– አቶ ጥላሁን ሮባ የለሚኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደ ከቦሌእና ከየካ ክፍለ ከተሞች ቀንሶ አዲስ የተቋቋመው የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ ከህብረተሰቡ የሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች አሉ።ከጥያቄዎቹ መካከል የተወሰኑትን በማንሳት በተለይም በክፍለ ከተማው አለ ስለሚባለው የመሬት ወረራ እና የፋይል መጥፋት ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ከዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ጥላሁን ሮባ ጋር ቆይታ አድርገን በዛሬው የ‹‹ተጠየቅ›› ዓምዳችን ላይ እንደሚከተለው ለንባብ አብቅተነዋል።
አዲስ ዘመን።- በቅድሚያ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ እናንተ ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቃችሁ ወደ ሥራ ከገባችሁ ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የተሰራውን ሥራ ይግለፁልንና ቃለምልልሳችንን በዚህ እንጀምር።
አቶ ጥላሁን።- የከተማ አጠቃላይ ከፍተኛ አመራር በመሬት እና መሬት ነክ አገልግሎት አሰጣጦች ላይ የነበሩ ብልሹ አሠራሮችን ሲከታተል ስለነበር፤ ጉዳዩን አይቶ ፈጥኖ እርምጃ ወስዷል።አመራሮችን ቀይሯል።እኛም ወደ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከመጣን ወዲህ ቅድሚያ የሠጠነው ሥራዎችን መለየት ላይ ነው።መሬት ልማት ማኔጅመንት ላይ ልምድና ቁርጠኝነት ያላቸውን አመራሮች ተክተናል።በዚሁ መሰረት ስራችንን ስንጀምር መጀመሪያ አገልግሎታችንን ለማሳለጥ ችግሮችን መለየት ላይ አተኩረናል።
የተተኩ አመራሮች ከሰራተኞች ጋር በመወያየት እና ችግሮችን በመለየት ወደ ተግባር ስራ ገብተዋል።በዛ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በክፍለ ከተማው ሊሠሩ የሚገቡት ሥራዎች ላይ ከአመራር፣ ከአርሶ አደርና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር መድረክ በመፍጠር ተወያይተናል።በአጭር ጊዜ ሊፈቱ የሚችሉ፤ ዕቅድ የሚያስፈልጋቸው፤ በረዥም ጊዜ መፈታት ያለባቸውን ለመለየት ያስቻለ መነሻ ላይ ደርሰናል።
አዲስ ዘመን።- በእርግጥ አሁን ላይ በተጨባጭ የተገኘውን ለውጥ ለመለካት ቢያዳግትም በዋናት የሚጠቀሰው ችግር የመሬት ጉዳይ ሲነሳ ከፋይል ጋር ይያያዛል።ፋይል ማደራጀትን በተመለከተ ‹‹ ፋይል ጠፋ›› የሚለውን የሙስና በር ለመዝጋት ምን ያህል ሔዳችሁበታል?
አቶ ጥላሁን።- በቅድሚያ መሥራት ያለብን ሰው ላይ መሆን እንዳለበት አምነናል።ሰው ላይ ሲባል ደግሞ ፋይሉን በተመለከተ ሊሠሩ የሚገባቸው ፈፃሚዎች ላይ ማለት ነው።የሥራ ክፍሎችን በመለየት ምን ጥንካሬ አለ? ምን እጥረትና ክፍተት አለ? የሚለውን በደንብ መለየት ላይ አተኩረናል።
ሌላው የትኛው የስራ አካባቢ ነው እንግልት እና ምልጃ ይጠየቅበታል? የሚለውን ለመለየት የመሬት ልማት ማኔጅመንትን ሥራ አቁመን ነበር።አሁን የጀመርናቸው እና መልሰንም ያቆምናቸው አገልግሎቶች አሉ።አንደኛው አርሶ አደር እና ከአርሶ አደር ጋር በተያያዘ መብት ፈጥራ፤ የይዞታ ባለቤትነት የተመለከተ ጉዳይ ነው።‹‹በከፍተኛ ደረጃ በደላሎች እየተዘረፍን ነው›› የሚለው በየመድረኮችም በሰፊው ሲነሳ ነበር።ይህ እስከ ሚጣራ ድረስ ይቆይብለናል።ስለዚህ አሁን የአርሶ አደር ይዞታ አገልግሎት አሰጣጥ ጉዳይ ቆሟል።
በሌላ በኩል የልማት ተነሺዎች ጉዳይም ግልፅ አይደለም።አንዱ ሌብነት የሚፈፀመው በልማት ተነሺ ስም ነው።ሁሉም የልማት ተነሺ ሌባ አይደለም።ነገር ግን ከዛ ጋር ተያይዞ አንዳንዶች ሳይገባቸው አብረው መጥተው መብት የሚያገኙበት ሁኔታ አለ።የሚል ሃሳብ በውይይቶች ስለተነሳ እና ይህንንም የሚያመለክቱ መረጃዎች በመኖራቸው፤ በዚህ ላይ ለጊዜው አገልግሎት ከመስጠት ለመቆጠብ ተገደናል።ስለዚህ 2011 ዓ.ም፣ 2012 ዓ.ም፣ 2013 ዓ.ም እና 2014 ዓ.ም ካርታ የወጣባቸውንና የልማት ተነሺዎች ላይም አገልግሎት መስጠትን በሚመለከት ለጊዜው የማቆየት ውሳኔ ላይ ተደርሷል።
ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ አልዘጋንም ነባር ይዞታዎች ላይ በክርክር በፍርድ ቤት አገልግሎት ማግኘት ለሚፈልጉ ነዋሪዎች አገልግሎት እየሰጠን ነው። አስቸጋሪ የሆኑትን እያጣራን ነው።እዚህ ላይ ጎን ለጎን ደግሞ ሁሉም ይዞታዎች በዲጂታል እንዲሆኑ እንፈልጋለን።ዲጂታል ሲሆኑ የፋይል መጥፋት እና መደራረብ ላይ ችግር የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን በቴክኖሎጂ ተመሥርተን እንቀንሳቸዋለን ብለን የአጭር ጊዜ ዕቅድ ይዘናል።
አገልግሎት የሚሰጥበት ቦታም ምቹ ያለመሆን ሁኔታ ነበር።ይህንን በማስተካከላችን የፋይል መዝረክረኮች ፈር እየያዙ ነው።ሁለተኛው ሩብ ዓመት ላይ በተሻለ እና በተደራጀ ሁኔታ እንጨርሳለን።አጠቃላይ እስከ አሁን አንደኛው ሩብ ዓመት የቻልነውን እየጨረስነው ነው።
ለአርሶ አደሩም አገልግሎት የመስጠት ጉዳይ ተዘግቶ አይቆይም።ትክክለኛ አርሶ አደሮችን እያጠራን እየለየን ነው።በትክክል ከደላላ ነጻ የሆነ ራሱንና ራሱን ብቻ የሚገልጽ አርሶ አደር ነው ወይ? በማለት አርሶ አደሮችን እየለየን የማጥራት ሥራ እየሠራን ነው።በዚህ ሂደት በስኬት እየሔድን ነው።ሲጠናቀቅ የደረስንበትን መሬት ልማት ማኔጅመንት ይሔድበታል።
መሬት ልማት ማኔጅመንትም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ከሰራተኞቹ ጋር በቅርበት በመነጋገር ችግሮቹን እየለየ የሚያንገላታው ማን ነው? በማለት እየገመገሙ እስከ ምሽት ሥራቸውን ይሠራሉ።በየዕለቱ ተግባራቸውን ይገመግማሉ፤ በዚሁ መሠረት የማጥራት ሥራ እየሠራን ነው።ከዚህ በተረፈ ወደ ሕግ በመሔድ ተጠያቂነት መኖር ካለበትም ከግኝት በመነሳት ወደ ተጠያቂነት እናመራለን።ማንም ቢሆን አመራርም ሆነ ፈፃሚ መጠየቅ ያለበት ይጠየቃል።
ታጭቀው የነበሩ የተለያዩ ምቹ ያልሆኑ አሠራሮችን ቅድሚያ በማስወገድ እየሔድን ነው።መጠነኛ መሻሻሎች መኖራቸው በተገልጋይ አስተያየቶች ላይ እየተገለፀ ነው።በኮሙኒኬሽን በኩል እያንዳንዱ ተገልጋይ ሲመጣ ምን አስተያየት አለ? ምን እናሻሽል? እያልን አልፎ አልፎ ተገልጋይን እየዞርን እናነጋግራለን።ይህንን ማድረጋችንም የተገልጋዩን ፍላጎት ለማወቅ እያገዘን ነው።ተገልጋይም በበኩሉ ‹‹በርቱ ቀጥሉ›› በማለት ላይ ይገኛል።አንዳንዴም ችግር ያለባቸው አካላት አሁንም ሲመጡ በማየታቸው ለምን ተጠያቂ አይሆኑም የሚሉ ሃሳቦችን ይሰነዝራሉ።ተጠያቂነቱ የታለ የሚል የሕዝብ ተደጋጋሚ ጥያቄ አለ።ይህንን በማስረጃ እና በመረጃ አስደግፈን በተደራጀ መልኩ የምንሔድበት ይሆናል።
አዲስ ዘመን።- ጥያቄውን ከፋይል ጋር ያያዝኩበት ምክንያት ብዙ ጊዜ የመልካም አስተዳደር ችግር እና ሙስና የሚፈፀመው ከፋይል ጋር ተያይዞ በመሆኑ ነው።በክፍለ ከተማችሁ ለጠፋ ፋይል ከ1 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር የሚጠየቅ ስለመሆኑ ይወራል።ፋይል ሲጠፋ ፋይሉ ሲገኝ እንደውላለን በሚል ሰበብ ስልክ ቁጥር ወስዶ መደራደር ስለመኖሩም ይነገራል።ስለዚህ ምን ትላላችሁ?
አቶ ጥላሁን።- እዚህ ላይ በትኩረት በመስራት ላይ ነን።ከየካ እና ከቦሌ ክፍለ ከተሞች ተቀናጅቶ 160 ሺህ ፋይል እዚህ ተመስርቷል።ርክክብ ስናደርግ ቀደም ሲል ፋይል ተደራጅቷል ብለው ያሳዩን ትክክል አልነበረም።በአንድ አቃፊ ውስጥ ሁለትና ሶስት ፋይሎች ነበሩ።በአንድ ሰው ስም ፋይሉ ሲፈለግ አይገኝም ነበር።ይህንን በአጭር ጊዜ ለመፍታት ያስቸግራል።
በሁለተኛው ሩብ ዓመት ላይ በዲጂታል ካደረግን 160ሺህ ፋይልን በአጭር ጊዜ ማደራጀት ያስቸግራል።ስለዚህ ሥራው ቦታውን ምቹ ከማድረግ ይጀመራል።በከፍተኛ ሥራ በሁለት ወር ውስጥ እናከናውነዋለን ብለን አስበናል።ነገር ግን ይህ ያለንበት ሕንፃ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የተደባለቀ እና ለአገልግሎት አሰጣጥም ምቹ ባለመሆኑ ያ ይስተካከላል።
ሌሎች ክፍለከተሞች የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ሕንፃው የተለየ ነው።ይህ ግን ከሌሎች ዘርፎች ጋር የታጨቀ በመሆኑ ለማስተካከል ያስቸግራል።ቢሆንም ሌሎች ሕንፃዎችን በኪራይ በማመቻቸት አሁን የምንለውን ፋይሎችን ዲጂታል በማድረግ መደራደር እንዳይኖር እናደርጋለን።በእርግጥ አሁን ባለው ሁኔታ ስጋቶች አሉ።ለዚህም ተነጋግረናል።ሆኖም ግን አሁንም ሙስና ተፈፀመ ከተባለ ወዲያው እርምጃ እንወስዳለን።አሁን ላይ ግን ሙሉ ለሙሉ የመልካም አስተዳደር ችግር የለም ፤ ዜሮ ሆኗል የሚለውን አናውቅም።
አሁን ለአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።መዘግየት ሲኖር የቅርብ አለቃም ሆነ እኛ እንሰማለን።ስለዚህ ለመደራደር ያለው አቅም አነስተኛ ነው።አገልግሎት በሚሠጥበት ጊዜ የሠራተኛው ቁጥር ውስን በመሆኑ ሊራዘም ይችላል።ይህ ወደ ፊትም ያጋጥማል።ነገር ግን መደራደር ስልክ ቁጥር መያዝና ለፋይል ተመን ማውጣት የለም።ነገር ግን ዜሮ ሆኗል? የሚል ጥያቄ ከቀረበ ያንን ለመግለፅ ያዳግታል።
አዲስ ዘመን።- እናንተ ወደ ስራው ከመጣችሁ በኋላም ሆነ በፊት ባለሙያም ሆነ አመራር ላይ የወሰዳችሁት ሊገለፅ የሚችል እርምጃ አለ?
አቶ ጥላሁን።- የመጀመሪያ ሥራው የፖለቲካ እርምጃ ነው።የመሬትን ሥራ ሲመሩ የነበሩት ላይ ከሹመት የማውረድ ሥራ ተሠርቷል።ይህ ማለት እኛ ስንረከብ ሁለቱ ሃላፊዎች ተነስተዋል።ከችግሩ ጥልቀት አንፃር የተወሰነ ሃላፊን በማንሳት ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትን በማስፈንም ጭምር የሚያስጠይቅበት ሁኔታ ሲኖር ደግሞ ባለፈው አንድ ወር ባገኘነው ግኝት እና በአጭር ጊዜ እየተጠኑ ባሉ ሁኔታዎች ወደ ፈፃሚም የሚወርድበት ሁኔታ ይኖራል።በቅድሚያ ግን አመራር በማንሳት ያንን ሊመራ የሚችል ዕውቀት ያለው አመራር ተክተናል።የመጀመሪያው እርምጃ እርሱ ነው።
ሁለተኛው አመራሮቹ ከተነሱ በኋላ ማንም ፈፃሚ አልገባም።አሽገን ነገሩ እስከሚገመገም እና ችግሩ እስከሚለይ የትኛውን አገልግሎት ብንጀምር ይሻላል የሚለውን እስከምንለይ ድረስ ሰራተኛውን አላስገባንም።በኋላም ሕዝቡን ስላቆየን ይቅርታ ጠይቀን ለማስጀመር ሞክረናል።
አዲስ ዘመን።- ለሚ ኩራ ላይ ካርታ መከነ የሚል ወሬ ይናፈሳል፤ በማህበራዊ ሚዲያም ሆነ በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ይገለፃል።ካርታ የሚመክነው ለምንድን ነው?
አቶ ጥላሁን።- አሁን እኛ እያጠራን ነው።ከላይ የገለፅኳቸው የአርሶ አደርን ጉዳይ ስናይ አርሶ አደር ሳይሆኑ እዚህ የገቡ በተለይ እኛ ከመጣን በኋላ የሉም።ነገር ግን ውጪ የሚሰሩ ካርታዎች ስለመኖራቸው መረጃ ይደርሰናል።ውጪ አሉ ማለት እኛ ጋር ወደ ፋይላችን ይገባሉ ማለት አይደለም።ነገር ግን ቀደም ሲል በዛ መልክ ተዘጋጅተው ወደ እኛ ፋይል የገቡ አሉ።ይህንን ለማግኘት የአርሶ አደርን መረጃ እያጠናን ነው።
ሁለተኛ የልማት ተነሺ እና ሌሎችንም ኦዲት ማድረግ እየጀመርን ነው።እርሱ ሲጠናቀቅ እነዚህ ካርታዎች ባለቤት የላቸውም፤ እኛን አይገልፁም፤ በአግባቡ ተደራጅተው የመጡ አይደሉም እያልን ብዛታቸውም ይህን ያክላል ብለን እናስወግዳቸዋለን።ነገር ግን ከዚህ በፊትም መቃጠል እና መወገድ የነበረባቸው ተከማችተው የነበሩ፤ አንዳንዴም ለሌላ አሰራር ሲያጋልጡ የነበሩ የመሬት ልማት አመራሮች እዛ አካባቢ ከተወከሉ በኋላ በአደባባይ አቃጥለናል።ይሔም እዚህ የተቀመጡ ከኋላ እየታዩ የሚሰሩ ካርታዎች መኖራቸውን በተመለከተ መረጃ ስላለን ነው።በተጨማሪ በከተማ አስተዳደር ደረጃም የተቀመጠ አቅጣጫ ነበር።
ካርታዎቹ አዲስ ናቸው።ተከማችተው ያሉ ነገር ግን ለፎርጂድ መስሪያ ይውላሉ በማለት የከተማ አስተዳደሩ ማስወገድ አለብን ባለው መሠረት ተቃጥለዋል።ይሔ በሌሎች ክፍለከተሞችም የተፈፀመ ሲሆን በይፋ ሁሉም ባለበት የተቃጠለ ነው።
አዲስ ዘመን።- በክፍለ ከተማው ያሉ ክፍት ቦታዎች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚያዙበት ሁኔታ ስለመኖሩ ይነገራል።እርሶ ግን በትክክል ደንብ የማስከበር ሥራ እየተሠራ ነው ብለው ያምናሉ።
አቶ ጥላሁን።- አሁን እኛ ከመጣን ወዲህ ሌሊትም ሆነ ቀን በማንኛውም ሰዓት ቢታጠር እርምጃ የሚወሰደው ወዲያው ነው።በየዕለቱ አሰሳ ይደረጋል፤ በግብረሃይልም ግምገማ ይደረጋል።በየዕለቱ ለሰላምና ፀጥታ ሕዝቡን በማደራጀት ደረጃ እንቅስቃሴ ይደረጋል።በቀደም ወረዳ አንድ ላይ አንድ ሔክታር የሚሆን መሬት በሌሊት ሲታጠር መረጃ ደረሰን፤ ወዲያውኑ ሄደን በቦታው ተገኝተን አስቁመናል።ሌሎችም በዓልን አስታከው የሚያጥሩ ነበሩ።ወዲያው መረጃው እንደደረሰን እርምጃ እንወስዳለን።
ክፍት ቦታዎች አሉ።ቦታዎቹ ግን አብዛኛዎቹ ለኢንቨስትመንት የሚውሉ እና ከተማው የሚወስናቸው ናቸው።በከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት ከዛም በካቢኔው ውሳኔ ለኢንቨስትመንት እና ለተለያዩ ተቋማት በዕውቀት ላይ በተመሰረተ መልኩ ይሰጣሉ።ሌላው ደግሞ አስተዳደሩ ራሱ የሚያስገነባቸው ተቋማት አሉ።እኛ ራሳችን ቢሮ የለንም።ወረዳዎቹ፣ ወጣት ማዕከላቱ፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ትምህርት ቤቶች እነዚህ ሁሉ ቦታና ግንባታ ይፈልጋሉ።ስለዚህ ከላይ ካልናቸው ‹‹የልማት ተነሺዎችና አርሶ አደር ነን›› ብለው በአርሶ አደር ስም የታጠሩ ቦታዎችን አሁን በማጥራት ሒደታችን በህገወጥ መንገድ ይዘው የተገኙ ከሆነ እርምጃ እንወስዳለን።
ማንም ሰው የሕዝብ እና የመንግሥት ንብረትን ማንም ሰው ከመሬት ተነስቶ መውሰድ አይችልም።ዋናው የሕግ የበላይነትን ማስፈን ነው።መሬት በፕላን የሚመራ ነው።ማንም እንደፈለገ አጥሮ የኔ መሬት ነው ብሎ ካርታ የሚያወጣበት አይደለም።ነገር ግን ይህ እንዴት ተሰጠ የሚለውን ከብሎክ ጀምረን እናያለን።በፍፁም ይህንን አንታገስም።ይህ የመንግሥት ቁርጥ አቋም ነው።ሕገወጦች ላይ እርምጃ እንወስዳለን።
ቀድመው ታጥረው የተገኙት ደግሞ ዝም ብለን በጅምላ ይፍረሱ ሳይሆን አሁን ባቋቋምነው አጣሪ ተጣርቶ የሚመክን ካርታ ካለ ይመክናል፤ መፍረስ ያለበትም ይፈርሳል።ባለመሬቱ ራሱ ካለ ደግሞ በመመሪያ መሰረት ይስተናገዳል።ሌላው ግን በእምነት ተቋማት ስም መጥተው መሬት የሚወሩበት ሁኔታ ፈተና ሆኖብናል።የእምነት ተቋማት ከጀርባቸው የእምነት ተከታዩ ሕዝብ አለ።ነገር ግን ሕዝቡ መሬት እንዲወረር ፍላጎት የለውም፤ ነገር ግን እነርሱ ሌላ ተልዕኮ ያላቸው፤ ይህንን ይፈፅማሉ።
አዲስ ዘመን።- ቀጣዩ ጥያቄዬ ይህ ነበር።እንዳውም የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማው በተቋቋመ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በክፍለ ከተማው በርካታ አዳዲስ ቤተዕምነቶች ስለመገንባታቸው ይነገራል።እንደውም ለአንድ ቤተ እምነት መገንቢያ ቦታ እጅ መንሻ እስከ 5 ሚሊዮን ብር ይሰጥ እንደነበርም ይገለፃል።ይሄ በእናንተም ግምገማ የታየ ነው ?
አቶ ጥላሁን።- እንደተባለው ‹‹እጅ መንሻ ይሰጣል፤ ደላላም በስፋት አለ›› የሚለው ወሬ መዓት ነው።መሬቱ በትክክል ሙስና ተሰጥቶ ነው የተገኘው የሚለውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።ለቤተ እምነትም ሆነ ለሌላ መሬት እንዴት እንደሚተላለፍ መመሪያ አለ።ለትላልቅ ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን እኛ ራሳችን ‹‹ትምህርት ቤት መገንባት እንፈልጋልን›› ብንል ቦታውን ለይተን ወደ ከተማ አስተዳደሩ እንልካለን።
የከተማው መሬት ማኔጅመንት ይወያያል፤ ለካቢኔ ቀርቦ ውሳኔ ይተላለፍበታል።ይህንን ሒደት ጠብቀው ያገኙ የእምነት ተቋማት አሉ።የተለያየ እምነት ተከታይ ሕዝብ በክፍለ ከተማው አለ።የሚያመልክበት ቦታ ሊጠይቅ ይችላል።ስንት ካሬ ሜትር መጠየቅ ይችላል? ከተባለ በከተማ ደረጃ ይታወቃል።እዚህ ቦታ ላይ ይህን ያህል ካሬ ይሰጣቸው ይባላል።ነገር ግን አሁን ያለው ችግር የእምነት ተቋማት ቀድመው ቦታ በመያዝ ያንን ቦታ እንዲፈቀድ የማድረግ ሁኔታዎች አሉ።
እንደውም አንዳንድ የእምነት ተቋማት በካቢኔ ተወስኖላቸው ሕገወጦች ይዘው አንለቅም ያሉ አሉ።እነዛ ‹‹ሕግ ይከበርልን›› ብለው የጠየቁ አሉ።አንዳንዱ ደግሞ የያዘውን እያሰፋ እና ሌላውን እያስለቀቀ ስለእውነት ያ ቦታ ለእምነት ቦታ የተፈቀደ ነው ወይ? ሲባል በፕላን ለትምህርት ቤት ወይም ለሌላ ዓላማ የተዘጋጀን ቦታ ቤተ እምነት ይገነባሉ።ወይም የማስፋፋት ሕግ ለማስከበር ሲኬድ ደግሞ ከእምነት ጋር የማያያዝ ሁኔታ አለ።በእርግጥ ሕዝቡ የሚያቀርባቸው ቅሬታዎች አሉ።በእርግጥ እነዚህ የእምነት ተቋማት የራሳቸው ካርታ አላቸው ወይ? በማለት በተፈቀደላቸው ቦታ ላይ ናቸው ወይ? የሚለውን ማጣራትን ይጠይቃል።
አሁን ግን ቅድሚያ የማጣራት ስራ የምንሰራው የአርሶ አደሩን እና የልማት ተነሺውን ጉዳይ ነው።የእምነት ተቋማት አጥር ራሱ በከተማ አስተዳደር ደረጃ እንጂ በእኛ ደረጃ አይፈቀድላቸውም።ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በቤተ እምነት ስም ቦታን ማስፋፋት እና ለእምነቱ ሳይሆን ለሌላ ዓላማ የመጠቀም ሁኔታ አለ።በእምነት ተቋም ውስጥ ሽብርተኛን ሲያሰለጥኑ ፣ መሳሪያ ሲያከማቹ የተያዙ አሉ።ይህንን የማንም እምነት አይፈቅድም።ሁሉም የእምነት ተቋማት መሪዎች በጉዳዩ ላይ በጥንቃቄ ማሰብ አለባቸው።ስሜታዊ የሚያደርግ ቢሆንም ሕግን ማስከበር ደግሞ ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን።- በክፍለ ከተማው ቀድሞም በነበሩ መኖሪያ ቤት አካባቢዎች ለአረንጓዴ ልማት እና ለነዋሪው መናፈሻ ቦታዎች ታስበው የተተዉ ቦታዎች አሉ።እነዚህን ቦታዎች ግለሰቦች የሚወሩበት ሁኔታ እንዳለ እየተነገረ ነው።ለምሳሌ ሻይ የሚያፈሉ አስመስሎ ሸራ መወጠር ከዛም አስፋፍቶ መያዝና ቀስ በቀስ እስከማጠር የሚደርሱ አሉ።እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ጥላሁን።- ይህንን የሚጠብቅና የሚከታተል ፅህፈት ቤት አለን።አንዱ መሬት የሚያዝበት መንገድ አረንጓዴ ልማት በሚል ነው።የጋራ መኖሪያ ቤት ላይ የመስክ ነው ብለው ዛፍ እየተከሉ ቀስ በቀስ ይይዛሉ።ነገር ግን በፕላኑ ላይ መሬቱ ለአረንጓዴ ልማት ከሆነ ለአረንጓዴ ልማት መዋል አለበት።ከዛም አልፎ የመንገድ አካፋይን ሳይቀር የሚይዙ ሰዎች ይኖራሉ።ሕብረተሰቡም እንደመብት ይቆጥራል። አረንጓዴ ልማት በመንግሥት የሚለማ አለ። በግል አልሚዎች የሚለማ አለ።ምንም መቀየር ሳይኖር በዛው ልክ መጠቀም ያስፈልጋል።ከዛ ውጪ በአረንጓዴ ልማት ስም ይዘው የሚያካትቱትን ህብረተሰቡ ሊጠቁም ይገባል።እኛም ሕግ እናስከብራለን።
አደባባይን ሳይቀር ሻይ ለማፍላት እየተጠቀሙ የሚይዙ አሉ።ወረራው ትንሽ አይደለም፤ ብዙ ነው። ሕብረተሰቡ ደግሞ የሚጠቁም ከሆነ መሬቱ ለሌላ ዓላማ እንዳይውል ማድረግ የኛም ግዴታ ነው።ሕብረተሰቡም መከላከል አለበት።በተጨማሪ መሬት መያዝ በተለያየ መልኩ አለ።ብዙ ኮንደሚኒየሞች አሉ።ኮንደሚኒየሙን አጥሮ በመያዝ ማንም ወደዛ እንዳይገባ የማድረግ ሁኔታ አለ።ይሔ የአረንጓዴ ልማት ቦታችን ነው ይላሉ።ማን ሰጠ? የሚል ጥያቄ ሲቀርብ ምላሽ የለም።ለምሳሌ የሪል ስቴት አልሚዎች መሬቱን በሊዝ ገዝተው ከሚገነቡበት ውጪ ያለውን ይሔ መናፈሻ ነው ሊሉ ይችላሉ።በሊዝ ስለያዙ ይችላሉ።
አዲስ ዘመን።- በክፍለ ከተማው ልዩ ስሙ 49 ማዞሪያ በሚባለው አካባቢ ባሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የ2011 ዓ.ም የ40 በ60 የቤት ዕድለኞች ‹‹ቤቱ እጣ ከወጣበት ሶስት ዓመት አለፈ።መንገድ ባለመሰራቱ ፍሳሽ ማስወገጃው ከጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ጋር አልተያያዘም።መንገድ እንዳይሰራ ደግሞ ካሳ አልተከፈለንም ያሉ ሰዎች የመንገድ መስሪያ ማሽን እናቃጥላለን በማለታቸው መንገዱ መሰራት አልቻለም።ክፍለ ከተማውም ጉዳዩን ማስተካከል ተስኖታል።›› ሲሉ ይደመጣሉ ፤ በዚህ ላይ ምን ምላሽ አለዎት ?
አቶ ጥላሁን።- በእርግጥ ጉዳዩን በቅርቡ ሰምቼዋለሁ።በአጋጣሚ አንድ መገናኛ ብዙሃን መጥቶ ሲጠይቅ ባለጉዳዮቹ ይምጡና ችግሩን እናየዋለን ብለናል። ጉዳዩን አናውቀውም ነበር።በክፍለ ከተማው ብዙ ችግሮች አሉ።ገና አሁን በእያንዳንዱ ላይ ውይይት ካላደረግን ችግሮችን አናውቃቸውም።ነገር ግን በየቀጠናውና በየወረዳው ውይይት እናደርጋለን። የሕብረተሰቡን ችግር ወደ ዕቅዳችን አስገብተን እንመልሳለን።
እነዚህ የጋራ መኖሪያ ቤት ሥራዎች በቅንጅት የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው።በእርግጥ ቤቱ ተገንብቷል።አንዳንዶቹ ቁልፍ ተሰጥቷቸዋል።ነገር ግን እነሱ ሲያስረዱን ለመኖር የሚያስችል ምንም ምቹ ሁኔታ አልተፈጠረም።ምክንያቱም ፍሳሽ ማስወገጃ የለም።ሰዎች ከሌላ ቦታ ውሃ እንኳን ቀድተው ለመጠቀም ቢሞክሩ አይሆንላቸውም።ምክንያቱም ፍሳሽ ማስወገጃው መስመር አልተገናኘም።
እዛ አካባቢ እንደውም ፍሳሹ በሚያርፍበት ቦታ ቤቶች ተሰርተዋል።ሰዎቹ በእርግጥም እስከዚህ ደረጃ መድረስ አልነበረባቸውም፤ ምክንያቱም መንገዶች፣ ቤቶች፣ውሃና ፍሳሽ እና እኛ ሆነን መስራት ነበረብን።የእነዚህ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶ ተገናኝቶ በሁለት ቀንም ይሁን በሳምንት ምላሽ ባለመስጠቱ ለዚህ ደርሰዋል።ነገር ግን በቅንጅት መሠራት አለበት።ሁላችንም ያጋጠሙ ችግሮችን እየገመገምን ችግሩን መፍታት አለብን።መንገድም፣ ውሃና ፍሳሽም፣ ቤቶችም ክፍለከተማውም ተቀናጅተን መስራት አለብን።
በእኛ በኩል በቦታው ላይ ሰዎች ካሉ እና ካሳ የሚያስፈልጋቸው ከሆነ ነዋሪ ስለመሆናቸው መረጃ ተደራጅቶ ለመሬት ልማት ቀርቦ ተረጋግጦ ይላክላቸውና ካሳ ይከፈላቸዋል።ሕገወጦች ከሆኑ ደግሞ ሕገወጥ ስለመሆናቸው ተረጋግጦ እርምት ይወሰዳል።የአካባቢውን ሰዎች አነጋግረናል ነገር ግን የብዙ ባለድርሻ አካላትን የያዘ ነው።ለወረዳዎችም እንዲያጣሩ ትዕዛዝ ሰጥተናል።
አዲስ ዘመን።- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ።ቶ ጥላሁን።- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
በምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥቅምተ 9 ቀን 2015 ዓም