በአሁኑ ወቅት የሳይበር ደህንነት የዓለም አገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውንና ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ በሚያደርጓቸው ጥረቶች ትልቅ ትኩረት እየሰጧቸው ካሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሆኗል። ከዚህ ባለፈም የሳይበር ዘርፍ አገራት የቴክኖሎጂ የበላይነታቸውን ለማሳየት ጭምር የሚጠቀሙበት መሳሪያም እየሆነ ነው። በፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ጉዳዮች አለመግባባት ውስጥ የገቡ አገራት አንዱ የፍልሚያ ግንባራቸው የሳይበሩ ዘርፍ ሲሆን መመልከት ተለምዷል። አገራት በሳይበር ቴክኖሎጂ ዘርፍ ልቆ በመገኘት በሌሎች አገራት ላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ስነ ልቦናዊ ጫና ለመፍጠር እልህ አስጨራሽ ፉክክር እያደረጉ ናቸው።
አብዛኞቹ ታዳጊ አገራት የሚጠቀሟቸው የሳይበር ደህንነት ቴክኖሎጂዎች ከበለፀጉ አገራት በግዥና በድጋፍ የሚያገኟቸው በመሆናቸው፣ የቴክኖሎጂዎቹ ባለቤት ለሆኑት አገራት የእጅ አዙር ቅኝ ተገዢ እንዲሆኑ እያስገደዳቸው ነው። በአፍሪካ የተፈጠረው የሳይበር ደህንነት የአጠቃቀም ክፍተት እና የቴክኖሎጂ ጥገኝነት አህጉሪቱ በየዓመቱ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንድታጣ እያደረጋት እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ።
የሳይበር ምኅዳር ዓለም አቀፍ ሉላዊነት እንዲፈጠር ያደረገ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ከሳይበር ምኅዳር ውጭ መሆን የማይታሰብ ሆኗል። ያለ ሳይበር አቅም እንደአገርም ሆነ እንደተቋም ተወዳዳሪ ሆኖ መዝለቅ ይቅርና ህልውናን ማስጠበቅ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። በአጠቃላይ ውጤታማ የሳይበር ቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ያላረጋገጠና የሳይበር ምህዳሩን ደህንነት ያላስጠበቀ አገር ሉዓላዊነቱንና ብሔራዊ ጥቅሙን ማስጠበቅ የማይችልበት ወቅት ላይ ተደርሷል።
የሳይበር ምህዳር የተለያዩ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን መሰረተ-ልማቶች ማለትም ኮምፒውተሮች፣ ራውተሮች፣ የኮምፒውተር ኔትዎርኮች፣ ወ.ዘ.ተ. ተሳስረው የፈጠሩት ምናባዊ ዓለም ሲሆን በዚህ ምህዳር ውስጥ ኢንፎርሜሽን ይቀመጣል፣ ይሰራጫል፣ እንዲሁም ይተነተናል። ሳይበር በባህሪው ድንበር የማይገድበው፣ ውስብስብ እና ኢ-ተገማች በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የአንድን አገር ሉዓላዊነት ከሚፈታተኑት አበይት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ሆኗል።
የሳይበር ጥቃት በኮምፒውተር ስርዓቶች፣ መሰረተ-ልማቶች እና ኔትዎርኮች ላይ ሆን ተብሎ ያልተፈቀዱ አጥፊ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም በህገ ወጥ መንገድ መረጃዎችን የመበዝበዝ እና አገልግሎት የማስተጓጎል ተግባር ነው። የሳይበር ጥቃቶች በአብዛኛው የኮምፒውተር ስርዓቶችንና እና የመጠቀሚያ መሳሪያዎችን ክፍተት በመጠቀም የሚሰነዘሩ ናቸው። በማህበራዊ የትስስር-ገፆች ላይ ደግሞ ከባህልና ከስነ-ምግባር ውጪ ባፈነገጠ መንገድ ከሚለጠፉ ምስሎች እና መልዕክቶች ጀምሮ የመረጃ መረብን ተገን በማድረግ በተለያዩ ደረጃዎች የሚፈፀሙ የመረጃ ስርቆቶች የሳይበር ጥቃት ማሳያዎች ናቸው።
የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ለመከላከል ሊወሰዱ ከሚገቡ የጥንቃቄ እርምጃዎች መካከል ከማይታወቁ አካላት ለሚላኩ የኢ-ሜይል መልእክቶች ምላሽ አለመስጠት፤ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ዝርዝር ግላዊ መረጃዎችን አለማጋራት፤ ህጋዊ ያልሆኑ ሶፍትዌሮችን አለመጠቀም፤ የመረጃ ማከማቻ ቁሶችን (እንደ ፍላሽ፣ ሀርድዲስክ…) አካላዊ ደህንነት መጠበቅ እንዲሁም የህዝብ ዋይፋዮችን አለመጠቀም ይጠቀሳሉ።
የኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትም በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። በ2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ የተሞከረው የሳይበር ጥቃት አንድ ሺህ 80 ነበር። ጥቃቱ በ2013 ዓ.ም ወደ ሁለት ሺ 800 ከፍ ብሏል። በ2014 ዓ.ም ደግሞ ስምንት ሺ 900 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን፣ ይህ አሀዝ ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ጭማሬ አሳይቷል። በ2015 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመትም አንድ ሺ 613 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተመዝግበዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ከስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ እና አሸባሪው ሕወሓት ከከፈተው ጦርነት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ የመገናኛ ብዙኃን እና የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የጥቃት ሙከራዎቹ ኢላማዎች ናቸው።
ከእነዚህ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች አሃዝ መረዳት የሚቻለው በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች በየዓመቱ እየጨመሩ መምጣታቸውንና ይህን ታሳቢ ያደረገ የሳይበር ደህንነት ጥበቃ ተግባር እንደሚያስፈልግ ነው። የ2014 ዓ.ም አገራዊ የሳይበር ደህንነት ዳሰሳ ሪፖርትም የአገሪቱ ተቋማት በሚያከናውኗቸው ተግባራት ለወቅቱ የሚመጥን የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በመተግበር ለሳይበር ደህንነት ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው ምክረ ሃሳቦችን አቅርቧል። በዚህ ረገድ የደህንነት ስትራቴጂዎችን አስቀድሞ ማዘጋጀት የሳይበር ጥቃቶች የሚያደርሱትን ኪሳራ መከላከል እንደሚያስፈልግ አቅጣጫዎችን ጠቁሟል።
የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማሳደግ አገራዊ የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። በዚሁ መሰረት የተቋማትን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችሉ ንቅናቄዎችን ለማከናወን፤ በአገራዊ የሳይበር ደህንነት ዘርፍ ላይ የግሉን ዘርፍ ሚና ለማሳደግና ለማበረታታት፤ በቂ እና ጥራት ያለው የሳይበር ደህንነት የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር፤ እና የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን ለመተግበር ያለመው ሦስተኛው ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ወር ጥቅምት አንድ ቀን 2015 ዓ.ም መከበር ጀምሯል። ‹‹የተቀናጀ የሳይበር ደህንነት ለአገር ሉዓላዊነት›› በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ያለው ሦስተኛው ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ወር፤ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን፤ የተቋማትን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት የመቀነስና የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ የማሳደግ ዓላማ እንዳለው ተገልጿል። ይህ የሳይበር ደህንነት ወር በተለያዩ የሳይበር ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮች ይከበራል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በሦስተኛው አገራዊ የሳይበር ደህንነት ወር ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ እንደተናገሩት፣ የሳይበር ደህንነት የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ በመሆኑ ከቴክኖሎጂ ልማቱ እኩል ለደህንነቱም ትኩረት ተሰጥቶታል።
‹‹የሳይበር ጥቃት የዓለማችን የወቅቱ የሥጋት ምንጮች ከሚባሉት አንገብጋቢ ጉዳዮች መካከል አንዱ በመሆኑ መንግሥት የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ ቁልፍ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ አድርጎ እየሠራበት ይገኛል›› ያሉት ምክትልና ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ የሳይበር ቴክኖሎጂ ደህንነት ለኢትዮጵያ ዕድገት ስኬት ዋነኛ አውታር መሆኑን በመረዳት ከ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ዋና ዋና ስትራቴጂክ የትኩረት መስኮች መካከል አንዱ ተደርጎ በመሠራት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ በዩኒቨርሲቲዎች እና መሰል ተቋማት ውስጥ በሳይበሩ ዘርፍ የአገሪቱ የመወዳደር አቅምና ተስፋ የሆኑ ታዳጊ ወጣቶችን ኮትኩቶ ለማሳደግ የሚያስችሉ ማዕከላት ተቋቁመው አመርቂ ውጤት ማሳየት መጀመራቸው ተስፋ ሰጪ ጥረት መሆኑንም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነትን የማረጋገጥ ሥራ በዋነኝነት ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተሰጠ ቢሆንም የሳይበር ደህንነት ውጤታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑንም ነው ያስታወቁት። አገራዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ለማረጋገጥ ብሎም የሳይበር ደህንነትን እውን ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ሚና ወሳኝ እንደሆነ ገልፀዋል። ‹‹የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አንዱ መገለጫ የሳይበር ምህዳሩ በመሆኑ በትብብርና በቅንጅት መሥራት ይገባል። ከዚህ አኳያ የሳይበር ዲፕሎማሲ ሥራችን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራበት መስክ ነው። የሳይበር ደህንነት ወር የባለድርሻ አካላት ቅንጅትን ለማጠናከር እና በጋራ አላማ ላይ ተመስርቶ ለመተባበር የሚያስችል ምቹ አጋጣሚን የሚፈጥር መድረክ በመሆኑ በውጤታማነት ልንጠቀምበት ይገባል›› ብለዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ በበኩላቸው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ካስቀመጣቸው አስቻይ ሁኔታዎች ውስጥ የመረጃ መረብ ደህንነት አንዱ መሆኑን ተናግረው፤ የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን ከጥቃት መከላከል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና በዲጂታል ክህሎት እና በመረጃ መረብ ደህንነት ላይ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ ተቋማት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነትን የማረጋገጥ ሥራ በዋነኝነት ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (Information Network Security Administration – INSA) የተሰጠ ኃላፊነት ነው። ተቋሙ በአገር ደረጃ የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ከማቀናጀት እና ከመምራት በላይ በየተቋማቱ የኢንፎርሜሽን ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚረዳ ባህል እንዲዳብር፣ መሰረተ ልማቶች እንዲገነቡ እና አደረጃጀቶች እንዲፈጠሩ የሚያግዙ ስራዎችን ያከናውናል። ኤጀንሲው ጥቃቶች ከመታሰባቸው ጀምሮ ክትትል በማድረግና ለይቶም በመተንተን ምላሽ ይሰጣል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የኢትዮጵያን የሳይበር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ባከናወናቸው ተግባራት አገርን ከከፍተኛ ኪሳራ መታደግ እንደተቻለ የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ይናገራሉ። እርሳቸው እንዳሉት፣ የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና በዘላቂነት በማሳደግ የአገርን የሳይበር ደህንነት ለማስጠበቅና የቴክኖሎጂ ባለቤትነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። ለአብነት ያህል በ2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ የተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶችን በማክሸፍ በቢሊዮን ብር የሚገመት ኪሳራን መከላከል እንደተቻለ ጠቁመዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የዜጎች የግንዛቤ ማነስና የቴክኖሎጂ ጥገኝነት ለሳይበር ጥቃቶች መበራከት ጉልህ አስተዋፅኦ አላቸው። በመከበር ላይ ያለው አገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር የተቋማትን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን የመቀነስ፣ በሳይበር ደህነንት ዘርፍ የግሉን ዘርፍ ሚና የማሳደግና የማበረታታት፣ በቂ እና ጥራት ያለው የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታን የመፍጠር እንዲሁም የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤን የማሳደግ ዓላማዎች አሉት። በዚህ የሳይበር ደህንነት ወር ላይ የሚከናወኑ ልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች በአጠቃላይ ከ10 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተደራሽ ያደርጋሉ።
አገራት የዜጎቻቸውን ብሎም የተቋሞቻቸውን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊና ለማሳደግ የሚያስችሉ የሳይበር ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን እንደሚያዘጋጁ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ዘላቂ በሆነ መልኩ ማሳደግና የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ ለሳይበር ደህንነት አስተማማኝ ዋስትናዎች እንደሆኑ ተናግረዋል።
ያለንበት ዘመን ከሳይበር ምህዳር ውጭ መሆን የማይቻልበት ሆኗል። ታዲያ በዚህ ዘመን በተቋምም ሆነ በአገር ደረጃ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ተወዳዳሪ መሆን ካልተቻለ አገራዊ ሉዓላዊነትም ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ህልውናም ከባድ አደጋ ውስጥ እንደሚገባ አያጠራጥርም። ስለሆነም የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ በማሳደግ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ባለቤትነት አቅምን በማጎልበት የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ፣ ሉዓላዊነትና ማስከበርና ህልውናን ማስጠበቅ ያስፈልጋል!
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም