የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ የኖረው የግብርናው ዘርፍ አሁንም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ ቀጥሏል። ከአገሪቱ ህዝብ አብዛኛው የሚተዳደረው በግብርና ስራ መሆኑ እንዳለ ሆኖ የአገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት ዘርፉ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ዘርፉ የአገር ውስጥ የግብርና ምርቶች ፍላጎትን በማሟላት ከፍተኛ ሚና ከመጫወት በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ መሆኑን ቀጥሏል። በተጠናቀቀው 2014 በጀት ዓመት አገሪቱ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ካገኘችው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ መጠን ያለው ገቢ ያስገኘው ይሄው የግብርናው ዘርፍ ነው።
ለውጭ ገበያ ከተላኩ የግብርና ምርቶች መካከልም ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት እየታወቀ ያለው ቡና ነው። ቡና ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ጉልህ ስፍራ ይዞ የቆየ ሲሆን፣ ባለፈው በጀት ዓመት ከቡና የወጪ ንግድ ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር በላይ ተገኝቷል። ይህም በቡና የወጪ ንግድ ታሪክ የመጀመሪያው ስኬት ለመባል በቅቷል።
በቡናው ዘርፍ እየተመዘገበ ላለው ውጤት መንግስት፣ በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮች፣ አቅራቢዎች፣ ቡናውን አዘጋጅተው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ላኪዎች ጉልህ ድርሻ አላቸው። በተለይ የኢትዮጵያ ቡና በመጠንና በጥራት ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል ብሎም በዓለም ገበያ ከፍ ያለ ዋጋ እንዲያወጣ እየተከናወነ ባለው ተግባር፤ ከአርሶ አደሩ ጋር በመሆን ሌት ተቀን ከሚተጉ በርካታ አካላት መካከል ዳዬ በንሳ ቡና ላኪ ድርጅት አንዱ ነው።
ድርጅቱ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በቡና ንግድ ላይ ቆይቷል፤ ካለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የቡና የንግድ ስራው በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መጥቷል። በአሁኑ ወቅትም በቡና ልማትና ግብይት እንዲሁም እሴት በመጨመር ዘርፉን ለማሳደግ የረጅምና የአጭር ጊዜ ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ቡናን በብዛትና በጥራት አዘጋጅቶ ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ቀዳሚ ከሆኑት ተርታ በመሰለፍ ተሸላሚ የሆነው ዳዬ በንሳ ቡና ላኪ ድርጅት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ቡና በብዛት አምርቶ ወደ ውጭ ገበያ በመላክ እና በጥራት ተሸላሚ መሆን ችሏል። በአገሪቱ በቅርቡ በተጀመረው የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ወድድር ባለፉት ሁለት ዓመታት ቶፕ ቴን ውስጥ ገብቶ የነበረው የዳዬ በንሳ ቡና ድርጅት፤ በ2014 ዓ.ም ለሶስተኛ ጊዜ በተደረገው ውድድር ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ተሸላሚ ሆኗል።
የድርጅቱ መሥራችና ባለቤት አቶ አሰፋ ዱካሞ ከሃያ ዓመታት በፊት ወደ ቡና ልማትና ለወጪ ገበያ መላክ ንግድ ከመግባታቸው በፊት ጫማ በማሳመር /የሊስትሮ ሥራ/ ተሰማርተው ሰርተዋል፤ በዱቄትና ሌሎች የንግድ ሥራዎችም ተሰማርተው ሰርተዋል። ከተሰማሩባቸው የንግድ ሥራዎች የቡና ንግድ አዋጭ ሆኖላቸው ቡናን ከማምረት ጀምሮ ለውጭ ገበያ እስከ ማቅረብ ደርሰዋል። አቶ አሰፋ ወንድማቸውን አቶ ሙሉጌታ ዱካሞን እና ሁለተኛ ትውልድ የሆነው ልጃቸው ወጣት ከንአን አሰፋን ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ በማድረግ ሥራቸውን ውጤታማ ማድረግ ችለዋል።
በለጋ ዕድሜው የቡና ንግድን የተቀላቀለውና ሁለተኛ ትውልድ የሆነው ከንአን አሰፋም ድርጅቱ እያስመዘገበ ላለው ውጤት የጎላ ድርሻ እያበረከተ እንደሆነ አጫውቶናል። ማንኛውም ሥራ በዕውቀት ሲመራ አመርቂ ውጤት ማምጣት እንደሚችል የሚያምነው ከንአን፤ በዕውቀት ተመስርቶና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የምርት፣ የጥራት፣ የኤክስፖርትና አጠቃላይ የውጭ ገበያውን ዘርፍ በመምራት የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል። ወላጅ አባቱ አቶ አሰፋ ዱካሞና ወንድማቸው አቶ ሙሉጌታ ዱካሞ ደግሞ ቡና በማምረት ስራ ተሰማርተዋል።
ቡናን አምርቶ ከመሸጥ ባለፈ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ጠቀሜታ በመረዳት ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚቻል የሚናገረው ከንአን፣ በቡናው ዘርፍ እሳተፋለሁ የሚል ሃሳብ አልነበረውም፤ ወላጅ አባቱ በቡና ልማትና ግብይት ውስጥ የነበራቸውን ትጋትና ለውጥ ሲመለከት ግን ዘርፉን ለመቀላቀል አላመነታም። በተለይም የኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርቱን ለመከታተል አሜሪካ በሄደበት አጋጣሚ የኢትዮጵያ ቡና ያለውን ተቀባይነትና ዋጋ ይረዳል። በመሆኑም በውጭው ዓለም የቤተሰቡን የቡና ድርጅት ቡና በመሸጥ ድርጅቱን ሲያግዝ ቆይቷል።
ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላም ድርጅቱን በሙሉ ጊዜው በማገልገል ውጤታማ እንዲሆን ሲሰራ ቆይቷል። የገበያ ልማቱን በቴክኖሎጂ በማዘመን፤ አዳዲስና ቀልጣፋ አሰራሮችን በመዘርጋትና ወጣቶችን አሰልጥኖ ወደ ሥራ በማምጣት ለውጥ ማስመዝገብ ጀመረ። ይህ ጥረቱም ድርጅቱ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ በአራትና አምስት እጥፍ እንዲያድግ ምክንያት መሆኑን ይናገራል። የዛሬ ሶስት ዓመት ድርጅቱ ለውጭ ገበያ ከሚያቀርበው ቡና በዓመት ስምንት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኝ ነበር። በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ በዓመት 37 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ችሏል።
ድርጅቱ በሲዳማ ክልልና በከፋ አካባቢ ባለው የቡና እርሻ ቡና ያለማል፤ በሲዳማ ክልል ከሚገኙ በርካታ ገበሬዎችም ከፍተኛ መጠን ያለው የቡና ምርት ይሰበሰባል። ከ45 እስከ 50 ሺ ከሚደርሱ የአካባቢው ገበሬዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና የሚሰበሰብ ይሆናል።
በሲዳማ ክልል በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎችም 71 የሚደርሱ የቡና መፈልፈያ ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን፣ በእነዚህ ጣቢያዎችም ቡናው ተሰብስቦ፣ ተፈልፍሎና ደርቆ ወደ አዲስ አበባ ይላካል። አዲስ አበባ የደረሰው ቡናም አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎለት ለውጭ ገበያ የሚላክ ይሆናል።
ከድርጅቱ ጋር ትስስር ፈጥረው ያመረቱትን ቡና ለድርጅቱ እያቀረቡ ከሚገኙ 50 ሺ ገበሬዎች በተጨማሪ 2500 የሚደርሱ ገበሬዎች ደግሞ የድርጅቱ አባላት ሆነው ቡና አምርተው እንደሚያቀርቡ ያጫወተን ከንአን፤ እነዚህን አርሶ አደሮች ድርጅቱ እያንዳንዳቸውን በስም ከማወቅ ባለፈ ምን ያህል ቡና እንደሚያመርቱ ጭምር እንደሚያውቅና ጥብቅ ግንኙነት እንዳለውም ያብራራል። ድርጅቱ ከእነዚህ አርሶ አደሮች ቡና የሚገዛው ከገበያው ዋጋ ከፍ ባለ እንደሆነም አጫውቶናል። ድርጅቱ የእነዚህ አርሶ አደሮች በቡና ልማቱ ምርታማ እንዲሆኑ ችግኝ በመስጠት፣ የግብርና ባለሙያዎችን በመመደብ ሙያዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ያደርጋል።
ድርጅቱ ቡና አምርቶ ወደ ውጭ ገበያ ከመላክ ባለፈ ዘርፉን ለማጎልበት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑንም ወጣት ከንአን ይጠቁማል፤ በዓለም ዙሪያ ያሉ ቡና ገዢዎች በየጊዜው የተለያየ አይነት አመራረት እንደሚፈልጉ ጠቅሶ፣ ይህን ታሳቢ ያደረገ ከጊዜው ጋር ሊሄድ የሚችል ሥራ በመሥራት የደንበኞችን ፍላጎት ማርካት የግድ ነው ይላል። ለዚህም ከዛሬ ሶስት ዓመት ጀምሮ ድርጅቱ በየዓመቱ 10 ልጆችን በማሰልጠን የተሻለ ውጤት ያመጡትን እየቀጠራቸው መሆኑን ይገልጻል። በዚህ በጀት አመት ደግሞ 20 ወጣቶችን ለማሰልጠን አቅዷል፤ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ደግሞ 100 ለሚደርሱ ወጣቶች ስልጠናውን በመስጠት ቡና በዕውቀት እንዲመረትና ለውጭ ገበያ እንዲዘጋጅ እንደሚሰራም አስረድቷል።
ቡና በማምረትና በኤክስፖርት ሥራ የተሰማራው ዳዬ በንሳ ቡና ላኪ ድርጅት፣ በኤክስፖርት ሂደት ውስጥ 110 ለሚደርሱ፣ እንዲሁም በማምረት ሂደት ውስጥ ለ250 በድምሩ ለ360 ሠራተኞች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ነው። ቡና በሚደርስበት ጊዜ ደግሞ 150 የሚደርሱ ጊዜያዊ ሠራተኞችን ወደ ሥራ ያስገባል። እነዚህ ሠራተኞችም በሲዳማ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ 71 የቡና መፈልፈያ ጣቢያዎች ቡና ተዘጋጅቶ ወደ አዲስ አበባ እንዲጓጓዝ የሚያደርጉ ናቸው። ተጓጉዞ አዲስ አበባ የደረሰው ቡናም ተበጥሮ፣ ተለቅሞና ታሽጎ ለውጭ ገበያ የሚላክ ይሆናል።
በሲዳማ ክልል ሰፋፊ የቡና እርሻዎች አለመኖራቸውን የጠቀሰው ከንአን፤ በትናንሽና በተበጣጠሰ የአርሶ አደር መሬት ቡና እንደሚለማ ይናገራል፤ በዚህ ሂደት ውስጥ እየሰራ ድርጅቱ በየጊዜው የሚያመርተውን የቡና መጠንና ጥራት በማሻሻል ተሸላሚ መሆን እንደቻለ ይናገራል። ባለፉት ዓመታት በዓመት ከስድስት ሺ አምስት መቶ እስከ ሰባት ሺ ቶን ቡና ወደ ውጭ ገበያ ይልክ እንደነበር በማስታወስ፤ በ2015 ዓ.ም 50 ሚሊዮን ኪሎ ግራም እሸት ቡና ለመሰብሰብ እንዲሁም 10 ሺ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ለመላክ አቅዶ እየሰራ መሆኑን አጫውቶናል።
የድርጅቱ የገበያ መዳረሻ አሜሪካ፣ ጀርመንና ኮሪያን ጨምሮ 25 የሚደርሱ የዓለም አገራት መሆናቸውን የተጠቀሰ ሲሆን፣ በቀጣይም ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግና ጥራት በመጨመር የገበያ መዳረሻቸውን ለማስፋት አቅዷል። ዓለም ላይ ትላልቅ ስም ካላቸው እንደ ስታር ባክስና ንስሌም ከሚባሉ ድርጅቶች ጋር በቀጥታ የገበያ ትስስር መፍጠርም ችሏል። ገበያውን በማስፋት የኢትዮጵያን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ገቢ በበለጠ አገርን በማስተዋወቅ ረገድ ቡና የጎላ ድርሻ እንዳለውም ከንአን ይናገራል።
‹‹ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሆና ቡና በተፈጥሮ የተሰጣት ስጦታ ቢሆንም፣ በሚገባን ልክ ግን አልተጠቀምንበትም›› የሚለው ከንአን፣ ቡና በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የመቶ ቢሊዮን ዶላር ኢንዱስትሪ እንደሆነና በቀጣይ ጥቂት ዓመታትም እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ የሚችል ኢንዱስትሪ እንደሆነ መረጃዎችን ጠቅሶ ያስረዳል። ከዚህ ውስጥ የቡና ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ያላት ድርሻ አንድ በመቶ ያህል እንደሆነም ጠቅሶ፣ የኢኮኖሚ ድርሻዋም በዛው ልክ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን በቁጭት አስረድቷል።
ለቡና ሥራ ቅርብ ከሆነ ቤተሰብ የተገኘው ከንአን፤ በተለይም በውጭ አገር ቆይታው ለቡና ያለውን እውቀት በማስፋት ዓለም ምን እንደሚፈልግ መረዳት ችሏል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ቡና አብቃይ አገር እንደመሆኗ በዘርፉ ብዙ ልትጠቀምበት እንደሚገባ በማመን አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን በተለይም ዘርፉን በእውቀት መምራት ላይ አበክሮ እየሠራ ይገኛል። ለዚህም ድርጅቱ በቀጣይ ትምህርት ቤት በመክፈት ስለ ቡና የማስተማር ዕቅድ እንዳለው አስረድቷል። በዚህም ቀጣዩ ትውልድ ቡናን አምርቶ ከመላክ ባለፈ በቡና ዙሪያ ያለውን ዕውቀት በመሸጥ ጭምር ገቢ ማግኘት እንደሚችል ነው ያመለከተው።
ቡና ከእርሻ ጀምሮ እስከ ካፌ ድረስ ያለውን ሂደት ለማስፋት ትምህርትና ስልጠና ለመስጠትና ዘርፉን በእውቀት ለመምራት የተዘጋጀው ዳዬ በንሳ ቡና ላኪ ድርጅት፣ በአሁኑ ወቅት እሴት በመጨመር ቡና ቆልቶ ለአገር ውስጥ ገበያ እያቀረበም ይገኛል። በቀጣይም ዘርፉን በማስፋት ለውጭ ገበያ የማቅረብና በአገር ውስጥም ካፌ የመክፈትና በውጭው ዓለም የሚቀርበውን አይነት የካፌ ቡና የማቅረብ ዕቅድ ይዞ እየሠራ ነው። በቅርቡም ሀዋሳ ላይ የመጀመሪያውንና ደረጃውን የጠበቀ ካፌ ለመክፈት ዝግጅቱን አጠናቅቋል።
ድርጅቱ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ የሲዳማ ክልል በንሳና አርቤጎናን ጨምሮ በአራት ወረዳዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ እያጠናቀቀ ነው። የትምህርት ቤቶቹንም ግንባታ በዚህ ዓመት በማጠናቀቅ ለመንግሥት እንደሚያስረክብም ከንአን ይጠቁማል። ድርጅቱ የመንገድ፣ የውሃና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ለማህበረሰቡ እያበረከተ መሆኑን ተናግሯል። በቀጣይም ዘላቂነት ባለው መንገድ አርሶ አደሩን በማገዝ፣ በማበረታታትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ራሱን እንዲለውጥ ለማድረግ ይሠራል ብሏል።
በቂ የሆነ የገበያ ተደራሽነት ያለው ዳዬ በንሳ ቡና ላኪ ድርጅት፤ በረጅም ጊዜ ዕቅዱ ከኢትዮጵያ ቡና በተጨማሪ በሌሎች አገራትም ቡናን አምርቶ ለገበያ በማቅረብ ዓለም አቀፍ ድርጅት የመሆን ራእይ አለው። ይህን ሃሳቡን እውን ለማድረግም ድርጅቱ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን የጠቀሰው ከንአን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ በመሆን የአፍሪካ ኩራት እንደሆነ ሁሉ በቡናው ዘርፍ ደግሞ ዳዬ በንሳ ቡና ላኪ ድርጅት ዓለም አቀፍ ድርጅት በመሆን ለሌሎች ምሳሌ ለመሆን እየተጋ እንደሆነም አጫውቶናል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2015