በራሳቸው በመሪዎች ከተጻፉ የኢትዮጵያ ታሪክ መጻሕፍት አንዱ የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ‹‹ሕይወቴ እና የኢትዮጵያ እርምጃ›› መጽሐፍ ነው። ከዚያ በፊት የነበሩት ታሪካቸው በዜና መዋዕል ፀሐፊዎች የሚጻፉ ናቸው። ከውጭ አገራት መሪዎች እና ከአገር ውስጥ መሳፍንት ጋር የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች ናቸው።
ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍነት ሊጠቀስ የሚችለው የመሪ መጽሐፍ የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ‹‹ትግላችን›› የሚሉት ሁለቱ መጻሕፍት ናቸው። በዚያው በደርግ ዘመነ መንግሥት ለሦስት ዓመታት ያህል (1979-1982) የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ‹‹እኛ እና አብዮቱ›› እና ‹‹እኔ እና አብዮቱ›› የሚሉ ሁለት የኢትዮጵያ ታሪክ መጻሕፍትን ለንባብ አብቅተዋል። በሌሎች መሪዎች የተጻፉት ከታሪክነት ይልቅ በፖሊሲ እና በተለያዩ ፍልስፍናዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው።
በመሪዎች በሚጻፉ የታሪክ መጻሕፍት ላይ በታሪክ ባለሙያዎች ሁለት ሀሳብ ይነሳል። አንደኛው፤ በራሳቸው በታሪኩ ተዋናዮች መጻፉ ‹‹ከፈረሱ አፍ›› ያደርገዋል የሚል ነው። ሁሉን ነገር በዝርዝር ስለሚያውቁት ዋናው ምንጭ ያለው እነርሱ ጋ መሆኑ ነው።
ሁለተኛው ሀሳብ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። የራሳቸውን ጥፋቶች በመሸፈን እና የተቀናቃኞቻቸውን ጥፋት በማጉላት አድሎ ያደርጋሉ የሚለው ነው። ታሪክ ከፖለቲከኞች (መሪዎች) ይልቅ በገለልተኛ የታሪክ ባለሙያ ቢጻፍ ይሻላል የሚል ምክረ ሀሳብ ያቀርባሉ።
ነገሩን እግረ መንገድ አነሳነው እንጂ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የታሪክ መጻሕፍትን መገምገም አይደለም። የዛሬ የዘመን ጥበብ መነሻችን ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 28 ቀን 2015 ዓ.ም በዋቤ ሸበሌ ሆቴል የተመረቀው የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ‹‹ሕይወቴ እና የኢትዮጵያ እርምጃ» መጽሐፍ ነው።
መጽሐፉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ1965 ዓ.ም ነው። አሁን ላይ የመጽሐፉን ተደራሽነት ለማስፋት እና ለዘመኑ አንባቢ በሚሆን መንገድ በድጋሜ ታትሞ ለንባብ በቅቷል። መጽሐፉ በድጋሜ የታተመው አዲስ ባህልና ጥበብ ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ነው። የመጽሐፉን አርትኦት ጋዜጠኛና አርታኢ ጥበቡ በለጠ ሠርቶታል።
ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጸው፤ መጽሐፉን በድጋሜ ማሳተም ያስፈለገው ተደራሽነቱን ለማስፋት እና ለዘመኑ አንባቢ ምቹ የሆነ ቅርጽ እንዲኖረው ነው። ንጉሡ መጽሐፉን የጻፉት ከ86 ዓመታት በፊት በስደት እንግሊዝ አገር በነበሩበት ጊዜ ነው። መጽሐፉ የታተመው በ1965 ዓ.ም ቢሆንም የጻፉት ግን ከ1929 ዓ.ም ጀምሮ በእንግሊዝ አገር በነበሩበት ጊዜ ነው።
እንደ ጥበቡ ገለጻ፤ በወቅቱ የነበረው የሥርዓተ ጽሕፈት ቅርጽ ለአሁኑ ትውልድ ምቾት አይኖረውም፤ ለምሳሌ በየቃላቱ መካከል ሁለት ነጥብ ነበር፤ አሁን በሁለት ነጥብ ምትክ በቃላት መካከል ክፍት ቦታ ነው የሚተወው። እንዲህ ዓይነት የሥርዓተ ነጥብ እና አንዳንድ በዚህ ዘመን ትርጉማቸው ሊታወቅ የማይችሉ ቃላት ላይ አማራጭ ትርጉም ተቀምጧል።
በሌላ በኩል በዚያን ዘመን እንደ መደበኛ ቃላት ያገለግሉ የነበሩ እና አሁን ላይ ግን በጊዜ ሂደት ትርጉማቸው የተቀየረ ወይም ነውር ትርጉም የሚሰጡ ቃላት እንዲቀየሩ ተደርጓል። ለምሳሌ የአካል ጉዳተኛን ለመግለጽ በቀድሞው ጊዜ የነበሩ ቃላት እና አሁን ላይ የምንጠቀማቸው ቃላት ይለያያሉ፤ እነዚህንና የመሳሰሉትን የቃላትና የቅርጽ ማስተካከያ ሲደረግ ይዘት ላይ ምንም የተነካ ነገር እንደሌለ ጥበቡ ተናግሯል።
ወደ ዕለቱ የመጽሐፉ ምርቃት ድባብ እንሂድ። በሄድኩባቸው መድረኮች የመጽሐፍ ምርቃት ላይ በብዛት የማስተውለው ብዙ ባዶ ወንበሮች ነበር። የሚመጣው ታዳሚም ከተጠቀሰው ሰዓት በብዙ ዘግይቶ ነው። ብዙ የመጽሐፍ ምርቃት ላይ ቀድሜ እየደረስኩ እስከሚጀመር መጠበቅ ተማርሬ ነበር።
በዚህ መጽሐፍ ምርቃት ዕለት 40 ደቂቃ አካባቢ ዘግይቼ ነበር የደረስኩ። ስደርስ ፕሮግራሙ ተጀምሯል፤ ምክንያቱም ወንበሩ ቀድሞ ነው የሞላው። እኔ ስደርስ የአዳራሹ በር ላይ የቆመው ሰው ብዙ ነው። ይህን ያህልም ቆይቼ አልተጀመረም ብዬ ቀድሜ በመድረሴ እየተቆጨሁ ጠጋ ስል ቦታ አጥተው የቆሙ ናቸው። ቁጭቴ ወዲያውኑ ‹‹ምነው በዘገየሁ ነበር!›› ከሚል፤ ወደ ‹‹ለምን ዘገየሁ!›› ተቀየረ።
ወደ ውስጥ ስገባ ‹‹ራስ ተፈሪያን›› የሚባሉት አረንጓዴ ብጫ ቀይ ለብሰው መግቢያውን አድምቀውታል። የይሁዳ አንበሳ ያለበትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የለበሱም ይታያሉ። ‹‹ድሬድ›› የሚባለው ረጃጅም ፀጉራቸው እነርሱነታቸውን ይናገራል። በኢትዮጵያ ወዳድነታቸው ይታወቃሉ።
እነዚሁ ራስ ተፈሪያን በፕሮግራሙ መጨረሻ አካባቢ የኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል። በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት አሸብርቀው፣ የይሁዳ አንበሳ ያለበትን (በንጉሡ ጊዜ የነበረው ማለት ነው) የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ይዘው የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል። ከመድረኩ ፊት ለፊት ደግሞ የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ፎቶ በአሁኑ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ (መሐሉ ላይ የኮከብ አርማ ያለው) ታጅቦ ይታያል። ራስ ተፈሪያኑ በተሰጣቸው የመድረክ ዕድል ስለቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ እና ስለኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር አንዳንድ የአማርኛ ቃላትም እየቀላቀሉ ተናግረዋል።
ሌላው በመድረኩ ላይ የተስተዋለው ነገር የአርበኞች ስሜት ነው። በተለይም አንድ አባት ስለቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ሲወራ ድንገት ነሸጥ አድርጓቸው ተነስተው ፉከራ ጀመሩ። ታዳሚውም መድረክ መሪውም በወኔያቸው ተማርኮ ስለነበር ሰፋ ያለ ዕድል ተሰጣቸው። የንጉሡን ሥራዎችና ብልህነቶች የሚገልጹ ቃላትን በመጠቀም በመድረኩ ላይ ሲጎማለሉ ቆይተዋል።
በመጽሐፍ ምርቃቱ ላይ እንደነ ዶክተር አየለ በከሪ እና መምህር ታዬ ቦጋለ ያሉ የታሪክ ሰዎች ገለጻ አድርገዋል። ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመናዊት ኢትዮጵያን ለመገንባትና ትምህርትን ለማስፋፋት ያደረጓቸው ሥራዎች ተነግረዋል።
ወደ መጽሐፉ ስንመጣ፤ በቅርጽ በኩል የምዕራፍ ይዘቶች ብቻ (መግቢያና መውጫ አካባቢ ያሉትን ሳይጨምር ማለት ነው) ከ260 ገጾች በላይ ነው። መጽሐፉ በ450 ብር ዋጋ ይሸጣል። የመጽሐፉ የፊት ሽፋን ‹‹ሕይወቴ እና የኢትዮጵያ እርምጃ›› ከሚለው ስሙ ሥር የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ፎቶ በትልቁ ይታያል። ከፎቶው ሥር የራሳቸው ስም ተጽፏል። የጀርባ ሽፋኑ ላይ የጋዜጠኛና አርታኢ ጥበቡ በለጠ መልዕክት ተጽፏል።
ይዘቱ የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን ግለሰባዊ እና ንጉሣዊ ታሪክ ጨምሮ በተለይም በእርሳቸውና በሥርዓታቸው የነበረውን የኢትዮጵያን ታሪክ ይነግረናል።
የተፈሪ መኮንንን ሕፃንነት፣ ደጃዝማችነት እና ከዚያም ንጉሠ ነገሥትነት። በእርሳቸው እና በልጅ ኢያሱ መካከል ስለተፈጠረው መቀያየም፣ በንግሥት ዘውዲቱ እና በእርሳቸው መካከል ስለነበረው ግንኙነት፣ የተለያዩ ዓለም አገራት ያደረጉትን ጉዞ እና የዓለም መንግሥታት ማህበርን ጨምሮ ለኢትዮጵያ ያደረጓቸውን እንቅስቃሴዎች፣ ስለአሰብ እና የባህር ወደብ፣ ስለሕገ መንግሥት፣ ስለጦር ሠራዊት ማደራጀት እና በአጠቃላይ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በዘለቀው የሕይወት እና የአገር መሪነት ታሪካቸው ይነግረናል።
መጽሐፉ ሥነ ጽሑፍም ነው ማለት ይቻላል። ንጉሡ የሚታወቁበት አንደኛ መደብ ብዙ ቁጥር አገላለጽ (እኛ) በመጽሐፉ ውስጥ በጉልህ ይታያል። የራሳቸውን ታሪክ ሳይቀር በአንደኛ መደብ ብዙ ቁጥር ነው የሚገልጹት። ከዚህ በተጨማሪ አገላለጻቸው ኃይማኖታዊ አገላለጽ ያለው ሲሆን ሥነ ጽሑፋዊ ውበትም አለው።
ታሪክ በባለቤቱ ሲጻፍ አድሎ ሊኖረው ይችላል የሚለውን ሀሜት ንጉሡ ያወቁት ይመስላል። ለዚህም ነው በመግቢያው ላይ ሆን ብለው ስህተት እንዳይሠሩ እና የሰዎችን ስም ያለአግባብ እንዳያነሱ ፈጣሪ እንዲጠብቃቸው ይማጸናሉ። ለእውነተኝነታቸው ፈጣሪ የልባቸውን እንደሚያውቅና መደበቁ ወይም መዋሸቱ እንደማይጠቅም ይገልጻሉ። ለምሳሌ፤
‹‹… በዚህ ታሪክ ውስጥ የሌላ ሰው ስም በሚጠራበት መስመር ሁሉ በማዳላት ወይም በመጥላት ሳይሆን በስህተት ከሚሆነው በስተቀር እውነቱን ብቻ ለመጻፍ ልባችንን ዳኛ ማድረጋችንን አንተ ታውቃለህ…›› ይላል።
ንጉሡ ትምህርት እና ዘመናዊነትን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ያደረጉት ጥረት በተለያዩ አጋጣሚዎች ይነገርላቸዋል። ትምህርትን ሲያስፋፉ ከምዕራባውያን ሥልጣኔ የቀሰሙት ስለነበር በአገር ውስጥ ያለው ማኅበረሰብ ለመቀበል ይቸግረው ነበር። ይህን ችግር ተረድተው ይመስላል በመጽሐፋቸው መግቢያ ላይ ይህ አገላለጽ ይገኛል።
‹‹… ሕፃንን ልጅ በማባበልና በማስለመድ ካልሆነ በቀር በእጁ የያዘውን ነጥቆ ቢወስዱበት ደስ አይለውም። በማሳየትና በመቅመስም ካልሆነ በቀር ማናቸውንም ምግብ ቢሰጡት ሊመገበው አይፈቅድም። ጥርስም እስቲያበቅል ወተት ወይም ሌላ ለስላሳ ምግብ ካልመገቡት ዳቦ ወይም ሥጋ ቢያቀርቡለት ሊመገበው አይችልም…›› ይላል።
አገላለጾቻቸው በእንዲህ ዓይነት ሥነ ጽሑፋዊ የሆነ የዘይቤ አገላለጽ የተጻፉ ናቸው። ነገሮችን በማመሳሰል፣ በማነፃፀር ይገልጻሉ። ሀሳባቸውን ግልጽ ሊያደርግ የሚችል ተምሳሌት ይጠቀማሉ።
ይህን አገላለጽ የተጠቀሙት የኢትዮጵያን ነባር ልማድ በአንድ ጊዜ መናድ አይቻልም ለማለት ነው። ልማዳዊ የሆኑ ነገሮችን በዘመናዊ ነገሮች ለመቀየር በኃይል ከማድረግ ይልቅ ጥቅሙን እያሳዩ ማለማመድ ይሻላል ለማለት ነው። በዘመኑ ከአውሮፓ የሚመጣ ነገር ሁሉ ተቃውሞ ያጋጥመው እንደነበር ይነገራል፤ ይህ የቆየና የኖረ ልማድ ንጉሡን አስቸግሯቸው ነበር ማለት ነው። ስለዚህ ዘመናዊ ትምህርትን ለማስፋፋት ትግል አድርገዋል ማለት ነው።
በተለምዶ ‹‹የ60ዎቹ ትውልድ›› የሚባሉት አብዮት አንቀሳቃሾች ወደ አውሮፓ ሄደው ይማሩ እንደነበር ራሳቸው አብዮተኞች የጻፉት መጽሐፍ ይነግረናል። እነዚህን ሰዎች ወደ አውሮፓ ሄደው እንዲማሩ ያደረጋቸው የንጉሡ መንግሥት ነው።
በዚያን ዘመን የተጻፉ መጽሐፎች ፖለቲካና ታሪክ ብቻ ሳይሆኑ የሥነ ጽሑፍ ማስተማሪያዎችም ናቸው። ልቦለዶችም ቢሆን እልም ያለ የፖለቲካ ይዘት ያላቸው ነበሩ። ለምሳሌ ፍቅር እስከመቃብር እና አልወለድም ሥነ ጽሑፍ እና ፖለቲካ ናቸው። የታሪክ መጻሕፍትም አጻጻፋቸው የሥነ ጽሑፍ ውበት ያለው ነው። ምሳሌያዊ ንግግሮችን ይጠቀማሉ።
በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች የአገራቸውን ነባራዊ ሁኔታ የማወቅ ዕድላቸው ሰፊ ነውና የአሁን ዘመን ሰዎችም የሕይወት፣ የሥራ እና የአመራርነት ታሪካቸውን ሊጽፉልን ይገባል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም