ወዳጆቼ! ስምና ግብራችን መጠሪያና ማንነታችን እጅግ እየተራራቀብኝ ተቸገርኩ። በስም አወጣጣችን የተካንነውን ያህል በምንሰይመው ስያሜ ትዝብት ውስጥ የምንወድቅም ብዙ ነን። ላሰብነው ወይም ለምንመለከተው ነገር መለያ ይሆን ዘንድ የምንሰይማቸው ወካይና ውክልና ሲነጣጠሉብኝ አብዝቼ ማሰብ ጀመርኩና ላወጋችሁ ወሰንኩ። ስያሜ ያለ ቦታው ሲውል፤ ትርጉም ያላግባብ ሲጠቀሙበት ከማግባባት ይልቅ ግራ ማጋባትን ያስከትላል።
ስምና ተግባር ሲገጥም አቤት ሲጥም:: «እናት ጓዳ» የተሰኘ ምግብ ቤት ውስጥ ገብቶ እናት ያዘጋጀችውን ያህል የሚጥም ምግብ በእናትነት ፍቅር በታጀበ መስተንግዶ ሲቀርብ ምንኛ ደስ ያሰኛል። አዎ ስምን መላዕክ ያወጣዋል የሚያሰኘን ብዙ አለ። ደግሞ በሌላኛው በኩል ከነዋሪና መገኛው የራቁ ሌላን መስለው የእናንተ የሚሉ ሞልተዋል «ዲሲ» ሽሮ ቤት፣ «ዋሽንግተን» ክትፎ፣ «በርሊን» ባህላዊ ምግብ ቤት…ስንቱን እንታዘብ። ይሄ ደግሞ የኛው ሌላ ገጽታ፤ አለመግጠምን ማጋጠም። ስምና ምግባር የሚለይ ባህሪና መጠሪያ የሚያራርቅ ውክልና።
ዛሬ ላይ የምንጠራበት ወይም የምንለይበት ስማችን እኛን ባይገልፅ ግድ የለም። ምክንያቱም ቤተሰብ የሰየመልን ነውና አያስወቅሰን ይሆናል። ወደንና ፈቅደን ስም የምንሰይማቸው የንግድ ድርጅቶቻችን እኛን የታረቁ እኛን የሚመስሉ ናቸውን? እኔ አይመስለኝም።
የበዛ ነገራችን እኛን መምሰል ቢሳነውም ለእኛ ተብሎ በኛዎቹ የሚቀርብልን ከኛነታችን ቢርቅም ጎልቶ በሚታይ መልኩ ፍጥጥ ያለ መራቅን የራቁት ግን የንግድ ድርጅቶችና ህንፃዎቻችን ናቸው። ሀገራት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እራሳቸውን ለማጉላት ሲጥሩ የራሳቸውን ለማስተዋወቅ ሲማስኑ እየታየ ምነው እኛ የራሳችንን ትተን ሌላ መጥራትን ለመድን። ክትፎ ቤታችንን «ዋሽንግተን ክትፎ»፣ሽሮ መሸጫችንን «በርሊን ሽሮ» እያልን ለኛ የእነሱ ስም መለጠፉ እስከመቼ ይቀጥል ይሆን። እነዚህ ከተሞች ጭራሽ የእኛን ባህላዊ ምግብ እስከነመፈጠሩስ ቢሆን ያውቁታል? ካወቁትም እኛው ያስተዋወቅናቸውን መሆኑ ይያዝ።
አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊያን መሰባሰቢያና የባህል ማሳያ የሀገሪቱ መዲና መሆኗን እስክጠራጠር ድረስ እኛ እኛን የሚሸት ሀገራዊ ትርጓሜ ያለው የእኛ የሚመስል ስያሜ ማየት ብርቅ ቢሆንብኝ ግራ ታጋባሁ። የህንጻዎቹ ስያሜ፣ የሰፈሮቹ መለያ፣ የድርጅቶቹ መጠሪያ ከኛነታችን ፈጽሞ ርቀው ለመያዝም የምንቸገርበት ለመግባባትም የምናወላዳበት ገጠመኞቻችን በዙብኝ። እንደ እኔው ግራ የተጋባ መኖሩ ግን አይቀሬ ነው።
ፒያሳ አንድ ቦታ ላይ ቆም ብዬ ፊት ለፊቴ ያሉት የንግድ ድርጅቶችን እያየሁ ነው። የተጻፉት በአማርኛ ፊደላት ነው። ግን ደግሞ ለአማርኛ ተናጋሪው ትርጉም አልባ የበዙ ስያሜዎች የተሰጣቸው የንግድ ድርጅቶች ተሰልፈዋል። አንድ ቦታ ላይ ቁሜ ዙሪያዬን መቃኘት ጀመርኩ ቬነስ ካፌ፣ ኢቫንስ ፋሽን፣ ጉድ ታይምስ ካፌና ባር፣ ዲሲ ክሎዝ ሲቲ፣ ትሪያን ሀውስ፣ ፋል ላውንጅ፣ ፌመስ ኮሌክሽን……ጉድ እኮ ነው። የእነዚህ ደንበኞች ግን እነ ማን ናቸው? እኛው!
እኔ የምለው የራሳችን ስያሜዎች ጠፍተውብን ወይም የምንሰይመው ያጣን ይመስል ለምን ግን ይሄንን ተላመድን? ስም እኮ ማንነትን መግለጫ እራስን ማስተዋወቂያ ነው። ሰው የራሱን እንዲህ ይጠላል? ወዳጆቼ ወዴት እየሄድን ነው? እግሬን ሳላነቃንቅ አንድ ቦታ ሆኜ ከ20 የማያንሱ የንግድ ድርጅቶች ውስጥ 15ቱ ተገልጋያቸውን ያላገናዘበ ስያሜና መገኛቸውን የማይወክል መጠሪያ ሰይመው በራቸውን ከፍተው ይጠባበቃሉ።
ሌላው የታዘብኩት ደግሞ የዜጎች መቅረጫ፣ የእውቀት ማፍለቂያ… እየተባሉ የሚጠሩት ትምህርት ቤቶቻችን በተለይም የግል ትምህርት ቤቶች ስያሜ የምንቀርፃቸው ዜጎቻችን ይሄንን ይዘው እንዲበቅሉ ነው ብለው የተነሱ ይመስላል የስም አወጣጣቸው። ሁሉም የግል ትምህርት ቤት ብዬ እንዳልወርድባቸው «አንድነት ኢንተርናሽናል» የሚል አይቼ ከጅምላ ፍረጃ ወጣሁ። ስኩል ኦፍ ቱሞሮ፣ ቪዝን አካዳሚ፣ ኢትዮ ፓረንት፣ ዩኒቱ፣ ሳፋሪ… ብቻ ስንቱ ይነሳል በአማርኛ መጠሪያ ያጡ ናቸው።
ስያሜ በቀላሉ ገበያን ሰብሮ ለመግባትና ከደንበኛ ጋር ለመተዋወቅ የሚረዳ መሳሪያ ሆኖ ሳለ ለምን ይሆን የንግድ ተቋማቶቻችን በዚህ መልክ ተደናብረው የሚያደናብሩን። የንግድ ውድድሩ ከፍ ባለበት ተጠቃሚው በተለያየ መልኩ መሳብና የራስ ደንበኛ ማድረግ ወሳኝ በሆነበት በዚህ ወቅት ስያሜያቸውን ከተጠቃሚው ማራቃቸው ለምን ይሆን? ቆዩኝማ! እኛ ሳንሰማ ለንግድ ድርጅቶቻችንና ህንፃዎቻችን ኢትዮጵያዊ የሆነ ስም እንዳይሰጥ የሚከለክል ህግ ወጥቷል እንዴ?
ይሄ ብቻም አይደለም የእኛ ቋንቋ ለስያሜ አነሰ እንዴ? ያሰኘኝ ።Joሊ ባር፣Yeኛ ምግብ ቤት… የሚለውም ለማን እንደተፃፈ ጭምር ግራ አጋቢ ነው። ለፈረንጁ ወይስ ለአራዳው መቼም ይሄንን ሁሉም ሰው ያነበዋል አንብቦም ይረዳዋል ብሎ ማሰብ አይቻልም።
አንድ ነገር እርግጥ ነው መዲናችን የአፍሪካ መዲና የዓለም አቀፍ ተቋማት መገኛ ናት ለዚያ የሚመጥን ሁሉንም ልያግባባ የሚችል መረጃዎች በየቦታው ቢለጠፉ፤ የንግድ ተቋማቱም ይሄን የሚመጥን አገልግሎት ቢሰጡ መልካም ነው። ነገር ግን 98 በመቶ እኛ የምንጠቀምባቸው የንግድ ተቋማት በምን ስሌት ነው ስያሜያቸው ከኛ የሚርቀው። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለስያሜ አንሰው ይሆን?
የድርጅቶቻችንና የአገልግሎት መስጫዎ ቻችን ስያሜ ብቻ እኮ አይደለም የኛ አሰያየም አስገራሚ መልኩ። የእኛ መጠሪያስ ቢሆን ካሰብነው ይደንቃል፤ ይገርማልም። ከራስ መጀመር መልካም አይደል ከራሴ ልጀምር። የቤት ስሜ የሺጥላ ነው። ቤተሰቦቼ ከኔ ብዙ ጠብቀው ይመስለኛል የሺጥላ ብለው ስም አወጡልኝ። ወይ ሺን ማስጠለል እኔ ለራሴ እንኳን ጥላ መሆን ተስኖኝ ይሄው ግማሽ ክፍለ ዘመን ተሻገርኩ። የኔ ቢጤ በየመንደሩ ሞልቷል «ቅዱስ ተብሎ ምግባሩ የእርኩስ «ሺፈራው» ተብሎ በቃላት የሚርበተበት ኧረ ስንቱን ታዘብን።
አንድ ሰሞን በሥራ ጉዳይ ወደ ደቡብ የሀገራችን ክፍል ተጉዤ ነበር። የሥራ ጉዳይ ሆነና የቀረበኝን ሰው ሁላ ማንነቱን መጠየቅ ስለሚያውቀው አካባቢያዊ ሁኔታ እንዲነግረኝ መወትወት ነበረብኝና ቀርቤ ስተዋወቅ ያስደመሙኝ ስያሜዎች ነበሩ። ማንቺስተር ቼልሲ፣ መሲ ባርሳ….. መጀመሪያ የሚቀልዱብኝ ሁላ መስሎኝ ነበር ተላመድኩና ሳጣራ አካባቢው ላይ የተለመደ መሆኑ ተነገረኝ። ስያሜዎቹ እንዴት ተሰጡ እንዴትስ ተለመዱ ለሚለው ጥያቄዬ የተሰጠኝ መልስ እንዲሁ «ደስ» የሚል ነበር። እርግጥ ስማቸውን መኮነኔና መቃወሜ አይደለም ግን ከራሳቸው የሚገጥምና ትርጉም ሰጪ ቢሆን መልካም አይመስላችሁም።
ስም ትርጉም ባለው መልኩ ቢሰየም ደስ እንደሚለው ሁሉ ትርጉም አላባ ስያሜን መላበስም አያስወቅስም ምክንያቱም የባለቤቱ መብት ነውና። ነገር ግን እራስን የሚገልጽ ሳይሆን ሲቀር ባህልና ማንነትን የዘነጋ ሲመስል ስያሜው ምን ነካው ያስብላል። ስሙ ከስያሜው ማንነት ያልመነጨ ከሌላ እንዲሁ የወሰደው ነውና አያስጌጠውም።
ቆዩኝማ ጠሪው ለመያዝ የሚቀለው፣ ደስ ብሎትም የሚጠራው የሚጠራውን ነገር እና ጠሪው የተቀራረበ ሲሆን አይደል እንዴ? ሰው የሚያውቀው ትርጉሙን የሚለየው ሲጠራ ለዛውም ያምራል፤ ከስህተትም ይድናል። የማያውቀውን አዛንፎ ሲሰባብር በራሱ የሚፈጥረው ነገር በራሱ ስያሜውን ያዛንፈዋል። እኔ እንዲህ ታዘብኩ ልንጠራው የማንቸገርበትን የራሳችንን የምናውቀው ትርጉም ያለውን ብንሰይምስ? እኔ እንዲህ ቢሆን አልኩ እናንተስ?
ምንም ያህል ትርጓሜው ጥልቅ የሆነ ስያሜን ለምንወክለው ጉዳይ ብንሰጥ የወከልነው ጉዳይ ባለቤቱን የሚመለከትና የሚገባው ካልሆን የያዝነው አላማ ማሳካቱ ላይ እርግጠኛ መሆን አንችልም። ቀለል ያለና ሊያዝ የሚችል በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉት ስያሜ እኮ ከደንበኛ በላይ በመንገድ የሚተላለፍንም ቀልብ ይገዛል።
ስም ማንነትን ማሳያ፤ እራስ መግለጫ ብሎም ስለራስ ብዙ መንገሪያ ነውና የስም አወጣጣችን ላይ ምክንያታዊ ብንሆን ምክንያታችን ደግም በትርጉም ያላቸው ስሞችን ይወልድልናል። የተገኘንበት ቦታ ያለንበት ሁኔታና ባህል በጠበቀ መልኩ እኛኑ የሚመስል ስያሜ መስጠቱ አንድም ለራሳችን የምንሰጠው ቦታ ከፍታን ያመለክታል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ማህበረሰቡ ስለኛ በቀላሉ የማሳወቅን ሥራ ሠራን ማለት ይሆናል አልኩ።
ተገኝ ብሩ