ትላልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን፣ የመኖሪያ ቤቶችን፣ እንደ መንገድ እና ድልድይ እንዲሁም የጤናና የትምህርት፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የመስኖ መሰረተ ልማቶች፣ ወዘተ. ያሉትን ለመገንባት ሲታሰብ ከሚያስፈልጉ ዋና ዋና ግብአቶች መካከል ብረት ይጠቀሳል።ሰፊ የልማት እቅድ ያለው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ከእድገታቸውና ከልማታቸው ጋር የሚጣጣም የብረት ግብአት አቅርቦት ሊኖራቸው ይገባል።
በዚህ ወቅት በመሠረተ ልማት፣ በቤቶች ልማትና በመሳሰሉት ዘርፎች ሰፋፊ ስራዎችን እያካሄደች ላለችው ኢትዮጵያ ደግሞ የብረት አቅርቦት እጅግ ወሳኝ ነው። በዚህ ወቅት ምክንያታዊና ምክንያታዊ ባልሆነ ግብይት ሳቢያ ጣራ እየነካ ባለው የብረት ዋጋ እነዚህን መሰረተ ልማቶችና የተለያዩ ግንባታዎችን ለማካሄድ ብረት ከውጭ በግዥ በማስገባት የልማት ሥራውን ማስቀጠል የሚታሰብ አይደለም።የዋጋ ንረቱ የግንባታውን ኢንዱስትሪ ፈተና ውስጥ ጥሎታል።ችግሩ የቅሬታ ምንጭ መሆን ከጀመረም አመታት ተቆጥረዋል፡፡
ከማዕድን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ኢትዮጵያ በ2013 እና 2014 በጀት አመት ብቻ ለብረትና ብረት ነክ ውጤቶች ግዥ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊየን ዶላር ወጪ አድርጋለች። አገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየገጠማት ባለው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ላለፉት ሁለት አመታት የዘለቀው ጦርነትና እሱን ተከትሎ በአገሪቱ ላይ የተደረጉ ጫናዎች፣ በተለያዩ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣው ዋጋ የውጭ ምንዛሬ በመመደብ በግዥ የብረት ግብአትን ለመሠረተ ልማት ለማቅረብ ታደርግ የነበረውን ጥረት በእጅጉ እየተፈታተኑት ይገኛሉ፡፡
መንግስት ይህን ችግር በመፍታት የመሠረተ ልማትና ሌሎች ግንባታዎችን ለማስቀጠል የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወሰድ ቆይቷል፤ አሁንም የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን ነድፎ መፍትሄዎችን እያመቻች ነው።
በመሰረቱ የዘርፉን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ምድር ውስጥ ካሉ የተፈጥሮ ፀጋዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን የብረት ማዕድን ወይንም ጥሬ ሀብት በጥናትና ምርምር ለይቶና አደራጅቶ በዘርፉ ላይ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች እንዲያለሙ በማድረግ የግብአት አቅርቦቱን ችግር መፍታት ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ለልማቷና ለዕድገቷ ሊያግዛት የሚችል የብረት ማእድን ሃብት ባለቤት ስለመሆኗ ይገለጻል።መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በብረት ዘመን የሮማን ኢምፓየር ያመርት የነበረው የብረት መጠን 85000 ቶን ሲሆን፣ ቻይና ደግሞ በአመት 5000 ቶን ብረት ታመርት ነበር። በኢትዮጵያ በጥናት የተረጋገጠ 300,145,000 ቶን የብረት ማዕድን አላት።ከዚህ ውስጥ 72,508,575 ቶን የተረጋገጠ ክምችት ኩባንያዎች እንዲያለሙት የምርት ፈቃድ ተሰጥቷል።የተቀሩት በጥራትና መጠናቸው ላይ ተጨማሪ ጥናት የሚፈልጉ ናቸው፡፡
የተለያዩ ኩባንያዎች በአማራ፣ በትግራይና በኦሮሚያ የፍለጋና የምርት ፈቃድ ወስደው በስራ ላይ ይገኛሉ።ከእነዚህም መካከል ሰቆጣ ማይኒነግ፣ ኤም ኤስ ፒ ስቲልና ኮዬጻ ማይኒን ሼር ኩባንያ (Koyetsa Mining share company) ይጠቀሳል።
መረጃው እንዳመለከተው፤ በጥናት የተረጋገጠው የብረት ማእድን ክምችት ጥቅም ላይ ቢውል ለብዙ አመታት እፎይታን የሚያስገኝ ነው።እነዚህን የቆዩ መረጃዎች መነሻ ወይንም መሠረት በማድረግ የጥናትና የምርምር ሥራው ቢጠናከር በግብአት አቅርቦት ራስን ለመቻል ተስፋ የሚሰጥ ነገር ስለመኖሩ መረዳት ይቻላል።አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታም ለዘርፉ የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ ያስገድዳል። የማእድን ሚኒስቴር ከሰሞኑ ይፋ ያደረጋቸው መረጃዎች ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳዩ ናቸው።ለዘርፉ ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄ ብሎ አስቀምጧል።
የመንግሥትና የህዝብ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የፈሰሰበት አገር ውስጥ ያለውን የብረት ሀብት በአግባቡ ፈትሾ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ሲገባ ሀብቱ እየባከነ መሆኑን የማእድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ዑማ አስታውቀዋል። ያገለገለውን ብረት መልሶ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ የአካባቢ ብክለት እያስከተለ አገርን እየጎዳ መሆኑን በመጥቀስም ሚኒስትሩ በዘርፉ የሚስተዋለውን ሌላውን ክፍተትም አሳይተዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ይህን ተደራራቢ ጉዳት ለማስቀረት የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።ከአገልግሎት ውጭ የሆነው የባቡር ሐዲድ እንዲሁም አገልግሎታቸውን የጨረሱ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች፣ ማሽነሪዎች፣ ቁርጥራጭ ብረቶች እርሳቸው የሚመሩትን ተቋምና ተጠሪ መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ በቀድሞ ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)፣ በመከላከያ፣ በኢትዮ ቴሌኮም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር በአጠቃላይ በእያንዳንዱ የልማት ድርጅት ውስጥ ብቻ በሚሊዮን ቶን የሚቆጠር የብረት ክምችት ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ በፌዴራል መንግሥት ተቋማት፣ ተጠሪ ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆች፣ በሁሉም ከተማ አስተዳደሮች፣ ክልሎችና በግለሰቦች ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት ተከማችቷል። ይህ በየአካባቢው የሚገኘው አገልግሎቱን የጨረሰና ለብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች ግብአት ሊሆን የሚችል የብረት ክምችት ቢያንስ ለሚቀጥሉት ሁለት አመታት የብረት ግብአት ለሚፈልጉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሊውል የሚችልም ነው፡፡
የዘርፉን የግብአት አቅርቦት ችግር በጊዜያዊነት በዚህ መልኩ ከመፍታት በተጨማሪ ለግዥ የሚወጣውን ወደ ሁሉት ነጥብ አምስት ቢሊየን ዶላር ማዳን ወይም ማትረፍ ይቻላል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ለብረት ግዥ ይወጣ የነበረውን ገንዘብም እንደ ማዳበሪያ ላሉ አገራዊ ጥቅም ላላቸው ግዥዎች ማዋል የሚቻልበትን ዕድል መፍጠር እንደሚቻልም ይጠቁማሉ፡፡
ለዚህ ጊዜያዊ ችግር መፍቻ ተብሎ በመንግሥት የተቀመጠውን የመፍትሄ አቅጣጫ አስመልክቶ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ እንዳስረዱት፤ የብረት ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ብክነትን ለማስቀረት መንግሥት አዲስ የፖሊሲና የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ ወደ ትግበራ ገብቷል።በዚሁ መሠረትም ባለቤት ያላቸውንም ሆነ የሌላቸውን ያገለገሉ ብረታ ብረቶችን ለብረታ ብረት ፋብሪካዎች በቀጥታ ሽያጭ እንዲተላለፉ ለማድረግ በመንግሥት ተወስኗል።
የብረታ ብረት ቁርጥራጮች ሽያጩም ገንዘብ ሚኒስቴር ባዘጋጀው የመነሻ ዋጋ እና ማዕድን ሚኒስቴር በመደበው የፋብሪካዎች የማምረት አቅም መሠረት ይከናወናል። የማስፈጸሙ ሥራውም በግብረ ኃይል የሚመራ ሲሆን፣ ይህም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በማዕድን ሚኒስቴር እንዲሁም በክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በተዋረድ በጋራ ይከናወናል። በፌዴራል መንግስት፣ በክልሎች፣ በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ያሉት የመንግሥት መዋቅሮችም የማስፈጸም ግዴታና ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡
ከዚህ በኋላ ያገለገሉ የተሽከርካሪ፣ ማሽነሪና መሰል የብረታ ብረት ክምችቶችን ይዞ መገኘት ተጠያቂነትን ያስከትላል። በትግበራ ላይ የሚገኘው ይህ የማሻሻያ እርምጃ አፈጻጸም በየወሩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርት የሚቀርብ ይሆናል። ይህን አገራዊ ተልእኮ ያለውን እንቅስቃሴ መደገፍ ከሁሉም ይጠበቃል፡፡
እንዲህ ባለው ጊዜያዊ መፍትሄ የአምራች ኢንዱስትሪው የግብአት አቅርቦት እየተፈታ ዘላቂነቱ ላይ ይሰራል ያሉት ኢኒጂነር ታከለ፣ መጠኑንና ሀብቱ የሚገኝበትን ቦታ በባለሙያዎችና በአማካሪዎች በጥናት ለመለየት ሥራዎች መጀመራቸውንም አስታውቀዋል። በዚህ ላይ መንግሥት፣ አምራቾች፣ኩባንያዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ያላቸው ሚና ተወስኖ ወደልማቱ የሚገባበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ገልጸዋል።
ይህ ጊዜያዊና ዘላቂ የመፍትሄ አቅጣጫ እርምጃ በግንባታው ዘርፍ ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት፣ ለብረት ግብአትና ብረት ግዥ በከፍተኛ ደረጃ የሚወጣውን የአገር መዋእለ ነዋይ፤ለማዳን እንደሚረዳ ጠቅሰው፣ ለዜጎች የሥራ እድል የመፍጠር ሚናውም ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የብረት ኢንዱስትሪ በቀላሉ የሚታሰብ እንዳልሆነና አንድ ትልቅ መንደር ወይም ወረዳን ያህል ተደርጎ እንደሚወሰድ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በሥራ ላይ የሚገኙት የብረት ኢንዱስትሪዎች ወይንም ፋብሪካዎች የሚያመርቱት መጠንም ሆነ የሚጠቀሙት ቴክኖሎጂ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ይላሉ።
120 ሚሊየን ህዝብ ላላት ትልቅ ኢትዮጵያ፣ የብረት ኢንዱስትሪው በመንግሥት ደረጃ ካልተመራ በስተቀር የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ብቻ ስኬታማ መሆን እንደማይቻልም አስገነዝበዋል። የማዕድን ፖሊሲውም ይህንኑ አቅጣጫ ማስቀመጡን ነው ያመለከቱት።
የብረት ማእድን ክምችት በአማራ ክልል ሰቆጣ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ ደቡብና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች እንደሚገኙ የሚያመለክቱ መረጃዎች መኖራ ቸውንም አስታውቀዋል።ጉዳዩ የክምችት አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፣ እንደ አገር ለዘርፉ ትኩረት አለመ ሰጠቱን ከዋና ዋና ችግሮቹ አንዱ አድርገው ይጠቅሳሉ።
‹‹ትኩረት ሁሉ ከውጭ በሚገባ ግብአት ላይ ነው የነበረው።እንደ አለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያ የሸቀጦች ማራገፊያ ሆና ነው የቆየችው፡፡›› ያሉት ኢንጂነር ታከለ፣ ያም ሆነ ይህ በዚህ ወቅት መንግሥት ለመሥራት በእቅድ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ከግንባታ ግብአት አቅርቦት አንዱ በሆነው ብረት ላይ ነው›› ሲሉም ያለፉ ችግሮች አሁን ላይ ያስከተሉትን ክፍተቶች አመልክተዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ የብረት ኢንዱስትሪን ለመምራት ቤተሙከራ (ላብራቶሪ)ማሟላት ወሳኝ ነው። ከዚህ አኳያ ከሞላ ጎደልም ቢሆን የኢትዮጵያ ጂኦሎጂ ኢኒስቲትዩት ላብራቶሪ አለው፡፡ ያለውን ማደራጀት፣ በቴክኖሎጂና በሰለጠነ የሰው ኃይል ብቃቱን በማሳደግ እውቅና መስጠት ይጠበቃል፡፡
ብረትን ለማስመርመር ናሙና ወደ ውጭ መላክ ይጠበቃል። በዚህ ወቅትም የተለያየ ወጪዎችን ማውጣት ይጠበቃል።ለምርመራ የተላከው ብረት ትክክለኛ መረጃ ማገኘት ላይም የራሱ ክፍተት አለው።ለምርመራ የሚላክብቻው አገሮች ግብአቱን መልሰው በግዥ የሚረከቡ በመሆናቸው ጥራት አለው ለማለት የሚደፍሩበት ሁኔታ ጥርጣሬ ውስጥ የሚከትና የጥቅም ግጭትም የሚያስከትል ሆኖ የሚገኝባቸው አጋጣሚዎች የበዙ ናቸው።
የኢትዮጵያ ጂኦሎጂ ኢንስቲትዩትን በተሻለ አደረጃጀት ማጠናከር የተፈለገው እነዚህን ሁሉ ክፍተቶች ለመሙላት ወይንም ለማስቀረት ነው። ኢንስቲትዩቱን በሰው ኃይል ለማደራጀት እየተደረገ ያለው ጥረት በቅርቡ ይጠናቀቃል። በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ካላቸው ድርጅቶች ጋር ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
እንዲህ ያለው እንቅስቃሴ ኢንስቲትዩቱን በቴክኖሎጂ ለማደራጀት ብቻ ሳይሆን፣ በቤተሙከራ ውስጥ የሚያከናወነውን የብረት ናሙና ፍተሻ ስራዎች ለማስተካከል ጭምር ይጠቅማል።ከዚህ ቀደም ለፍተሻ ተብሎ ከመሬት ውስጥ ይወሰድ የነበረው ናሙና በቂ አልነበረም። ናሙናው በጥልቀት ከተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ መወሰድ ይኖርበታል።
የኢኮኖሚና የአዋጭነት ጥናት የሚያካሂድ፣ በአጠቃላይ አማራጭ የሆኑ ኢንዱስትሪውን ወደ አንድ ደረጃ የሚያደርስ ሥራ በመንግሥት እየተሰራ ይገኛል። ይህም በሶስትዮሽ የሚከናወን ተግባር ነው። መንግሥት ዋናው ሲሆን፣ አምራች ኢንዱስትሪዎችና በቴክኖሎጂው በቂ እውቀት ያላቸው ኩባንያዎች ባለድርሻ ናቸው። ማዕድን ሚኒስቴር በግንባታው ዘርፍ ከተሰጠው አንዱ ተልእኮ የብረት ማዕድን ላይ እንደሆነና በዚህ ረገድም የሚጠበቅበትን ለመወጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ከንግግር ባለፈ ተግባር ይቀድማልም ብለዋል፡፡
በአጭር ጊዜና በዘላቂነት በመንግሥት የተጀመረው የመፍትሄ እርምጃ እንደተባለው በክትትልና በቁጥጥር ከተተገበረ በዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን የግብአት እጥረት በመፍታት የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እንዲሁም አጋጣሚን ተገን በማድረግ በመካከል ላይ ሆነው ያልደከሙበትን ለማግኘት የሚሯሯጡት አንዳንድ ኃይሎች ከሰንሰለቱ ማስወጣት ይቻላል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥቅምተ 11 ቀን 2015 ዓም