“በቅናት ውስጥ አትገኝ፤ በሕይወት ጉዞ ውስጥ አንዳንዴ ትቀድማለህ አንዳንዴም ትቀደማለህ” ይህን ያሉት ሜሪ ሽሚች (Mary Schmich) የተባሉ የሃርቫርድ ምሩቅ ጋዜጠኛና ደራሲ ናቸው። መቅደምና መቀደምን አስልቶ የሚነግር አወዳዳሪ በሌለበት ነገር ግን የተቀደምን ወይንም የቀደምን የሚመስለን የራሳችን ስሌት ቅንዓት ከተሰኘው ፌርማታ ላይ አድርሶን ራሳችንን ልናገኘው እንችላለን። ቅንዓት በልባችን ውስጥ ቦታን ሲይዝ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽእኖ ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ጥናቶችን እያጠኑ የሰው ልጅ ከመርዝ ራሱን እንዲጠብቅም ይመክራሉ።
መንደርደሪያ ታሪካችን ውስጥ እንለፍ፤
በጥቃቅን በሚባል የሱቅ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሁለት ጎረቤታም ወጣቶች ናቸው። አንደኛዋ የሞባይል ቻርጀርና የጆሮ ማዳመጫ (ኤርፎን) የምትሸጥ ስትሆን ጎረቤቷ ደግሞ የባልትና ውጤቶችን ትሸጣለች። ሁለቱም በማለዳ ሱቃቸውን የሚከፍቱ አመሻሽተው ወደ ቤታቸው የሚሄዱ አብረው ሳምንታዊ እቁብ የሚጥሉ የሥራ ባልደረባ ናቸው።
አንዳቸው ስሌላቸው ስራ አንስተው የሚያደርጉት ወሬ ቀስ በቀስ በልባቸው ውስጥ የቅንዓት መንፈስን የሚፈጥር እየሆነ ነበር። የባልትና ውጤት አቅራቢዋ የራሷን ስራ ለማዋደድ፤ ባልትና ለሰው የሚሆን ምግብ ነው፤ ያለ ባልትና የሚሰራ ስራ የለም፤ ያለ ባልትና እንዴት ሆኖ የሰው ልጅ የአመጋገብ ሥርዓቱን ሊያስብ ይችላል። ወዘተ በማለት የባልትና ውጤት ላይ መሰማራት ስላለው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ታብራራለች። ጎረቤቷ ደግሞ ስልክ በዚህ ዘመን ስላለው ቦታ፤ ሁሉም እንቅስቃሴ ከስልክ ጋር የተገናኘ መሆኑን፤ ስልክ ደግሞ ያለ ሞባይል ቻርጀር ምንም መሆኑን ታነሳለች። የኮሌጅ ተማሪዎች የራሳቸውን የትምህርት ዘርፍ አዋደው በማቅረብ እንደሚያደርጉት ፉክክር፤ ህጻናትም በተመሳሳይ ሁኔታ ባላቸው ነገር ሌላኛውን ለማስቀናት የሚሄዱበት የእንቁልልጭ አይነት መንገድ።
ሁለቱ ጓደኛሞች እንደ ቀልድ ሁሌም የሚያነሱትን የባልትና ውጤትና የሞባይል ተጓዳኝ ስራን ፉክክር የሚመለከት አንድ የጋራ ጓደኛቸው አንድ ቀን፤ እናንተ እኮ “ቅንዓት ሲመቸው” ናችሁ አላቸው። ቅንዓት ሲመቸው ማለት ሰው የፈለገውን ሥራ እየሰራ ነገር ግን ሌሎች በሚሰሩት ስራ የሚቀና ሆኖ የሌሎችን ሥራ በማጣጣል በውስጡ የሚሰማውን የቅንዓት ስሜት የሚያስታግስበት ማለት ነው አላቸው። ሁለቱም የጎረቤታቸውን ትርጉም እንደማይቀበሉ ነገሩት። እነርሱ መካከል ቅንዓት እንደሌለም አስረዱት፤ ለጨዋታ ሲባል የሚያቀርቡትን ነገር እንደ ቁምነገር ወስዶ እንዳከረረውም ነገሩት። እርሱ ግን ከልቡ ነበርና በሃሳቡ ጸና።
የመንደርደሪያ ታሪኩን ወደ ቀን ተቀን ውሏችን እናምጣው። በምንሰራበት የሥራ ቦታ እርስ በእርስ ባለን ግንኙነት ውስጥ ቅንዓት ሲመቸው እንዴት እንደሚታይ እንመርምር። በቤተሰብ መካከል ከወንድሞቻችንና እህቶቻችን መካከል ባለን ግንኙነት ውስጥ ቅንዓት ሲመቸው እንዴት ሥጋ ለብሶ እንደሚታይ እንመልከት። ቤተዘመድ ለደስታም ሆነ ለሃዘን በሚገናኝበት ጊዜ የሚኖረው የመገፋፋት ሆነ የመቀራረብ ስሜት ትርጉሙን እናጢነው። የቅንዓት ጉዳይ በሰፊው በቀን ተቀን ሕይወታችን ውስጥ ቦታ እንዳለው የተለያዩ ጥናቶች ያረጋገጡት እውነታ ነውና ወደ ውስጣችን ተንፍሰን በምን ያህል እንደጎዳንም እንመርምር። በባልና ሚስት መካከል ያለው ቅንዓት ደግሞ ትርጉም ከፍ ያለ የግንኙነት ችግር ሆኖ የሚገኝም ነው።
ሁለቱን ባለ ሱቅ የቅንዓት ሲመቸው ማሳያዎችን የጋራ ጓደኛቸው እንዲህ አላቸው “የተመቸንን ስራ በገዛ ፈቃዳችን መርጠን እየሰራን ሌሎች መርጠው በሚሰሩት ስራ ላይ አይናችንን ማድረግ አይገባም” ሲልም መከራቸው።
ዝርዝሩን አለማወቅ
የሌሎችን ሥራ ተመልክተን ከራሳችን ጋር በማነጻጸር ውስጥ ለስራችን አነስተኛ ግምት እንድንሰጥ በሌሎች እንድንቀና የሚያደርገን አንዱ ነገር ዝርዝሩን አለማወቅ ይሆናል። ከሩቅ ሆኖ አንድን ሥራ ስንመለከተው በቀላሉ የሚሰራ እንደሆነ እናስባለን። ስራውን ጠጋ ብለን ስንመለከት፤ ሥራውን ለመስራት ጥረት ስናደርግ ግን ዝርዝሩ ውስጥ ያለውን ሰይጣን እንጋፈጠዋለን። ሥራን መሰረት ያደረጉ መቀናናቶች የከፋ ጉዳት በግንኙነት ውስጥ በማይፈጥሩበት ደረጃ ውስጥ ሊገኙ ቢችሉም የራስን ስራ አሳንሶ የሚያሳይ ሆኖ ሊገኝ ይችላል።
ሥጋ ቤት ያለው ሰው ስራውን ከጋራዥ ቤት ጋር ሲያወዳድር እኔ ያለሁበት ዘርፍ ይህን ያህል አድክሞኝ ይህን ያህል አውጥቶ አውርዶኝ ሲል፤ ጋራዥ ቤቱ ደግሞ ከትምህርት ቤት ጋር አነጻጽሮ ትምህርት ቤት ቁጭ ብሎ ገንዘብ ማፈስ እንደሆነ ሲረዳ፤ ትምህርት ቤት ከቡና ሻጩ ጋር አወዳድሮ የራሱን ትርጉም ሲሰጥ፤ ቡና ሻጩ ከሪል ስቴት ጋር አወዳድሮ ለራሱ ስራ ተራ ትርጉም ሲሰጥ ወዘተ ዝርዝሩን አለማወቅ የፈጠረው ቅንዓት ይወለዳል።
የቅንዓት ስሜቱ ከውሳኔዎቻችን ጀርባ የሚገኝ፤ ሰዎች በጀመሩት ነገር ላይ አተኩረው እንዳይጸኑ የሚያደርግ ሁሌም ከአንድ ዘርፍ ወደ ሌላ ዘርፍ እየዘለሉ እየሄዱ አተኩረው በአንድ ነገር ላይ ውጤት እንዳያመጡ የሚከለክል ነው።
በመንገድ ላይ ከምናስተውላቸው ነገሮች መካከል አንዱ በመኪና ላይ ተጽፎ የሚገኙ ጽሁፎችን ነው። በመኪና ላይ ተጽፈው የሚገኙ ጽሁፎች አስቂኝ፣ አዝናኝ እንዲሁም በማህበረሰብ ውስጥ ያለውን ማህበረሰባዊ አስተሳስብን የሚያሳዩ ሆነው እናገኛቸዋለን። እንደ ማህበረሰብ ሃዘንንም ሆነ ደስታን በተለያዩ መንገዶች የማስተዋወቅ ልማድ ያለን መሆኑ ይታወቃል። እረኞች በዜማ ሃሳባቸውን ያንጸባርቃሉ። የበዓል ቀናት ላይ የሚቀርቡ ባህላዊ ጭፈራዎች ከፖለቲካዊ እስከ ልዩ ልዩ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ድረስ መልእክት የሚተላለፍባቸው መሆኑ ይታወቃል። ስለ ቅንዓት የሚናገሩ የታክሲ ውስጥ ልጥፎችን እናያለን። አንዳንዱ ከመኪናው ጀርባ ላይ ስለሚቀኑበት ሰዎች ይጽፋል። በማህበራዊ መስተጋብራችን ውስጥ ያሉ ህጸጾች ተጽፈው እናነባለን። ስለ ቅንዓት፤ ስለ ፍቅር፤ ስለ ማሴር፤ ስለ ምቀኝነት ወዘተ።
በሌሎች ሥራ፣ ውበት፣ ትዳር፣ ትምህርት ወዘተ ላይ የሚፈጠር የቅንዓት ስሜት ለምን ሊፈጠርብን እንደሚችል እንጠይቅ። እንዲሁ ለምቀኝነት ወይንስ ራሳችን አንሰን እንዳለን በመመልከት። ቅንዓት በስፋት በሚገኝበት ቦታ ላይ ምቀኝነት ቤቷን ሰርታ ስለመገኘቷ ጥርጥር የለውም።
ቅንዓት የወለደችው ምቀኝነት
ሸገር 102.1 ከሰሞኑን ከተላለፉት መሰናዶች መካከል አንዱ በአዲስ አበባ ስለሚገኝ የምቀኞች ሰፈር ይመለከታል። የሰፈሩ አባላት ራሳቸውን ምቀኛ እንደሆኑ እየገለጹ ስለሰፈራቸው ያብራራሉ። የሰፈሩ አባላት ምቀኞች መሆናቸውን ለጋዜጠኛው ምላሻቸውን ሲሰጡ ይደመጣል። መመቅኘት አንዱ በአንዱ ላይ መሸረብ የሰፈሩ ሰዎች ባህሪ መሆኑን ይናገራሉ። ወሬው ትኩረት የሚስብ ነው። ጋዜጠኛው እንዴት ይህ ሊሆን እንደቻለ ጥያቄ ሲያቀርብ ያገኘው ምላሽ ወደ ደርግ ጊዜ በምናብ መሄድን ይጠይቃል። በደርግ ዘመን ነዋሪው መሰረታዊ ፍጆታዎቹን በራሽን ከመንግሥት ለመቀበል ይሰለፋል። ሰው ሁሉ ተሰልፎ በሚገኝበት ቦታ ላይ የእዚያ ሰፈር ሰዎች ጣልቃ ለማስገባት ፍቃደኛ ስላልሆኑ እርስ በእርሳቸው የሚመቀኙ አድርገው ራሳቸውን ቆጠሩ። የሌላ ሰፈር ሰዎች ሌላውን ለማስቀደም ፍቃደኝነት የሚታይባቸው መደጋገፍ ያለባቸው ሲሆኑ የምቀኛ ሰፈር ሰዎች ግን ወይ ፍንክች ስለሚሉ ለራሳቸው እኛ ምቀኞች ነን በማለት የሰፈራቸው ስም መጠሪያ አደረጉት። መጠሪያውም እስከ ዛሬ ድረስ ዘልቆ ለራዲዮ ዘገባ በመብቃቱ ሰማነው።
በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፉ ሰዎች ምን ቢሆን ይሻላል ትላላችሁ? ተብለው ሲጠየቁ ሁሉም ያስተላለፉት መልእክት አስደሳች ነበር። ሁሉም ምቀኝነት ኮነኑ፤ ሁሉም መተጋገዝ ለሰው ልጆች አስፈላጊ እንደሆነ አስረዱ፤ ሁሉም በዚህ ዘመን በመተጋገዝ እንጂ በመመቀኛኘት መሻገር እንደማይችል ድምጻቸውን አሰሙ። አንድ እናት ግን ሰፈሩ ሙሉ ለሙሉ መፍረስ አለበት ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጡ። የምቀኞች ሰፈር የሚባለው ከየት እስከየት እንደሆነ አመልክተው የምቀኝነት ታሪክ እንዲዘጋ ሰፈሩ መፍረሱ መፍትሔ እንደሆነ ተናገሩ። እዚህ ጋር ጥያቄ እናንሳ፤ በትውልድ መካከል እየተላለፈው የመጣው የምቀኞች ሰፈር የምቀኝነት ሕይወት እንዴት ተጀመረ? ከሚለው ጥያቄ ጀርባ በምን ያህል ርቀት ቅንዓት እንደምትገኝ እንጠይቅ።
ቅንዓት ያደረብን ነገር እንዲሳካለት ካለመፈለግ የተነሳ የምናደርገው ነገር ምቀኝነትን ያስከትላል። በእያንዳንዱ ውሳኔያችን ውስጥ ምቀኝነት እየተተገበረ እንደሆነ በመጠየቅ ከሰዎች ጋር ያለንን መስተጋብር ማስተካከል ለራሳችን ስንል አስፈላጊ ነው። መፍትሔውም የቅንዓት ገመድ ከልባችን በምን ያህል ርቀት ላይ እንደሚገኝ መመርመር።
ከልባችን ምን ያህል የራቀ ነው
ብዙ ሰው ከካንሰር በላይ የሚሞተው በቅንዓት እንደሆነ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች የጠቀሱትን አንብበናል። ቅንዓት ከበሽታዎች ዝርዝር ውስጥ የሚመደብ መሆኑንም ያስረዳል። ሰዎች በእኛ ላይ በቅንዓት ቢነሱ አንፈልግም። በምንሰራው ስራ ላይ በምቀኝነት የሚነሳም እንዲኖር ፈጽሞውኑ መሻታችን አይደለም። በምናደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ ተጽእኖው እንዳያድርብን እንፈልጋለን። ቅንዓትም ሆነ ምቀኝነት ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆነው በሕይወታችን ውስጥ ቦታ ባይኖራቸው እንፈልጋለን። ወደ መፍትሔው እንሂድ ስንል የምናገኘው ምላሽ ከልብ ጋር የተገናኘ ነው፤ ልብን ማንጻት።
እያንዳንዱ ሰው ልቡን የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት። ምቀኝነት ከልባችን በምን ያህል ርቀት ላይ እንደሚገኝ መረዳት አስተዋይነት ነው። የማህበረሰባዊ አኗኗራችን እና ስሪታችን ምን መሆን እንዳለበት በመረዳት ቅንዓትንም ሆነ ምቀኝነትን በአግባቡ ማድረግ ይኖርብናል። የሰዎች እድገት ውስጥ ትምህርት የሚሆነን ከመፈለግ ባሻገር ጠልፎ መጣልን ማሰብ ተገቢነት የለውም። ሰዎች አልሳካላቸው ሲል የሚሰማን ደስታ ይኖር ይሆን? የሰዎች ገመና በአደባባይ ሲወጣ ወሬውን ስንቀባበል በውስጣችን የሚፈጥረው ስሜትስ ምን ይሆን? ልባችንን በታማኝነት በጥንቃቄ ስንጠይቅ ለዚህ ምላሽ ትክክለኛ መልስ እናገኛለን። የሰዎች ውድቀትን ለማውራት የምንፈጥነው ደስ ስለሚለን ይሆን?
እነዚህ ጥያቄዎች ለራስ ግልጸኛ በመሆን ውስጥ ምላሽ የሚፈልጉ ናቸው፤ ከልብ ጋር አብሮ በመምከር ያለንበትን ሁኔታ መረዳት እንድንችል የሚያደርገን። ሰው ከሰው ጋር አብሮ የሚሰራ፤ አብሮ የሚበላ፤ አብሮ የሚኖር፤ አብሮ ችግርንም ሆነ ደስታን የሚያሳልፍ እንደመሆኑ በአብሮነት ውስጥ ዋጋን የሚያሳጡ አላስፈላጊ ባህሪዎችን ማስወገድ አለብን። እርስ በእርስ የሚኖር የኑሮ ውድድር ወዴት የሚያደርሰን እንደሆነ መመርመር ያስፈልጋል። ባለን ነገር እርካታ እንዳይሰማን ሁሌም ሌላው የያዘውን ነገር አድንቀን የምንይዝ ሆነን እንዳንገኝ ልናስብ ይገባናል።
ነገሮች ከልባችን ጋር ባላቸው ርቀት መመልከት አዋጭ የሚሆንበት ዋና ምክንያት ልባችን ውስጥ የሞላውን ለመኖር በብዙ ትኩረት የምናደርግ ስለሆነ ነው። እንደ ማንኛውም ሰው ስኬትን እንፈልጋለን። እንደማንኛውም ሰው ያሰብነውን አሳክተን ማለፍን እንፈልጋለን። እንደ ማንኛውም ሰው ስንወድቅ መነሳትን፤ ስንዝል መበርታትን፤ ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ በዚያው አለመቅረትን፤ በፈተና ብዛት ጠንክሮ መውጣትን እንፈልጋለን። ምናልባትም በዙሪያችን ካሉ ሰዎች በተለየ ሁኔታ ለጥረት ቦታ የምንሰጥ በታታሪነታችን ስማችን የሚጠራም ሊሆን ይችላል። ይህ ሁሉ ግን ከልባችን ጋር ባለው ቅርበት እግራችንን የሚ ያራምድ ነው።
ዛሬ ልብህን የሞላውን አዳምጠው። በልብሽ ውስጥ ቦታ የያዘውን ነገር መርምሪው። በጥያቄው ውስጥ አድርገን የተግባራ እርምጃችንን እንመልከት። ልባችንን የሞላውን ለማድረግ አብዝተን እንራመድ። አንዳንዴ እያመነታንም ይሁን በልበ ሙሉነት እንቅስቃሴ የምናደርገው ልባችን በሞላው ነገር ልክ ነው። ልባችንን የሞላው ምቀኝነት ከሆነ ቆም ብለን ማስተካከያ ለማድረግ መዝግየት የለብንም።
በተጨባጭ ልባችንን የሞላው በሌሎች ስኬት በመቅናትና አቃቂር በማውጣት ከሆነ ለራሳችን ፈጥነን መገኘት አለብን፤ እየጎዳን ያለነው ያንን ሰው ሳይሆን ራሳችንን ስለሆነ። ከወዳጅ ላይ የማይታየን ጉድፋት ቅናት ባደረብን ሰው ላይ ጎልቶ የሚወጣ ከሆነ እንቅስቃሴያችን የመርህ አይደለም ማለት ነው። አንዳችን በሌላችን ላይ ያለውን ድክመት ነቅሶ በማውጣት ረገድ ጎበዞች እንደሆንን ይታያል። የራሳችንን ድካም ለመመልከት ግን የምናየው ነገር እምብዛም ነው። በተጨባጭ ግን የራስን ድካም እየመረመሩ መመላለስ አስፈላጊነቱ የሚካድ አይደለም። ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ውስጥ ልባችንን እየመረመሩ መንቀሳቀስ መልካሙም ሆነ ክፉ ስሜት ከልባችን ጋር ካለው አንጻር ብንመረምር አትራፊ እንሆናለን። የምርመራውን የመጀመሪያ ተግባር ልክ እንደ እንቅልፍ የእረፍት ምእራፍ ነው። ከራሳችን ጋር ጊዜ በመውሰድ ውስጥ ውስጣችን ያለውን መርዝ የምናጥብበት ሰዓት።
እንደ እንቅልፍ ስምንት ሰዓት
በቅንዓት ውስጥ ሕይወታቸው ችግር ውስጥ ላሉ ሰዎች ካሉበት ሁኔታ ወጥተው ጥሩ የሕይወት አቅጣጫ ላይ እንዲሆኑ ከራሳቸው ጋር የሚመክሩበት ጊዜ አስፈላጊ ነው። ከሰዎች ጋር ባለመስተጋብር የተጎዳ ሕይወታቸውን ለማስተካከል የሚያስችል ከነገሮች ገለል ብሎ የሚታረፍ የእረፍት ጊዜ። ከውስጥ ሰውነት ውስጥ መርዝን አውጥቶ ለመጣል የሚረዳ እረፍት።
በእንቅልፍ ላይ ጥናት የሚያደርጉ የሳይንስ ሰዎች እንደሚናገሩት አንድ ሰው ለስምንት ሰዓታት እንቅልፍ መውሰዱ ዛሬም የግድ እንደሆነ ይናገራሉ። በስምንት ሰዓታት ውስጥ አእምሮችን ስራውን ለመስራት የሚያመነጨውን መርዝ በማጠብ ስራ እንደሚጠመድ ይናገራሉ። እንቅልፍ የሚያጣ ሰው የተረጋጋ ሕይወትን መምራት የሚቸገረው ለጤና እክልም የሚዳረገው ከእዚህ የተነሳ እንደሆነም ይናገራሉ።
ቅንዓት፤ ምቀኝነት፤ ከሰዎች ጋር ራስን እያገናኙ መብሰክሰክ በቀላሉ የሚፈጠር አይደለም። ጊዜ ወስዶ ራስን መመልከት ያስፈልጋል። አካላዊ ሰውነታችን ተገቢውን እረፍት እንዲያደርግ በአእምሮ ውስጥ የሚቀመጥ መርዝን ለማጠብ ስምንት ሰዓታት የሚፈጅ እንደሆነ ሁሉ፤ ከሰዎች ጋር ያለንን መስተጋብር በመመርመር ሁሌም በራሳችን በመተማመን የራሳችን ነገር ላይ ትኩረት አድርገን ሕይወትን በጤናማ መንገድ ለመምራት የእረፍት መርህን ለመከተል በቂ ጊዜ ያስፈልገናል። የፈውስ እንቅልፍን በመተኛት ከራስ ጋር
በመሆን፤ ነገሮችን በጥሞና በመመርመር፤ አንደበታችን ውስጥ የሚወጡ ቃላትን በማከም ከጥፋት መንገድ የምንመለስበት ጊዜ ምክንያቱም ቅንዓት በሕይወታችን ውስጥ እንዳይመቸው ሊሆን ስለተገባ። አብሮ ከመውደቅ ስለተሻለው።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2015