ጤና ይስጥልን አንባቢዎቻችን እንደምን ከረማችሁ? መንትዮቹ የዘመን ሀኪሞች ነን። ለዛሬ በአዲስ ዘመን ቅዳሜ ያዘጋጀነውን የጤና መረጃ እናካፍላችኋለን። ላለፉት ሶስት እትሞች ስለ ጤና ምንነት እና የጤና አይነቶች ለሶስት(3) አበይት ክፍሎች በመክፈል እያንዳንዳቸውን ምን አይነት የጤና አይነቶች እንደሆኑ ለመግለጽ ሞክረናል።
ባለፈው ሳምንትም የአስም ህመምን አስመልክቶ ለቀረቡልን ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተናል። ለዛሬ ደግሞ የሀሞት ጠጠር ምንነት፣ ምልክቶች፣ እንዲሁም ህክምናውና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ከአንባቢዎቻችን በርከት ያሉ ጥያቄዎች ደርሰውናል። በመሆኑም የሀሞት ጠጠርን በሚመለከት ዘርዘር ያለ መረጃ እናካፍላችኋልን።
ስለ ሀሞት ጠጠር ምንነት እንዲሁም የችግር እይነቶች በዝርዝር ከማውራታችን በፊት ስለ የሀሞት ከረጢት ስራ በትንሹ ብለን ስለ ዛሬው ርዕሳችን ማለትም ስለ ሀሞት ጠጠር ለማብራራት እንሞክራለን።
የሀሞት ከረጢት በሰውነታችን የቀኝ የላይኛው የሆድ እቃ ውስጥ፤ ከጉበታችን በታች የሚገኝ የሆድ እቃ አካል ነው። የሀሞት ከረጢት በጣም አነስተኛ እና የእንቁላል ቅርፅ ያለው ሲሆን ከወደ መጨረሻ ክፍል ጠበብ ያለ ነው። የሀሞት ከረጢት በውስጡ «Bile» የተሰኘ ወይም ሀሞት ተብሎ የሚጠራውን በምግብ መፍጨት ሂደት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያለውን ፈሳሽ ያጠራቅማል። ይህ ሀሞት የሚባለው ፈሳሽ የሚመረተው በጉበታችን ነው። አንዴ ከተመረተ በኋላ ወደ ሀሞት ከረጢት በተለያዩ ቱቦዎች አድርጎ ወደ ሀሞት ከረጢት ውስጥ ይከማቻል።
የሀሞት ጠጠር ምንነት እና አፈጣጠር
ከስሙ ለመረዳት እንደሚቻለው የሀሞት ጠጠር ማለት በሀሞት ከረጢት ውስጥ የሚፈጠር የጠጠር/የድንጋይ ይዘት ያለው ነገር ነው። ይህ ጠጠር በተለያየ መጠን፣ ብዛት እንዲሁም ቅርፅ ሊፈጠር ይችላል። አንድ አንድ ሰዎች ግን አንድ ተለቅ ያለ ጠጠር ብቻ ሊኖራቸው ይችላል። በአንፃሩ ደግሞ ሌሎች ሰዎች በጣም ብዙ እና ትናንሽ ጠጠሮች ሊኖሯቸው ይችላል።
የሀሞት ጠጠር አይነቶች
የሀሞት ጠጠር በዋናነት በ 2 የሚከፈሉ ሲሆን የመጀመሪያው «cholesterol gall stones» ወይም የስብ ጠጠሮች ናቸው። ይህ የጠጠር አይነት በጣም የተለመደ እና በብዛት የሚያጋጥም የጠጠር አይነት ነው። እነዚህ ጠጠሮች ቀለማቸው ወደ ቢጫነት የሚያደላ ነው። አፈጣጠራቸውም መቅለጥ የነበረበት እና ወደ ደም መቀላቀል የነበረበት ኮሌስትሮል (ስብ) እዛው የሀሞት ከረጢት ውስጥ በመቀመጥ እና እርስ በእርሱ በመያያዝ ወደ ጠጠርነት ሲቀየር ነው።
ከሀሞት ጥቅሞች መካከል በዋናነት ሰውነት ውስጥ ያለ ስብ (ኮሌስትሮል) ከደም ጋር ማዋሀድ ሲሆን ይህ በማይሆንበት ጊዜ ከላይ የተጠቀሰውን ቅባታማ (የኮሌስትሮል) ጠጠር እንዲፈጠር ያደርጋል።
ሁለተኛው የሀሞት ጠጠር አይነት «pigmented gall stones» ወይም ቀለማማ ጠጠር በማለት የምንጠራው ነው። ይህ የጠጠር አይነት ቀለሙ ወደ ጥቁር ቡኒ ወይም ጥቁር ሊሆን ይችላል። የዚህ የጠጠር አይነት በውስጡ «Billirubin» ቢሊሩቢን የሚባለውን የቀይ የደም ሴል ንጥረ አካል በብዛት ከሀሞት ውስጥ በሚከማችበት ጊዜ የሚፈጠር የሀሞት ጠጠር አይነት ነው። እነዚህ ጠጠሮች በብዛት የማይከሰቱ ሲሆን ከተከሰቱም በአብዛኛው የደም የጤና እክል «blood disorder» እንዲሁም በጉበት በሽታ ካለባቸው ህሙማን ጋር የሚታይ ነው።
የአጋላጭ ሁኔታዎች
የሀሞት ጠጠር በማንኛውም እድሜ፣ ፆታ፣ የዘር ሁኔታ ሊከሰት የሚችል የጤና ችግር ቢሆንም በብዛት ግን ለህመሙ አጋላጭ ሁኔታዎች ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል በዋነኝነት እነዚህ ይገኙበታል።
- ሴቶችን
- እድሜ 40 እና ከዛ በላይ
- እርግዝና
- ከፍተኛ የስብ እና የኮሌስትሮል መጠን ያለው ምግብ መመገብ
- ከፍተኛ ውፍረት
- የጉበት በሽታ
- የስኳር በሽታ
- አንድ አንድ የመድሃኒት አይነቶች ለምሳሌ በአፍ የሚወሰድ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒት
የሀሞት ጠጠር መዘዞች
የሀሞት ጠጠር የሀሞት ከረጢትን እንዲቆጣ ያደርጋል። ይህም በሚሆንበት ሰዓት ከፍተኛ የሆነ ትኩሳትን እና በቀኝ የላይኛውን ወይም በመካከለኛው የሆድ አካባቢ ከፍተኛ ህመምን ያመጣል።
የእነዚህ ጠጠሮች በተለያዩ የሀሞት ቱቦዎች ውስጥ በመሰንቀር የሀሞት ፈሳሽ በአግባቡ እንዳይተላለፍ ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ ያክል ወደ አንጀት የሚሄደውን ቱቦ ከዘጋ ምግብ በአንጀት ውስጥ የሚኖረውን ዝውውር ያግዳል። ጠጠሩም ቱቦውን ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ቢዘጋው «Obstructive Jaundice» የተባለውን ህመም ሊያመጣ ይችላል። አልፎ ተርፎም ኢንፌክሽን በመፍጠር ህመሙን ሊያባብስ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ጣፊያ የሚሄደውን ቱቦ ሊዘጋም ይችላል።
በሀሞት ጠጠር የተጠቁ ሰዎች በሀሞት ከረጢት ካንሰር የመያዝ እድላቸው በጣም አናሳ ነው። ሆኖም ግን ህመሙ ካንሰርን የማስከተል አቅም ግን አለው።
የህመሙ ምልክቶች እና የህክምና አማራጮች
የሀሞት ጠጠር ያላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ምንም ምልክት የማያሳዩ ናቸው። ነገር ግን ህመሙ እየጠነከረ በሚመጣበት ጊዜ የሀሞት ጠጠሩ በራሱ ወይም ከላይ በተጠቀሱት መዘዞች ጋር ተያይዞ የሚመጡ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላሉ። ከነዚህም በዋናነት የሚታዩ ምልክቶቹ ውስጥ
- በቀኝ የላይኛው እና ወይም በመሀል የሆድ አካባቢ ከፍተኛ ህመም፤
- ህመሙም ቅባታማ ምግብን ሲመገቡ የመባባስ ስሜትን የሚያስከትል ነው፤
- ህመሙ ወደ ትከሻ ወይም/እና ወደ ጀርባ የመሰራጨት ስሜት፤
- የአይን እና የሰውነት ቢጫ የመሆን/ የቱቦ መዘጋትን የሚጠቁም ምልክት፤
- የሰገራ ወደ ነጭነት መቀየር/የቱቦ መዘጋትን የሚጠቁም ምልክት፤
- ከላይ የተጠቀሱት ዋና ዋና ምልክቶች ከትኩሳት ጋር ወይም ያለ ትኩሳት ሊከሰቱ ይችላሉ። የትኩሳት መኖር ኢንፌክሽን ወይም የሀሞት ከረጢትን መቆጣት ያመለክታል።
ታካሚዎች ከላይ የተጠ ቀሱት ምልክቶችን ባዩ ወቅት ወደ ሀኪም በመቅረብ ያለባችሁን ችግር በማማከር እና ሌሎች ተጨማሪ ምርመራ ዎችን ማድረግ ይገባል። የህ መሙ መኖርን እና አለመኖርን በማረጋገጥ ወደ ህክምና አማ ራጮች መሸጋገር ይገ ባል። ከህክምናው በፊት ሊደረጉ የሚገቡ ምርመራዎች ውስጥ የአልትራሳውንድ፣ የሲቲ ስካን ምርመራዎች ዋና ዋና ዎቹ ናቸው።
እነዚህ ምርመራዎች የጠ ጠሩን መጠን፣ ያለበትን ቦታ፣ ያስከተለውን መዘዝ የማሳየት አቅም አላቸው። ከዚህ ውጪ የሚደረጉ የጉበት እና የተለያዩ የደም ምርመራዎችም ይደረጋሉ። እነዚህም ምርመራዎች ተደርገው ህመሙን የሚጠቁሙ ከሆነ በዋናነት ቀዶ ህክምና የሚደረግ ይሆናል። እንደ ጠጠሩ ሁኔታ እንዲሁም እንደ መዘዙ ሁኔታ የቀዶ ሕክምናው አይነት ሊለያይ ይችላል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28 ቀን 2011