አንዳንዴ ሰው ሆና መፈጠሯን እስትረግም ራሷን ትጠላለች። ያሳለፈችውን መከራ መለስ ብላ ስትቃኝ ሆድ ይብሳታል ። እሷ የልጅነቷን ደስታና ፈገግታ አታስታውስም። ብሶት ለቅሶና መከራ ደጋግመው ፈትነዋታል። ያለፈችበት መንገድ እሾሀማ ነው። በየደረሰችበት እየወጋ አድምቷታል። አንዳንዴ ደግሞ ልክ እንደ ሳማ ነበር። አብዝቶ የሚያቃጥል፣ በቶሎ የማይተው ስቃይ አለው።
ከህይወቷ ስንክሳሮች ሁሉን ላስታውስ ካለች ዕንባዋ በዋዛ አይቆምም። ያለፈው ታሪኳ ተመላልሶ ይረብሻታል። ዛሬም ድረስ ያላለፈው ችግሯ ከኋላ እየተከተለ ያስጨንቃታል። ሁሌም አንገቷን ደፍታ በሀሳብ ትቆዝማለች። አሁን ደግሞ ገና በማለዳ ዕንቅልፍ እየነሳ ሆድ የሚያስብሳትን አላጣችም።
እንደልማዷ ውስጧን ካዳመጠች እንደሁሌው ይከፋታል፣ ዝም እንዳትል አትችልም፣ ውሰጧ የሚላትን እታደርግ ነገር እጅ አጥሯታል። ወፍ ሳይንጫጫ ከራሷ ትግል የምትገጥመው ሴት በውስጧ ለሚገላበጠው የርሀብ ጥያቄ ፈጽሞ መልስ የላትም። በሆዷ ነፍስ ዘርቶ በየአፍታው ለሚረግጣት ፍጡር የፍላጎቱን አትሞላም። ዕንባዋን ውጣ ርሀቧን ለማስታገስ ያላት ምርጫ አንድ ብቻ ነው። እጆቿን ለልመና መዘርጋት።
የዕለት ርሀቧን ለማስታገስ የምግብ ትርፍራፊ አታጣም። አንዳንዴ ደርሶ ውል ለሚላት አምሮት ግን መፍትሄ የላትም። ነፍሰጡር ናትና የማያምራት፣ የማይሸታት የለም። አንዳንዴ ልታገኘው ቀርቶ ፈጽሞ ልታየው የማይቻላት በዓይኗ እየዞረ፣ ሽታው በአፍንጫዋ ያውዳል። ይህኔ አይኖቿ በስስት እየቃበዙ እጆቿ ያማራትን ሊያጎርሷት ይሻሉ።
በበዛ ፍላጎት የሚቃብዘው ውስጠቷ ግን ሁሌም ‹‹ሲያምርሽ ይቅር ›› ሲል ያሳቅቃታል። አዎ ! ሁሉንም ሲያምራት ከመተው ውጭ ምርጫ የላትም። ሁሌም የሆዷን በሆዷ ይዛ ለቀን ውሎዋ ትባዝናለች። አጋጣሚው ከቀናት ለርሀቧ ታክል አታጣም። አንዳንዴ ግን ከልመናዋ ጋር የምትቀበለው ስድብና መመናጨቅ ሰው መሆኗን ያስረሳታል። የአንዳንዶች ክፉ ልማድ ራሷን ጠልታ፣ ማንነቷን እንድትንቅ ጭምር ያስገድዳታል።
ለልመና እጆች በተዘረጉ ጊዜ ከበስተጀርባ የሚከተል ችግር መልከ ብዙ ነው። አንዳንዱ ሲያመናጭቅ፤ አንዳንዱ ይራገማል፣ አንዱ ፍርድ ሲሰጥ ሌላው ለዓይን ይጠላል። ደርሰው ‹‹እንምከር ›› ባዮች ሲቀርቡ ደግሞ ኩነኔያቸው በዝቶ፣ ቃላቸው አጥንት ይበሳል።
እነሱ ከራሳቸው ሀሳብ በላይ ስሌላው ስሜት አይጨንቃቸውም። እንዳመጣላቸው እየተናገሩ ብሶትን ያግማሉ፣ ቁስልን ያደማሉ። እንዲያም ሆኖ መፍትሄ የላቸውም። ሳይላቸው ነካክተው ዕንባን ሳያብሱ፣ ህመምን ሳያክሙ እብስ ይላሉ። እንዲህ አይነቶቹ ልመናን ስለምን ሲሉ ለቀጣዩ ህይወት መላ የላቸውም። ሰውዬውን ኮንነው፣ ድርጊቱን ተቃውመው ብቻ ያልፋሉ።
አንዳንዶች ሌሎችን ጎዳና ላይ ስላዩ ብቻ በጎነቱ የላቸውም። በዚህ ህይወት ያሉ ሁሉ ሌባና ዱርዬ ይመስሏቸዋል። የጎዳና ላይ ነፍሶች ከእነሱ አቻ እንዳልሆኑ እያሰቡም የአንደበታቸውን ቃል በክፉ ሀሳብ ይመነዝራሉ። ይህ አይነቱ አጋጣሚ ጠኔ እጃቸውን አዘርግቶ፣ የሰው ፊትን ላሳያቸው ብሶተኞች መኖርን ያስጠላል፣ ከከፋ ሀዘን ይጥላል።
ቅድመ- ታሪክ
አበባ አርአያ የልጅነት ህይወቷ እንደ እኩዮቿ ሆኖ አላለፈም። ወላጆቿ ገና ጡት ሳትጥል መሞታቸውን ስትሰማ አድጋለች። ከእናት አባቷ ማለፍ በኋላ ዕጣ ፈንታዋ በዘመድ እጅ ቢወሰን ቀጣይ ህይወቷ በሰው ቤት ሆነ። በማደጎ የተቀበሏት ዘመዶቿ ነፍስ እስክታውቅ በእንክብካቤ ያዟት። ዕድሜዋ ሲጨምር ግን አልተመቻትም። በደሏ በዛ፣ ሰላሟን አጣች። ጠዋት ማታ የዘመድ ቤት ኑሮ ሆድ አስባሳት። ስታለቅስ፣ ስተክዝ መዋል ማደር ልምዷ ሆነ።
የአበባ ዘመዶች ኑሮ ከእጅ ወደአፍ የሚባል ነው። በእጅጉ ድህነት ያጠቃው ቤተሰብ ሰርቶ ማግኘትን፣ ሸምቶ መብላትን አያውቅም። ሁሉም ጠዋት ማታ የሰው እጅ አይተው፣ ለምነው ያድራሉ። የልመናው ውሎ ካልቀና ደግሞ ቀምሶም ማደር ይቸግራል።
አበባ በዘመድ ቤት ስትኖር እንደ እኩዮቿ መማር አልቻለችም። ይህን ማድረግ ብትሞክር እንኳን የአሳዳጊዎቿ አቅም ርቆ አይወስዳትም። ከሁሉም ግን ከቤቱ ልጆች አንደኛው እየደበደበ የሚያሰቃያትን ልማድ መቋቋም አልቻለችም። ልጁ ሰበብ እየፈለገ ይሰድባታል፣ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በጭካኔ ይመታታል።
አንዳንዴ ልጅቷን ጎረቤቶች ደርሰው ያስጥሏታል። እንዲህ ካልሆነ በስቃይ የምትውለው አበባ እውነቱን የሚያውቅላት አላገኘችም። ይባስ ብሎ የልጁ ችግር በእሷ ተሳቦ ጥፋተኛ መሆኗ ይነገርባት ያዘ። እየተደበደበች ደብድባለች፣ እየተሰደበች ተሳድባለች የምትባለው ልጅ ሰሚ ጆሮን አጣች። የነገሮች እንዳይሆን መለዋወጥ ባይተዋር ያደረጋት አበባ ክፉኛ አንገቷን ደፋች።
አሁን አበባና የዘመድ ቤት ህይወት እንደቀድሞው አልሆኑም። በየምክንያቱ የሚመጣው ግጭት ለእሷ ትርጉም ይኖረው ያዘ ። በየሰበቡ የሚነሱ ችግሮችን ‹‹ይሁነኝ›› ማለት አልቻለችም። ቁዘማዋ ጨመረ። ሲቆጧት እያዘነች፣ ሲቀጧት ቂም ያዘች። የኑሮዋ አለመመቸት በኩርፊያና ቅያሜ ብቻ አልቀረም። ብዙ ያሰበው ውስጧ እግሯን ለመንገድ አነሳሳቶ ልቧን ውጭ አሳደረ።
ከቤት መውጣት ያሰበችው አበባ የዕቅዷን ልትፈጽም ዕንቅልፍ ይሉት አጣች። በኋላም ካለችበት ቤት ኑሮ ይሻለኛል ያለችውን የጎዳና ህይወት መረጠች። ከቤት ወጥታ ከጎዳና ጓደኞቿ ስታድር ማንም የፈለጋት የለም። ለጊዜው የጎዳናው ዓለም ሰላም ነጻነቷን ሰጣት። በዚህ ቦታ የሚጨቀጭቅ፣ የሚያስከፋት የለም። ይህ ሲገባት ፊቷ በደስታ በራ፣ ‹‹እፎይ›› ስትል አረፍ አለች።
ጎዳናው – ውሎ አድሮ
አበባና የጎዳና ህይወት ከተዋወቁ ጊዜያት ተቆጥረዋል። አሁን በውስጧ የትናንቱ እፎይታ የለም። በጎዳና የከፋ ብርድና ቅዝቃዜ አለ። በጎዳና ዝናብና ጸሀይ ይጨክናሉ፣ በጎዳና ርሀብና ችግር ያብራሉ። ጎዳና እንደቤት አይደለም። ይህን ህይወት በብዙ ጭንቅና ስጋት፣ በበርካታ ጉስቁልናና መከራ ሊኖሩት ግድ ነው። በጎዳና የብዙ ሴት ልጆች ልብ ተሰብሯል፣ የህጻናት ህይወት ተፈትኗል። የወጣቶች ተስፋ በሱስ በመጠጡ መክኗል።
አበባ ከቤት እንደወጣች ማረፊያዋ ብሄራዊ አካባቢ ከነበረ ጎዳና ሆነ። በስፍራው ካገኘቻቸው ባልንጀሮች ብዙዎቹ ሲጋራና ጫት ይጠቀማሉ። ማስቲሽ ከቤንዚን ይስባሉ። ተጠግታ ልትመስላቸው ሞከረች። አቀራረቧ ከእነሱ አልሄድ ቢላቸው እንግድነቷን አልፈለጉም። ደርሳ ጨዋ ልምሰል ማለቷን አልወደዱትም።
እነሱ የቀረባቸውን ይመስላሉ። የመሰላቸውን ይወዳሉ። የመጀመሪያ ቀን አበባ በመሀላቸው ተገኝታ ከአንዱ ጥግ አረፍ አለች። በመምጣቷ ያልተከፉት ልጆች ከለበሱት አጋርተው፣ ከቀመሱት አጉርሰው አሳደሯት። ውሎ አድሮ ከብዘዎች ተግባባች፣ የበሉትን በልታ የሆኑትን መሆን ግድ አላት። ከሱስ ከጫቱ ዓለም ለመ ቀላቀል አልዘገየችም። የጎዳና ልጅ ከሆነች ይህን ልታደርግ ያስፈልጋል። አልያ ከመንጋው ትለያለች፣ ከሁሉ ትነጠላለች።
ከአንድ- ሁለት
አበባ በጎዳና ያሉ መሰሎቿን አስተዋለች። አብዛኞቹ በፍቅር ጥንድ ሆነው ያድራሉ። በዚህ ህይወት ጋብቻና መተሳሳብ ይሏቸው እውነቶች እንዳሉ ነው። በጎዳና ሴት ልጅ ባልና ጓደኛ ከሌላት የብዙዎች ዓይን ያርፍባታል፣ በማንም መጎተት መደፈሯ አይቀርም። ይህ እንዳይሆን አበባ ከአንዱ መጠጋት አለባት። ‹‹ባሌ›› የምትለው ‹‹ሚስቴ›› ሲል የሚጠራት አጋር ያሻታል።
በጎዳናው አበባና አንድ ሰው ለፍቅር ተፈቃቀዱ። ሁለቱም ልባቸው ለመውደድ ተገዛ፣ መተሳሰባቸው ከአንድ ውሎ እያሳደረ አብሮነታቸውን አጎላው። አሁን አበባ በዚህ ሰው ዓይን ገብታ ከክንዶቹ አርፋለች። ማንም በተለየ አስቦ ሊያጠቃት፣ ሊመኛት አይሞክርም። ብቸኝነቷ በፍቅር አጋሯ ተቀርፏል። አሁን የሚያሳስባት ቢኖር ድንገት የገባችበት የሱስ ልማድ ብቻ ነው።
አበባ በምታጨሰው ሲጋራና በምትቅመው ጫት ሳቢያ ለህመም እየተዳረገች ነው። ይህን ችግሯን ከመቻል ውጭ ግን ደፍራ መናገር አልተቻላትም። እንዲህ ልሞክር ብትል የሚቃወማት ይበዛል። የሚያነውራት ይበረክታል። ሱስ ማለት ለጎዳና ልጆች የመደበቂያ ዋሻቸው ነው። ይህን ዋሻ ያናናቀ፣ በሰበቡ ታመምኩ፣ ተቸገርኩ የሚል ቢኖር እንደ ነውረኛ ይቆጠራል። አበባ ይህን እውነት አሳምራ ታውቃለች። እናም በሱሱ ምክንያት መታመሟን ለመናገር አትደፍርም። ሁሌም ልቧን እያመማት ትቅማለች፣ ከነስቃይዋ ታጨሳለች። ለመኖር፣ ሌሎችን ለመምሰል ደግሞ እንዲህ መሆን የግድ ይላል።
የአበባ ጓደኛ ተሸክሞ፣ ለፍቶ አዳሪ ነው። ቀኑን ጉልበቱን ገብሮ ላቡን አንጠፍጥፎ ይውላል። ምሽት የሰራበትን ቋጥሮ ካገኘው አካፍሎ ከአነስተኛ ቤርጎ ቢጤ ያሳድራታል። ሌቱ ሲነጋ ሁሉም እንደልምዱ ይሰየማል። እሷ በምታመጣው ብር ጓደኞቿ እየቃሙ ያጨሳሉ፣ እያጨሱ ከቡሌው፣ ከትራፊው ይበላሉ። አንዳንዴ አበባ ያሰበችው አይሞላም። የምታመጣው ገንዘብ ለባልንጀሮቿ የማይበቃ ሲሆን ትሳቀቃለች። ሳይቀናት ቀርቶ ከእጅ በጠፋ ግዜ ውጤቱ የከፋ ነው። ከእሷ የሚጠብቁት የጎዳና ልጆች ሊያዩዋት አይፈልጉም። እየሰደቡ ያርቋታል፣ እያመናጨቁ ያባርሯታል።
ይህ አይነቱ አጋጣሚ ለአበባ በእጅጉ ፈታኝ ነበር። ከጓዳዋ ያጣችውን ሰላም ከጎዳና አላገኘችም። ከቤት ወጥታ ያረፈችበት ጥግ ከችግር አላዳናትም። አበባ በእጅጉ እየከፋት ነው። የውስጧን ያወቀ የለምና ቸግሯታል። አንዳንዴ ደርሶ ራስሽን አጥፊ ከሚል ስሜት ትገባለች። መልሳ ደግሞ የነገውን ተስፋ እያሰበች ትጽናናለች።
አንድ ቀን አበባ በህመም ከወደቀችበት ጎዳና የአንድ መልካም ሰው ዓይኖች አስተዋሏት። ይህ በጎ ሰዉ አይቷት ብቻ አላለፈም። ቀረብ ብሎ ችግሯን ተረዳ። ከሆስፒታል አድርሶም በወጉ አሳከማት። ችግሯ የልብ ህመም መሆኑን ያረጋገጠው ሀኪም በክትትል እንድትቆይ አደረገ። ሰውዬው የመድሀኒቱን ሙሉ ወጪ ከፍሎ ከህመሟ አዳናት። ከስቃይዋ መለስ ስትል ራሷን ባሏ ጉያ አገኘችው። ዳግመኛ ፍቅራቸው ደራ ትዳራቸው ጀመረ።
አበባ የመጀመሪያ ልጇን ጎዳና ላይ ወልዳ አሳደገች። ሁለተኛ ልጇም ከዚህ ዕጣ አላለፈም። በጎዳና ተወልዶ በጎዳና አደገ። ህይወት ከቀድሞው በባሰ የከፋባት እናት አበባ ልጇቿን ለማሳደግ ባዘነቸ። ትናንት አብሯት የነበረው የልጆቿ አባት በድንገት የደረሰበት ቢጠፋት ችግሮችን ለብቻዋ ተጋፈጠች። ከራሷ አልፎ ለልጆቿ ጉሮሮ ለመድረስም ሌት ተቀን ለፋች፣ ሮጠች።
ከጥቂት ጊዚያት በኋላ አበባ ሶስተኛ ልጇን ታቀፈች። ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ›› እንዲሉ ሆኖ የዚህኛውም ወላጅ አባት በሞት ተለያት። ለአበባ ሶስት ልጆችን ያለ አባት ማሳደጉ በእጅጉ ይከብዳል። እንዲያም ሆኖ ችግሯን ለመቋቋም ትከሻዋ ሰፊ ሆኖ የመከራ ቀናትን ተሻግራለች። አሁንም አልፎ ያላለፈው ችግሯ ከእሷው ተጣብቆ አብሯት ቀጥሏል።
ዛሬን- ስለነገ
ጠዋት ማታ በተስፋ የምትኖረው አበባ ከጎዳና የምትወጣበት ቀን እስኪመጣ የእሷ መከራ በልጆቿም ጭምር ሲያልፍ ቆይቷል። አበባን ብዙዎች በማንነቷ ያውቋታል። በተለይ ተወልዳ ባደገችበት አካባቢ ችግሯን አውቀው የሚያዝኑላት ጥቂቶች አይደሉም። እንዲህ መሆኑ ስምንት ዓመታትን በስቃይ ከኖረችበት የጎዳና ህይወት ለመውጣት ምክንያት ሆኗል።
አበባን ከልጅነቷ አንስተው የሚያውቋት የአካባቢው ሰዎች ወደቀድሞ መኖሪያ ቤት እንድትገባ አግዘዋታል። አሳዳጊ አክስቷ መሞታቸውን ተከትሎ የቀበሌ ቤቱን ትኖርበት ዘንድም የብዙ ሰዎች እጅ ተባብሯታል።
ዛሬ የትናንቷ አበባ ልጅነቷን ካሳለፈችበት ቤት ተመልሳ ልጇቿን በጣራ ስር ማሳደር ችላለች። ቀድሞ ተገፍትራ ከተባረረችበት ጎጆ ተመልሳም አዲስ ህይወትን ጀምራለች። አሁንም ግን በወጉ ልጇቿን አብልቶ ለማሳደር አቅሟ ደካማ ነው።
በልደታ አካባቢ በተገነባው የተስፋ ብርሀን የምገባ ማዕከል በቀን አንዴ ብቅ እያለች የተሰጣትን ለልጆቿ ታቀምሳለች። አበባ እስከዛሬ ህይወትን ከእነሾሁ ተቀብላው ኖራለች። ረጅሙንና ፈታኙን መንገድ በድል እየተወጣች ዛሬ ላይ ስትቆም ደግሞ ስለነገው ድካምን አታውቅም። ህይወትን ለማሸነፍ፣ ኑሮን ታግሎ ለመጣል በሩጫ ላይ ነች። በፈጣን የሩጫ ሜዳ ላይ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2015