ሙሉጌታ ተስፋዬ የሚታወቀው በግጥም መድብሎቹ እና በዘፈን ግጥሞች ነው። ይህን ሰው በቅርብ የሚያውቁትን ሰዎች ጨምሮ ታሪኩ የሚናገረው ግን ሥራዎቹ ብቻ ሳይሆን ሕይወቱ ራሱ ቅኔ ነው። የጽሑፋችን ዓላማ የሕይወት ታሪኩ ላይ ስላልሆነ እንጂ ገጠመኞቹ ሁሉ አስቂኝና አሳዛኝ ናቸው። በአጠቃላይ ከተለመደው ወጣ ያለ ሕይወት የነበረው ነው።
ስለሙሉጌታ ተስፋዬ ብዙ ቢባልም ለዛሬው ስለእርሱ ሥራዎች ለማውራት የተነሳነው ግን ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ‹‹አያ ሙሌን በነቢያት ጉባኤ›› በሚል ውይይት ተደርጎ ስለነበር ነው። መድረኩን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻፍት ኤጄንሲ (ወመዘክር)፣ ኢጋ ሚዲያና ኮምኒኬሽን እና ጎተ ኢንስቲትዩት ናቸው።
አርክቴክትና የስነ ጽሑፍ ባለሙያው ሚካኤል ሽፈራው ለውይይት መነሻ ሀሳብ አቅርበዋል፤ ከታዳሚዎች ሀሳቦች ተነስተዋል። በተለያዩ ገጣሚያን የተገጠሙ ግጥሞች እና የሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ) ግጥሞች ቀርበዋል።
የውይይት መነሻ ሀሳቡን፣ ከታዳሚዎች የተነሱትን እና አጠቃላይ ስለባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ የተባሉትን ጠቅለል አድርገን እናቀርባለን።
ሙሉጌታ ተስፋዬ የኖረበትም ሆነ የግጥም ሥራዎችን የጀመረበት ዘመን የፈተና ጊዜያት ነበሩ። በተለይም ታዋቂ ገጣሚ የሆነው ኢህአዴግ በመጣባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት (1980ዎቹ) ነው። የመጨረሻው ግጥሙ ደግሞ በ1996 ዓ.ም ነው። አንዳንዶቹ ግን ቀን የሌላቸው ናቸው።
ኢህአዴግ ደርግን አስወግዶ አገሪቱን ሲቆጣጠር መደማመጥ አልነበረም፤ በዚያን ጊዜ ትንሽ ማስተዋል የነበራቸው ባለቅኔዎች ነበሩ። ጸጋዬ ገብረመድኅን የዚያን ጊዜ ነው ‹‹ሀ ሁ ወይም ቀ ቁ›› የተሰኘውን ሥራውን የጻፈው። ወይ አዲስ ታሪክ እንጀምራለን ወይም የነበረውን እናስቀጥላለን ለማለት ነው። እነዚህ ሰዎች የግላቸውን ጉዳይ ሳይሆን አገራዊ የሆኑ ሁኔታዎች ላይ ያስቡ ነበር።
ሙሉጌታ ተስፋዬ ግጥሞቹን የሚጽፈው አጠገቡ ካሉ ነገሮች ነው፤ አይቷቸው ስሜቱን የነኩትን ነገሮች ነው። ኃላፊነትን ሌሎች ሰዎች ላይ መጣል ሳይሆን ራስን መታዘብን ይናገራል።
የሙሉጌታ ግጥሞች የክርስትና ኃይማኖት መንፈስ ያላቸው ናቸው። በሕይወቱም የዓለም በቃኝ አይነት የምናኔ ሕይወት ያለው ነው። መቆዘም እና ብቻውን መሄድ ያበዛል። ራሱን ሁሉ እስከመጣል ደርሷል፤ በእነዚህ ፍልስፍናዎቹ ነው ሀሳቦችንም እያረቀቀ የሚጽፋቸው። በመንፈስ የሰመጠ ሰው ስለሆነ ሥራዎቹም ከዚያ የሚቀዱ ናቸው።
ሙሉጌታ ግጥም ሲጽፍ ከቃል ውስጥ ቃል ይፈጥራል። ለምሳሌ መስከረም የሚለውን ቃል መሰከረ፣ መስክ.. የሚሉ ቃላት ሊያወጣለት ይችላል።
አሁን በመድብል የሚታወቁት የሙሉጌታ ተስፋዬ ግጥሞች አንዳንዶቹ በስንዱ አበበ አማካኝነት ተሰብስበው የታተሙ ናቸው። በቅርበት የሚያውቁት ሰዎች እንደሚሉት ሙሉጌታ ግጥም ጽፎ የሆነ ቦታ ጥሎት ሊሄድ ይችላል። ስለዚህ ለህትመት ያልበቁ ወድቀው የቀሩም ሊኖሩ ይችላሉ።
ገጣሚ መንግሥቱ ዘገየ የሙሉጌታ ተስፋዬ ግጥሞች ወደ ተረትነት እንዳይቀየሩ ስጋት እንዳለው ተናግሯል። ስለዚህ ሙሉጌታ ማነው የሚለው መነገር አለበት። ብዙ ጊዜ በመገናኛ ብዙኃን ቃለ መጠይቅ አያደርግም፤ ግን የቅርብ ጊዜ ታሪክ እና በሕይወት ያሉ ሰዎች የሚያውቁት ነው።
መንግሥቱ ዘገየ ላሊበላ ለሥራ ጉዳይ ሄዶ፤ ‹‹ከሙሉጌታ ተስፋዬ በዕድሜ ሊያንስ የሚችል ሰው አግኝቼ ‹ሙሉጌታ ተስፋዬን ታውቀዋለህ?› ብየ ጠይቄው ‹ጓደኛዬ ነው!› አለኝ›› ብሏል። የሚያውቁት ሰዎች ሁሉ ‹‹ጓደኛዬ ነው›› ብለው ነው የሚናገሩ።
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፤ የሙሉጌታ ግጥሞች የሕዝብ የቃል ግጥሞችን አይነት ለዛ ያላቸው ናቸው። በዚህም ምክንያት እነርሱ የገጠማቸው መሆናቸው ካልተገለጸ ምናልባትም የሕዝብ ስነ ቃል ሊመስሉ ይችላሉ። ምክንያቱም ሀሳቦቹ ሁሉ ከአገር ቤቱ ባህልና ወግ የሚቀዳ ነው። ለምሳሌ፤ ‹‹ደስ ይላል መስከረም›› የሚለው ግጥም የገጠሩን አርሶ አደር ሕይወትና ለጋስነት የሚገልጽ ነው። ግጥሞቹ ፎክሎራዊ ባህሪ ያላቸው ናቸው።
በውይይቱ ላይ ከተነሱት ሀሳቦች አንዱ፤ የሙሉጌታ ግጥሞች ጠጠር ያሉ ቃላት የያዙ ናቸው። ስለዚህ አዘጋጁ (የነብያት ጉባኤን መድብል) የግርጌ መግለጫ ቢያስቀምጥባቸው የሚል ነው። በነገራችን ላይ በዕውቀቱ ሥዩም በአንዳንድ ግጥሞቹ ሥር አዲስ ይሆናሉ ብሎ ያሰባቸውን ቃላት የግርጌ መግለጫ ያስቀምጥባቸዋል።
የሙሉጌታ ግጥሞች እንደተባለውም ጠጠር ያሉ ቃላት የያዙ ናቸው። የግዕዝ ቃላት አሉት፤ አንዳንድ ቦታ ደግሞ የአገር ቤቱን ለዛ ላለመልቀቅ ሲል ማህበረሰቡ በሚጠቀማቸው ቃላት የጻፋቸው አሉ። እነዚህ ቃላት ለከተሜው ነዋሪ አዲስ እንደሚሆኑ ግልጽ ነው። ስለዚህ አዘጋጆች መግለጫ ቢያደርጉባቸው ያስፈልግ ነበር።
ሙሉጌታ ተስፋዬ በግጥም መድብሎች ላይ ባሉት ግጥሞች መጽሐፉን ያነበበ ያውቀዋል። አብዛኛው ሰው ግን የሙሉጌታ ተስፋዬ ግጥሞች ባሉባቸው ዘፈኖች ተመስጧል፣ ተክዟል፣ ተደስቷል፣ አልቅሷል።
ለምሳሌ፤ የታምራት ደስታ ‹‹ሐኪሜ ነሽ›› የተሰኘው ዘፈን ግጥም የሙሉጌታ ተስፋዬ ነው። ይህን ዘፈን ብዙ ወጣቶች ፍቅራቸውን ገልጸውበታል።
የብፅዓት ሥዩም ‹‹አደራ ልጄን አደራ›› ዘፈን በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል፤ ይወደዳል። የዚህ ዘፈን ግጥም የባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ ነው። በሌሎች የብጽዓት ሥዩም ዘፈኖች ውስጥም የሙሉጌታ ግጥሞች አሉ።
ሙሉጌታ ለብዙ ዘፋኞች ግጥም ሰጥቷል። ለዘፋኞች በጣም ቅርብ ነበር። ፍቅርአዲስ ነቃዐጥበብ በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ሙሉጌታ ብዙ ዘፋኞችን እንዳበረታና ትልቅ ደረጃ እንዳደረሰ ረዘም ያለ አስተያየት ስትሰጥ ሰምቻለሁ።
ከሙሉጌታ የዘፈን ግጥሞች ውስጥ በብዙዎች ዘንድ የታወቀውና የተለመደው የአበበ ተካ ‹‹ወፍዬ›› ነው። በዚህ ዘፈን ግጥሞች ከወጣት እስከ አዛውንት ያልተመሰጠ፣ ያልተከዘ፣ በምናብ ያልተዋጠ የለም። ሙሉጌታ ተስፋዬ በዚያ ዘፈን ውስጥ ባሉ ግጥሞች፤ ተፈጥሮን ከምናብ፣ እንስሳትን ከሰው፣ አካባቢን ከጠፈር፣ የቅርብ ያለን ነገር ከሩቅ ያቆራኘበት ነው። የሰውን ልጅ የማሰብ ህሊና የሚታዘብ ግጥም ነው። የዚህን ዘፈን ግጥሞች እናስቀምጣቸው።
ጭራ ጭራ የምታድረው
ጭራ ለቅማ የምታድረው
ጭራ ጭራ የምታድረው
ጭራ ለቅማ የምታድረው
እንዲህ አስናቀችኝ…
ቀድማኝ ጎጆ ወጥታ ጎጆ አስተማረችኝ
ጎጆ …አቤት ጎጆን… ወፍዬ አስቀናችኝ፤
እህህ… ምነው ባደረገኝ
እህህ… የሷ ጋሻ ጃግሬ
እንደምንም ብዬ እኔም ጥሬ ግሬ
ያገዳ ጎጆዬን ባቆምኳት ማግሬ፤
እህህ… አጉል በቃኝ ላ’ይል
እህህ… አይን አይቶ ገምቶ
ወይ ሞልቶ ላይሞላ ጆሮ አይችሉ ሰምቶ
እንዴት ጎጆ ይቅር አርሶና ሸምቶ
ገመና ከታቹ የሣር ቤት ያማረሽ
ሚስጥረ መለኮት ማነው ያስተማረሽ
ካፈር ክዳን ጎጆ መሬቱን ፈልፍሎ
ከሰማይ ቤት እጣሽ ማን በሰጠኝ ከፍሎ
እኔን እኔን እኔን ይብላኝ
እኔን አይኔን እኔን ይብላኝ…
እኔን እኔን እኔን ይብላኝ
እኔን አይኔን እኔን ይብላኝ…
የቀን ሰው ሌጣ አፈር
ልቤ ሩቅ አሳቢው ቅርብ አድሮ ሲደፈር
ምን ነበር ቢቆጨው ጎጆ አጥቶ ከማፈር፤
እህህ… ፈጣሪዋን አምና
ያፏን ጥሬ ሰጥታ
ለጭሮ አዳር ውሎ በዝማሬ ወጥታ
አዳኝ እንዴት ያጥቃት ፍርድና ዳኛ አጥታ
እህህ… አጣሁ፣ ነጣሁ ብላ
እንደሰው ባይከፋት
ምፅዋት ባትለምን ተርፎን ባንደግፋት
ጎጆዋ ለቻላት ምን ነበር ባንገፋት
ታማ ትንፋሽ አጥሯት ደክማ ስታጣጥር
ማን ያቃናት ይሆን፥ ውለታ ሳይቆጥር
ወልዶ ማሳደጉን ብዙ ሰው ቢያውቅበት
ያፉን ማን ይሰጣል የእጁ ሲርቅበት
እህህ… ወፊቱ
ኡሁሁ… ወፍዬ
በእነዚህ ስንኞችና እንጉርጉሮዎች ውስጥ የራሱ የሙሉጌታ ተስፋዬ ሕይወት ይታያል። ‹‹ታማ ትንፋሽ አጥሯት፣ ደክማ ስታጣጥር፤ ማን ያቃናት ይሆን ውለታ ሳይቆጥር›› የምትል ስንኝ አለች። አንድ የሙሉጌታን ድርጊት ብቻ እንጥቀስ።
መቼም ብዙ ጊዜ ብቻውን መሄድ ይወዳል ነው የሚባለው። አንድ ዕለት አንድ በባዶ እግራቸው የሚሄዱ ሰውየ ያገኛል። ያስቆማቸውና ትንሽ ካወራቸው በኋላ ‹‹እስኪ ይሄን ጫማ ይለኩት›› ብሎ ጫማውን አውልቆ ይሰጣቸዋል። ሰውየው ጫማውን ሲለኩት ልክክ አለ። ‹‹አሁን መሄድ ይችላሉ›› ብሎ በባዶ እግሩ ጉዞውን ቀጠለ።
የሙሉጌታ ግጥሞች አብዛኞቹ ረጃጅም ናቸው። ከቃል ላይ ቃል እየፈጠረ፣ ከአንድ ሀሳብ ላይ ሀሳብ እያወጣ አንባቢን ጭምር ሌላ የራሱን ሀሳብ እንዲያስብ ያደርጋል። ሲፈልግም አንባቢው የራሱን የሕይወት ውጣ ውረድ በገጠመኞቹና ሙሉጌታ ባስተዋላቸው ዕይታዎች ውስጥ እያስገባ ይመሰጣል።
እንዲህ አይነት ፈላስፋዎች ብዙ ጊዜ የራሳቸውን ሕይወት በምቾት አይኖሩም ይባላል። የሙሉጌታ ተስፋዬ ሕይወትም እንደዚያ ነው፤ ብዙ የምቾት አጋጣሚዎችን ጥሎ ይሄዳል ይባላል። መሽቀርቀር የሚያስችል አቅም እያለው የተጎሳቆለ ሕይወት ሲኖር ቆይቷል። በዚህ ሕይወቱ ውስጥ የጎስቋሎችን ሕይወት የሚያሳዩ ሥራዎችን አስቀምጣል።
እነሆ ከጎስቋላ ሕይወቱ ይልቅ በሥራዎቹ ሲታወስ ይኖራል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2015