መምህር ሆነው የተማሪዎቻቸውን የቀለም ጥማት አርክተዋል።አርበኛ ሆነው አገራቸውን ከጠላት ለመታደግ ተዋግተዋል።ዲፕሎማት ሆነው ስለአገራቸው ኢትዮጵያ ብዙ ሰርተዋል፣ ሚኒስትር በመሆን በተለያየ ዘርፍ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ለውጠዋል። ደራሲ ሆነውም በአገሪቱ ውስጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነ ስነ ፅሁፋዊ ስራ አበርክተዋል።የተለያዩ ሙያዎች ባለቤትም ነበሩና በልዩ ልዩ አለማቀፍ ተቋማት ውስጥ አገልግለዋል።አንድ ሆነው ብዙ ቦታ የተገኙ ብርቱ ሰው ናቸው።
በፈጠሩት ምዕናባዊ ዓለም ውስጥ በእውን የሚታየውን ዓለም የገለጡ ታላቅ የስነፅሁፍ ሰው።ጉዱ ካሣን አሳብደው በነፃነት እውነትን ያስለፈለፉ፣ ሰብለወንጌልን በፍቅር አሸፍተው የመውደድን ሀያልነት ያመላከቱ፣ በዛብህን አሳምፀው የሰው ልጅ ግለዊ ነፃነት ምን ያህል እንደሚሻ ለፍቅርና ለሰብዓዊነት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው የገለፁ ድንቅ ብዕረኛ።
ያኔ የነበረውን የፊውዳሉ ዘመን ባህል፣ አስተሳሰብ እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤ በዘመኑ ያልተፈጠረና ዛሬ ላይ ያለውን አንባቢን ጭምር በምናቡ ዘመኑን እየሳለ ያልኖረበትን ዘመን ጣእም እንዲያጣጥም ያስቻሉ የምንጊዜም ሀያል ፀሐፊ የ “ፍቅር እከ መቃብር” አባት ክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ልደት በዚህ ሳምንት ነበረና እሳቸውን መዘከር ወደድን፡፡
በኢትዮጵያ ስነ ፅሁፍ ውስጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነ፤ የአገሪቱን ስነ ፅሁፍ በአንድ እርምጃ ወደፊት ያራመዱ ታለቁ ልቦለድ “ፍቅር እስከ መቃብር” የእርሳቸው ምዕናባዊ ዓለም ፍሬ ነው።ዛሬ ድረስ ከ ግማሽ ምዕተ ዓመተ በላይ ተደጋግሞ ከሚነሳው “ፍቅር እስከ መቃብር” ከተሰኘው መፅሀፍ ባሻገር በርካታ ድርሰቶችን አበርክተዋል።በተለያዩ ሀላፊነቶች አገራቸውን አገልግለዋል፡፡
በተለይ በወቅቱ በኢትዮጵያ የነበረው ንጉሳዊ ስርዓትና አንዳንድ አስተዳደራዊ ገፅታን ፍንትው አድርገው የገለፁ ታላቅ የስነ ፅሁፍ ሰው ነበሩ።ክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ የተወለዱት ጥቅምት 7 ቀን 1902 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ አውራጃ በጎዛምን ወረዳ በእንጾር ኪዳነ ምኅረት ቀበሌ ነው።
ዲፕሎማት፣ መምህርና ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ደራሲ አባታቸው ከቄስ ዓለማየሁ ሰለሞን እናታቸው ከወይዘሮ ደስታ ዓለሙ ይባላሉ።ገና በጨቅላ እድሜያቸው በቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን ትምህርት በቤተሰባቸው አጠገብና ባባታቸው አገር ደብረኤልያስ ሄደው የግእዝ ትምሕርት ቤት ቅኔ ተቀኝተዋል። የተለያዩ ሀይማኖታዊ ትምርቶችን ተምረዋል፡፡
በቅኔ ዘረፋ የተዋጣላቸው የነበሩት ሀዲስ አለማየሁ ልጅ ሆነውም በብዙ ተማሪዎች ዘንድ በፈጣንነታቸው ይታወቁ ነበር።በእርግጥ አባታቸው ቄስ አለማየሁ የቅኔ ሊቅ ነበሩ።በእርሳቸው የበዙ የቅኔ ተማሪዎች ፈርተዋል።በተለይ ቅኔን በዜማ በመቀኘት በብዙዎች የታወቁ ነበር።ሀዲስ ለአባታቸው አንድ ልጅ ሲሆኑ በኋላ ላይ ከአባቱ የተፋቱት እናቱ ግን ከሌላ ሁለት ልጆችን ወልደዋል።
የቤተክርስቲያን ስርዐታትንና መንፈሳዊ ትም ህርትን በጎጃም ገዳማት በደብረ ኤልያስ፣ በደብረ ወርቅና በዲማ በመማር አጠናቀቁ።በ1917 ዓ.ም. አስተማሪያቸው ከነበሩት ጋር ተከትለው አዲስ አበባ በመሄድ በስዊድን ሚሽነሪ ትምህርት ቤት ገብተዋል።እዚያ የቋንቋና ሌሎች ትምህርቶችን እስከ ሶስተኛ ክፍል ተከታትለዋል፡፡
ከሶስተኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ ራስ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ቤት ትምህርታቸውን ተከታተሉ። በዚያ ትምህርት ቤት ሳሉ ነበር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ልዩ የሆነው የስነፅሁፍ ክህሎታቸው መገለጥና ለስነጥበብ ልዩ ትኩረት መስጠት የጀመሩት።በተለይ በትምህርት ማብቂያ ላይ ይቀርቡ የነበሩ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ላይ በመሳተፍ ጥበብን ሀ ብለው ጀመሩ።በወቅቱ በንጉሱ ፊት ይቀርቡ የነበሩ የመድረክ ተውኔቶች ላይ የመካፈል እድልም ገጥሟቸው ነበር።ለዚህ የሚሆን ተውኔትም አዘጋጅተው ነበር።ይህ ቃለ ተውኔት፤ በኢትዮጵያ ስነ ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ቃለ ተውኔቶች የሚጠቀስ መሆኑን በመስኩ ላይ ጥናት ያደረጉ ሙህራን ይገልፃሉ። በዚህ የተውኔት ስራና በስነፅሁፍ እንቅስቃሴያቸው ከንጉስ ሀይለስላሴ የእጅ ሰዓትና 50 ብር የተበረከተላቸው ዶክተር ሀዲስ ሽልማቱ እጅግ ብርቱ እንዲሆኑ ረዳቸው፡፡
ከትምህርት ቆይታቸው በኋላ የመምህርነት ስልጠና በመውሰድ አዲስ አበባ ላይ ለዓመታት ለበርካታ ተማሪዎች የቀለም አባት ሆነዋል።ተማሪዎቻቸውን ፊደል በማስለየት ከመሀይምነት አላቀዋል፤ አዳዲስ እውቀትና እሳቤዎችን የማውረስና የማስገብየት ስራን በትጋት ሰርተዋል፡፡
ወደ ጎጃም ሄደውም ዳንግላ ላይ በእርሰ መምህርነት አገልግለዋል።በአስተማሪነት ሥራ ተሰማርተው እንዳሉ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ተከሰተ። የኢጣልያ ወረራ ሲከሰት ከልዑል ራስ ዕምሩ ኃይለ ሥላሴ ጦር ጋር በምዕራብ ኢትዮጵያ በአርበኝነት ሲዋጉ፤ አገራቸውን ከዚህ ወራሪ ጠላት በመከላከል ቆዩ።በየቦታው ህዝብ ለአገሩ እንዲዋጋ አነሳስተዋል።በዚያ ወቅት ቀስቃሽን አነሳሽ የሆኑ ተውኔቶችን በመፃፍም ህዝቡ ለአገሩ እንዲዋደቅ በሙያቸውም አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
ሙሉ ለሙሉ ወደ ውጊያ በመግባት ትግራይ አካባቢ ሽሬና አካባቢዋ ላይ ከጠላት ጋር ተፋልመዋል።በጦር ሜዳም ሆነው ጊዜ ሲያገኙ የተለያዩ ግጥሞችን በተለይም አርበኞች የሚያነሳሱ ግጥሞች ያዘጋጁ ነበር።ሽሬ አካባቢ የነበረው ጦርነት በድል ተወተው ወደ ጅማ በማቅናት ላይ ሳሉ ጅማ በጣሊያን እጅ መውደቅዋ ሰምተው ከጉዞዋቸው ተገቱ።ወደ ኋላ በማፈግፈግም ለጥቂት ጊዜ ቆዩ።በኋላ ላይ በወራሪው የኢጣሊያ መንግስት በመያዛቸው ከልዑል ራስ እምሩ ጋር በግዞት ለሰባት ዓመታት ጣሊያን በሚገኘው በፖንዛ ደሴትና በሊፓሪ ደሴት ታስረው በእስር አሳልፈዋል።
በተለይም በዚያ እስር ላይ በነበሩበት ወቅት ሀይለኛና ስር የሰደደ የሳንባ ምች በሽታ ተይዘው ተሰቃይተዋል። ይህ በሽታ ለዓመታት ፀንቶባቸው ቆይቷል። ከዚያም የተባባሪ ኃያላት ማለትም በእንግሊዝ ወታደሮች በ1935 ዓ.ም. ከእስር ቤት አስመለጡዋቸው፡፡
ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ለትምህርት ልዩ ፍቅርና አዲስ ነገር ለማወቅ ልዩ ፍቅር የነበራቸው ክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ በኦክስፎርድ ትምህርታቸው ከገፉ በኋላ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ወደማገልገሉ ተመለሱ።ትጉህና ታታሪ የነበሩት እኚህ ድንቅ የብዕር ሰው በተለይም በትምህርት ሚኒስቴር ለረጅም ጊዜ አገልግለዋል።
በመንግስት መስሪያ ቤቶችና በተለያዩ ተቋማት የቆዩባቸው የስራ እና የሀላፊነት ቦታዎች ለመግለፅ ያህል፡- 1936 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኛ፣ 1937 እስከ 1938 የኢትዮጵያ ቆንሲል በኢየሩሳሌም፣ 1938 – በ International Telecommunications Conference አትላንቲክ ከተማ የኒው ጄርሲ ወኪል፣ 1938 እስከ 1942 በተባበሩት መንግሥታት ቢሮ ኒው ዮርክ ሠራተኛ፣ 1942 እስከ 1948 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዳይሬክተርና ምክትል፣ 1948 እስከ 1952 የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ 1952 የትምህርት ሚኒስትር በመሆን፣ 1952 እስከ 1957 የኢትዮጵያ አምባሳደር በእንግሊዝና ሆላንድ፣ 1957 እስከ 1958 የልማት ሚኒስትር፣ 1960 እስከ 1966 ሴናተር በመሆን አገራቸውን እና የተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማት ላይ በማገልገል ለአገራቸው አስተዋፅዖ አበርክተዋል።
በተለይም በዓለማቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ድምፅዋ ጎልቶ እንዲሰማና ተፅዕኖ ፈጣሪ ትሆን ዘንድ በተለያ መድረኮች ኢትዮጵያን በመወከል ተሟግተዋል፤ ስለ አገራቸው አቅማቸው በፈቀደው ሁሉ ሰርተዋል።እኚህ ዘርፈ ብዙው ሙያተኛና የስነፅሁፍ እንቁ ያኔ ፕሬስና ፕሮፓጋንዳ መምሪያ ይባል በነበረው መስሪያ ቤት (ያሁኑ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት) ውስጥ አገልግለዋል፡፡
አብዛኛ የስነፅሁፍ ቤተሰብ የሚያውቀውን “ፍቅር እስከ መቃብር” የተሰኘው በአቀራረቡና በስነ ፅሁፋዊ ይዘቱ ከፍ ያለው የረጅም ልቦለድ መፅሀፋቸው በተጨማሪ ቁጥራቸው በርከት ያሉ መፅሀፎችን፣ ተውኔቶችን፣ ግጥሞችና የተለያዩ ፅሁፎችን ለተደራሲው አድርሰዋል።ክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ እስራኤል እያሉ ያገቡዋቸው ባለቤታቸው ወይዘሮ ክበበ ፀሀይ በመሞታቸው ትልቅ ሀዘን ውስጥ ለዓመታት ቆይተዋል።አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ የነበረው መኖሪያ ቤታቸው በባለቤታቸው ስም በመሰየም ለህፃናት ማሳደጊያ ይሆን ዘንድ ለአዲስ አበባ መስተዳድር አስረክበዋል።ባለቤታቸው ከሞቱ በኋላ ሌላ ባለማግባት ለባለቤታቸው ያላቸው ታላቅ ፍቅር በተግባር ያሳዩም ሰው ነበሩ፡፡
የክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ በርካታ ከስነጽሑፍ ሥራዎቻቸው መካከል፡- ከነዚህም ውስጥ ታላቅ አድናቆትንና እውቅናን ያተረፈው ሥራቸው “ፍቅር እስከ መቃብር” (1958) የተሰኘው ረጅም ልቦለድ ሲሆን በሁለት የተለያዩ መደቦች ውስጥ የሚገኙ የሁለት ሰዎች የፍቅር ታሪክ ላይ ሲያተኩር፤ በጊዜው የነበረውን ወግና ልማድ ይገልጻል።
ሌላኛው በ1970 “ወንጀለኛው ዳኛ” የተሰኘ የረጅም ልቦለድ መፅሀፍ ሲያበረክቱ በ1980 ደግሞ ስለ ማህበራዊ ጉዳዮችና ስለ ጣሊያን ውርስ የሚዳስሰውን “የልም እዣት” የተሰኙትን ልብ ወለድ ታሪኮች ለንባብ አቅርባዋል። ከታተሙ ስራዎቻቸው ይልቅ ሳይታተሙ የቀሩት እጅጉን እንደሚበልጡ ደራሲው በአንድ ወቅት የሰጡት አስተያየት ያስረዳል።
ከረጅም ልቦለድ መፅሀፎቻቸው በተጨማሪም በሌላ ዘርፍ የስነ ፅሁፍ ስራዎቻቸው ዛሬ ድረስ የሚነሱት እኚህ ታላቁ ብዕረኛ “የአበሻና የወደኋላ ጋብቻ” የተሰኘ ተውኔት ፅፈው አዘጋጅተውም ነበር።መፅሀፍም “ተረት ተረት የመሰረት” የተሰኘ መፅሀፍና “ትዝታ” የተሰኘ በራሳቸው ህይወት ላይ የተመሰረተ መፅሀፍም አበርክተዋል።በእርግጥ እነዚህ ህዝብ ጋር የቀረቡ በመሆናቸው ተጠቀሱ እንጂ ሀያሉ የብዕር ሰው ክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ከትምህርት ቤት ጀምረው በብዕራቸው የጥበብ ዓለም በተለያየ መልኩ ሲያስዳስሱ ኖረዋል፡፡
ሀዲስ ዓለማየሁ በኢትዮጵያ የስነ ጽሑፍ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማበርከታቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዶክተርነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል። ደራሲው በኅዳር 26 ቀን 1996 ዓ.ም. በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ይህንን ፅሁፍ ስናዘጋጅ በደራሲ ሀዲስ አለማየሁ የተዘጋጀው “ትዝታ” የተሰኘው ስለራሳቸው ህይወት የሚተርከው መፅሀፍ፣ ደራሲውን የተመለከቱ ልዩ ልዩ ፅሁፎችንና ድህረ ገፆችን ተጠቅመናል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም