የዛሬው ‹‹የዘመን እንግዳችን›› በቀድሞው መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በመድፈኝነትና በስለላ ሥራ አኩሪ ተግባር የፈፀሙ ሰው ናቸው ።ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ ደግሞ ትሕነግን በመታገል ረገድ ከፍተኛ ሥራ በመሥራት ይታወቃሉ። እንግዳችን የተወለዱት በቀድሞው አጠራር ኢሉባቦር ክፍለ ሀገር ቴፒ ከተማ ውስጥ ነው ።የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቴፒ አንደኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም በነቀምት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በቀጥታ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ በመግባት በውርሶ መኮንኖች ማሰልጠኛ ሰልጥነው የመቶ አለቃነት ማዕረግ አግኝተዋል።
አንደኛው አብዮታዊ ሠራዊት በመካናይዝድ ብርጌድ ውስጥ በመድፈኝነትና በቅየሳ ወታደራዊ ሞያ በመድፈኝነት ከ46 ባላነሱ ግንባሮች ተሰልፈው የሃገራቸውን ዳር ድንበር በማስጠበቅ ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን የሚናገሩት እኚሁ ሰው በተለይም በጅግጅጋ፣ ቶጎጫሌና ቀብሪደሐር ተሰልፈው ሃገር ሊወር የመጣውን ጠላት ድባቅ መምታቸውን ይጠቀሳሉ። እንዲሁም በራሺያና ኩባ ኤክስፖርቶች የተለያዩ ወታደራዊና የቅየሳ ስትራቴጂ ትምህርት ቀስመዋል ።በሰላም ሥራ ምስራቅ አፍሪካ ላይ የተለያዩ ወታደራዊ ግዳጆችንም የተወጡ ሲሆን በተሰለፉባቸው የውጊያ ዐውዶች አራት ጊዜ ያህል ተመትተው የመቁሰል አደጋ አጋጥሟቸው ነበር ።
በሀገሪቱ የመጣውን የሥርዓት ለውጥ ተከትሎ ሠራዊቱ ሲበተን ወደ ሱዳን ተሰደዱ ። ከዚያች ጊዜ ጀምሮ በተደረገው የፀረ-ወያኔ ትግል ውስጥ በሱዳን የጠረፍ አካባቢዎች ይደረጉ በነበሩት የሽምቅ ውጊያዎች ውስጥ ተሳትፈዋል ።በሱዳን ለጥቂት ወራት ከቆዩ በኋላ በስለላ ሥራቸው ምክንያት ሕይወታቸው አደጋ ላይ በመሆኑ በሌሎች መንግሥታት እርዳታ ካናዳ ገቡ ።ካናዳ ከገቡ በኋላም ትግላቸውን አላቆሙም፤ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን የለውጡ መንግሥት እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ሀገሪቱን ከትሕነግ ቀንበር ለማውረድ በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡
በኮሎኔል ጎሹ ይመራ በነበረው የመድህን የፖለቲካ ድርጅት በአባልነት፣በጄኔራል ኃይሌ መለስ በሚመራው የኢትዮጵያ የነፃነት ግንባር በአባልነት እንዲሁም በኢንጅነር ዶክተር ቅጣው እጅጉ በሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ግንባር ውስጥ ወታደራዊ ስለላና የመረጃ ከፍተኛ አማካሪ በመሆን በሀገር ውስጥና በውጭ ሐገር በሚደረጉት ፀረ ወያኔ ትግል ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ።በተለይም በማስተባበር በኬኒያ፣ በሱማሌ ፣በሰሜን አሜሪካ ጭምር በመዘዋወር በአሜሪካ ኮንግረስና ሴኔት ውስጥ ከትግል አጋሮቻቸው ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እንዳይነካ በሚደረጉት የዲጂታል ዲፕሎማሲና የጎዳና ላይ ሰልፎች በአስተባባሪነት ባከናወኑት አኩሪ ተግባር ስማቸው ይጠቀሳል፡፡
እንግዳችን ላለፉት 30 ዓመታት በቆዩባት ካናዳ ኮምፒውተር ቴክኖሎጂ እንዲሁም በፊልምና በቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ዲፕሎማ ያገኙ ሲሆን በባዮሎጂካልና በኬሚካል መሣሪያዎች ከአልበርታ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ኮር ኢትዮጵያ የተሰኘውንና በዲያስፖራው የተቋቋመውን የትግል ድርጅት ውስጥ ወሳኝ ሚና የነበራቸው እኚሁ ሰው በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የቦርድ አባልና ዋና ጸሐፊ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው ።በካናዳ የሊበራል ፓርቲ አባልና የደህንነት ተቋም ውስጥም በሙያቸው እየሠሩ ይገኛሉ ።አቶ ጌታቸው ተፈራን የዛሬው የዘመን እንግዳ ያደረግናቸው በሕይወት ተሞክሯቸውና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- የሱዳንና የሱማሌን ሠራዊቶች በማሰልጠን ከፍተኛ ሥራ መሥራትዎ ይታወቃል፤ እስቲ ስለሥራዎ በጥቂቱ ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ጌታቸው፡- በሠራዊቱ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ በመንግሥት ኃላፊነት ተሰጥቶኝ በጆን ጋራንድ የሚመራውን የሱዳን ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ሠራዊት በጋምቤላ፣ አኮቦ፣ በአሶሳ፣ ጊዘን፣ በደባዚን አሰልጥኛለሁ። በተጨማሪም የሱማሌ ብሔራዊ ንቅናቄ ኩልኒስ የሚባለውን ድርጅት ጅግጅጋ ላይ ከፍተኛ ስልጠና አድርጌ ሀገራቸውን ነፃ እንዲያወጡ እርዳታ አድርጌያለሁ። በተጨማሪም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ሱዳን ውስጥ በስለላ ሥራ ተመድቤ ኃላፊነቴን በሚገባ ተወጥቻለሁ ።በተለይም ከፍተኛ የመረጃ ምንጭ በመሆን ለመከላከያም፤ ለኢትዮጵያ ደህንነት ተቋም ከቲያ ጀምሮ እስከ ገዳሪፍ ፤ ካርቱም ሁንዱርማን ድረስ ያልሄድኩበት የሱዳን ምድር የለም ።የኢትዮጵያ ዳር ድንበሮችን በመቃኘትና ከፍተኛ የስለላ ሥራዎች በመሥራት ኢትዮጵያ ከሚደርስባት ከፍተኛ ጉዳቶች በታሪክ የተመዘገቡ ብዙ ሥራዎች ሠርቻለሁ ።
አዲስ ዘመን፡- ከሀገር የወጡበትን አጋጣሚ ምን ነበር?
አቶ ጌታቸው፡- ከሃገር የወጣሁበት ምክንያት ትሕነግ ሃገሪቱን ሲረከብና ሠራዊቱ ሲበተን ነው። በውትድርናው ዓለም ያሰለጠኑኝ መምህሮቼ ለጠላት እጅ መስጠትን አላስተማሩኝም ፤ ለባንዲራዬም ቃል የገባሁ በመሆኔ ተመልሼ መጥቼ የመዋጋት እቅድ ስለነበረኝ ነው ከሃገሬ የወጣሁት ።እናም አሁን በሕይወት ከሌሉ የትግል አጋሮቼ ጋር በመሆን ታግለን ጠላትን ድባቅ መተን ነው ወደ ሱዳን ድንበር የገባነው ።በነገራችን ላይ ወደ ሱዳን ከተጓዝነው 150 አባላት ውስጥ ሰባት ብቻ ነን በሕይወት የተረፍነው ።በሱዳን ገዳሪፍ በነበርኩበት ጊዜ በነካፒቴን ሐሰንና በኮማንደር ጣሰው በሚመራው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲ አሊያንስ የሚባል ድርጅት ስር ታቅፌ የተለያዩ ፀረ ትሕነግ ሥራዎችን አከናውኛለሁ። ይሁንና ሁኔታው ምቹ ባለመሆኑና በተለይ ደግሞ ሱዳን ውስጥ ከዚያ በፊት ሚሽን ተሰጥቶኝ በሠራሁት የስለላ ሥራ ሕይወቴ አደጋ ውስጥ ስለነበር በተለያዩ የዓለም መንግሥታት ድጋፍ በአስቸኳይ ሀገሪቷን ለቅቄ ወጣሁ ።በነገራችን ላይ ሱዳን ውስጥ የቆየሁት ዘጠኝ ወር ብቻ ነው፤ እንደነገርኩሽ በነበረኝ ሚና ምክንያት በፍጥነት እንድሄድ ነው የተደረገው ።ደግሞም ወቅቱ የመጨረሻው የገልፍ ጦርነት የተነሳበትና ሱዳን ውስጥ የነበሩ ኤምባሲዎች በሙሉ ሃገሪቱን ለቀው ወጥተው ስለነበር በተለይ ሱዳን ለኢራቅ ዋነኛ አደጋ ስለነበረች ለእኔ ቅድሚያ ተሰጥቶኝ የመጨረሻው በረራ ከአምባሳደሮች ጋር ይዘውኝ አምስተርዳም ሄድኩኝ፤ ከአምስተርዳም ወደ ካናዳ ገባሁኝ ።
አዲስ ዘመን፡- ካናዳ ከገቡም በኋላ የትሕነግን ሥርዓት ለመጣል በርካታ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል። እስቲ ይህንን ያጫውቱን?
አቶ ጌታቸው፡- ልክ ነሽ፤ ከሃገሬ ብወጣም ትግሌን አላቆምኩም ነበር ።በመሠረቱ እኔ ከሱዳን ራሱ መውጣት አልፈለኩም ነበር ።ምክንያቱም ተመልሼ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኅብረት (ኢዲዩ) ከሚባለው ድርጅት ጋር በመሆን ትሕነግን መዋጋት ነበር እቅዴ ።ደግሞም የሕክምና ባለሙያም ስለነበርኩኝ ለኢዲዩ አባላት በሕክምና አገለግላቸው ነበር። እንደገና ወደ ሱዳን ተመልሼ ውጊያ ጀምሬም ነበር ።ሆኖም በወቅቱ ሁኔታው ጥሩ ስላልነበር ዛሬ በሕይወት የሌሉት አንዳንድ ሰዎች ከሃገር ብወጣና ወደፊት ተመልሼ ብመጣ ሃገሬን እንደምጠቅም ስለሚያውቁ እንድወጣ አደረጉኝ ። እንደወጣሁም በመጀመሪያ ትግል የጀመርኩት በኮሎኔል ጎሹ ይመራ በነበረው የመድህን የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ነው፡፡
በዚህ የፖለቲካ ድርጅት አማካኝነት እዚህ ድረስ በመምጣት ታጋዮችን አደራጅ ነበር ።ለምሳሌ በቴፒ፣ በሚዛን ተፈሪ፣ ከአማን እስከ ጎንደር ጭልጋ ድረስ እየሄድኩኝ አንዳንድ የሚያስፈልጉ ዋና ዋና ወታደራዊ ስትራቴጂ ቦታዎችን ካርታዎች በማውጣት አቀርብ ነበር። በመቀጠልም ከዚያ ድርጅት በመውጣት ከጀነራል ሃይሌ መለሰ ጋር በመሆን በተለያዩ ዘመቻዎችና ኦፕሬሽኖች ውስጥ በመርዳት እገዛ አደርግ ነበር ።ከዚያም በኢንጂነር ዶክተር ቅጣው እጅጉ ይመራ በነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አርበኞች ግንባር ውስጥ ነው የገባሁት። በተለይም የኢንጂነር ቅጣው የቅርብ አማካሪ ሆኜ ስሠራ ነበር ።በተለይ በወታደራዊና በኢንተለጀንሲ አማካሪ በመሆን በኬኒያ፤ በኡጋንዳና በኢትዮጵያ መሬት የወረደ ሥራ ሠርቻለሁ ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ አርበኞች ግንባር ውስጥም ታጋዮችን በማደራጀትና የተለያዩ ዝግጅቶች በማድረግ ሥርዓቱን ለመገልበጥ ጥረት ስናደርግ ነበር ።በአጠቃላይ አሁን ልገልፅልሽ የማልችላቸው ወታደራዊ ተግባሮችን ፈፅመናል፤ ብዙ ውጤቶችንም አምጥተናል ።በዚያ ወቅት ኬኒያ ድረስ እየመጣሁ ኮማንደር አበረ አዳሙ ጋር ትግሉን በሚመለከት ግንኙነት እናደርግ ነበር። በመሠረቱ ኮማንደር አበረን ከኤርትራ ያስፈታነው እኛ ነን። እሱን ጨምሮ ብዙ ወታደሮች አስፈትተናል ።የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኬኒያ በተጉላሉበት ጊዜ የመጀመሪያውን የገንዘብ፣ መድኃኒትና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ከካናዳ ይዤ የመጣሁት እኔ ነኝ ።እንዳልኩሽ የሙዚቃ ባለሙያዎችን በማስተባበር የተሰባሰበውን መዋጮ የድርጅቱ ተጠሪ ከነበሩት ከአቶ መላኩ ስዩም ጋር በመሆን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይዘን መጥተናል ።ለኮማንደር አበረ ደግሞ ለአርበኞቹ ግንባር የሚያስፈልገውን የሳተላይት መሣሪያዎች ከተለያዩ የውጭ ድርጅቶች ጋር በመሆን አሟልተን ትግላችን በሚገባ ቀጥለናል ።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ድረስ በመምጣት በድፍረት የነበረውን ሥርዓት ለመገልበጥ ኅቡዕ ወታደራዊ ድርጅት በማቋቋም ሂደት ያጋጠመዎት አደጋ እንደነበር ሰምተናል ።እስቲ ስለዚህ አደጋ ይንገሩን?
አቶ ጌታቸው፡- እውነት ነው፤ በርካታ ችግሮች አጋጥመውኝ ነበር፤ እስር ቤቶችም ገብቼ የወጣሁበት አጋጣሚ አለ። ትልቁና ከፍተኛ የሚባለው አደጋ ግን ዋቢሸበሌ ሆቴል ከተሰበሰብን በኋላ በምግብ አድርገው እንድመረዝ አድርገውኝ የነበረበት ጊዜ ነው ።በአስቸኳይ በኬኒያ አየር መንገድ በኩል በቀጥታ ናይሮቢ በመሄድ ቀጥሎም አምስተርዳም ከገባሁ በኋላ ካናዳ ደርሼ ሕክምና የተደረገልኝ ።በዚያ አደጋ ምክንያት ልቤ ክፉኛ የተጎዳ ሲሆን ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ያህል እግሮቼ ሽባ (ፓራላይዝ) ሆነው ነበር ።ልቤን እዛው ካናዳ ታክሜ ብድንም እግሬ መዳን ባለመቻሉ እዚህ መጥቼ በፀበል ነው የተፈወስኩት ።ከተመረዝኩኝ በኋላ እስትሮክ(ድንገተኛ የአንጎል ደም መፍሰስ)እንኳን አራት ጊዜ አጋጥሞኝ ነበር ።ይህ ሊሆን የቻለውም የሰጡኝ መርዝ በጣም አደገኛ ስለነበር ነው፡፡
በነገራችን ላይ ይህ መርዝ ስሪቱ ከቻይና የሆነ ነው፤ ይህንን መረጃ እስካሁን ይፋ ሳይደረግ የቆየው የካናዳ መንግሥት የሕክምና ሕግ መሠረት ከእኔ በስተቀር መረጃውን ማስተላለፍ ስለማይቻል ነው ።ይህ ቢሆን ኖሮ ስልጣን ላይ የነበረውን የትሕነግን መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ መክሰስ የሚቻልበት እድል ነበር ። በመሠረቱ እኔ ብቻ ሳልሆን በርካታ የኢትዮጵያ ምሑራንና ፖለቲከኞች በእስር ቤት የነበሩ ዜጎች ይመረዙ የነበሩት ከውጪ በሚመጣ አደገኛ መርዝ አማካኝነት ነው። እነዚህ የመርዝ አይነቶች በምግብ መልኩ የሚሰጡ ሲሆኑ አዕምሮንም ሆነ ሌሎች የሰውነት አካላትን ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጭ የሚያደርጉ ናቸው ።ለዚህም ነው አብዛኞቹ የሃገራችን ፖለቲከኞች ይህንን መርዝ ተቀብለው ወጥተው ፈዘውና የተለያዩ አካል ጉዳተኛ ሆነው የሚቀሩት ።እኔ ግን በፈጣሪ እርዳታ የካናዳ መንግሥት በልቤ በኩል የሚደረገውን ሕክምና ካደረገልኝ በኋላ እግርና እጄን እዚህ መጥቼ ዳንኩ ።በአሁኑ ሰዓት እስትሮክ የሚባል ነገር የለብኝም፤ መላው ሰውነቴ ጤነኛ በመሆኑ እንዳሻኝ እንቀሳቀሳለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡-ከነኢንጂነር ዶክተር ቅጣው ጋር በሚታገሉበት ጊዜ የነበረውን ሥርዓት ለመጣል ነድፋችሁት የነበረው ስትራቴጂ ምን ነበር?
አቶ ጌታቸው፡- እንደሚታወቀው ኢንጅነር ዶክተር ቅጣው ኢትዮጵያ ካጣቻቸው ትላልቅ ሰዎች ዋነኛው ናቸው ።በእሱ ይመራ የነበረው የፖለቲካ ድርጅትም ሃገሪቱን ከፅንፈኛው ትሕነግ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት የሚያስችል በኢኮኖሚ ከፍተኛ ደረጃ የሚያደርስ ስትራቴጂ ነድፎ ነበር ።በነገራችን ላይ በስትራቴጂ ደረጃ ከማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት ቀድሞ የፖለቲካ ፕሮግራም የነበረው ድርጅት ነው ።እንዳልኩሽ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚ እንዲሁም ይህ ብቻ ሳይሆን የመከላከያን ስትራቴጂም ነድፈናል።በተለይም የመከላከያን አቅም ለማሳደግ በተነደፈው ስትራቴጂ በአየር ኃይልም ሆነ በእግረኛና በመካናይዝድ አቅም ሠራዊቱን ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ ያለመ ነበር። ሳውዲዓረቢያን ጨምሮ ኢትዮጵያ ላይ በጠላትነት ከተፈረጁ እነግብፅንም ሳይቀር መቆጣጠር የሚያስችል በቴክኖሎጂ የታነፀ ተቋም ለመገንባት አቅደንም ነበር ።
የሚገርምሽ በዚያ ጊዜ አሁን እየሠሩ ያሉትን የሳይበር ቴክኖሎጂ ሳይቀር ለመገንባት ስትራቴጂ ቀርፀን ነበር። አሁን ላይ እነዶክተር ዐቢይ የሚሠሩትን ነገር ስመለከት በእውነት ነው የምልሽ ቅጣው ቢሞት ዐቢይ ተተክቷል ብዬ እንድፅናና አድርጎኛል ።ኢንጅነር ቅጣው አስቧቸው ከነበሩት ሥራዎች መካከል ከፊሎቹ አሁን በአዲሱ ኃይል እየተሠራ መሆኑ በራሱ ትልቅ ደስታ ፈጥሮብኛል። ሰሞኑን የተመረቀውን የሳይንስ ሙዚየም ስመለከት በቀጥታ ኢንጅነር ቅጣው ፔንታጎን ውስጥ ያደርገው የነበረውን ገለፃ አይነት ያህል ነው የተሰማኝ ።
እንዳልኩሽ ትልልቅ ስትራቴጂዎችን ብንነድፍም ወደመሬት ማውረድ አልቻልንም ነበር ።ምክንያቱም ደግሞ በዚያ ወቅት ይደግፉን የነበሩት ምዕራባውያን እዚህ ያሉትን የፖለቲካ ድርጅቶች ወደአንድ በማምጣት እንድናደራጅ ጠይቀውን እኛም ይህንን ማድረግ ስለተሳነን ነው ።የነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች አብዛኞቹ ስልጣን ብቻ ናፋቂዎች በመሆናቸው እንደታሰበው አንድነቱን ማምጣት አልተቻለም ። እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ቤተ-መንግሥት መግባት እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይታያቸውም ነበር ።ሕዝብ ተኮር ቢሆኑና ወደአንድነት ቢመጡ ኖሮ ትልቅ ውጤት እናመጣ ነበር። ያ ቢሆን ኖሮ የእኛ ስትራቴጂ እንደታሰበውም ወያኔን ከመሠረቱ የሚጥል ነበር ።በወቅቱ ከከፍተኛ የአውሮፓ ማኅበረሰብ፤ ከአሜሪካ ኮንግረስ አባላት በመነጋገር የተለያዩ ድጋፎች ለማድረግ ፍቃዳቸውን አሳውቀውን የነበረ ቢሆንም የፖለቲካ ድርጅቶቻችን ወደአንድ ስላልመጡ እቅዱ ሳይሳካ ቀረ ።
አዲስ ዘመን፡- የትግላችሁ ውጤት የሆነው ለውጥ ከመጣ በኋላ ከስልጣን የተወገደው የት ሕነግ ኃይል አሁንም ሃገሪቱን በጦርነት ውስጥ እንድትዘፈቅ ማድረጉ ሲያስቡ ምን ይሰማዎታል? ይህን ጽንፈኛ ኃይል ለማስወገድስ ምን መሠራት አለበት ብለው ያምናሉ?
አቶ ጌታቸው፡- ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 27 ዓመታትም በሃገሪቱ ላይ ምስቅልቅል ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ተደርጓል። በተለይ በትሕነግ መራሹ መንግሥት ትውልድንና ሃገርን ከመገንባት ይልቅ ወደማፍረስ ተግባር ነው የተሄደው ።አንድ ብሔር ወይም ቋንቋን እያገነኑ ኢትዮጵያን ወደ መበታተንና ወደራሳቸው ጥቅም የሚሄዱበትና ሃገሪቷን ለምዕራባውያንና ለጠላቶች ከፍተው ሰጥተው ነበር ።እርግጥ ነው፤ እኛ ስር-ነቀል ለውጥ የምንሻ የነበረው ይሄ ጦርነት እንደሚመጣ አስቀድመንም እናውቀው ስለነበረ ነው ።ትሕነጎች ለኢትዮጵያ ምንግዜም እንደማይተኙ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ አለበት ።እኛ አሁን ትሕነግ ኢትዮጵያ ላይ የፈፀመውን በደል አስቀድመን እንደሚመጣ ስለተረዳን ነው ከመሠረቱ መጥፋት አለበት ብለን ተነስተን የነበረው።
በመሠረቱ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በነበርንበትም ወቅት ጦርነቶች ነበሩ ። በተለይም በምዕራብ ኢትዮጵያ ወለጋ አካባቢ አሁን እንደሚታየው አይነት እንቅስቃሴዎች ነበሩ ።ይሁንና እነዛን ጦርነቶች የምናከሽፋቸው እዛው አካባቢ ያለውን ኅብረተሰብ በሚሊሻ በማሰልጠን ነው ። መከላከያ ምዕራብ ዕዝ ቢኖርም ጦርነቱ ውስጥ የሚገባው በጣም ከባድና ከሕዝቡ አቅም በላይ ሲሆን ብቻ ነበር። ምክንያቱም ከባድ ካልሆነ በስተቀር እንደ አሊ በርኬ ያሉ ጀግናዎች ናቸው ሚሊሻውን እያንቀሳቀሱ ጠላትን የሚመክቱት። አሁንም መሥራት የሚገባን በኅብረተሰቡ ላይ ነው ። ኅብረተሰቡን ማንቃት፣ ማስተማር አለብን።ትሕነግን ከነጭራሹ በማጥፋቱ ሂደት የምክር ቤት አባላት፣ ሚኒስትሮች የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች በሙሉ ዶክተር ዐቢይን ማገዝ አለባቸው ።በተለይ የሕዝቡን የልብ ትርታ በማድመጥ መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ሌት ተቀን መሥራት ይገባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን:- በተለያየ ጊዜ መንግሥትንና ትሕነግን ለማደራደር ሲደረግ የነበረው ጥረት በአሸባሪው ቡድን ቅድመ ሁኔታዎችን የመደርደርና የሰላምን በሮች የመዝጋት ሁኔታ ይስተዋላል። አሁንም በአፍሪካ ኅብረት አማካኝነት ለማካሄድ የታሰበው ድርድር ይሳካል ብለው ያምናሉ?
አቶ ጌታቸው፡- ከዚህ በፊት ትሕነግ ደብረብርሃንና ሰላ ድንጋይ ሲደርስ ያንን ሁሉ የአማራና የአፋርን ሕዝብ ጨፍጭፎና ደፍሮ ሳለ ለምን ምዕራባውያኑም ሌላው አካል ተደራደሩ አላሉም? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው የሚል እምነት አለኝ ።ታስታውሺ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦር ሜዳ እስኪዘምቱ ድረስ የትኛውም አካል ተደራደሩ አላለንም ። ምዕራባውያኑ መከላከያ ሠራዊታችን ትሕነግን ድባቅ ሲመታው ጠብቀው ተደራደሩ የሚሉት ለምን እንደሆነ ማጤን ተገቢ ነው ።በእኔ እምነት ከዚህ በኋላ የውጭ ኃይሎች በእኛ ላይ ሊጫወቱና እንዳሻቸው ሊዘውሩን አይገባም ።ምናልባት የኢትዮጵያን ደህንነት አይተው ሊመጡብን ይችላሉ፤ ግን ኢትዮጵያ ከኒውክሌር የበለጠ ስውር ኃይል አላት ።የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጀግና ነው ።ፈጣሪ ራሱ ለኢትዮጵያ የገባው ቃል በመኖሩ ለጠላቶቿ አሳልፎ ይሰጣታል ብዬ አላምንም፤ በመሆኑም ሃገርን ለመበተን የሚሠራውን ይህንን ጽንፈኛ ቡድን እስከወዲያኛው ለማጥፋትም በህብረት ልንታገል ይገባል ባይ ነኝ ።
በእርግጥ እርቅ ጥሩ ነው፤ በበኩሌ ግን ከወያኔ ጋር የሚደረግን እርቅ አልደግፈውም ።ደግሞም እርቅ ላይ የምትቀርቢው እኮ የሚቀበልሽ አካል ሲኖር ነው ።ትሕነግ ጭንቅላቱ ለፍቅርም ሆነ ለእርቅ የተዘጋ ነው ።መቀበልም መስጠትም አይችሉም ።ደግሞም እነዚህ ሰዎች ምን ያህል የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንዳወደሙ መገንዘብ ይገባናል ።ለዓመታት የፈፀሙት በደል እያለ ሕዝቡ ምህረት ቢያደርግላቸውም በደሃ ሕዝብ መዋጮ የተገዛውን የጦር መሣሪያ በመጠቀም ኢትዮጵያን ወግተው ዛሬ በ10 እና 20 ዓመታት ሊገነቡ የማይችሉ ትምህርት ቤቶችን እና የሃይማኖት ተቋማትን አፍርሰው ሄደዋል ።
ለሞቱት ማነው ተጠሪ? በትግራይ ላለቀው ያ ሁሉ ወጣት ተጠያቂው ማነው? እርግጥ የውጭ ኃይሎች ሁልጊዜም ቢሆን የሕዝብ ቁጥር እንዲቀንስ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዳያድግ ነው የሚሠሩት ።በዚህ አካባቢው ያሉ ሃገራትም ስልጣኔ ያለው እዚህ ስለሆነ የኢትዮጵያን እድገት አይፈልጉትም ።ምክንያቱም በኢትዮጵያ የተደበቁ ሚስጥሮች በመኖራቸው ነገ የዓለም የበላይ ይሆናሉ የሚል ስጋት ስላለባቸው ነው ። በአጠቃላይ አሁን ተደራደሩ የሚሉን አካላት በእርግጥ ለእኛ አስበው ስለመሆኑ መመርመር አለብን ። እኔ ግን ጥርጣሬው አለኝ ።
አዲስ ዘመን:- እንደዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት አባልነትዎ ምክር ቤቱ የሃገርን ገፅታ በመገንባትና በዲፕሎማሲው መስክ ምን ያህል ሚናውን ተወጥቷል ብለው ያምናሉ?
አቶ ጌታቸው፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እናደርጋለን ።ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ የአሜሪካ ኮንግረሶችን በማነጋገር ከከፍተኛ ባለስልጣኖችም ጋር ብዙ ሥራ ሠርተናል ።የተለያዩ መርሐ ግብሮች ሲዘጋጁ አቅም ለሌላቸው ዜጎች አስፈላጊ ድጋፍ አድርገናል። በተለይ በካናዳ በመንግሥት ደረጃ ያሉ ሰዎችን በመጠቀም ስለሃገራችን እውነታ እንዲገነዘቡ ጥረት ሳደርግ ነበር ።ሰልፍ ሲደረግም የትራንስፖርት ኩባንያ ስላለኝ ለሰልፈኞቹ የትራንስፖርት አገልግሎት በነፃ እሰጣለሁ ።በሌሎችም መድረኮች ዲፕሎማሲያዊ ትግሎችን እናደርጋለን ።አሁንም የተግባር ምክር ቤቱ ደብዳቤዎችን በመጻፍ፣ በተለያዩ የዓለም ብዙኃን መገናኛዎች በመቅረብ ስለኢትዮጵያ ትክክለኛ ገጽታ ያደረጋል ።የራሺያ መንግሥትም ኢትዮጵያን እንዲረዳት ከውጭ ሆነን ግፊት እናደርጋለን፣ በተዘዋዋሪ መንገድ ባሉ ጠበብቶች ሁሉ የእኛ እጅ አለበት ።እዚህም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሌሎቹ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ ከጀርባ ሆነን ያለውን ውስጣዊ አሠራር እናከናውናለን፡፡
አዲስ ዘመን:- ዲያስፖራው ሃገርን በማሳደግ ረገድ ምንዓይነት ሚና ሊኖረው ይገባል ይላሉ?
አቶ ጌታቸው፡- በተግባር ምክር ቤቱ ያሰብነው ሦስት መሠረታዊ ነገሮች አሉ ።ለምሳሌ በልማት ላይ እንደዜጋና አገራዊ ተሳትፎ ለማድረግ ዲያስፖራው በአገር ቤት ኢንቨስት እንዲያደርግ የተለያዩ ነገሮችን እናመቻቻለን ።የውጭ ዜጎችንም ጭምር እናበረታታለን። የገጽታ ግንባታም ሥራም በስፋት እንሠራለን ።በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ግለሰቦችና ጠላቶቻችን ሳይሆን ኢትዮጵያ ሃገራችን ለኢንቨስትመንትም ሆነ ለቱሪዝም አመቺ ሁኔታዎች አሏት ።በተለይ በዶክተር ዐቢይ እየተሠሩ ያሉ ፕሮጀክቶች ሁላችንንም ሃገራችን ላይ መዋለ ንዋያችንን እንድናፈስ የሚያግዙ ናቸው ።በግሌ ለዓለም አቀፍ ዲያስፖራዎች መናገር የምፈልገው ውጭ ሆኖ ከማየት ውስጥ ገብቶ ሃሳብ መስጠትና መደገፍ እንደሚገባቸው ነው ። ከሚሰሙት ነገር ብቻ ተነስቶ ክፉ ከመናገር ይልቅ መልካም ነገር አይቶ መልካም መናገርና ኅብረተሰብ ማሳደግ ያስፈልጋል ።ሃገር ሃገር ናት፤ አትለወጥም ።ዶክተር ዐቢይ የሚሠራው ለሀገር ነው፤ ለማንም አይሠራም ።ጊዜውን ሲጨርስ ይሄዳል ደግሞ ሌላ መሪ ይተካል፡፡ይህንን መገንዘብ ይገባል ።
አዲስ ዘመን:- በቅርቡ የተመድ የሰብዓዊ መብትን አስመልክቶ ያወጣውን ሪፖርት ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?
አቶ ጌታቸው፡- በአጠቃላይ በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ለመሥራት የተቋቋሙ የውጭ ድርጅቶች አድሏዊ ናቸው። ሪፖርቱ በእኔ በኩል ተቀባይነት የለውም ።የተግባር ምክር ቤቱም አይቀበለውም ። ከ1945 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቋቋሙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጨምሮ ማንኛውም ድርጅት ኢትዮጵያ ላይ አድልዎ ያደርጋሉ ።ሁሌም የኢትዮጵያን መከላከያ ይወነጅላሉ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በዓለም በስነ-ምግባርና በብቃት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከሚቀመጡ ዋነኛው ነው። ደግሞስ የትግራይ ሕዝብን ለመጠበቅ ላለፉት 20 ዓመታት ልጁን፣ ቤቱንና ንብረቱን ጥሎ የሄደ ሠራዊት መሆኑን እንዴት ይዘነጋል? ።እነሱ እንደሚሉት ወንጀለኛ ከሆነ የሚማረኩትን የሚያበላው፣ የሚያጠጣው ለምንድን ነው? ።መቀሌ ለመግባት ያልፈለገው ሕዝብን ከአደጋ ለማዳን እንደሆነ ግልፅ ነው ።ኮንጎም ሆነ ኮሪያ ዘምተናል በዲሲፕሊናችንም በጀግንነታችንም የታወቅን ነን፤ አሁንም ድረስ ኮሪያ ውስጥ ሠራዊታችን የሚነሳው በመልካም ዝናው ነው ።በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን ሄዶ አገልግሏል ።ከአለባበስ ጀምሩ ጥሩ ዝና ስነ ምግባር አለው።
ተመድም ሆነ ሌሎች የምዕራብ ሃገራት እውነት ለፍትሕ የሚጨነቁ ከሆነ ለምን የታረደውን፣ የተረገጠውንና ታንክ የሄደበትን ሠራዊት፣ በአንድ ቤት የተቃጠለውን ሬሳ ለምን አልዘገቡትም? ።የሰብዓዊ መብትስ ድርጅቶቹ ያንን የአፋር ሕዝብ፣ የተጎዱ ልጆች፣ ሕጻናት አስከሬን ጡት ሲጠቡ የታየበትን ለምንድን ለተባበሩት መንግሥታት ያላቀረቡት? ።የአማራ ሕዝብ በማይፀብሪ፣ በጠለምት፣ በጭልጋ፣ በዳባት፣ በደባርቅና በተለያዩ ቦታዎች የሞተውን በፎቶ ግራፍ አስደግፈው ለምን አያቀርቡም? ።ይህንን ነው ሁላችንም መመርመርና መጠየቅ የሚገባን ።እርግጥ ጦርነት ላይ ትንሽ ስህተት ሊኖር ይችላል ። ደግሞም ሰው መርጦ አይመታም ።ማንኛውም አካል ጦር ሜዳ እስከተገባ ድረስ የማይመታበት ምንም ምክንያት የለም ።ምክንያቱም ሌላውም አካል ቢሆን ለመግደል ነዋ የሚመጣው ።እኔስ ብሆን ሊገለኝ እየመጣ ዝም እላለሁ እንዴ? ።ይሁንና ከሰብዓዊ ጥሰት፣ ሴት መድፈር፣ አልባሌ ነገር መፍጠርና መሰል ተግባራት ጋር ተያይዞ የቀረበበት ክስ ፈፅሞ የመከላከያ ሠራዊታችንን የሚመጥን አይደለም ። በኢትዮጵያ ታሪክ ሠራዊቱ አድርጎት አያውቅም ወደፊትም አያደርግም ።በአጠቃላይ በሰብዓዊ መብት ድርጅቱ የቀረበው ሪፖርት ፈፅሞ ከእውነት የራቀና ማንም ሊቀበለው የማይችል ነው ።
አዲስ ዘመን፤ ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎችና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ጌታቸው፡- እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/ 2015 ዓ.ም