ከዋናው ጎዳና አለፍ ብሎ ከሚገኝ የሆቴል ቤት በረንዳ አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ተደራርበው ተኝተዋል። በወጉ ያልተሸፈነው የአብዛኞቹ እግር ውሀ አይቶ የሚያውቅ አይመስልም። የጎዳና አቧራ፤ ጭቃ፤ ዝናብና ጸሃይ ስለተፈራረቀባቸው ወጣቶች ቢሆኑም በለጋ ዕድሜያቸው ወይበዋል።
ሁሉም በሚባል መልኩ በከባድ ዕንቅልፍ ውስጥ ናቸው። እንዲህ መሆኑ አዲስ የሚባል አይደለም። ምናልባት አንዳንዶች ርሀብ ቀስቅሷቸው ሊነሱ ይችሉ ይሆናል። በርካቶቹ ግን ወፍ ተንጫጭቶ እግረኞች መንገድ እስኪጀምሩ ከአስፓልቱ ጥግ ተዘርረው ማርፈዳቸው ተለምዷል።
ወደቀደመው መነሻዬ ልመለስ፣ ከመንገዱ ዳርቻ ወዳስተዋልኩት የሆቴል ቤት በረንዳ። በዚህ ምሽት አስቀድመው ጥግ የያዙ የጎዳና ልጆች ጎናቸውን አሳርፈው ዕንቅልፋቸውን እየተለማመጡ ነው። በእንዲህ አይነቱ ስፍራ ከዕንቅልፍ ጋር በዋዛ መገናኘት ዘበት ይሆናል። ባልተመቸው መኝታ መሀል እራፊን ተጋፈው ከሚጋሩት ትንፋሽ በምትገኝ ስስ ሙቀት ራስን እያታለሉ ብርድን ማሸነፍ የግድ ይላል። አጋጣሚው አግዞ በድካም መረታት ከተቻለ ደግሞ ዕድለኛነት ነው። ይህን አልፈው ባልተመቸ ጎናቸው ህልም የሚያዩና ቅዠት ጭምር የሚጎበኛቸው አይጠፉም። ይህም ዕድል ነው ከተባለ ‹‹እሰዬው›› ነው።
ምሽቱ ተገባዷል። ምናልባትም እኩለሊቱ እየተጋመሰ ነው። አሁንም ርዕሰ ጉዳዬ ከሆቴሉ በረንዳ ነው። ተደራርበው ከተኙት የጎዳና ልጆች መሀል በአይኗ ዕንቅልፍ ይሉት ያልዞረባት ወጣት በንቃት ተቀምጣ አካባቢዋን ትቃኛለች። ወጣቷ በዙሪያዋ ተኝተው ዕንቅልፍ በጣላቸው ባልንጀሮቿ የቀናች አትመስልም። አሁንም ትኩረቷ ዙሪያ ገባውን መቃኘት ብቻ ነው። ለአፍታ እረፍት ይሉት የላትም። ኮሽታ እያዳመጠች፣ ዓይኖቿ እዚህም እዚያም ይቃብዛሉ።
ለሊቱ እየገፋ ቅዝቃዜው እየከፋ ነው። እንዲያም ሆኖ ወጣቷ ጎኗን ከጓደኞቿ አስጠግታ ሙቀት መጋራት አላሻትም። እንዲህ ላድርግ ብትል የሚሆነውን አሳምራ ታውቃለች። ቢደክማትና ቢያማት እንደሌሎች መኝታን አያምራትም። ድካም ህመሟን ዋጥ አድርጋ እንደሁሌው ዙሪያ ገባዋን ትቃኛለች። በንቃትና በተለየ ጥንቃቄ።
የጎዳናዋ ወጣት ምሽቱን ተቀምጣ ስታሳልፍ ብቻዋን አይደለችም። በሁለቱ እጇቿ አጥብቃ የያዘችውን ማስቲሽ የተሞላበትን የሃይላንድ ላስቲክ ደጋግማ ትስባለች። በዚህ ሰአት ማንም ምንም ቢላት ጉዳይዋ አይደለም። ለእሷ የማስቲሹ መኖር ዋስትናዋ ነው። እሱን ከያዘች ዕንቅልፍ አይወስዳትም። ዕንቅልፍ ካልጣላት ደግሞ ራሷን አታስደፍርም። ሌቱን ቀን አድርጋ ማንነቷን ከዕንቅፋት የምትጠብቀው ወጣት ስጋትና ፍራቻ ቢኖራትም የጎዳናውን ህይወት እንዲህ መጋፈጧ ግዴታዋ ሆኗል።
ይህ አይነቱን እውነት በርካቶቹ የጎዳና ላይ ሴት ልጆች ማድረግ የሚሹት ቢሆን ይወዳሉ። አይቻላቸውም እንጂ ቢቻላቸው ኖሮ ሁለም ይህን ዘዴ እንደ አማራጭ ተጠቅመው ከሚመጣባቸው ችግር በሙሉ ባመለጡ ነበር።
የጎዳና ህይወት ለማንም ቢሆን ፈታኝና አስቸጋሪ ነው። ይበልጥ ግን በህጻናትና ሴቶች ላይ የሚያሳርፈው ጠባሳ ከሁሉም ይለያል። ሴቶች ከቤት ከወጡባት ዕለት ጀምሮ ፈተናቸው የበዛ ነው። ‹‹መሬት የወደቀች እርጥብ ስጋ አፈር ይዛ ትነሳለች›› እንዲሉ ከጎዳና የተገኘች ሴትም የምትሸከመው ግፍና መከራ የበረከተ ይሆናል።
ማንም ቢሆን ከተመቸ መኖሪያው ወጥቶ የጎዳና ህይወትን ምርጫው ሲያደርግ የራሱ መነሻ ምክንያት ይኖረዋል። አንዳንዱ በዕለት ቅያሜ ከቤተሰቡ ተጋጭቶ እንደወጣ ይቀራል። ሌላው የራሱና፣ የቤተሰቡ ድህነት ገፍቶት ጎዳና ‹‹ይሻለኝ›› ሲል ይወስናል። በርካታው ደግሞ ተወልዶ ካደገበት ቀዬ እንደዋዛ ወጥቶ ዕድሜውን ከጎዳና ጥግ ያገምሳል። ከነዚሀ ነፍሶች መሀል የሚገኙት ሴቶች ደግሞ ክብር ይሉትን እውነት ፈጽሞ አያውቁትም። በእንዲህ አይነቱ ህይወት አንቀጥል ካሉም ሴትነታቸውን አሳልፈው ሊሰጡ ይገዳዳሉ።
ብዙ ጊዜ ይህን ዋጋ የሚከፍሉ ሴቶች ለኔ የሚሉትን አቻ እስካልመረጡ ማንም እንዳሻው ሲጎትታቸው መዋል ማደሩ የተለመደ ነው ። ጉዳዩ በዚህ ብቻ አይቋጭም። በልጅነታቸው የልጅ እናት በሆኑ ጊዜ ኃላፊነቱን የሚጋራላቸው አያገኙምና ችግራቸውን ለብቻቻው ይጋፈጣሉ።
ሁኔታዎችን ለመሸሽ አቻ ይሉትን አጋር በመረጡ ጊዜም አብዛኞቹ ወንዶች አብረዋቸው ሊዘልቁ አይፈቅዱም። የልጅ እናቶች በሆኑበት አጋጣሚ አካባቢውን ጥለው ከሌሎች መላመዳቸው የተለመደ ነው። ሴቶቹ ራሳቸውን ለመርሳትና ችግሮችን ለማለፍ ሲሉ በሱስ መጠመድን ምርጫቸው ያደርጉታል። በልመና የሰው አይንን ከማየት ባለፈ በጫትና ሲጋራ፣ በመጠጥና ሀሺሽ ሱስ ናውዘው ራሳቸውን ለችግር ያጋልጣሉ። ‹‹የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል›› እንዲሉ ሆኖም ለተደራራቢ ችግሮች ለመጋፈጥ ያመቹ፣ የተመቹ ይሆናሉ። ለሴቶች በጎዳና ራስን ከችግር ጠብቆ፣ ከክፉ ሁኔታዎች ተጠብቆ ለመዝለቅ መሞከር ምናልባትም ፌዝ ሊባል ይችላል ። ይህን እንሞክር የሚሉ ቢኖሩ እንኳን መንገዳቸው ከእርምጃ ጉዞ አያልፍም። ብዙዎች በሚፈተኑበት ጥልፍልፍ ወጥመድ ተጠልፈው ሊወድቁ ግድ ይላል።
በጎዳና ላይ የሚወለዱ ህጻናት ዕጣ ፈንታም ቢሆን ከእናቶቻቸው ማንነት የተለየ አይሆንም። በተለይ ሴቶቸ ከሆኑ ከህጻንነታቸው ጀምሮ በጾታዊ ትንኮሳ መፈተናቸው አይቀሬ ይሆናል። ለሴቶች በጎዳና ላይ የሚኖረው የህይወት መልክ በእጅጉ ይለያል። ለእነሱ መኖር ማለት እንደሌሎች ተኝቶ መነሳት ብቻ አይደለም። ብዘዎች ከተለያዩ አባቶች የሚወልዷቸውን ልጆች አብልቶ ለማሳደር እንደመፍትሄ የሚወስዱት ራስን ለችግር አሳልፎ መስጠትን ነው። የያዙት የችግር ቋጠሮ በወጉ ሳይላላ ለተመሳሳይ ችግር መጋፈጣቸውም የተለመደ ነው።
ሁሌም ቢሆን የጎዳና ላይ ህይወት በሴቶች ላይ የከፋ በትሩን እንዳሳረፈ ነው። እናትነት ከሚያሳድረው ኃላፊነት በዘለለ በሌሎች ዘንድ የሚኖረው ያልተገባ አመለካከትም ከማንነታቸው አፈንግጠው እንዲታዩ ተጽዕኖውን የጎላ ያደርገዋል።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከሀምሳ ሺህ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎች ይገኛሉ። አሳሳቢውን የጎዳና ላይ ህይወት ለመታደግም የማህበራዊ ህይወት ተሞክሮዎችን ባህል ከማድረግ ባለፈ እስከዛሬ በመንግስት በኩል የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ክረምት ከበጋ ፈተናዎችን ተጋፍጠው ህይወታቸውን ለሚመሩ ነፍሶች ዘለቄታዊ መፍትሄ በማፈላለግም ወደ ትውልድ ቦታቸው እንዲመለሱ የማጓጓዙ ስራ እንደ አማራጭ ሲተገበር ቆይቷል። አንዳንዴ በደጋግ ልቦች አነሳሽነት ለነዚህ ወገኖች ማዕድ የማጋራት ሂደቱ የተለመደ ቢሆንም አሁንም ግን ከዳር ሊያደርሳቸው የሚያስችል ዘላቂ መፍትሄ ሊፈጠር የግድ ይላል።
ቀደም ሲል የጎዳና ነዋሪዎችን ህይወት ለማሻሻል ሲባል በዕቅድ የተያዙ ፕሮጀክቶች በስፋት መተረጎማቸው ደግሞ ይበልጥ ወሳኝነት ይኖረዋል። ለዓመታት በጎዳና ላይ ህይወትን በፈተና የኖሩ ጥቂት የማይባሉ እናቶች የቤት ባለቤቶች የመሆናቸውን ተሞክሮ በማስፋት በርካታ ወገኖች ከአስከፊው የጎዳና ላይ ኑሮ እንዲላቀቁ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ማህበራዊ ግዴታ ሊሆን ይገባል። መልዕክታችን ነው።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2015