አምራች፣ አዘዋዋሪና ላኪዎችን (ኤክስፖርተር) በአንድነት አጣምሮ የሚይዘው የጌጣጌጥ ማዕድን ዘርፍ ሰፊ ቁጥር ያለው ኃይል በማሳተፍ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው። በዚህ ረገድ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ለዓለም ገበያ ቀርቦ የሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከፍ ያለ ድርሻ ያለው ነው ።
በዓለም ገበያ ላይ በህብረ ቀለማቸው ተፈላጊና በዋጋቸውም ውድ ከሆኑት የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት መካከልም ኦፓል፣ ኤመራልድ፣ ሳፋየር በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ ።የእጅ ጥበበኞች ደግሞ በቅርጽ ማውጫና በተለያየ የመስሪያ ማሽን በመታገዝ አስውበዋቸው ለጣት ቀለበት፣ለአንገት ሀብል፣ ለጆሮ ጉትቻ፣ ለእጅ አምባር፣ ለእግር አልቦ ጌጣጌጥ እንዲውል በማድረግ አገልግሎታቸውና ጥቅማቸው ከፍ እንዲል ያደርጓቸዋል። እሴት ተጨምሮበት ለገበያ ሲቀርብ ዋጋቸውም የበለጠ ከፍ ስለሚል የሚገኘው ገቢም እንዲሁ ይጨምራል፡፡
ኢትዮጵያ የምድር ውስጥ ፀጋ የሆኑ ከላይ ያነሳናቸው ማእድናት ሀብቶች ባለቤት ነች። አገሪቱ ከዘርፉ እየተጠቀመች ቢሆንም በሚፈለገው ያህል የውጭ ምንዛሪ ገቢ እያገኘችበት እንዳልሆነም ግን የዘርፉ ባለሙያዎች ደጋግመው ያነሳሉ ።በዘርፉ በተለያየ የሥራ መስክ ከተሰማሩት በሀብት የበለፀጉት ጥቂት ብቻ እንደሆኑ ይነገራል ።ማዕድን ለማልማት በምርት ሂደት ወቅት በሚፈጠር የጥራት መጓደል፣ ህገወጥ ግብይት፣ በገበያ ላይ የመደራደር አቅም ውስኑነት፣በጠንካራ የቁጥጥርና ክትትል ሥርአት አለመመራት ከምክንያቶቹ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ዘርፉ ለሙስና የተጋለጠ መሆኑ ሌላው ተግዳሮት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ ።በጥብቅ የቁጥጥርና ክትትል ሥርዓት ካልተመራ ተጋላጭነቱን መቀነስም ሆነ ማስቀረት አይቻልም፡፡በዚህ ረገድ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ።እየሰራም ይገኛል ።ይህም ሆኖ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችንና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ አልተቻለም ።ለውጥ እስኪመጣ ጥረቶችን አጠናክሮ መቀጠል ግድ ሆኗል ።
የጌጣጌጥ ማዕድናት ግብይትን በተመለከተ የማዕድን ዘርፉን የሚመራው ማዕድን ሚኒስቴር ከዛሬ ሶስት ወር በፊት የማሻሻያ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል ።ማሻሻያው በኦፓል፣ሳፋየርና ኤመራልድ የጌጣጌጥ ማዕድናት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። በእነዚህ ዘርፎች የግብይት ሰንሰለትን ለማቃለልና ሀገርም ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ገቢ እንድታገኝ ያለመ ነው። ቀደም ሲል በሥራ ላይ የነበረውን በመንግሥት የወጣ ወይንም የተቀመጠ የመሸጫ ዋጋ ተመንና ደረጃ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ መስፈርቶች ተነስተዋል። ይህንን አስመልክቶ የንግድ ሥርአቱ በገበያ ብቻ የተመራ እንዲሆን መወሰኑን፣ ውሳኔው በአዋጅና መመሪያ የተደገፈ ስለመሆኑ በዚሁ አምዳችን ላይ ማቅረባችን የሚታወስ ነው ።
በማሻሻያው ውስጥ ከተካተተው መካከል ደረሰኝ አለመጠየቅ አንዱ ሲሆን፣ሌላው የማሻሻያ እርምጃ የይለፍ ሰነድ ደብዳቤ መያዝን ያስቀረ ነው። የማዕድን ሚኒስቴር ባለሙያዎች (ኤክስፖርተሮች) ልየታ አድርገውበት የዋጋ ውሳኔ ይሰጡበት የነበረውን አሰራርንም አስቀርቷል ።ላኪው (ኤክስፖርተሩ) ቀደም ሲል በነበሩ አሰራሮች ውስጥ ሳያልፍ ግብይቱን እንዲያካሂድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ መተማመን ላይ የተመሰረተ ግብይት እንዲካሄድ ያስቻለ ነበር ።በወቅቱም ይህንኑ መሠረት በማድረግ አንዳንድ ላኪዎችን አነጋግረን በማሻሻያ ውሳኔው መሠረት ላኪው የሸጠበትን ትክክለኛ ዋጋ ካልገለፀ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚያውቅበት መንገድ እንደሌለና ይህም ሀገርን ተጠቃሚ እንደማያደርግ ነበር ሃሳብ የሰጡት፡፡
የማሻሻያ እርምጃው ከተወሰደ ከሶስት ወር በኋላ ግን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አሰራሩን በመፈተሽ ግብይቱ በተደረገው ማሻሻያ መሠረት እንዲቀጥል ሳይሆን፣ከማሻሻያው በፊት ይከናወን በነበረው የግብይት ሥርአት የመሸጫ መነሻ ዋጋ እንዲቀመጥ ክለሳ አድርጓል፡፡ሚኒስቴሩ ይህንኑ ውሳኔውን ከነምክንያቶቹ ሰሞኑን በዘርፉ ላይ በተለያየ ሥራ ከተሰማሩትና ዘርፉን ለሚመሩት የክልል የሥራ ኃላፊዎች ለውይይት በማቅረብ ምክክር አድርጓል፡፡ሚኒስቴሩ እንደገለጸው፤ በሶስት ወራት የማሻሻያ ጊዜያቶች ውስጥ በተከናወነው ሥራ መልካም የሚባሉ ጥሩ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ትልቁ ውጤት የሆነው ገቢን ማሳደግ ወይንም ከፍ ማድረግ ላይ ግን ድክመት ታይቷል ።እንደገና መከለስ ያስፈለገውም በዚህና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ነው። በማሻሻያው ጊዜያቶች ከፍተኛ መጠን ያላቸው የኦፓል፣ሳፋየርና ኤመራልድ የማዕድን ጌጣጌጦች ለዓለም ገበያ ቀርበዋል ።በዚህ ወቅት የላኪዎች ቁጥርም ጨምሯል ።አሜሪካን፣ታይላንድ ሀገሮችን ጨምሮ የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋትም ተችሏል ።እንዲህ ያሉ መልካም ውጤቶች ቢመዘገቡም ከሽያጩ የተገኘው ገቢ ግን በዚህ ልክ አልሆነም ። ያለመጣጣም ክፍተት ተፈጥሯል።መነሻ የመሸጫ ዋጋ አለመኖር ወይንም አለመቀመጡ የፈጠረው ችግር እንደሆነም በሚኒስቴሩ ጠቅሷል። ይህን ክፍተት ለመሙላትም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያወጣውን የመሸጫ መነሻ ዋጋ ለውይይት አቅርቧል፡፡በገበያ የመወዳደር አቅም አለመፈጠሩንም በሌላ በኩል ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዳግም በከለሰው የማዕድን ጌጣጌጦች ግብይት ኦፓል በኪሎ ግራም 150 ዶላር፣ ሰሜን ሸዋ ራፍ ኦፓል በኪሎ ግራም 50 ዶላር፣ ክሪስታል ኦፓል በኪሎ ግራም 80 ዶላር፣ ፖሊሽ ኦፓል በኪሎ ግራም 1000 ዶላር፣ ራፍ ኤመራልድ በኪሎ ግራም 1000 ዶላር፣ ራፍ ሳፋየር በኪሎ ግራም 1000 ዶላር በሚል ያስቀመጠውን መነሻ የመሸጫ ዋጋ ለውይይት አቅርቧል ።በሚኒስቴሩ የቀረበውን መነሻ መሸጫ ዋጋ ጥቂት የሆኑት የውይይቱ ተሳታፊዎች ቢቀበሉትም ጠንካራ የመከራከሪያ ሃሳብ ባቀረቡ የውይይቱ አንዳንድ ተሳታፊዎች እንደገና እንዲታይ ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በኤመራልድ፣ በሳፋየርና በኦፓል የማዕድን ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ፈቃደኛ የሆኑ ላኪዎች ከሚኒስቴሩ ጋር በመሥራት የጋራ የሆነ የመነሻ ዋጋ እንዲወጣ በማድረግ ከየዘርፉ ፈቃደኞች እንዲመረጡ አድርገዋል ።የተመረጡት ላኪዎችም ውይይቱ በተደረገ ማግስት ጠዋት በሚኒስቴሩ እንዲገኙ ጥሪ አድርገውላቸዋል፡፡በጥሪው መሠረት ተገኝተው ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ ግን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያስቀመጠው መነሻ የመሸጫ ዋጋ ተግባራዊ እንደሚሆን ነግረዋቸዋል፡፡
በዕለቱም የመነሻ የመሸጫ ዋጋ ማሻሻያውን በተመለከተ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በጋራ ለመወሰን ያቀረበውን ጥያቄ ፍቃደኛ ሆነው ከተቀበሉት መካከል አቶ ዓለምነህ የሻነህ አንዱ ነበሩ ።አቶ ዓለምነህ የጌጣጌጥ ማዕድን ለውጭ ገበያ በማቅረብ በሥራው ላይ የቆዩ ኤ ዋይ ኤስ ኤስ ፕሪሺየስ ስቶን ኤንድ ጁለሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤት ናቸው ።አቶ ዓለምነህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዳግም የማሻሻያ እርምጃ ለማድረግ ስለተገደደበት ጉዳይና በማሻሻያ ትግበራው ወቅት ማን ተጠቀመ? ማንስ ተጎዳ? ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ቀድሞውኑ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወሰደው የማሻሻያ እርምጃ በጥናት የተደገፈ ውሳኔ እንዳልነበር ተሰምቷቸው ነበር ።ቅሬታም ነበራቸው ።ዳግም ክለሳ እንደሚደረግም ጠብቀው ነበር ።እርሳቸው ከማሻሻያው በፊት የነበረውን የግብይት ሥርአት ነበር የሚደግፉት ።ማዕድናቱ ለገበያ ከመቅረባቸው በፊት በኦፓል የማዕድን አይነት ብቻ ወደ ስድስት አይነት ደረጃዎች ወጥቶላቸው፣ መነሻ የመሸጫ ዋጋም ተቆርጦላቸው ነበር የሚሸጡት ።በዚህ የግብይት ሥርዓት ላኪውና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አንዳንድ ባለሙያዎች ከማዕድናት ደረጃ አወጣጥ ጋር በተያያዘ በስምምነት እንዲሰሩ እድል ፈጥሯል።ለሙስና መንገድ ከፍቷል በሚል እሳቤ ይህን ለማስቀረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማሻሻያ እርምጃ ለመውሰድ እንደተገደደ ነው ከውሳኔው የተገነዘቡት ።
አቶ ዓለምነህ የሚኒስቴሩን ሥጋት ይጋራሉ። ለሙስና መንገድ አይከፍትም ብለውም አልተከራከሩም። ከማሻሻያው በፊት የነበረው ገበያ የአንድ ኪሎ ግራም የኦፓል ማዕድን ዋጋ 200 ዶላር ነበር ።ይህ ትልቅ ዋጋ ነበር። በርግጥ የገበያ መነሻ ዋጋውን መሠረት አድርጎ ሲሸጥ የነበረው ህግን ተከትሎ ከማይሰራው ጋር ተጠቃሚነቱ ሲነጻፀር ላኪውንም ሀገርንም ተጠቃሚ ያደረገ አልነበረም ።ይህንንም ለማስቀረት ነበር ሚኒስቴሩ ማሻሻያ ለማድረግ የተገደደው ።ይሁን አንጂ የተሻለ ነው ተብሎ በሚኒስቴሩ የተወሰነው የማሻሻያ እርምጃ ከሀገር ተጠቃሚነት አንጻር ከፍተኛ ጉዳት ነው ያስከተለው። ገዥዎች የፈለጉትን ዋጋ እንዲወስኑ በማድረጉና ከላኪውም በሀገር ደረጃ የተቀመጠ የመሸጫ መነሻ ዋጋ ባለመኖሩ ለመከራከር እድል የለውም ።ላኪው የተሻለ ገበያም ቢያገኝ ግልጽ ሆኖ የሸጠበትን ዋጋ ማሳወቅ በእርሱ በጎፈቃደኝነት ላይ ነው የተመሰረተው። ይህ አሰራር የተወሰኑ ላኪዎችን ከገበያው እንዲወጡ አድርጓል፡፡
የዳግም ማሻሻያ ክለሳውን እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ አብዛኛው ላኪ የሚፈልገው መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዓለምነው ፤ ማዕድን አላቂ ሀብት በመሆኑ በአንድ ጊዜ ነፃ መለቀቅ የለበትም ።ሀገርን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ነው ግብይቱ መከናወን ያለበት፡፡እንደርሳቸው በዘርፉ ላይ የሚገኘው ዘርፉን በደንብ የሚያውቀው በመሆኑ በመሸጫ መነሻ ዋጋው ላይ ሊሳተፍ ይገባል ።
ከሶስት ወር በፊት የነበረውን የማሻሻያ እርምጃ በጥሩ ጎኑም በክፍተትም የነገሩን ሌላው አስተያየት ሰጪ የከበሩ ድንጋዮች ጌጦችና ቅርጾች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤት አቶ ሄኖክ ግርማ ናቸው። ማሻሻያው ቀጣይነት እንደማይኖረው እምነቱ ነበራቸው ።ያም ሆኖ ግን ጥሩ ጎንም ነበረው ። በግላቸው ኃላፊነት ተሰምቷቸው በእቅድ እንዲመሩ አድርጓቸዋል ።ግብይቱም ጨምሯል። እንዲህ መልካም ጎን ቢኖረውም ገቢ ላይ ዝቅተኛ ዋጋ መመዝገቡ ሀገርን የሚጎዳ ሆኖ ተገኝቷል ።ዋጋ ተቀባይ መሆናችን ጎድቶናል የሚሉት አቶ ሄኖክ፤ መነሻ የመሸጫ ዋጋ ባለመኖሩ ገዥዎች በወረደ ዋጋ ለመግዛት ዕድል ፈጥሮላቸዋል ።ገዥ ደንበኞች ማዕድኑን በብዛት ገዝቶ ማከማቸት ነው የተያያዙት ።ላኪውም ከብዛት አገኛለሁ በሚል በተሰጠው የወረደ ዋጋ ለመሸጥ ተገዷል። በድካም ውስጥ አልፎ የተገኘን የማዕድን ሀብት ጥቅም እያገኙበት ያሉት ገዥ ሀገራት ናቸው፡፡የኢትዮጵያን የጌጣጌጥ ማዕድን በስፋት እየገዛች ያለችው ህንድ ናት። ከኢትዮጵያ በወረደ ዋጋ የገዙትን የጌጣጌጥ ማዕድን በተለያየ ኤግዚቢሽን ላይ በተሻለ ዋጋ ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል ።አጠቃላይ በትምህርትና በእውቀት የተደገፈ የንግድ ክህሎት አለመኖርንም እንደ አንድ ክፍተት አቶ ሄኖክ አንስተዋል ።የመሸጫ መነሻ ዋጋ መኖር እንዳለበትም ያምናሉ ።
የማእድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ በዚሁ ወቅት በሰጡት ማሳሰቢያ መንግሥት በፖሊሲ፣በአዋጅና በተለያየ መንገድ ዘርፉን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው። በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ እንዲገኝ ነገሮችን ያመቻቻል ። በተለይ አምራችና ላኪው ከዓለም አቀፉ ጋር የልምድ ልውውጥ ተሞክሮ እንዲያደርግ፣ ገበያውን እንዲያሰፋና የተለያዩ ዕድሎችን እንዲያገኝ አውደ ርእይና ኤክስፖዎችን በማዘጋጀት ያመቻቻል ።በዘርፉ ላይ የተሰማራው ባለሃብት ግን በንግድ መንፈስ በመንቀሳቀስ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር እርሱንና ሀገርን ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅበታል ።ያሉበትን ችግሮችንም ለመፍታትም ሆነ ከመንግሥት የሚፈልጋቸውን ድጋፎች ለማግኘት ጠንካራ የሆነ ማህበር በመመስረት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል ።ሰብሰብ ሲሉ ወይንም ሲደራጁ ለመንግሥት ድጋፍም አመቺ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡
ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ዘርፉ ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችንና ክፍተቶችን በተመለከተ በአንዳንድ የውይይቱ ተሳታፊዎች የቀረቡ ሃሳቦች ላይም ሚኒስትሩ ከዕለቱ አጀንዳ ጋር ተያያዥ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ በሌላ ጊዜ በሚዘጋጁ መድረኮች እንደሚወያዩባቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/ 2015 ዓ.ም