ሠው ምንድን ነው?» የሚለው መጽሐፍ በመምህር ዶክተር ዘበነ ለማ የተጻፈ ሲሆን፤ ሦስት ዋና ምዕራፍና 27 ንዑስ ምዕራፎችን ይዟል። በአንድ መቶ ሰባ ስድስት ገጾች ተዘጋጅቶ፤ አንድ መቶ ብር የመሸጫ ዋጋ ተቆርጦለት ለንባብ የበቃው ይህ መጽሐፍ ከውጭ ዓለም ጥበብ ይልቅ የራሳችንን ለመመርመር እንድንችል እና እንድንነቃ ተደርጎ የቀረበ ነው።
የዚህ መጽሐፍ ደራሲ መምህር ዶክተር ዘበነ ለማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መምህር ሃይማኖት፣ የቤተ ክርስቲያን እምነትና ስርዓት ከንባብ እስከ ትርጓሜ፣ ስርዓተ ቅዳሴን ከብጹዕ አቡነ ሰላማና ከመጋቤ ምስጢር አለቃ መሰረት ተሰማ ተማሩ፡፡ በነገረ መለኮት ትምህርት ከቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ስለዓለም እምነቶች ጥናትና ፍልስፍና ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በዛው ዩኒቨርሲቲ በሥነ አመራር እና አንትሮፖሎጂ ጥናት በከፍተኛ ማዕረግ ተምረው ተመርቀዋል።
አሁን ላይ በቡዊ ስቴት ዩኒቨርሲቲ «በአጃንከት ፕሮፌሰር» በሀዋርድ ዩኒቨርሲቲም «ገስት» ፕሮፌሰር ናቸው። በሊሊ ኢንዶውመንት በሚደገፍ ቴዎሎጂካል ኢጁኬሽን በምርምር ሥራ፣ ሲኢኦኤስ ለተባለ የአሜሪካን ድርጅት በቦርድ አባልነት እያገለገሉ ይገኛሉ። በዋናነት በአሜሪካን ሀገር በደብረ ገነት መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በዋሽግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ያገለግላሉ። ኑሯቸውም ከባለቤታቸው ከወይዘሮ ኅሊና ታደሰ ጋር በአሜሪካን ሀገር በቨርጂኒያ ግዛት ነው።
እንደ ማሳሰቢያ ይቆጠር! ይህ ሙያዊ አስተያየት ሳይሆን አስተውሎት ነው። ፀሐፊው ካላቸው የንባብ ልምዳቸው፣ ከሠፋው ሥነ-መለኮታዊና ፍልስፍናዊ ዕውቀታቸው፣ በትምህርት ከቃረሟቸውና፣ በምርምር ካገኟቸው መረጃዎች በመነሳት የፃፉት እንደሆነ መፅሐፉ ምስክር ነው። በሁለተኛው ክፍል ውስጥ በተገለፁት የሶስቱ ተራሮችን አስተሳሰብና ርዕዮት እናያለን። የመጀመሪያው የሳይንስ፤ ሁለተኛው የፍልስፍና፤ ሶስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ የሃይማኖት ተራራ ነው።
የተለያዩ መፅሐፍትን በመተንተን የሚታወቀው አናቲዮስ እሸቱ እንዲህ ይላል «መምህር ዶክተር ዘበነ ለማ በምናብ በሃሳብ ሠረገላ እየተጓዙ ሦስቱን ተራሮች እያናገሩና ከራሳቸው ሃሳብ ጋር እየተሟገቱ የተራራዎቹን ርዕዮትና ውስጠ ወይራ ምስል እየፈጠሩ ያስገበኙናል። እርግጥ ነው ከሦስቱ ተራሮች የመጨረሻው ተራራ ግዝፈቱን፣ ረቂቅነቱን፣ ምሥጢራዊነቱንና የበላይነቱን በሚገርም አንድምታዎችና ሃሳቦች እያቃረኑና እያዋሃዱ ረቅቀው ተፈላስፈውበታል።»
የመጀመሪያው የሳይንስ ተራራ ሲሆን «ሠውነት በሳይንስ» ምን እንደሚመስል ፀሐፊው ለማሳየት ሞክረዋል። በመጽሐፉ በገፅ 27 ላይ ‹‹ሳይንስ ለዓለም የማውቅላት እኔ ነኝ ካለ ሠንብቷል። ሌሎቹ የሚመክሩትን አይሠማም። ለዚህም ትልቁ ችግሩ ሚስቱ ትሁን እመቤቱ ባላውቅም ይህን ሁሉ የምታደርገው ገንዘብ ናት።» ይላሉ።
ሳይንስም ቁሳዊውን ዓለም ጨርሶ ሳያውቅ ስለሠማያዊውና መንፈሳዊ ዓለም በመላምቱ ሲደሰኩር እናያለን። እርግጥ ሳይንስ በሳይንስና ቴክኖሎጂው ረቅቆ ስጋዊ ሕይወትን ቀለል ቢያደርግም መንፈሳዊ ሕይወት ላይ አንድ ስንዝር መጨመር አልቻለም። በስጋዊ ዕውቀት መንፈሳዊውን ጥበብ የሚደርስበት መስሎት ያለመንገዱ መንገድ ጀምሯል። የረቂቁን በቁሱ፣ የሠማዩን በምድሩ፣ የማይታየውን በሚታየው ይደመድማል። ምርምሩ፣ ልፋቱ፣ ለማወቅ ያለው ጉጉቱ ደግ ቢሆንም ሳይንስ ያለአቅሙ የማይችለውን ሁሉ አውቃለሁ ብሎ መታበዩ ግን ልክ አይደለም።
ሳይንስ አውቆ ከደረሰባቸው ቁሳዊ ግኝቶች ይልቅ ያላወቃቸው፣ ገና ያልደረሠባቸውና ያልነካቸው እልፍ ናቸውና እነሱ ላይ ቢበረታ ጥሩ ነው። አልያ ግን የማይታየውን መንፈሳዊውን ጥበብ ረቂቁን ተፈጥሮ አያለሁ ብሎ መነሳቱ የሚያዋጣው አይመስለኝም።
የመፅሐፉ ፀሐፊ ስለዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሃሳብ ባለቤት ስለሆነው ዳርዊን ሲያነሱ ደግሞ ዳርዊን የሠው ልጅን ከጦጣና ከዝንጀሮ ጋር የተመሳሰለ መሆኑን በፈረንጆች አቆጣጠር በ1859 (On the origin of species by means of Natural Selection) በሚል ርዕስ ባሳተመው መፅሀፉ መግለጡን ያወሳሉ። ቀጥለውም ለምን ዳርዊን ከእግዚአብሔር ጋር እንደተኳረፈ በመፅሐፋቸው በገፅ 32 ላይ እንዲህ ሲሉ ያስነብባሉ።
‹‹ዳርዊን በጣም የሚወዳት አን የተባለች ልጁ በጠና ታማበት ለአምላኩ ቢፀልይና ቢለምንም ልጁ በዘጠኝ ዓመቷ ሳትድንለት ሞታበታለች። በዚህም ከአምላኩ ጋር ተኳርፏል።›› ይሉንና ምናልባት ዳርዊን ከአምላኩ ጋር የተጣላበት ሠበብ ይሄ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ይሠጡናል። በመቀጠልም የዳርዊን አስተሳሰብ በእንግሊዝ የንጉስ ዘር ባላቸው ማህበረሰብ መሠበሩን የሚገልጽ “Darwinian Theory is broken and may not be fixable” የሚል ፅሁፍ እንዳዩ ያወጋሉ።
ይህ ንድፈ ሃሳብ የከሸፈ እንደሆነና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በቀላሉ ልንረዳ የምንችለው አንድም ጥቁሮችን ከጦጣ የመጡ (simians) ናቸው ሲል፤ ሁለትም ነጮቹን ደግሞ የተሻሻለ ዝርያ (Advanced species) ያላቸው መሆኑን በመፅሐፉ በዘረኝነት አስተሳሰብ ጥቁርና ነጭ ብሎ ለይቶ ስለሚገልፅ ነው። ለዚህም ነው የእሱ ተከታዮች የሆኑት የዳርዊኒዝም አቀንቃኞች ጥቁሮችን በ “Natural Selection” ማጥፋት አለብን ያሉት። ይህ ደግሞ ዶክተሩ እንዳሉት ተቀባይነት ያለው እውነት በመሆኑ በብዙ ምዕራባውያን ዩኒቨርሲቲዎች የዳርዊን ይሄ ትምህርቱ እንዳይሠጥ እስከመታገድ አድርሶታል።
ሌላው ፀሐፊው ታዋቂው ሳይንቲስት ፍራንሲስ ኮሊንስን (the language of God) የተባለ መፅሐፍን በመጥቀስ ሳይንስ ከሃይማኖት ጋር ስሙም መሆኑን ያነሳሉ። ይህ ሳይንቲስት ከዚህ ቀደም ኢአማኝ የነበረና በኋላም አማኝ መሆኑን በመግለፅ ሳይንስ ከሃይማኖት ጋር እንደማይጣላ የሚያሳይ (Biologos) የተባለ ድርጅትም እንዳቋቋመ ያስረዱናል።
በፀሐፊው ሃሳብ ላይ ለመጨመር ፍራንሲስ ኮሊንስ ፀሐፊው በገለፁት መፅሐፍ ውስጥ የኮሶሞሎጂስቱን የሮበርት ጃስትሮን ሃሳብ “God and the Astronomers” ከሚለው መፅሐፉ ተውሶ እንዲህ ይለናል ‹‹በዚህ ቅጽበት በሚመስለው ሳይንስ መቼም ቢሆን የፍጥረትን መጋረጃ ሊገልጥ እንደማይቻለው ነው። በአመክንዮ ኃይል ሲመካ ለኖረ ሳይንቲስት ታሪኩ የሚያበቃው እንደክፉ ቅዠት ነው። የድንቁርናን ተራራ ቧጥጦ ከፍተውን ለመቀዳጀት ደርሷል። የመጨረሻውን አለት ተሻግሮ ብቅ እንዳለም አቀባበል ያደረጉለት በስፍራው ለዘመናት የከረሙ የሃይማኖት ሊቃውንት ነበሩ›› ይለናል።ለዚህም ነው ሳይንቲስቱ ፍራንሲስ ኮሊንስ ሳይንስ ብቻውን ሁሉንም ጥያቄዎች መመለስ አይችልም የሚለን።
ሁለተኛው ተራራ የፍልስፍና ነው። ሰውነት በፍልስፍና እንዴት እንደሚገለፅ ያተቱበት ክፍል ነው። በዚህ በሁለተኛው ተራራ የማይነሱ ጉዳዮች እንደሌሉ ፀሐፊው ይጠቅሱና ፍልስፍና እውነት ምንድናት የሚል አስተሳሰብ ይዞ (Reality) የሕልውና እና ሕይወት (Existence) ምንነትን ይመረምራል ይሉናል።
የዚህ ተራራ ነዋሪዎች ከመጀመሪያው የሳይንስ ተራራ ነዋሪዎች ይልቅ ከሦስተኛው ተራራ ከሆነው ከሃይማኖት ነዋሪዎች ጋር እንደሚቀራረቡ መፅሐፉ ይገልፃል። በዚህ ተራራ የሚገኙ ነዋሪዎች አለቃ የላቸውም ይሉንና የሃሳብ መዘበራረቅ እንደሚታይባቸውም ይናገራሉ። የፍልስፍና ተራራ ነዋሪዎች ስለሠው ብዙ መመርመራቸውንና ብዙ መፈላሰፋቸውን ይገልጻሉ።
በእርግጥ የተራራው ግማሽ ነዋሪዎች የምዕራቡ ወደሆነው ግለኝነት ያደላሉ ሲሉን የምስራቆቹን ግን አንድ ላይ ስለመኖር ይሠብካሉ በማለት ልዩነታቸውን ነግረውናል። በተጨማሪም ስለሠው ምንነትና ነፍስ በተመለከተ አፍላጦንና አርስጣጢሊስ የተለያዩበትን ጉዳዮች አንስተዋል። ፕሌቶ (አፍላጦን)፡- ‹‹ሠው ማለት በሥጋ ውስጥ የታሠረ ነፍስ ነው። ምክንያቱም ነፍስ ቀድማ የነበረችና የማትሞትም ናት!›› ብሎ ሠውነትን ሲበይነው አርስጣጢሊስ ግን ‹‹ነፍስ ማለት ከሥጋ የተለየች ሳትሆን የሥጋ ቁመና ናት። ሥጋ ሲሞት አብራ የምትሞት ሥጋ ከሌለ ነፍስ የለም›› በማለት የአፍላጦንን ሃሳብ በመቃወም ነፍስ ሟች መሆኗን የተለየ ሃሳብ አቅርቧል ይሉናል።
ፕሌቶ ነፍስን በተመለከተ ያለው ሃሳብ ከሶስተኛው የሃይማኖት ተራራ ተገልብጦ የቀረበ እንደሆነ ፀሐፊው ይገልጻሉ። ፕሌቶ ‹‹ይህ ዓለም የእውነት ቢመስልም ምሣሌነቱ ለሌላ ዓለም ነው። ነፍስ ተመንጥቃ ለመጣችበት ዓለም ነው።›› በማለት የገለፀውን ሃሳብ ከሃይማኖቱ አስተሳሰብ ጋር የተገናኘ መሆኑን ያሠምሩበትና ከፕሌቶ 300 ዓመት በፊት የነበረውና የሃይማኖት ተራራ ነዋሪ የሆነውን ኢሣያስን በትንቢት መፅሐፉ በምዕራፍ 65 የገለጠውን ሃሳብ ያነሳሉ።‹‹ይህ ምድርና ዓለም ጠፊ ስለሆነ ሌላ አዲስ ምድርና አዲስ ሠማይ አለ። ለዘላለም የምትኖሩት በዚያ እንጂ በዚህ አይደለም›› ብሎ ተናግሯል ሲሉ ያስረዱናል።
ፕሌቶ የሠውነትን ነገር እውነታን ለመረዳት የሚጠየቁ ዋና ዋና ጥያቄዎች ብሎ በምናብ የዘረዘረላቸው ‹‹ለምን እዚህ ሆንን? ዋና ዋና ምክንያቱስ ምንድነው? የሚታየው ሁሉ እውነት ነው? ይህንን ለመረዳት ማድረግ ያለብኝ ምንድነው ነው?›› ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ሠውነትን መረዳት ያስችላል። ሆኖም ግን ‹‹ይሄ ቁሳዊ ዓለም ሁሉንም ነገር የሚያሳይህ በግማሹ ነው›› በማለት ፀሐፊው ፕሌቶ በምናብ እንዳስረዳቸው ይገልጻሉ።
ሌላው ሠውነትን፣ ዓለሙንና ሁሉንም ነገር ለመረዳት የራሳችን አስተሳሰብ፣ ግንዛቤና መረጃዎች ሚና እንዳላቸው ፀሐፊው ያሠምሩበታል። ለዚህም ምሣሌ በመፅሐፉ በገፅ 56 ላይ አቅርበዋል። ‹‹ከልጅነታቸው ዕድሜ ጀምሮ ስለሌላው ዓለም ምንም ግንዛቤ ሳይኖራቸው በአንድ ዋሻ ውስጥ የታሠሩ ሠዎች ነበሩ። ኋላ ላይ ነፍስ ሲያውቁ በዋሻው ግድግዳ ላይ ስለሚያዩት ነገር መነጋገር፤ መጨዋወት የዕለት ዕለት ኑሯቸው ሆነ። ያሉት በዋሻ ውስጥ ነው። ከዋሻው በስተጀርባ እሳት አለ። በመካከል ደግሞ ሠዎች የሚመላለሱበት መንገድ አለ። ሰዎች ወደ ሥራም ሆነ ወደ ገበያ ወይም ወደ የዕለት ተግባራቸው በዚህ መንገድ ዘወትር ይመላለሳሉ። ግማሹ እቃ ተሸክሟል። ግማሽ በፈረስና በበቅሎ ይጓዛል። ሌላው ከብት ይነዳል፤ አንድ ሠው ወይም ብዙ እየሆኑ ይመላለሱበታል።
በዋሻው ውስጥ ያሉት ስለውጪው ዓለም አንዳች አያውቁም። እነሱ የሚመለከቱት ከፊት ለፊታቸው ያለውን የዋሻውን ግድግዳ ሲሆን፤ ከውጭ ያሉት ሠዎችና ከብቶች ሌላውም ሲመላለስ ከእሳቱ ብርሃን የተነሣ የእነሱን እንቅስቃሴ በዋሻው ግድግዳ እንደተውኔት የእንቅስቃሴያቸው ጥላ ነበር። ይህ ነው የዋሻው እስረኞች እውቀትና ግንዛቤ።ሕይወት ማለት ለእነሱ ይህ ነበር። እንዲያውም ሲጨዋወቱ፣ ሲነጋገሩ፣ የዋሻው ግድግዳ ላይ ምስል እያዩ ነበር። ቀጥሎ የሚመጣው እንዲህ ዓይነት ምስል ነው እያሉ ይናገራሉ፤ ይተነብያሉ። የተሳካለት ከመካከላቸው እንደሊቅ ይታያል።
አንድ ቀን ከዋሻው እስረኞች መካከል አንዱ አምልጦ ከዋሻውና ከእስሩ ወጣ። ተደነቀ፣ ተገረመ የሚያየው ነገር ሁሉ አስደመመው። እውነታው ይህ እንደሆነ ተረዳ። በዋሻው ግድግዳ ሲያየው የነበረው ሁሉ የእውነታ ነፀብራቅ እንጂ እውነታው ሌላ ነው። ገስግሶ ሄዶ ለእስረኞቹ ጓደኞቹ ነግራቸው ፤አላመኑትም፤ «እብድ ነህ! ከዚህ ሌላ ዓለም የለም» ብለው ሊገድሉት አሰቡ። እሱ የተረዳውን እነሱ ሊያስተውሉት አልፈለጉም፤ነፃ መሆንን አልፈለጉም። ለእነሱ ሕይወት የእውነተኛው ዓለም ጥላ የሆነው ይህ ዓለም ነውና።
ምሣሌው እውነት አለው! የዘመኑን አውቃለሁ ባዮች አስተሳሰብን የሚያሳይ ነው። ያላዩትን ነገር የለም የሚሉ ሁሉ ይሄ ምሣሌ ይመለከታቸዋል። የማይታይ ሁሉ የለም ማለት አየር ስለማይታይ፣ ነፋስ ስለማይጨበጥ የለም ወደሚል ጭፍን ድምዳሜ ይወስዳቸዋል። አምላክ አይታይምና የለም ለሚሉ ኢአማንያንም ከጠባብ የአስተሳሰብ ዋሻቸው እንዲወጡና ከሃሳብ እስራታቸው እንዲፈቱ ፀሐፊው ያስቀመጡት ምሣሌ ጥሩ አስተማሪ ሆኖ አግኝተነዋል። ያልደረስንበትና የማይታየን ሁሉ የለም ማለት አይደለምና።
ፀሐፊው ስለፍልስፍና ተራራ ነዋሪዎች ብዙዎቹን ነካክተዋል። ከሊቅ እስከ ደቂቅ በምናብ ሁሉንም እንዳናገሩ፣ የሠውን ማንነት እንደፈተሹና በፍልስፍና ተራራ እንደተመላለሱ ይገልጻሉ። እርግጥ በዚህ ክፍል ፀሐፊው የመጀመሪያውን የግሪክ ፈላስፋን ታሌስን፣ አናክሲ ማንደርን ነካ አድርገው፣ ስለሌሎቹም ጥቂት ቢሉም፣ የምክንያታዊነት ዘመን ፈላስፎችን ጠቀስ አድርገው ቢያልፉም ስለሠው ምንነት ያላቸውን ሃሳቦቻቸውን በተገቢው መጠን በጥልቀት ግን አልፈተሹትም።
ስለምስራቅ ፍልስፍና እና ፈላስፎች አነኮንፊሽየስን፣ ሜንስየስን እና ቡዳሃን ስማቸውን ጠቅሰዋል። ነገር ግን ስለሠው ምንነት የተናገሩትን በሠፊው አልዘረዘሩትም። ይሁን እንጂ ፀሐፊው በዚህ በፍልስፍና ተራራ ያለውን አስተሳሰብ በአጭሩ አሳይተዋል። ፍልስፍና ከሳይንስ የበለጠ ብዙ ሃሳቦች፣ ምርምሮችና ፍልስፍናዎች የተከማቹበት እንደሆነ ተናግረዋል።
በመጨረሻም የእንግሊዛዊውን ፈላስፋ የጄምስ አለንን ሃሳብ ያነሣሉ። ጄምስ አለን (As a man thinketh) በሚል ርዕስ በፃፈው መፅሐፉ ስለ ሠው ምንነት ሲናገር ‹‹ሠው ማለት ለራሱ የደስታና የሐዘን ፈጣሪ ነው። ይህ ደግሞ ከፈጣሪ ወይም ከሠይጣን የመጣለትና የመጣበት ሳይሆን ከራሱ ከውስጥ አስተሳሰብ የተገኘ ነው።›› ይላል በማለት የፈላስፋውን ሃሳብ ያቀርባሉ። ሃሳቡ ከሶስተኛው ከሃይማኖት ተራራ አስተሳሰብ ጋር የሚገጥም ስለመሆኑም በምሣሌ 18፤21 ‹‹ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው። የሚወዷትም ፍሬዋን ይበላሉ›› ከሚለው የሠለሞንን አባባል ጋር ተመሳሳይ መሆኑንና የመፅሐፉ ርዕስ እንኳን ከጥበበኛው ሠለሞን እንደተወሰደ ያሳዩናል። ሠውነት በፍልስፍና ብያኔው ብዙ ነው!
‹‹ሠውነት በሃይማኖት›› ምን ይመስላል የሚለውን በሃይማኖት ተራራ የሚያነሳቸውን ቁምነገሮች እንዳስሳለን። ፀሐፊው መምህር ዶክተር ዘበነ ለማ በምናብ ወደ ሃይማኖት ተራራ ሲያቀኑ የመጀመሪያው በዓይነ ሥጋ፤ ሁለተኛው በዓይነ ሥጋና በትንሽ ዓይነ መንፈስ፤ ሦስተኛው ግን እነዚህን ሁለቱን ይዞ ዓይነ ነፍስን ጨምሮ ማየት እንደሚገባ ቀድመው እንደተረዱ ይነግሩናል።በመፅሐፉ በገፅ 83 ላይ አንድ ሃሳብ እናገኛለን። ሃሳቡ ‹‹ሳይንስ ያለን ነገር ያሳይሃል እንጂ የሌለ ነገር ምንም ቢሆን ማምጣት አይችልም። ደግሞ የሠው ልጅ ጥበበኛ ነኝ ብሎ ወገኑን የሚጎዳ ከሆነ ከንቱ ነው።›› ይላል።
ሌላው ፀሐፊው በመፅሐፉ ገፅ 85 ላይ ያነሱት ሃሳብ ‹‹የሠው ልጆችን ታላቅነት የምትረዳበት አንዱ መንገድ ቀና ብለው ቀጥ ብለው የሚሄዱበት ምሥጢር ነው።›› ይሉንና ከራሳቸው ሃሳብ ጋር ለምን ይሄ እንደሆነ ይጠያየቃሉ። ከዛም አስከትለው እንዲህ ይላሉ ‹‹በአንደኛው ተራራ፣ በሁለተኛውም ተራራ ስለዚህ የተሠጠ ምርምር የለም›› በማለት ይደመድማሉ።
እውነት ነው! ሠው ለምን ቆሞ እንደሚሄድ፤ እንስሳትም ለምን አጎንብሠው እንደሚንቀሳቀሱ የተደረገ ጥናትም ሆነ ምርምር፤ በመላምት ደረጃ እንኳን የተቀመጠ ምንም ነገር እስካሁን ድረስ አላየንም። ምናልባት ዳርዊን የሠውን ዝግመታዊ ለውጥን ሲገልጽ ማጎንበሱንም፣ ቀና ማለቱንም በለውጥ ሂደቱ ለማሳየት ሞከረ እንጂ አሁን ድረስ አጎንብሠው የሚሄዱትን እንስሳትና የሠው ልጅ ቆሞ የሚሄድበትን ምስጢር ሊገልጥ አልቻለም፤ ጉዳዩም በወጉ የተመረመረ አይመስለኝም።
ፀሐፊው ግን ሙሴ በምናብ እንደነገረኝ ብለው ያስቀመጡት ሃሳብ እንዲህ ይላል ‹‹ሠው ገዢ ስለሆነ፤ አራዊት እንስሳት ተገዢ ስለሆኑ ይህን የሚያመለክት ምስጢር ነው›› በማለት የሠውን ቆሞ መሄድ የእንስሳት ገዢ በመሆኑ ነው ይላሉ።
የሠውን ቆሞ መሄድ ሌላም ምስጢር አለው ይሉናል። ‹‹እንስሳቱ ማጎንበሳቸው፤ ሠው ቀና ብሎ የመሄዱ ምሥጢር ግን እነሱ ከሞቱ አይነሱም። ሰዎች ግን ከሞት በኋላ በትንሣኤ ዘጉባኤ ተነስተን ለዘላለም ሕያዋን እንሆናለን›› በማለት ሠው ቆሞ መሄዱ የዘላለማዊነቱ ማሳያ እንደሆነ ይገልጻሉ። ሌላው ‹‹ሰው ማለት በግዕዝ ሰብዕ ማለት ነው›› ይሉንና ‹‹ይህም ከሰባት ጋር አንድ ነው። ሰው ማለት ሰባት ባህርያት ያሉት ማለት ነው››
በመፅሐፉ በገፅ 94 ላይ ሠውን በይነው እንዲህ ያስቀምጡታል ‹‹ሰው ማለት የተፈጠረ፤ መፍጠር የማይችል፤ የሚመግበውና የሚጠብቀው ያለው፤ ነፍስና ሥጋ ያለው፤ ከነፍሥ ከስጋ አንድ የሆነ፤ በነፍስ አካልነት የቆመ፤ የሚያስተውል፣ የሚያስብ፤ የሚናገር፣ የሚንቀሳቀስ፤ ሥጋ ብቻ ያልሆነ፤ ነፍስም ብቻ ያልሆነ፤ ፍፁም ሥጋ ወነፍስ፤ ፍጹም ፀጋ፤ ምሉዕ ጸጋ፤ ፍጥረት ነው። በዚህ ላይ ደግሞ መንፈስ የተጨመረለት ድንቅ ፍጡር ነው።››
በኖህ ዘመን የሠው ልጅ ከተፈጠረበት ክቡር ማንነቱ ተለይቶ እንስሳዊ ማንነቱን በመተግበሩና ከበዛው ሐጥያቱ የተነሣ ለ150 ቀናት በዘነበ ዝናብ ከምድረ ገፅ ጠፋ። የተረፉት ኖህና ልጆቹ ብቻ ነበሩ።ፀሐፊው ይሄን አስመልክተው ሰው ‹‹ራሱን ከማጥፋቱ በተጨማሪ ለሌሎች ፍጥረታት መጥፋት ሁሉ ተጠያቂ ነው›› ይሉናል።
በመጨረሻም ፀሐፊው ከገፅ 107 እስከ 113 ድረስ ያነሱትና በሠፊው የዘረዘሩት ስለዘመናችን የሳይንስ ፕሮጀክት ነው። የሳይንሱ ዓለም ስልጣኔ የሰብዓዊነትን ዘር ድምጥማጡን ሊያጠፋ የሚችል ስለመሆኑ የዩቫል ኖኅ ሃራሪን “The brief history of tomorrow” መፅሐፍ ይጠቅሳሉ። ሠው ከሃምሣ ዓመት በኋላ ወደ አምላክነት ይለወጣል። ይሄም “ሆሞ ዲዩስ” ትርጉሙም “ሰው አምላክ”፤ይባላል ይሉናል።
ፀሐፊው ይሄንን ሲያብራሩ ‹‹ሐራሬ እንደሚለው የሠው ልጅ ሶስት ጠላቶች አሉት። እነዚህም ረሃብ፣ ጦርነትና የተፈጥሮ አደጋ ናቸው። ከእነዚህ ነገሮች በሃይማኖትና በፖለቲካ ስላልዳነ ይህን ችግር ለመፍታት ሠው ግዴታ ወደአምላክነት መለወጥ አለበት (The rise of human god):: ይህም ሊሆን የሚችለው በቴክኖሎጂ ውጤት ሰውን ወደ አምላክነት ከፍ በማድረግ (Upgrade human beings in to gods) ነው። የሚሳካውም በጄኔቲክ ኢንጀነሪንግ የምርምር ውጤት ነው። የ21ኛው ክፍለዘመን አዲስ እምነት ይባላል። የሳይንቲስቶች ትልቁ ሃሳባቸው ሠው ሁልጊዜ ደስተኛ ሆኖ ሞትን ድል አድርጎ ለዘላለም ሳይሞት በሕይወት ለመኖር ነው።››
ፀሐፊው በመቀጠልም ‹‹ሐራሬ የሠው ልጅ ፍጻሜና የArtificial Intelligence መነሣት (The end of Humanity and the rise of AI) በመፅሐፉ ይናገራል። ይህም የሚከናወነው በአንድ ስውር ሸለቆ ውስጥ ነው። ሸለቆውም በአሜሪካን ሐገር በደቡባዊ የሳንፍራንሲስኮ ባሕር ዳርቻ ላይ ያለ ኤስቪ (SV) ተብሎ በአጭሩ በሚጠራው የሲልከን ሸለቆ ነው። ሲልከን ቫሊ በዓለም ላይ ለሚገኙ ታላላቅ የሀይቴክ ኮርፖሬሽን ቤታቸው ነው። የሲልከን ቺፕስ የተፈበረኩበት ቦታ ነው። የስተም ሴል ምርምርም የሸለቆው ዋና ተግባር ነው።››
ፀሐፊው ከሃራሬ በተጨማሪ «የቴዎሬቲካል ፊዚክስ» ሊቅ የሆነውን ትውልደ ጃፓናዊ አሜሪካዊው ሚቺኦ ካኩን በመጥቀስ የወደፊቱ ሠው የማይሞት ይሆናል በማለት ስለሕያው ሆኖ መኖር ብዙ ተናግሯል ይሉናል። ካኩ እንደሚለው ሠውነት ሟች መሆኑ አብቅቶ ለዘላለም በሳይንስ ውጤት ሕያው ሆኖ የሚኖርበትን በሁለት መንገድ ይገልፀዋል። ይሄም Biological immortality እና Digital immortality ተብሎ ተሠይሟል ይላሉ። ለማንኛውም መፅሐፉ ታነቡት ዘንድ ጋበዝናችሁ! ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2011
አብርሃም ተወልደ