ከመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች አንዱ ነው። ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ሊኖረው የሚገባ ጉዳይ ነው። ሰው በዜግነቱም ሆነ ሰብዓዊነቱ የዚህ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት ተጠቃሚ የመሆን ሙሉ(ወይም፣ ያልተሸራረፈ) መብት አለው። ይህንን ስንል ግን ግዴታውን አሟልቶ ሲገኝ ነው።
ከላይ ግዴታውን (መስፈርቱን አላልንም፤ ምክንያቱ ደግሞ መስፈርት እንደየግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ርዕዮቶች … ስለሚለያይ) ስንል ልክ እንደ መሰሎቹ ማግኘት የሚያስችለውን ግዴታ አሟልቶ ከተገኘ እንዳያገኝ የሚያደርገው ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል ”የለም” ማለት ነው።
“በ’97 የተመዘገባችሁ …” የሚለው ርዕሳችን ጥሪ ከመሰለ ይቅርታ እየጠየቅን ጥሪ አለመሆኑን እንገልፃለን። ጥሪ አለመሆኑን ስንገልፅ ግን በ2015 ዓ.ም ሳይቀር “በ’97 የተመዘገባችሁ …” ማለቱ ከማንኛውም መመዘኛ አኳያ ሲታይ የሚያስኬድ አለመሆኑን በመግለፅ ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያን ከመሰለና የጠንካራ መንግሥት ባለቤትና ተምሳሌት ከሆነ አገር (እንድገመውና በ2015 ዓ.ም) “በ’97 የተመዘገባችሁ …” የሚለው እማይጠበቅና እማይመጥናትም ጭምር መሆኑንም በመግለፅ ነው።
ይህንን ካልን ወደ አንድ ታሪካዊ ጉዳይ እንሂድና ተሞክሮዎችን እንመልከት – American Dream። (ላይ ላዩንም ቢሆን) በቀላሉ መረዳት እንደሚቻለው American Dream የአሜሪካ ሕልም ነው። ሀገር እንደ ሰው ሕልም ያየበት፣ ራዕይ የሰነቀበት …. መሆኑ ነው።
ይህ በእነሱ አቆጣጠር በ1931 ለአደባባይ የበቃውና ወደ ሥራ ቋንቋነት የተቀየረው American Dream ዋና ተዋንያኑ ሰዎች ሲሆኑ፤ እነሱም አሜሪካውያኑ ናቸው። የሕልሙ ዓላማም አሜሪካውያንን የሁሉም ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች፤ በተለይም የመኖሪያ ቤት(ቶች) ተጠቃሚ (ሰነዱ ”owning your own house” ነው የሚለው) በማድረግ አሜሪካንን የበለፀገች ማድረግ ነው። (ዝርዝር ታሪኩን ከየትም መረዳት ስለሚቻል እንዝለለው።)
ይህን፣ በመዝገበ ቃለት(ዲክሽነሪ) የተካተተን ፅንሰ ሀሳብ ኦክስፎርድ ፍቺ የሰጠው ሲሆን፣ በፍችውም ግዴታዎችን (hard work, determination, and initiative) አካትቷል። እነዚህን ያሟላ ሁሉ ወደ ብልፅግና ማማው መረማመድ የሚችል ሲሆን፤ አሠራሩ ለአድሏዊነት፣ ወገናዊነት … ምንም አይነት በር እንደ ሌለ ያመለክታል።
እንግዲህ የቤት ባለቤት (የመንግሥት ቤቶች ፕሮግራም ተጠቃሚ) ለመሆን ጥያቄው የተጠቀሱትን ግዴታዎች ሟሟላት ነው።
የቤት ፕሮጀክቱን፣ ፕሮግራሙን፤ ለዛውም የቆመበት መሠረት ”ለደሀው …” የሆነውን … ድብን ያለ የ… መሣሪያ ማድረግ፣ የችግሩ ገፈት ቀማሾች እንደሚሉት ”በምድርም በሰማይም ያስወቅሳል፤ ያስጠይቃልም።” ይህ ግን የሚሆነው ወቃሽም ጠያቂም ሲኖር እንጂ ከሌለ “በ’97 የተመዘገባችሁ …” ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። ከአጠቃላይ የግንባታ ፕሮጀክቶች አኳያ ወደ ዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንምጣ።
እንደሚታወቀው፣ ኢትዮጵያ ይህንንም ሆነ ሌሎች (ሜጋዎችን ጨምሮ) ፕሮጀክቶችን (ለምሳሌ የስኳር) በተመለከተ የጥቂቶች የገቢ ምንጭ ይሆኑ ዘንድ ሆን ተብሎ፣ በእቅድ የተሠራ እስኪመስል ድረስ (ካልሆነ ማለት ነው)፣ መፈንጫ ሆና እንደ ነበር ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉና እነሱን መለስ ብሎ መቃኘት ነው። ከዛ ወዲህስ?
ሁላችንም እንደምንመለከተው ከለውጡ ማግስት የግንባታ ፕሮጀክቶች ለማመን በሚያቅት ደረጃ ሁሉ ጥሩ አፈፃፀምን እያሳዩ ነው (ለዛውም ጥራትን ከውበት ጋር – ይህ የባለሙያ አስተያየት አይደለም)። ይህንን ለማረጋገጥ 1፣ 2፣ 3 … እያሉ ከመዘርዘር ይልቅ በቀላሉ ለመናገር ከመስቀል አደባባይ ተነስቶ፣ በአራት ኪሎ አድርጎ ወደ እንጦጦ ማቅናቱ ብቻ ለማሳያነት በቂ ነውና በዚሁ ማለፍ ይቻላል። ያንሳል ከተባለም፣ ከእንጦጦ ወደ ፒያሳ ወረድ ብሎ የአድዋውን ”ዜሮ ፕሮጀክት” መመልከት ነው፤ ተስፋን ሁሉ ያጭራል። ችግሩ፣ ድህረ ዐቢይ አስተዳደር የግንባታ አመራርም ይሁን አሠራር በእነዚህ እየታየ ያለው ለውጥ ለምን ወደ ኮንዶሚኒየሙ ዘርፍ ጎራ ብሎ፣ ከተማዋ አስተዳደር የሌላት የሚያስመስለውን ”በ’97 የተመዘገባችሁ …” አገላለፅ ለማስቀረት፤ ተረት የማድረግ፣ በዘርፉ ያለውን … ለመፍታት ጥረት አላደረገም ነው።
ዛሬ፣ ምንም እንኳን የመኖሪያ ቤት ችግር የትም አገር ያለ ቢሆንም፣ የተሻለ አፈፃፀም ያሳዩ ሀገራት የሉም ማለት አይደለም፤ ሞልተዋል። ደቡብ አፍሪካ እኮ የአጠቃላይ ሀገሪቱን የቤት ችግር የፈታችው በ5 ዓመት የልማት ፕሮግራም ነው፤ ፊሊፒንስ በተሻለ ምሳሌነት የምትጠቀስ አገር ነች። መጥቀሱ ቤት አይሠራም እንጂ ብዙ መጥቀስ ይቻላል።
አንድ ጠንካራ መንግሥት ያላት ሀገር ውስጥ፣ ያልተቋረጠ አስተዳደር ባለቤት የሆነች አገር ውስጥ፣ የከተማ ውስጥ የባቡር መስመርን በ5 ዓመት የገነባች ሀገር ውስጥ፣ … ውስጥ፣ …. ውስጥ …፤ እንዴት በ2015 ዓ.ም “በ’97 የተመዘገባችሁ …”ይባላል? ነው ወይስ ”ምርጫ 97”ን እናስታውስ ይሆን? (ወይስ ዓመቱ፣ በዓመታት ታሪክ ውስጥ ባለ ታሪክ ሆኖ ይታወስ፣ ይዘከር … ዘንድ ታስቦለት? ጉዳዩ (ነፍሳቸውን ይማረውና) አማረ ማሞ “… ያወያያል፣ ያነጋግራል፣ ያመራምራል” እንዳሉት ነውና እኛም ይህንኑ እንላለን።)
በዚህ ጸሐፊ እምነት፣ 2015 ዓ.ም ላይ ሆኖ አይደለም 2005 ዓ.ም ላይ ሆኖ እንኳን “በ’97 የተመዘገባችሁ …” ማለት ኢትዮጵያንና አስተዳደሯን አይመጥንም፤ ለማንኛውም አካል ቢሆን ከደረጃ በታች ነው። 2015 ላይ ሆኖማ፣ ጭራሽ ኢትዮጵያን ለ20+ ምናምን ዓመታት ያለ መንግሥት የኖረችውን ሶማሊያን እንኳን አይመጥንም። ስለዚህ?
ስለዚህ በ2020 ዓ.ምም “በ’97 የተመዘገባችሁ …” የሚለው ዜና በዛን ሰዓት ”ዓበይት ዜናዎች” ሆነው ከሚታወጁት አንዱ እንዳይሆንና የዛን ዘመን ጋዜጠኞች (የዛሬ ተማሪዎች) ”በ’97 የተመዘገባችሁ …” የሚለውን በአስገምጋሚ ድምፃቸው እንዳያሰሙን ማድረግ ያስፈልጋል። ነገሩ ከማማረርና ማሳዘን አልፎ ወደ ”ሳቅ ጨዋታ”ነት እንዳያዘነብልብን እንቋጨው።
በምንም መልኩ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ቁመና ለኮንዶሚኒየም ግንባታ እና “በ’97 የተመዘገባችሁ …”ን ለማስቀረት (ተረት ለማድረግ) አይሰንፍም። በምንም መንገድ በአዲስ አበባና ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተገነቡ ያሉ ግንባታዎችን በጥሩ ሁኔታ እያጠናቀቀች ላለች ሀገር ይሄ ”ኮንዶ” የሚባለውን በመገንባት፣ ይሄ መጪውንና አዲስ ተመዝጋቢውን ትውልድ ተስፋ የሚያስቆርጥ አሠራር፣ “በ’97 የተመዘገባችሁ …”ን ከስሩ በመንቀል ተረት ማድረግ አያቅታትም። ይህንን ስንል ኮንዶሚኒየሙን ቁጭ ቁጭ ማድረግ ቢያቅታት ኖሮ የመጀመሪያውን ዙር ባልገነባች ነበርና ነው። ”ያቅታታል” ካልን ግን ኢኮኖሚያችን የመጀመሪያውን ዙር ኮንዶሚኒየም ስንገነባ ከነበረበት ወርዷል እያልን ነው ማለት ነውና ብዙ ነገሮች ይጣረሳሉ።
በመጨረሻም፣ ከላይ American Dream እንዳልነው ሁሉ “በ’97 የተመዘገባችሁ …” እየተባሉ የሚጠቀሱት ሁሉ (ቢያንስ በሕይወት ያሉት) ሕልማቸው እውን ሆኖ ያዩት ዘንድ፤ ”በ’97 የተመዘገባችሁ …” ይሉ አባባል ተረት ይሆን ዘንደ እንመኛለን!
ግርማ (MaR)