‹እራበ — ን ወገን ጧሪ ቀባሪ ልጅ የለንም›› ይሄን እያሉ ሲለምኑ ያስተዋልናቸው አረጋውያን ሴት እጅግ አንጀት ይበላሉ። ልብሳቸው የተዳደፈ ነው። በዚህ ላይ ቡጭቅጭቅ ብሎና ተጣጥፏል። በእጅጉ ተጎሳቁለዋል ። በያዙት ዱላ ታግዘውና ተደግፈው ለመቆም ቢሞክሩም የዕድሜ ጫና አቅምና ጉልበታቸውን እየተፈታተነው ራሳቸውን ችለው መቆም ተስኗቸዋል ። እንደምንም እየተንገታገቱና እየተንቀጠቀጡ የሚያወጡት የልመና ድምፅ ይጎተትና ይቆራረጣል።
ዕድሜ ከጉስቁልና ጋር ተዳምሮ የእሳቸውን ያህል አቅም ያሳጣቸው አረጋዊ ባለቤታቸው አንጀት በሚበላ አሳዛኝ ሁኔታ ከፊት ለፊታቸው መሬት ላይ ተኝተዋል። ‹‹እራበ — ን–›› አረጋዊቷ ራበን ሲሉ ያወጡት የልመና ድምጽ እኝህን መሬት ላይ የተኙ ባለቤታቸውንም ይወክላል። ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ያለውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን አጥር ተደግፈው በጠዋት የሚለምኑ የነዚህ ጥንድ አረጋውያን ሁኔታ የመንገድ ተላላፊውን ትኩረት ሁሉ የሚስብ ነበር።
‹‹ነግ በኔ ›› የሚለውን ያሰቡት የመሰሉ ሁለት ወደ ሥራ የሚሄዱ ባልና ሚስቶች በየፊናቸው ከንፈራቸውን እየመጠጡ የቋጠሩትን ምሳ ሳህን ፈትተው በአቅራቢያው ካለው ሱቅ በደረቴ ፌስታል በመግዛት ለአረጋውያኑ ጥንዶች ዘረገፉላቸው። ደግሞ ወንድየው ከኪሱ ድፍን 50 ብር አውጥቶ ከተኙት ባለቤታቸው ፊት ያነጠፉት ጨርቅ ላይ ጣለላቸው። ይሄ ወደ ሥራ የሚጓዙት ባልና ሚስቶች በጎነት ብዙዎች በሀዘኔታ ለጥንዶቹ አረጋውያን እጃቸውን እንዲዘረጉ አደረገ ። ዕውነት ለመናገር እርጅና ያዛላቸው ወንድና ሴት አዛውንቶች መንገድ ዳር ወድቀው እያዩ በኩራት ተራምዶ በዚያ አካባቢ ማለፍ የቻለ ማንም መንገደኛ አልነበረም ።
አረጋውያን አሁንም በከፋ ድህነትና ጉስቁልና ውስጥ ሕይወታቸውን እየገፉ ይገኛሉ። ከባዱ ኑሮ ውድነት እንግልትና መከራቸውን አባብሶታል። ከነዚህ አረጋውያን መካከል አንዳንዶች ጧሪ ቀባሪ ያጡት ዕድሜ ተጭኖ ከሚያብረከርከው ጉልበትና አቅማቸው ጋር እየታገሉ በየመንገዱ ይለምናሉ ።ለልመና የሚሆንም አቅምና አንደበት አጥተው በየመንገዱ ወድቀውም ይታያሉ። በጡረታ ዘመናቸውም እንኳ ጧሪ ደጋፊ ስለሌላቸው ራሳቸውን መሸከፍ የማይችሉ በርካታ አረጋውያን በሀገራችን በየአካባቢው ይገኛሉ። እነዚህ አረጋውያን በሕይወት ዘመናቸው ዓይናቸውን በዓይናቸው ማየት አለመቻላቸው ጧሪና ቀባሪ አሳጥቷቸዋል ።ሁለት ሦስትና ከዛ በላይ ወልደው ልጆቻቸው ያለቁባቸው፤ ብኩን የሆኑባቸው እንዲሁም እንደነሱ ሁሉ ከእጅ አይሻል ዶማ ›› እንዲሉት ተረት እንኳን ለእነሱ ሊተርፉ ለእራሳቸውም የማይሆኑበት ሁኔታ አለ።
እናት አረጋዊ አልማዝ አሰፋ ለዚህ ማሳያ ይሆናሉ። እንዳወጉን በሕይወት ዘመናቸው የወለዷቸው ልጆች 10 ናቸው የተወሰኑት በልጅነታቸው ሞተዋል። ሰባቱ ግን አሁንም በሕይወት አሉ። ሆኖም ፊቱኑ ጉልበታቸው ሳይደክም በወጣትነት ዘመናቸው ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ነበር። በዚህ ምክንያት እሳቸው እንዳለመማራቸው ሁሉ ልጆቻቸውን ሊያስተምሩ አልቻሉም። ጥበቃ በሚሰሩት ባለቤታቸው ገቢ ነበር ለረጅም ጊዜ ሲያስተዳድሯቸው የቆዩት። ከ15 ዓመት በፊት እኝህ ባለቤታቸው በሞት ሲለይዋቸው ልጆቻቸውም በየአቅጣጫው ራሳቸውን ለማዳን ተበታተኑ።አሁን ላይ የት እንዳሉ እንኳን አያውቁም። ሕይወታቸውን በልመና መግፋት ከጀመሩም 15 ዓመት ያህል አስቆጥረዋል።
አባት አረጋዊ ተስፋሁን ድፋባቸው ደግሞ ልጅ አልወለዱም። ባለቤታቸውም እሳቸውም መካን ናቸው። አሁን ላይ ባለቤታቸው በአቅም እጦት እቤት ከዋሉ ዓመታት አስቆጥረዋል። እሳቸው የመንግሥት ሠራተኛ ስለነበሩ ጥቂት የጡረታ አበል አላቸው። ሆኖም ከኑሮ ውድነቱ ጋር መጣጣም አልቻለም። የቀበሌ ቤት ኪራይ፤ የውሃና መብራት እንዲሁም ቀለብ መሆን ባለመቻሉ በእጅጉ እየተቸገሩ ነው። አንዳንዴ ለመብራት ብቻ ከፍለውት ቀለብ ሳይተርፋቸው ይቀራል። ይሄኔ አፍ አውጥተው የሚያውቋቸውን ሰዎች እየለመኑ ሲያሟሉት ቆይተዋል ።አሁን ላይ ግን ሰው ሰልችቷቸዋል ። የሰው ፊት ማየቱም ገርፏቸዋል። ሲብስባቸው ልመና ወጥተው የእራሳቸውንና የሚስታቸውን ኑሮ ይደጉማሉ። በተለይ የንግስና የበዓላት ቀን ከቤተክርስቲያን ውለው የበሰለ ምግብ ሳይቀር እየወሰዱ ባለቤታቸውን ይመግባሉ ።
ሆኖም በየትኛውም የሀገራችን አካባቢ በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ያለው ማኅበረሰብ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች አይቶ እንዳላየ የማለፍ ጨካኝ ልቦና የለውም። በግልም፤ በጋራ ተደራጅቶና ተሰባስቦም እንዲሁም ማኅበር አቋቁሞ ሳይቀር የመደገፍ ባህል አዳብሯል። በርግጥ መንግሥትም ቢሆን የወደቀ ቤታቸውን በአማረ ሁኔታ አፍርሶ ከመገንባትና አልፎ አልፎም ቢሆን ማዕድ ከማጋራት ጀምሮ ለአረጋውያን አቅሙ የፈቀደውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
አሁን ላይ ኑሮ ከመወደዱና ጫናው ለአረጋውያን በመክበዱ ኅብረተሰቡ ፀበል ፃዲቅ ሲያደርግ እንዲሁም ዝክር ሲዘክር እንኳን እንዲህ ዓይነት አረጋውያንን ሰብስቦ የሚያበላበት ጊዜ ቀላል አይደለም። አራት ኪሎ ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙት እማሆይ አስካለ ገብረመስቀል ኅብረተሰቡ እንዲህ ዓይነቱን ልምድ እንዲያዳብር ከሚያበረታቱ እናቶች መካከል አንዷ ናቸው ። እሳቸውም ዓመታዊና ወርሐዊ የማርያምን በዓል የሚዘክሩት አቅማቸው ለደከመና ጠዋሪ ቀባሪ ያጡ አረጋውያን ሰብስበው በማብላት እንደሆነ ይናገራሉ ። ቄስ አለማየሁ ሁንዴሳ እንደሰጡን አስተያየት ቤተክርስቲያን እንዲህ ዓይነቱን ባህል ታበረታታለች ። ማኅበረሰቡ ሰርግ ፤ተዝካርና የተለያዩ ድግሶች ሲኖሩት ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ይልቅ አረጋውያንን ጠርቶ እስከማብላት የደረሰበት ሁኔታ አለ።
ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት እንዳገኘነው መረጃ አረጋውያን በድህነት፣ በሕመም፣ በጉልበት ማነስ፣ ከማኅበራዊ ሕይወት መገለል፣ በአመጽ፣ በብቸኝነት፣ በብዝበዛ፣ ለሰው ልጅ መሠረታዊ ፍጆታ በሆኑ በምግብ፣ በልብስ እና በመጠለያ እጦት እንደሚሰቃዩ ይታወቃል። እንደ መንግሥት ይሄን ታሳቢ አድርጎና የአረጋውያንን ጉዳይ በዳይሬክቶሬት ደረጃ አቋቁሞ የሚደረግ ድጋፍ ቢኖርም ሀገሪቱ ካለችበት የኢኮኖሚ አቅም ማነስና በእንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ሕይወታቸውን የሚገፉ አረጋውያን ብዛት አንፃር በኅብረተሰቡም እንዲደገፉ ይፈልጋል ። በበቂ የጤና እንክብካቤ ማነስ፣ በጠያቂ መጥፋት፣ አመጽ እና ጦርነት በሚቀሰቀስበት ጊዜ በቂ ድጋፍ የማያገኙበት ጊዜ ቀላል ባለመሆኑ ኅብረተሰቡ በቅርቡ ካሉ ከአረጋውያን ጋር እርስ በእርሱ መደጋገፍ ግድ ይለዋል ። አረጋውያን ላካበቱት የሕይወት ልምድ እና እውቀት አስፈላጊውን ክብር መስጠትም ይገባል። በማኅበራዊ ሕይወት እንዲሳተፉ ማድረግ መገለልን የሚያስወግድ በመሆኑ ለማኅበረሰቡ ትምህርት፣ ስልጠና፣ ዘላቂነት ያለው ግንዛቤ ማስጨበጫ እና የአቅም ግንባታ ሥራ መሠራት ተገቢ በመሆኑ በዚሁ ጉዳይ እየተሠራ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ አቶ ደረጀ ታዬ ያወሳሉ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም