የሰው ልጅ በሕይወት መቆየት እንዲችል ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያና ልብስ የግድ ቢሆኑም፣ በተሻለ ሁኔታ ለማምረት፣ ኑሮን ቀላልና የተቀላጠፈ ለማድረግ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል ያስፈልጋል ።ኢነርጂ ወይም የኤሌክትሪክ ኃይል ለሰው ልጆች ብርሃን ከመስጠት ባሻገር ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታዎችን ያበረክታል ።
ከተማ ተወልዶ በማደግ ከሚገኙ የተለያዩ ጥቅሞች መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት አንዱ ነው። የኤሌክትሪክ ኃይል ብርሃን ከመስጠት ባለፈ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ይሰጣል ።በተለይም በከተሞች አካባቢ የእያንዳንዱ ሰው እንቅስቃሴ በኤሌክትሪክ ላይ ጥገኛ ከመሆኑ የተነሳ መብራት ሲጠፋ ሁሉም ነገር ቀጥ ይላል ቢባል ማጋነን አይሆንም ።
የኤሌክትሪክ ኃይል ፋይዳ ይህን ያህል ቢሆንም ታዲያ አብዛኞቹ በገጠር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ኃይል አያገኙም፤ ከጨለማ የሚታደጋቸውን ብርሃን የሚያገኙበት መንገድ ኋላቀር ነው ።ዛሬም ድረስ በኩራዝ ጭስ፣ በማገዶ ጨለማውን ይገፋል፤ አጠቃላይ ሕይወቱንም እጅግ አስቸጋሪ፣ ፈታኝ፣ አድካሚና አሰልቺ በሆነ መንገድ እየመራ ይገኛል ።
የሰዎችን ሕይወት ቀላልና ቀልጣፋ በማድረግ ትልቅ ድርሻ ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል በመላው ሀገሪቱ ተደራሽ መሆን ባለመቻሉ መንግሥት በርካታ የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጮች ተግባራዊ እንዲሆኑ እየሠራ ነው ።በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለመታደግ አቅዷል። ከንፋስ ኃይል በማመንጨት ላይም ይገኛል ።እንዲያም ሆኖ ፍላጎቱና አቅርቦቱ የሰማይና የምድር ያህል ነው፤ የተለያዩ የኃይል አማራጮችን መጠቀም የግድ ሆኗል። የጸሐይ ኃይልን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ውስጥ ከተገባም ቆይቷል፡፡
ይሄ ሁሉ ተደርጎም ዛሬም ድረስ የኃይል አማራጭ የሆነውን ሶላር ማግኘት ያልቻሉ ኢትዮጵያውያን በርካታ ናቸው ።እነዚህ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ለመድረስ ታዲያ መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ የግልና የውጭ ድርጅቶች ጭምር በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል ።እንዲያም ሆኖ ታዲያ ተደራሽነቱ ገና ይቀራል ።
የሶላር ኢነርጂ ማመንጨት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብና በመገጣጠም ሥራ በርካታ ድርጅቶችና ዜጎች ተሰማርተዋል፤ ይህም ወደ ሀገሪቱ ገጠር አካባቢዎች ዘልቆ ገብቷል ።
የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች አማራጭ የሆነውን ሶላር ተደራሽ በማድረግ፤ ጨለማ ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች ብርሃን መሆን ከቻሉ ድርጅቶች መካከል ግሪን ሲን /Green Scene/ የተባለው ድርጅት አንዱ ነው ።የድርጅቱ መሥራችና ማናጀር ረቂቅ በቀለ ትባላለች ።
ረቂቅ ተወልዳ ባደገችበት አዲስ አበባ ከተማ መብራት የማግኘት ዕድሉን ብታገኝም፤ ጭርሱኑ መብራት ምን እንደሆነ የማያውቁ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ የሚል ግምት ግን አልነበራትም ።የከፍተኛ ትምህርቷን አጠናቃ ወደ ሥራ ዓለም በተቀላቀለችበት አጋጣሚ ይህንን እውነት ተረዳች ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው ረቂቅ፤ በኤሌክትሪካል ዲዛይን ለአንድ ዓመት ስትሠራ አሁን በደረሰችበት ደረጃ የኃይል አማራጭ የሆነውን ሶላር አከፋፍላለሁ የሚል ሀሳብ አልነበራትም ።ይሁንና ኢነርጂ ለሰው ልጆች የቱን ያህል አስፈላጊና የግድ እንደሆነ ግን በሚገባ መረዳት ችላለች ።
የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ ለዛሬ ሥራዋ መሠረት የሆነውን አንድ የሶላር ኩባንያ ተቀላቀለች ።ኩባንያው በአንድ የገጠር ወረዳ ሶላር ለማስገባት ለሚሠራው ሥራ ሠራተኞችን እያፈላለገ መሆኑን ትረዳለች ።ረቂቅ የኩባንያው አንዷ ሠራተኛ ሆና ተቀላቀለች ።
የመጀመሪያ ሥራዋም መብራት ባለውና ሁሉ ነገር በተሟላበት ቢሮ ውስጥ መሥራት ሳይሆን መብራት ከማያውቃት ገጠር ውስጥ ገብቶ ሶላር ማስገባት የመጀመሪያ ሥራዋ እንደነበር ታስታውሳለች ።
አካባቢው እጅግ ገጠራማና መብራት የሌለበት ነው፤ በወቅቱ ሶላሩ ይገባ የነበረው ለጤና ጣቢያ ብቻ ነበር። ‹‹ሥራውን ሠርተን እስክንጨርስ በቦታው ለአሥራ አምስትና ከዛም ላለፉ ቀናት መቆየት የግድ ነበርና በቆይታዬ ብዙ ነገሮችን ተማርኩ›› የምትለው ረቂቅ፤ በዚሁ የሥራ አጋጣሚዋ የመብራትን ጥቅም በጥልቀት መረዳት ቻለች፡፡
ሶላር ለመግጠም የሄደችበት አካባቢ እጅግ የተዋበና በተፈጥሮ የታደለ ለምለም ነው፤ የግብርና ምርት በዓይነት በዓይነቱ ይገኛል ።ሁሉም ነገር ያላቸው እነዚህ ነዋሪዎች ግን መብራት አያውቁም ።የጤና ባለሙያዎች በምሽት ለሚመጣ ታካሚ የእጅ ስልኮቻቸውን በአፋቸው በመያዝ እንዲሁም በኩራዝ አገልግሎት ለመስጠት በብዙ ሲቸገሩ አስተውላለች ።በዚህ መጠን ለሚቸገር ማኅበረሰብ መፍትሔ መሆን መቻል ደግሞ የሚሰጠውን ደስታ መገመት አያስቸግርምና ረቂቅም ለዚሁ ትርጉም ላለው ሥራ ተሰጠች፡፡
ከቀጠራት ደርጅት ጋር ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ሶላር የምታስገባው ረቂቅ፤ በዚሁ አጋጣሚ የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችን ከማወቅ ባለፈ ሥራውን በስፋት ለመሥራት ምቹ አጋጣሚን ተፈጠረላት ።ይህን አጋጣሚ ተጠቅማ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት በግሏ ኢነርጂ የማከፋፈል ሥራዋን ‹‹ሀ›› ብላ ጀመረች ።በወቅቱ የፋይናንስ እጥረት ቢገጥማትም ለሥራው ከፍተኛ ፍላጎት፣ ተነሳሽነትና ቁጭት ስለነበራት ችግሩ አልታያትም ።ምክንያቱም መሰል የግል ድርጅቶች ካልተበራከቱ ችግሩን መፍታት እንደማይቻል ተረድታለችና ።
በተለያዩ የሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች በነበራት እንቅስቃሴ በተለያየ ጊዜና ቦታ በኩራዝ ምክንያት ልጆች ስለመቃጠላቸው፣ ቤት ንብረት ስለመውደሙና ሌሎችም በርካታ አደጋዎች ስለመድረሳቸው ከማኅበረሰቡ ተረድታለች ።ታዲያ የኤሌክትሪክ አማራጭ የሆነውን ሶላር እንዲህ ላለው ማኅበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ ከራሷ ጋር ተሸቀዳደመች ።ግሪን ሲን የተባለ ድርጅት በመክፈት ከውጭ ሀገራት ሶላር እያስመጣች ማከፋፈል ጀመረች። በሥራዋም ትርጉም ያለው ውጤት ተመለከተች። ለብዙዎች ብርሃን ለመስጠት ምክንያት መሆን በመቻሏ እርካታዋና ደስታዋ እየበዙ መጡ ።
ከውጭ ሀገራት የተለያዩ የሶላር አይነቶችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለብዙዎች ብርሃን መሆን የቻለችው ረቂቅ፤ 90 በመቶ የሚሆነው ዕቃ ከአገረ ቻይና እንደሚገባ ነው ያጫወተችን ።ሥራው ከፍተኛ ፋይናንስ የሚፈልግ መሆኑን ጠቅሳ፣ በእዚህ ላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ድርጅቱ ከፍተኛ ችግር ገጥሞት እንደነበር ታስታውሳለች ።ያም ቢሆን ግን ሶላሩን ከማከፋፈል በተጨማሪ በዘርፉ አዳዲስ ሃሳቦችን በማምጣት፣ በመወዳደርና አሸናፊ በመሆን ተጠቃሚ ሆና ማንሰራራት ችላለች ።
‹‹ኤሌክትሪክ ለሁሉም ነገር ትልቅ አማራጭ ነው›› የምትለው ረቂቅ፤ በተለይም አርሶ አደሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት ካልቻለ ሕይወቱን መለወጥ አይችልም። ኤሌክትሪክ በቤት ውስጥ ብርሃን ከመስጠትና ምግብ ከማብሰል ባለፈ የግብርና ሥራውን ያቀላጥፍበታል ትላለች ። ለአብነትም አነስተኛ የግብርና ሥራቸውን በማቀላጠፍ በሶላር ውሃ ከጉድጓድ አውጥተው እንዲያመርቱ፣ ምርቶቻቸውን በቀላሉ መሰብሰብና ማከማቸት እንዲችሉ ኤሌክትሪክ ከአማራጭም ባለፈ የግድ ነው በማለት ታብራራለች ።
በአሁኑ ወቅት 56 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ያላገኘ መሆኑን በመጥቀስ፣ በዚህም የተነሳ በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ይደርስበታል ትላለች ። ከዚህም ባለፈ የኃይል አማራጭ የሆነውን ሶላር በመጠቀም በኩል በተለይም ነጋዴው ያለዕውቀት በመሸጡ የሚፈጠር ችግር እንዳለ ነው ታነሳለች ።
የእሷ ድርጅትና መሰሎቿ ግን ከመንግሥት ጋር በመሆን እንደሚሠሩ ትናገራለች ። በአሁኑ ወቅት የሶላር ኢነርጂን ቁሳቁስ እያከፋፈለች ያለችው ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብና ከሲዳማ ክልሎች ጋር ስምምነት በመፍጠር ነው ።የእሷና መሰል ድርጅቶች የሶላሩን ጥቅምና እንዴት መጠቀም እንደሚገባ በማስረዳት ተደራሽ ያደርጋሉ ።ሕጋዊ ሆነው በመሥራታቸውም ቢበላሽ እንኳ ሄደው ይጠግናሉ፡፡
ደንበኞቿ ሙሉ ለሙሉ መብራት የማያውቁ በመሆናቸው ቤታቸው በብርሃን ሲሞላ እጅግ ደስተኞች ሲሆኑ መመልከት የዓመታት ሥራዋ ሆኗል ።ክፍያውን በተመለከተም ጥሬ ከፍለው የሶላር መሣሪያውን ከመግዛት በተጨማሪ በአቅራቢያቸው ከሚገኙ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር በረጅም ጊዜ ክፍያ እንዲከፍሉ ሁኔታዎች አመቻችታላቸዋለች ።ሦስተኛው የክፍያ አማራጭ ደግሞ እየተጠቀሙ መክፈል ነው፤ ይህም መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር በማበልጸግ እየተጠቀሙ መክፈል የሚችሉበት መንገድ ተፈጥሯል ።ተጠቅመው ገንዘቡ ሲያልቅ መብራቱ ይጠፋል ።በጠፋበት ፍጥነትም ጨለማውን አይፈልጉምና ክፍያቸውን ይፈጽማሉ ።
የሶላር አይነቶቹ የተለያየ አገልግሎት ያላቸው ሲሆን፣ አርሶ አደሩ እንደየአቅሙና ፍላጎቱ ይገዛል ።አነስተኛ ከሆነው አንስቶ ረጃጅም መስመሮች ያላቸውና በተለያዩ ክፍሎች መራዘም የሚችሉና የእጅ ስልኮችን ቻርጅ ማድረግም የሚያስችሉም አሉ ።ከዚህ በተጨማሪም ኢነርጂ በማግኘታቸው ቴክኖሎጂን መጠቀም ይችላሉ ።ለአብነትም በእጅ ስልኮቻቸው አማካኝነት በገቡት ውል መሠረት ክፍያ የሚፈጽሙ በርካቶች ናቸው ።የሶላር ኢነርጂ በመጠቀም የውሃ ፓምፕ እንዲሠራ ማድረግም ሌላው ቴክኖሎጂ ሆኗል፡፡
ኑሮውን በጨለማ ውስጥ ላደረገ ማኅበረሰብ ጨለማውን መግፈፊያ ብርሃን ከመስጠት ባለፈ የተለያዩ አገልግሎቶችን በሶላር ኢነርጂ እንዲጠቀም እየሠራች ያለችው ረቂቅ፣ የዛሬ ስድስት ዓመት ወደ ሥራው ስትገባ 20 ሺ ብር መነሻ ካፒታልና አንድ ጓደኛዋን በመያዝ ነበር። በአሁኑ ወቅት ካፒታሏ 13 ሚሊዮን ብር ደርሷል፤ ለ18 ሰዎችም የሥራ ዕድል ፈጥራለች ።
በስድስት ዓመት የሥራ ጉዞዋም ሱማሌ ክልልና ቤኒሻንጉል ጉሙዝን ጨምሮ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራና በሲዳማ ክልሎች 40 ሺ ለሚደርሱ ግለሰቦች አገልግሎቱን መስጠት ችላለች ።በእዚህ አገልግሎትም ዘጠኝ ሺ የሚደርሱ የተለያየ መጠን ያላቸውን ሶላሮች ተደራሽ አድርጋለች ።
‹‹መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይልን በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ ባለመቻሉ፤ የግል ዘርፉ ደግሞ በመዘግየቱ ምከንያት አብዛኛው ማኅበረሰብ ጨለማ ውስጥ ሊሆን ተገዷል፤ ስለዚህ መፍጠን ያስፈልጋል›› የምትለው ረቂቅ፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ባልደረሰበት ቦታ ሁሉ መድረስ ለነገ የሚተው ሥራ አይደለም፤ እጅግ አስቸኳይና አንገብጋቢ ነው ትላለች፡፡
ለዚህም መፍትሔው ቀላል መሆኑን ነው የምትጠቁመው፤ የኃይል አማራጭ የሆነውን የሶላር ኢነርጂ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች አሉ ።እነዚህን ወጣቶች ደግሞ ትልቅ ኃይል አላቸውና ምን እና ለምን እንደሚሠሩ የሚያውቁ በመሆናቸው እነሱን በመጠቀም ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያላትን እምነት አካፍላናለች፡፡
በየአካባቢው ግዙፍ የሶላር ፓኔሎችን በመትከል ኤሌክትሪክ ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተጋች ያለችው ረቂቅ፤ በቀጣይ ሥራውን በስፋት ለማሰራጨትና በፍጥነት ተደራሽ የመሆን ዕቅድ አላት ። ለዚህ ዕቅዷም የውጭ አገር ኢንቨስተሮችን በመሳብ ፋይናንስ እንዲያደርጉ ሥራ ጀምራለች ።ከዚህ በተጨማሪም የሶላር ኢነርጂ እቃዎችን በማከፋፈል በተንቀሳቀሰችባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች በሙሉ የግብርና ሥራ በስፋት ያልተሠራና ብዙ ማትረፍ የሚቻልበት የሥራ ዘርፍ እንደሆነ ተገንዝባለች ፡፡
ትዝብቷን በቁጭት ወደ ሥራ የመቀየር ልምድ ያላት ረቂቅ፣ አሁን የጀመረችውን የሶላር እቃዎችን የማከፋፈል ሥራ አጠናክራ በመቀጠል ሕዝቡ ሙሉ ለሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል እስኪያገኝ ድረስ የመሥራት ፍላጎት አላት፤ በተመሳሳይ ደግሞ በግብርናው ዘርፍ የመሰማራት አቅዳለች ።በየአካባቢው የተመለከተቻቸው የተፈጥሮ ሀብቶች እጅግ የሚያጓጉ እንደሆኑ ትጠቅሳለች፤ ከአፈሩ ጀምሮ አየሩና መሬቱ ለሁሉም ነገር እጅግ ተስማሚ መሆኑን የገለጸችው ‹‹ሀብት እያለን የምንራብ ዜጎች ነን›› በማለት ነበር፡፡
በዙሪያችን በርካታ ችግሮች ስለመኖራቸው ያነሳችው ረቂቅ፤ ‹‹አይናችንን መግለጥ አለብን›› ትላለች ።ከወጣቱ ብዙ የሚጠበቅ ነገር እንዳለ በማንሳትም ችግሮች ሁሉ ዕድሎች እንደሆኑ ነው የምታስረዳው ። ብዙ ችግር አለ ማለት ብዙ ዕድሎች አሉ ማለት ነውና እያንዳንዱን ችግር ወደ ዕድል በመቀየር መፍትሔ ማምጣትና ገቢ ማግኘት ይቻላል ትላለች ።ሁሉም ሰው ሥራ ፈጣሪ መሆን እንደማይችል በመጥቀስ ሥራ ከሚፈጥረው ጋር በመሆን ተቀጥሮ በመሥራት መፍትሔ መሆን እንደሚቻልም ትጠቁማለች ።በሚሠሩት ሥራም ያላቸውን ሙሉ አቅም በመጠቀም ከልባቸው መሥራት ይኖርባቸዋል። ያኔ እነሱም፣ የሚሠሩበት ተቋምም ውጤታማ መሆን ይችላሉ ።በማለት ወጣቶች ለሥራቸው ታማኝና ትጉ በመሆን ውጤታማ እንዲሆኑ መክራለች ።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/ 2015 ዓ.ም