ህይወት ብዙ ውጣ ውረድ አላት ። ለአንዱ ምቹ ለሌላው ደግሞ ጎርበጥባጣና እሾሃማ ናት ።ጫናዋ ከጫንቃ በላይ ይሆናል ።በእርግጥ ሁሉንም እንደ አመጣጡና ሁኔታው መቀበልና መሸኘት አስፈላጊም ግዴታም ቢሆንም አንዳንዴ ከአቅም በላይ ሆኖ “ምነው ይህ ሁሉ ለእኔ ብቻ “ የሚያስብልበት ጊዜ ብዙ ነው ።
ሰው በምድራዊ ህይወቱ ሊፈተን ግድ ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ ከፈተናዎች ሁሉ በኋላ አንጸባራቂ ድልን መጎናጸፍ ስላለ፤ አንዳንዶች ይህንን የህይወትን ፈተና ለመሸከም ጫንቃቸው ብርቱ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በትንሽ በትልቁ ስብር እንክት ሙትት ሲሉም ማስተዋሉ የተለመደ ነው ።ነገር ግን ለህይወት ፈተና እጅ አለመስጠቱ ሳይሻል አይቀረም ።
በተለይም ሶስተኛው አለም ተብሎ በሚጠራው አፍሪካ እንደ እኛ አገር ደግሞ ለማደግ ለመበልጸግ ሩጫ ላይ ባለች አገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ በኑሮ ውጣውረድ ይፈተን ዘንድ ግድ ነው ።ይህንን ፈተና ማለት ግን የአለም ፍጻሜ አለመሆኑን ከተበረታ ችግርን ማሸነፍ ጨለማን አልፎ ብርሃን ማየት ጽልመቱ ተገልጦ ብሩህ ቀን ላይ መድረስም እንደሚቻል ማመን ግድ ነው ።
የዚህ ሃሳብ መነሻችን የአቶ ከድር አህመድ የሱፍ ታሪክ ነው ።አቶ ከድር ተወልደው ያደጉት በስልጤ ዞን አምቢቾ ወረዳ ገሶ ገበሬ ማህበር ነው ።አቶ ከድር ለእናታቸው አንድና ብቸኛ ልጅ ቢሆኑም አባታቸው ሌላ ትዳር መስርተው የወለዷቸው በርካታ እህትና ወንድም አሏቸው ።አቶ ከድር እንደ አገር እንደ ወግ ባህሉ የልጅነት እድሜያቸውን ከእኩዮቻቸው ጋር አሳልፈዋል። ያን ያህል የተደላደለና ያማረ ኑሮን መኖር ባይችሉም ሳይርባቸው ሳይጠማቸው ነው ያደጉት ።ኋላም ለአቅመ አዳም ደረሱና እሳቸውም ትዳር መሰረቱ ፤ ለእናታቸው ብቸኛ ልጅ የሆኑት አቶ ከድር ከአባታቸው ልጆች ጋር በተካፈሏት አነስተኛ የእንሰት ማሳም እንሰት እንዲሁም ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን እየተከሉ ኑሮን ተያያዙት። ሳይደላቸውም ሳይከፋቸውም ከባለቤታቸው ጋር ልጆች እየወለዱ እናታቸውን እየጦሩ መኖር ቀጠሉ ።ነገር ግን በዛች የበሬ ግንባር በምታክል የእንሰት ማሳ ምክንያት ከአባታቸው ልጆች (ወንድሞቻቸው) ጋር መስማማት አቃታቸው ።
አቶ ከድር ሲወጡ ሲገቡ የሚያዩት፣ የሚሰሙት ሁሉ አላምር ቢላቸው እንዲሁም እየሆነባቸው ያለው ነገር ለጤናቸውም አስቸጋሪ ሲመስላቸው የእሳቸውን ህመም ወደጎን በመተው አቶ ከድር ልጆቻቸውን ማሳደግ ብቻ ነበር ህልማቸው፤ የጀመራቸው ህመምም እጃቸው ተንቀሳቅሶ ስራ እንዳይሰራ ወደማሰሩ ደረጃ ሊሄድ ሆነ፤ አቶ ከድር “እኔ ብሞት ልጆቼ ምን ይሆናሉ” ብለው በማሰብ በበሽተኛ እጃቸው ለልጆቻቸው አንገት ማስገቢያ ጎጆ ቀለሱ፤ ልጆቻቸውን በዛ ካሳረፉ በኋላም ወደ ህክምና ለመሄድ ወሰኑ ።
እዛው የተወለዱበት አካባቢ “አጣጥ ሆስፒታል” ህክምናቸውንም ጀመሩ ፤ በህክምና ላይ እያሉም ጤናቸው ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ ጭራሽም እጃቸው አልታዘዝ ብሎ ተቆላለፈ ።
“…..አገር ቤት ልጆቼን ለማሳደግ እንሰት እተክላለሁ የጓሮ አትክልትም ነበረኝ፤ በጠቅላላው ልጆቼን ሳላስርብ እያኖርኩ ነበር፤ነገር ግን ወንድሞቼ ብቸኝነቴን አይተው የሚያደርሱብኝን ጫና መቋቋም አቃተኝ፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ ታማሚ ሆንኩ ፤ከዛው እዛው አጣጥ ሆስፒታል ያደረኩት ህክምናም ለውጥ አላመጣ አለኝ። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ የእህቴ ልጅ ለአረፋ በዓል ወደቤት መጣ ያለሁበትን ሁኔታ አይቶ በጣም በማዘን አዲስ አበባ ለህክምና አመጣኝ በዛው እዚሁ ቀረሁ” ይላሉ ።
አዲስ አበባ ያመጣቸው የእህታቸው ልጅም ሆስፒታል አስገብቶ ህመምተኛው እጃቸው ኦፕሬሽን እንዲሆን አደረገ ፤ የመጀመሪያው ኦፕሬሽን በቂ ስላለነበር ከስምንት ወራት በኋላ ዳግም ኦፕሬሽን ተደረጉ ።በዚህ ሁሉ መካከል ግን አገር ቤት ጥለዋቸው የመጡት ቤተሰቦቻቸው ሁኔታ ያሳስባቸዋል ምን ሆነው ይሆን ምን በልተው ዋሉ አደሩ ትምህርታቸውስ የሚለው ነገር በጣም እንቅልፍ ይነሳቸው ነበር ።ፈጣሪ ፈቅዶም ጤናቸው መሻሻልን ሲያሳይ ልጆቻቸውን ለማገዝ ስራ ማፈላለግ ጀመሩ ፤ በዚህ መካከል የቅርብ ዘመዳቸው የሆነ በኑሮው ጥሩ ደረጃ ያለ ሰው “ና ከእኛ ጋር እየኖርክ ስራ “ ብሎ አስጠጋቸውና አብረው እየኖሩ ሰዎቹ ባላቸው ድርጅት ውስጥ እየሰሩ ልጆቻቸውን ማሳደግ ተያያዙት ።
ይህም ቢሆን ግን የአቶ ከድር የህይወት ፈተና በቀላሉ የሚያበቃ አልሆነም፤ አዲስ አበባ በስራ ላይ እያሉ የባለቤታቸውን በጠና መታመም ሰሙ ።በዚህ ጊዜ ስራቸውን ትተው ያሉበትን ሁኔታ ለማየት አገር ቤት ገቡ ።ያዩት ነገር ግን በጣም አሳዘናቸው ባለቤታቸው ትተዋቸው እንደሄዱት አልጠበቋቸውም፤ የኑሮ ጫና፣ ህመም፣የልጆች ኃላፊነት በጠቅላላው በጣም ተጎድተዋል ።በዚህን ጊዜ አቶ ከድር ባለቤታቸውን አዲስ አበባ አምጥተው ማሳከምና መንከባከብ እንዳለባቸው ወሰኑ እናም ይዘዋቸው መጡ ።
ባለቤታቸው ያለባቸው የመገጣጠሚያ ኢንፊክሽን ብዙ ህክምና የሚያስፈልገው የዶክተሮችን የቅርብ ክትትል የሚጠይቅ ሆነ ።አቶ ከድር ጥበቃ እየሰሩ ወዲህ ወዲያ ብለው የሚያመጧት ገንዘብ ሆድ ሞልታ ለህክምና የምትተርፍ አልሆነችም እናም አይናቸውን ጨፍነው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ይዘዋቸው ሄዱ፤ የእድል ጉዳይ ሆኖም የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ባልደረቦች ባለቤታቸውን ተቀበሉላቸው ።በዚህም አንድ አመት ከስድስት ወራት ያህል ሆስፒታል ተኝተው የህክምና ክትትላቸውን አደረጉ ።
በዚህ መካከል ግን ሌላ የህይወት ፈተና በባልና ሚስቶቹ ዘንድ መጣ ።አገር ቤት ጥለዋቸው ከመጡት ልጆች መካከል ሶስተኛው ልጃቸው ሰዒድ ከድር ይባላል፤ የሚወዳቸው እናቱ ታመውበት አንድ አመት ከስድስት ወራት ሆስፒታል ሲተኙ እሱ ደግሞ በገጠር ያሉትን ታናናሽ እህትና ወንድሞቹን በሚችለው አቅሙ ይንከባከብ ነበር ።ለእህትና ለወንድሞቹ እናትም አባትም ወንድምም እየሆነ ከትምህርቱ ጎን ለጎን የጉልበት ስራ እየሰራ ሆዳቸው አዳይጎል፣ ከትምህርት እንዳይቀሩ ብዙ ይለፋ ነበር ።አባቱ እናቱን በማስታመም እየደከሙ መሆናቸውን ተረድቶም እሱም ያቅሙን ያህል ቤተሰቡን ያግዛል ።
አባት በዚህ ጊዜ ጠሮ መስኪድ አካባቢ ማታ ጥበቃ ስራ እየሰሩ ቀን ባለቤታቸው ጋር እየሄዱ ባለቻቸው ትንሽ ጊዜ ደግሞ ሙስሊም ህጸናትን ሰብስበው ቁርዓን እያስቀሩ ኑሮን ተያይዘውታል ።ልጅም በበኩሉ የአባቱን ዱካ ተከትሎ ወንድም እህቶቹን ያግዛል ።
ነገር ግን ሰዒድ የሚሰራው ስራ እያለፈበት ያለው የህይወት ጎዳና ከአቅሙና ከእድሜው በላይ ነበርና ድንገት እሱም ሆነ ቤተሰቡ ያላሰቡት ነገር ገጠመው ።ሰዒድ በትንሽ በትንሹ የጀመረው ህመም ተባባሰ ።ይህም ቢሆን ግን እናቱና አባቱ የእሱን ሁኔታ ሰምተው እንዲጨነቁ አልፈለገም ።ህመሙን ደብቆ ሲሻለው እየሰራ ሲብስበት እቤት እየዋለ ኑሮን ቀጠለ። ይህ አካሄድ ግን ረጅም ርቀት አላስኬደውም ።ችግሩ እየተባባሰ ሰዒድ ከመቀመጫው ተነስቶ መራመድ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደረሰ ።ይህ ሁሉ ሲሆን አባት አቶ ከድርም ሆኑ እናቱ የሚያውቁት ነገር አልነበረም ።
ሰዒድ ለብዙ ጊዜያት ህመሙን ችሎ ኋላም ደብቆ ቢቆይም ከአባቱ ጋር የሚገናኝበት አጋጣሚ ተፈጠረ። አባት አቶ ከድር ወንድማቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ሰምተው ወደ አገር ቤት ሄዱ ።ሲሄዱ ግን የገጠማቸው ነገር ለእሳቸው ራሱ የሞት ሞት ሆነባቸው። ቀልጣፋና ጎበዙ የእሳቸውን ቀንበር ተቀብሎ የቤተሰቡ ምሰሶ የነበረው ትንሹ ልጃቸው እንደ እድሜ እኩዮቹ መሯሯጥ መራመድ አቅቶት እጥፍጥፍ ብሎ ተቀምጦ አገኙት ።
ያዩትን ማመን ያቃታቸው አባት አቶ ከድር “ ልጄ ምን ሆነህብኝ ነው ፤ ምን አገኘብኝ?” ሲሉ ጠየቁ ልጅም “አባቴ ከታመምኩ ትንሽ ቆየሁ፤ አጣና ስሸከም ነው እንዲህ የሆንኩት፤ነገር ግን መታመሜን ብነግርህ ትጨነቃለህ ብዬ ነው” አላቸው ።አባት አዘኑ ልባቸው ተሰበረ፤ ምንም እንኳን ባለቤታቸውን አሳክመው የጨረሱ ባይሆንም ህመምተኛውን ትንሹን ጎበዝ ልጃቸውን እዛው ጥለውት መምጣት አልፈለጉም፤”ለምኜም ቢሆን አሳክምሃለሁ ና እንሂድ ብለው አዲስ አበባ ወደተከራዩት ቤት ይዘውት መጡ” ።
አቶ ከድር ሁኔታው እሳቸውንም በሽታ ላይ የጣላቸው ቢሆንም ለልጃቸው ሲሉ ግን ቆሙ ጠነከሩ ፤ ጥርሳቸውን ነክሰው መራመድ የማይችለውን ልጃቸውን በጀርባቸው አዝለው ሆስፒታል ለሆስፒታል መመላለስ ያዙ፤ ቆሞ እንደኩዮቹ እንዲሄድላቸው የሚችሉትን ሁሉ ሊያደርጉ ለራሳቸው ቃል ገቡ አላህን እየተማጸኑም ጉዟቸው ቀጠሉ ።
አባት አቶ ከድር ከአጠገባቸው የሚያግዛቸው ማንም የለም፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ የጥበቃ ስራቸውን ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርገው ትተው ታማሚ ልጃቸውን በጀርባቸው አዝለው በቀን አንዴ እየተመገቡ አቤት ሆስፒታል መመላለስ ስራቸው ሆነ ። አሁን ላይ ልጃቸው በደጋግ ኢትዮጵያውያን አማካይነት በአቤት ሆስፒታል ህክምና እየተደረገለት ቢሆንም ምስኪኑ አቶ ከድር ግን ፈተናቸው አላበቃም፤ እርሳቸው እዚህ እየተሰቃዩ ማየትን ያልመረጡት ባለቤታቸው ህክምናቸውን አቋርጠው ገጠር ገብተዋል ።በሌላ በኩል ደግሞ የሰዒድ ታላቅ እህት ሉባባ ከድር ትምህርት ቤት ወድቃ እጇ በመሰበሩና በወቅቱ መታከም ባለመቻሏ ችግር ውስጥ እንደሆነች ሰምተዋል ።
አቶ ከድር ምንም እንኳን እሳቸውም ጤና እያጡ ቢሆንም ይበሉት ይጠጡት ለልጆቻቸውም ይሰጡት ነገር የሌላቸው አዛውንት ቢሆኑም ሴቷን ልጃቸውንም አሳክመው ለማዳን አዲስ አበባ እንድትመጣ አድርገዋል።
“…አሁን ሰኢድ ልጄ በደጋጎች አማካይነት በአቤት ሆስፒታል ህክምና እያገኘልኝ ነው ።ነገር ግን ታላቅ እህቱ ደግሞ እጇ ተሰብሮ መማር አልቻለችም ።እሷንም ለማሳከም አምጥቻታለሁ ።ሰዒድ ከተሻለው እሷን ደግሞ አሳክማለሁ “ ይላሉ ።
ስራ ላቆሙት አባት ከድር ይህ ጊዜ በጣም ከባድ ነው፤ በመከራ ላይ መከራ እየተደራረበባቸው ነው፤ ልጃቸው አቤት ሆስፒታል ህክምና ቢደረግለትም አንዳንድ ተጨማሪ ምርመራዎች ያስፈልጉታል ይህንን ማድረግ ፤ መድሃኒትና ምግብ መግዣም የላቸውም ፤ ሴቷ ልጃቸውም መጥታለች፤ እሷን ለማሳረፊያ የሚሆን ቤት ቢከራዩም አሁን ላይ ኪራዩን መክፈል አቅቷቸዋል፤ አባት ከድር ይህንን ሁሉ ሲናገሩ እንባቸው እንደ ጎርፍ ይወርዳል፤ አታልቅሱ ሲባሉም ሌት ተቀን ስራዬ ምን ሆነና ይላሉ ።ከእንባቸው ሌላ አሁን ላይ ምንም አቅም የላቸውም ።
በሌላ ጎን ደግሞ ይህ ሁሉ ፈተና ቢወርድባቸውም የችግራቸውን ግዝፈት ያህል አያማርሩም፤እንደውም አላህን ደጋግመው ያመሰግኑታል፤ ለሰጪዬ ይስጥልኝ በማለትም የምርቃት መዓት ያወርዳሉ ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/ 2015 ዓ.ም