እንደ መንደርደሪያ ቢያግዘን፤
“ኃያሲያን የሌሉት ሀገር ህመሙ ብዙ ነው” ይሉት ዓይነት አባባል በብዙዎች ዘንድ የተለመደ አነጋገር ነው። ብሂሉ የተሸከመው መልእክት የገዘፈ ብቻ ሳይሆን መገለጫውም በርከት ይላል። በምሳሌ እናመላክት ከተባለም አንዳንድ ማሳያዎችን መጠቋቆም ይቻላል። የማሕበረሰብ ሕይወት በዘርፉ ባለሙያዎች (Social critics) በሚገባና በጥልቅ ዐይን ይፈተሻል። የሀገር ሥነ ጥበብም ለሙያው ቅርበት ባላቸው “በባለ አራት ዐይናማ” ኃያሲያን (Art critics) እየተገመገመ “ጥሬው ከብስል” ይለያል።
ኢኮኖሚውና ፖለቲካውም በልሂቃኑ እየተመረመረ “እንዲህ አይሁን ወይንም እንዲህ ቢሆን ይሻላል” እየተባለ መፍትሔው ይጠቆማል። የየዘርፉ ድካምና ብርታት የሚጠቋቆመውና ህፀጾች እንዲታረሙ የሚደረግበት ዋነኛ ምክንያት የማሕበረሰብ ሕይወት ሳይጎመዝዝ እንዲጣፍጥና የተረጋጋና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲቻል በመቆርቆር ብቻም ሳይሆን ግዴታም ጭምር ስለመሆኑ ልብ ይሏል።
ይህ ጸሐፊ ላለፉት በርካታ ዓመታት በዚሁ ታሪካዊ ጋዜጣ ላይ የብዕሩ አቅም በፈቀደለት መጠን የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት በሀገሩ መልከ ብዙ ጉዳዮች ላይ የዜግነት ድርሻውን መወጣትን ቀዳሚ ዓላማው በማድረግ ሃሳቡን በነፃነት ሲያካፍል ኖሯል። እንደ አንድ ማሕበራዊ ኃያሲም መቀረፍ የሚገባው ሀገራዊ ችግር እንዲቀረፍ፣ መታረም የሚገባውም እንዲታረምና ውጤታማ ተግባራትም እንዲበረታቱ “ጫን ያሉ ሙግቶችንና አስተያየቶችን” በግልጽነት እየሰነዘረ በቤትኛነት መሰንበቱ ይታወቃል።
ዛሬም ቢሆን በማሕበራዊ፣ በኢኮኖሚውና በፖለቲካው አካሄዶችና ሥሪቶች ላይ የቢሆን ምኞቱንና የባይሆን ፍላጎቱን እንደ ሌሎች አቻ አምደኞች በዚህ ነፃ አምድ ላይ በነፃነት ከማጋራት አልቦዘነም። እውነታው ይህንን ቢመስልም የሀገራችን ችግሮች በሙሉ በዚህ ጸሐፊም ሆነ በመሰል ትጉሃን “ቀለም” ተጠቃቅሶ ተጠናቋል ለማለት አያስደፍርም።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በየሚዲያው ሲተላለፍ እንደነበረው አንድ የምርት ማስታወቂያ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ከዕለት ዕለት እየባሰባቸው “ጠብ ሲሉ ስንደፍን፣ ሲያንጠባጥቡ ስንደቅን” መኖራችን የሚካድ አይደለም። በሽታው ተፈውሶ ያልተጠናቀቀው ይህን መሰሉ ሀገራዊ ህመማችን መልኩም ሆነ ባህርይው ዝንጉርጉርና ውስብስብ ሆኖ ግራ እንዳጋባን መዝለቁ የእንቆቅልሻችንን ጥልቀት የሚያሳይ ነው።
የተጣቡን ጉልህ ሀገራዊ ችግሮቻችን መልካቸው ምን እንደሚመስል በውሱን ገለጻ ለመጠቋቆም እንሞክር። እየዳኸ ያለው ሀገራዊ ፖለቲካችን ከእንፉቅቁ ተላቆ ቢያንስ ቢያንስ ድክ ድክ ያለማለቱ ያሳስበናል። በልምሻ የተጠቃውን ይህን መሰሉን ደዌ የምህዳሩ ዋነኛ ተዋንያንና ኃያሲያን “ወፌ ቆመች፣ ወፌ ቆመች!” እያሉ በማበረታታት የላሸቀውን ጉልበታቸውን በመደማመጥ፣ በመከባበርና በመቀባበል እስካላጸኑ ድረስ መከራችን መራዘሙ አይቀሬ ይሆናል። ይህን ጉዳይ በተመለከተ ብዙዎች ብዙ የመፍትሔና “የቢሆን ምኞታቸውን” ደጋግመው ቢገልጹም ሥር ሰዶ በደዌ የተጠቃው ፖለቲካችንና ህመምተኞቹ ፖለቲከኞቻችን ለፈውስ ከመሥራት ይልቅ እህህታንና ማቃሰትን ስለመረጡ እኛም ተራ ዜጎች በእነርሱ “ጦስና ጥንቡሳት” አሳራችንን ከመብላት ነጻ ልንሆን አልቻልንም።
ሀገሪቱ የተለከፈችበት የኢኮኖሚ አብሾም በነጋ በጠባ በማገርሸት ከእብደቱና ከወፈፌነቱ ፈውስ ማግኘት ስላልቻለ ዜጎችና ገበያው ሆድና ጀርባ ከሆኑ ሰነባብቷል። “በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተደምሮ” እንዲሉም የዓለም አቀፉ የምጣኔ ሀብት ሥርዓት በኢንፍሉዌንዛ ሲጠቃ በሀገራዊ ኑሯችን ላይ ጫናውን እያሳረፈ በማስነጠስ ወደ መኖርና አለመኖር አደጋ ላይ ጥሎ ሊጨፈልቀን የቀረው አንድ ሐሙስ ብቻ ነው። ያ “አንድ ሐሙስ” መቼ ሞልቶለት ቁርጣችንን እንደምናውቅ እርግጠኞች ስላልሆንን ኑሯችን ሁሉ “እንደ ምፀዓት ቀን” እንዳስፈራን ዛሬን ደርሰናል።
ከረጅም ዓመታት በኋላ የሚናፍቃትን የእናት አባቱን ሀገር ለማየት ዕድል ያገኘ አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ወጣት በቅርቡ በአንድ መድረክ ላይ ተገኝቶ በባእድ ቋንቋ ንግግር ሲያደርግ አድምጠነው ነበር። ይህ ወጣት ዲስኩሩን የደመደመው እንዲህ በማለት ነበር፤ “የኢትዮጵያ ሀገሬ አየር እንደ ዳቦ የሚገመጥ፤ የወገኖቼ ፍቅርም እንደ ሸማ የሚለበስ እንደሆነ በዐይኔ አይቼ ለማረጋገጥ ችያለሁ። ” የሚለውን መልእክቱን አስተላልፎ እንደ ወረደ አንድ አባት ጎላ ባለ ድምጽ፡- “እውነት ተናገርክ የእኔ ልጅ። የኢትዮጵያ ሕዝብ እየኖረ ያለው በፈጣሪ ኪነ-ጥበብ አህል ሳይሆን አየር እየገመጠ ነው። ‹ሰው የሚኖረው በእንጀራ ብቻ ሳይሆን› አየር እየተመገበም ጭምር መሆኑ የእኛ ኑሮ ምስክር ነው። ” በማለት የታዳሚውን ስሜት ኮርኩረው የምር አስቀውናል። እንደዚህ ጨርቁን ጥሎ ላበደው ሀገራዊ ኢኮኖሚያችን የዘርፉ ልሂቃንና ኃያሲያን መፍትሔውን አመላክተው ወደ ቀልቡ እስካልመለሱልን ድረስ የዜጎችን ናላ ያዞረው ወፈፍታው የሚያስከትለው ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።
ክፉ ቀን የገጠመው አንድ አባወራ ኑሮ እንደ ወስከንባይ ተደፍቶበት ግራ ቢገባው ሚስቱን ለምንትስ ፈንጋዮች ለመሸጥ ተስማማ ይባላል። “ይባላል” መሆኑ ይያዝልን። ይሄው ግራ የገባው ባል ከፈንጋዮቹ ጋር በምሥጢር ተስማምቶ የተሸጠችውን ሚስቱን ራቅ አድርጎ ለመሸኘት አብረው ሲጓዙ ደግሞ ደጋግሞ “የቦርከና ወንዝ ማለት ይሄ ነው!” እያለ ይለፈልፍ ነበር አሉ። መልእክቱ “ምናልባት ዕድል ቀንቶሽ ከገዢዎችሽ አምልጠሽ የምትመለሺ ከሆነ ‹የቦርከና ወንዝ› ምልክት ይሁንሽ ማለቱ ነበር።
ይህ ከጥንት የወረስነው “ተራ ምሳሌ” ሊጠቀስ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት “እንደ ብርቅ እያየነው ያለው የእለት እንጀራ ፍላጎታችን ቋፍና ጫፍ ላይ ደርሶ ‹መኖር ወይ አለመኖር›” ወደሚለው ውሳኔ ላይ ዜጎች ከመድረሳቸው አስቀድሞ ወፈፌው ኢኮኖሚያች ቢያንስ እብደቱ እንዲበርድለት ክንዶችና እግሮቹ በብረት ሰንሰለት ታብተው አደብ እንዲገዛልን ማድረጉ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ላይ የተደረሰ ይመስለናል። ሆዱ ባዶ ሆኖ ሆድ የባሰው ሕዝብ ርሃቡን ለማሰማት አደባባይ መዋል ከጀመረ ቁጣውን ማስታገስ ስለሚያስቸግር ከወዲሁ ቢታሰብበት አይከፋም። ለመንግሥታችንና ለዘርፉ ተዋንያን የምናስተላልፈው መልእክትም “ልብ ያለው ልብ ያድርግ” የሚለውን የተውሶ አባባል ይሆናል።
ደፈር ብለን እንዋቀስ!
እስከ ዛሬ ድረስ ደፈርና ጫን ብለን ለመኄስ “ፈራ ተባ” ስንል የቆየንበትን አንድ መሠረታዊ ጉዳይ እናንሳ። “እባጩን ጫን ብለን ከመዳሰሳችን” አስቀድሞ ግን አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን በመጠቃቀስ ለትዝብታችን መደላደል የሚሆኑ ሃሳቦችን እንጎዝጉዝ። ሀገራዊው ስታትስቲክስ እንደሚነግረን ለመቶ ፐርሰንት ጥቂት ሽርፍራፊ አሀዞች ሲቀሩ የሀገሪቱ ዜጎች በሙሉ በተለያዩ የሃይማኖት ጥላ ሥር የተሰባሰቡ ናቸው።
ጥቅል ፍረጃ ሆኖ እንዳይቆጠር ሰጋን እንጂ በኢትዮጵያ ምድር በአሁኑ ወቅት “ሃይማኖት የለኝም” የሚሉ ቡድኖች ስለመኖራቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም። በየከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ አንዳንድ የዲያሌክቲክስ ፍልስፍና አስተማሪዎችም ቢሆኑ ደፍረው “አምላክ የለሽነታቸውን” በግላጭ የሚያውጁ አይደሉም። ስለዚህም ነው እያንዳንዱ ዜጋ “የእኔ” የሚለው ሃይማኖት ባለቤት ነው ለማለት የተደፈረው።
እያንዳንዱ ቤተእምነት የሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ለአንድ ደቂቃም ቢሆን ሲያስተጓጉል ያለመታየቱም የየሃይማኖቶቹ ጥንካሬ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በየአብያተ ክርስቲያናቱ ጉልላት ላይ ከፍ ብለው የተሰቀሉት ድምጽ ማጉያዎች ለፈጣሪ የማያቋርጥ ምሥጋና ሲያቀርቡ ማድመጥ ነፍስን በሃሴት ያረሰርሳል። “አላሁ ክበር!” በሚል አዋጅ በየመስጊዶቹ የሚደመጠው አዛንም የፈጣሪን ታላቅነት አጉልቶ ለማሳየት የሚተላለፍ ዘወትራዊ የማንቂያ ታላቅ መልእክት ነው። የወንጌል አማኞች “የሃሌሉያ ዝማሬም” ከአማንያኑ አንደበት አልጎደለም። የባህላዊ እምነት ተከታዮችም ቢሆኑ በአምልኮታዊ ሥርዓታቸው መሠረት ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑት በመሰጠት ነው። ለጊዜው ከድምጽ ከፍታና ዝቅታ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን “የዴሲቢሉን” ፍተሻ ጣጣ ቦታው ስላይደለ አንነካካውም።
እንደየእምነቶቹ ቀኖናና ሥርዓት መሠረት ምእመናን በሚሰበሰቡባቸው ጉባኤዎችም የየሃይማኖት መምህራን አባላቶቻቸውን ስለ ቀኖናና ትውፊታቸው የሚያስተምሯቸው ከልባቸውና ለእምነታቸው ቀናዒ ሆነው ነው። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት አንጻራዊም ቢሆን፤ ትልቁ ጥንካሬያቸው በራሳቸው ዶግማና ትምህርት ብርቱ መሆናቸው ብቻም ሳይሆን አንዱ የእምነት ክፍል ከሌላኛው ጋር ተከባብሮ መኖራቸው ድንቅና አስመስጋኝ የጋራ እሴታቸው ነው።
ይህ መሠረታዊ አቋማቸውና የእምነታቸው አስተምህሮ እንደተጠበቀ ሆኖ ግራ እያጋቡን ያሉ የጋራ ጉዳዮች መኖራቸውንም መካድ አይቻልም። ዛሬ ሀገሪቱ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚው ወይንም በሌሎች ማሕበራዊ ጉዳዮች እንዳትረጋጋ ምክንያትና ሰበብ በመሆን ጦርነት፣ ውድመትና ክፋት ቆስቋሽና አስፈጻሚ ሆነው የምናያቸው የጥፋት መልእክተኞች በሙሉ በሀገሪቱ ካሉት የሃይማኖት ተቋማት መካከል በአንደኛው ሥር የተጠለልን ነን ማለታቸው አይቀርም።
በንግዱ ሥርዓት ውስጥም ቢሆን ባልተገባ መንገድ ሲስተሙን የሚበክሉ፣ በግፍ ተግባር ተክነው ባእድና ገዳይ ቁሶችን ወገኖቻቸው ከሚመገቡት ምግብ ጋር ቀላቅለው የሚሸጡ መኖራቸው የአደባባይ ምሥጢር ከሆነ ውሎ አድሯል። የሕዝብን መሬትና ሀብት ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ሉዓላዊ ክብር ለመሸጥና ለመለወጥ ሌት ተቀን የሚያደቡትም ቢሆኑ “ሃይማኖታችሁ ምንድን ነው?” ተብለው ቢጠየቁ ወደ አንዱ የእምነት ጎራ ጣታቸውን መጠቆማቸው አይቀርም።
በጉቦ፣ በዘረፋ፣ በቢሮክራሲውና በፖለቲካ ቡድናቸው ታዛ ስር ተጠልለውና ተሸሽገው ባለጉዳዮችን በማጉላላትና በማስለቀስ የተካኑትም ቢሆኑ ነፍሳቸውና ሥጋቸው መበከሉን እያወቁ እንኳን “የየትኛው ሃይማኖት ተከታዮች ናችሁ?” ተብለው ቢሞገቱ እንደተለመደው “የእከሌ ነና!” ብለው ማረጋገጫ መስጠታቸው ብቻም ሳይሆን በውጭ መገለጫቸውና በቋንቋቸው ጭምር በእምነታቸው እንደሚኩራሩ ለመመስከር የሚያቅማሙ አይደሉም። እንደዚህ የዘረፋውንና የውንብድናውን ወዘተ. ፈጻሚና አስፈጻሚዎች በየፈረጃቸው እየዘረዘርን እንፈትሽ ብንል እያንዳንዱ ተዋናይ በእርግጠኛነት “የአንደኛው ሃይማኖት ተከታይ ነኝ” ማለቱ አይቀሬ ነው።
እነዚህን የመሳሰሉ ሀገራዊ ህፀጾቻችንን ለማረቅና ምእመኑን ከመሰል ድርጊቶች ለመመለስ የየሃይማኖቶቻችን የትምህርት ጉልበቶች ስለምን አቅም አጥተው ተልፈሰፈሱ ብለን ብንሞግት ሊያስወቅሰን አይገባም። የሃይማኖት አስተማሪዎች ለሰማያዊው ጽድቅ ብቻ ሳይሆን በምድራዊው ኑራችንም እረፍት እዲኖረን ጠንክረው ለመስራት ስለምን አቃታቸውው? በትምህርቶቻቸው ፍሬስ ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋ የሚሄደው ኑሯችን ስለምን ሊፈወስ አልቻለም። ፆሙና ጸሎቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ምነውሳ የምእመናን የሕይወት ለውጥ እንደ ሰማይ ሊርቅብን ቻለ?
ኢሥነምግባራዊ በሆነ መልኩ አንዱ በሌላው ላይ ለመጠፋፋት እንዲነሳሳ ክፉ ዘር ሲዘሩ ውለው የሚያድሩት የክፋት መገለጫ ዜጎች “ሃይማኖቴ!” የሚሉት መሸሸጊያ እንዳላቸው የሚያጠያይቅ እንዳልሆነ የተግባባን ይመስለናል። “ከመልካም ተግባር የተፋታ ሃይማኖት የሞተ ስለመሆኑም” መምህራኑ “ሰዎቻቸውን” ስለምን በሥልጣነ “ክህነታቸው” እየገሰጹ እንደማያርሟቸው ግራ ያጋባል። እነዚህን መሰል በሃይማኖት “አርቲፊሻል የወርቅ ቀለም የደመቁ” ዜጎች አንድም በቋንቋቸው አለያም “ሃይማኖተኛ” ስለመሆናቸው በበርካታ ጠቋሚ ምልክቶች በቀላሉ የሚለዩ ሆነው እያለ ቸል መባላቸው ወይንም ለመንግሥት ውሳኔ ብቻ መተዋቸው ምክንያቱ ሊገባን አልቻለም። የሃይማኖት አባቶች መክረውና ዘክረው ሲታክታቸው “ያወግዛሉ” የሚባለው “እውነትስ” ምነው አዚም ሸፍኖት ደበዘዘብን?”
ከጥቂት ቀናት በፊት ይህ ጸሐፊ በተገኘበት አንድ ሃይማኖታዊ ጉባዔ ላይ የዕለቱ መምህር ትኩረት ሰጥተው ለምእመኑ ያስተላለፉት ትምህርት በበጎ አርአያነት የሚያስመሰግን ነበር። “አንዳንዶቻችሁ…” ብለው ጀመሩ መምህሩ። “ከዚህ ጉባኤ ውስጥ አንዳንዶቻችሁ ከድሃ ላይ በግፍ እየዘረፋችሁ ከምትሰበስቡት ገንዘብ አሥራት፣ መባ፣ በኩራት ወዘተ. እያላችሁ ለእግዚሃር ቤት አገልግሎት የምትሰጡት ስጦታ ተገቢ ስላልሆነ ረክሳችሁ የፈጣሪን ቤት አታርክሱ። በግፍ የሚገኘውን ገንዘባችሁን በላብ ዋጋ ከተሰበሰበው የምእመናን ገንዘብ ጋር አትቀላቅሉ። ”
“ፍትህን የምታጓድሉ፣ መደበኛ ተግባራችሁን ስትከውኑ ተገልጋይ የምታስለቅሱ፣ በንግዳችሁ እያጭበረበራችሁ ክብረትን የምትናፍቁ እንደ ጅማሬያችሁ ፍጻሜያችሁ ስለማያምር ቀኑ ሳይመሽባችሁ ፈጣሪ አምላካችሁ ኑና እንዋቀስ እያለ ጥሪ በማቅረብ ይጋብዛችኋል። በበደላችሁና በግፋችሁ የምትቀጥሉ ከሆነ ግን የምትመኩበት ሁሉ እንደ ጉም ይበናል፤ እንደ ትቢያም ከንቱ ይሆናል። ሳይመሽ በተሰጣችሁ ዕድል ንሰሃ ገብታችሁ ተመለሱ። ”
ከቤተ እምነቶቻችንና ከየምስባኮቻችን የጎደለብን ይህን መሰል ጠንክር ያለና ለንሰሃ የሚያደፋፍር ትምህርት ይመስለናል። ለጊዜው ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን። በዚህ ጽሑፍ በዋነኛነት ለማስተላለፍ የተሞከረው መልእክት የሃይማኖት መምህራኖቻችን በትምህርቶቻቸው እያነጹ እኛን ምእመናን ያርቁ የሚል ነው። ይህ እስካልሆነ ድረስ ሀገራችን ከገባችበት አረንቋ ፈጥና ልትወጣ ትችላለች ማለት ዘበት ነው። ታዲያ ማን ከማን ይዋቀስና ንሰሃ ይግባ? ለሚለው ጥያቄ መልሱ በቀዳሚነት ከህሊናችን ጋር፣ ቀጥሎም ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚመክረን ከፈጣሪ ጋር ሊሆን ይገባል። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9 ቀን 2015 ዓም