስሎ ስለሚሰማው ነው:: በዚህ ሂደት ተጎጂዎቹ ልጆቹ ናቸው::
ራሳቸውን፤ ተሰጥኦቸውን፤ ዝንባሌያቸውን መለየት አይችሉም:: ሁሉም ነገር ላይ ጎበዝ ናችሁ ስለተባሉ የእውነትም ሁሉም ነገር ላይ ጎበዝ የሆኑ ይመስላቸዋል:: እንዲህ ሆነው ሄደው ነው እንግዲህ ብሔራዊ ፈተና ላይ የሚቀመጡት:: ያኔ ልጆቹ ከምቾት ቀጠናቸው ይወጣሉ:: ከምቾት ቀጠናቸው ሲወጡ እና እውነታውን ሲጋፈጡ ደግሞ ብስጭት ይመጣል:: ፈተናው ከበደኝ፤ ፈታኞቹ አጉላሉኝ፤ የተፈተንበት ቦታ አልተመቸኝም፤ ወዘተ የሚመጣው ከምቾት ቀጠና ከመውጣት ነው::
አሳዛኙ ነገር ልጆችን በዚህ መልኩ በምቾት ቀጠናቸው ውስጥ ብቻ ሆነው እንዲማሩ እና እንዲያድጉ መደረጋቸው ከትምህርት እና ፈተናውም ባለፈ በመቀጠል ለሚመጣው ሕይወት ዝግጁ እንዳይሆኑ ማድረጉ ነው:: ሕይወት ላይ የሚያግዝ ፈታኝ የለም:: ለመልስ ዝግጁ ሆኖ የሚዘጋጅ የሕይወት ጥያቄም የለም:: የሕይወት ጥያቄ ከባድ ነው:: ፈታኙም ራሱ ሕይወት ነውና ጨካኝ ነው:: ከጎን ሆኖ አይዞህ የሚልም የለም:: ዛሬ ማርክን ማጋሸብ ይቻላል:: እውቀትን ግን እንደ ማርኩ መቆለል አይቻልም::
ስለዚህም ስራው መጀመር ያለበት ወደኋላ ተሂዶ ነው:: ተማሪዎች ፈተናን መለማመድ ያለባቸው ከታች ጀምሮ ነው:: ደብተራቸው ላይ አንዳንዴ ኤክስ ምልክት ሊኖር ይገባል:: የተሳሳቱትን እና ያልገባቸውን ከታች ጀምሮ እያወቁ፤ እየጠየቁ፤ የእውቀት ክፍተታቸውን እየደፈኑ ሊመጡ ይገባል:: ወላጅ ልጁ በምን ትምህርት ላይ ጎበዝ እንደሆነ በምን ላይ ደግሞ ድጋፍ እንደሚፈልገው እያወቀ መሄድ አለበት:: ወላጅ የልጁን ደብተር ገልጦ ሲያይ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ራይት ሲያይ መጠራጠር አለበት:: ምክንያቱም ይህ እውነት እና ጤናማ ስለማይሆን ነው::
ይህ በእንዲህ እንዳለ በግል ትምህርት ቤቶች የሚታየው የውጤት መጋሸብ እንዳለ ሆኖ በመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚታየው የውጤት መላሸቅ፤ ኩረጃ እና ሌሎችም ብዙ የሚያሳስቡ ናቸው:: ተማሪዎች ከሚገባቸው በላይ ውጤት ሊሰጣቸው አይገባም የተባለውን ያህል በዚያው ልክ የተማሪዎችን ሙከራ እና ጥረት እውቅና የማይሰጥ እንዲሁም ተማሪዎች ያሉባቸውን ተግዳሮቶች ግንዛቤ የማይሰጥ የትምህርት አሰጣጥም ሆነ ትምህርት ቤት ብሎም መምህር መስተካከል አለበት::
ሲጠቃለል የትምህርት ሚኒስቴርም ጥረት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች እኩል የሆነ የመወዳደሪያ መፍጠር ነው:: የዘንድሮው ብሔራዊ ፈተናም የዚያ ጥረት መገለጫ ነው:: ትምህርት ሚኒስቴር ይህን ግሩም ሙከራ ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ ለማድረግ እና በዘለቄታው ኩረጃን ከኢትዮጵያ የትምህርት ስርአት በማስወጣት ጥራት ያለው ተማሪ ለማፍራት እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው:: ነገር ግን ከብሔራዊ ፈተናው ባለፈ በሁሉም ደረጃ ላይ መሰራት አለበት:: የውጤት ግሽበትም ሆነ የውጤት ልሽቀት እንዳይኖር ሁሉም ተማሪ በፍትሃዊነት የሚመዘንበት ምዘና ስርአት በሁሉም የክፍል ደረጃ ላይ ሊዘረጋ ይገባል::
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2015