የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ሲሰጥ ፈተና ላይ የሚወልዱ እናቶች ያጋጥማል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የ10ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ስለቀረ ክስተቱ የሚታየው 12ኛ ክፍል ላይ ነው:: ብዙ ጊዜ አገር አቀፍ ጉዳዮች ላይ (ለምሳሌ ምርጫና ፈተና) የሚወልዱ እናቶች ዜና ይሆናሉ::
የዘንድሮ 12ኛ ክፍል ተማሪዎች መውለድ ግን ከባለፉት አንፃር ቁጥሩ የጨመረ ይመስላል:: ዋናዎቹን መገናኛ ብዙኃን ጨምሮ በማህበራዊ የትስስር ገጾች ከብዙ ዩኒቨርሲቲዎች የወሊድ ዜና ተሰምቷል:: ለዚያውም ገና መግባት እንደጀመሩ እና በመጀመሪያው ዙር ፈተና ነው:: በሁለተኛው ዙር ፈተናም የሚከሰት ከሆነ ቁጥሩ ይጨምራል ማለት ነው:: ልጅ መውለድ ፀጋ ስለሆነ ለእናቶችና ለቤተሰቦቻቸው ልጆቻቸውን አሳድገው ለቁም ነገር እንዲያበቁ እንመኛለን::
የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መውለድ አጀንዳ ስለሆነ የትዝብቴ መነሻ አደረኩት እንጂ የጽሑፉ ዓላማ ምን ያህል የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ወለዱ የሚለውን አይደለም:: ሽፋን የማግኘት ዕድል ስላለው በብዙዎች ዘንድ ተዳረሰ እንጂ ከ4ኛና 5ኛ ክፍል ጀምረው የሚወልዱትን ቤት ይቁጠራቸው::
ዋናው ጥያቄ ‹‹ተማሪዎች ይወልዳሉ?›› የሚለው ነው:: አዎ! ለምን ይወልዳሉ?
ይህ ክስተት በብዛት የሚስተዋለው በገጠሪቱ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ነው:: የሰሞኑ ዜናዎችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ:: የገጠርን ሕይወት በመኖር ስለማውቀው እየታዘብኩት የኖርኩትን ልናገር:: ልጆቹ ገና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያሉ ነው እንዲያገቡ የሚደረገው:: የአንዳንዶቹ የትዳር አጋሮች እስከ ሁለተኛ ደረጃ ወይም እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያስተምሯቸዋል፤ የአብዛኞቹ ግን እንዲያቋርጡ
ነው የሚያደርጓቸው:: እነዚህን አግብተው ትምህርት የሚያቋርጡ ሴቶች ማንም ልብ አላላቸውም:: እነዚህ 12ኛ ክፍል ፈተና ላይ ወልደው የዜና ሽፋን ያገኙት በጣም ጥቂቶች ናቸው::
11ኛ፣ 10ኛ፣ 9ኛ… ክፍል ሁሉ የሚወልዱ አሉ:: ሲወልዱ ከአራት እስከ ስድስት ወር ያህል ክፍል ውስጥ አይገቡም:: የማጠቃለያ ፈተና ላይ ሊገኙ ቢችሉ ነው፤ ለዚያውም ከወለዱ በኋላ ትምህርቱን ያላቋረጡት ማለት ነው:: እንዲህ እንዲህ እያሉ አገር አቀፍ ፈተና ላይ ይደርሳሉ:: ስለዚህ ለትምህርቱ በቂ ጊዜ አልሰጡም ማለት ነው::
አሁንም ‹‹ተማሪዎች ለምን ይወልዳሉ?›› ብለን እንጠይቅ:: የሚወልዱት ወደውና ፈቅደው ሳይሆን ተገደው ነው:: ተገደው ሲባል በአስገድዶ መድፈር አይነት አይደለም:: የቤተሰብ እና የአካባቢ ዘመድ አዝማድ ጫና ይደረግባቸዋል:: ቤት ውስጥ ቁጣ ይበዛባቸዋል:: ‹‹ትምህርትሽን አታቋርጭም፤ አግቢና ተማሪ›› እያሉ ያታልሏታል::
ካገባች በኋላ ደግሞ ልጅ መውለድ እንዳለባት ግፊት ይደረግባታል:: የትዳር አጋሯ ደግሞ እሷን ለመያዝ ሲል እንድትወልድ ይፈልጋል፤ ልጅ የትዳር ማፅኛ ነው ተብሎ ይታመናል:: እንዲህ እንዲህ እያሉ ታረግዛለች፤ ከዚያም ትምህርቱን ታቋርጣለች ማለት ነው:: በኖርኩበት አካባቢ በዚህ ሁኔታ ትምህርት ያቋረጡ ብዙ ሴት ልጆችን ስለማውቅ ነው::
ይህን ትዝብት ሳጋራ አንድ ነገር ልብ ይባልልኝ:: ሁሉም ተማሪዎች ተገደው ነው የሚያገቡ ማለቴ አይደለም፤ እያወራሁ ያለሁት ስለአብዛኞቹ ስለሆነ ነው:: የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ክስተትም መነሻዬ እንጂ መደምደሚያ አይደለም:: ወደውና ፈቅደው እንዲሁም የማግባትና ልጅ የመውለድ ደረጃ ላይ የደረሱ ሴቶች አሉ:: እነርሱ የራሳቸው የሆነ መተዳደሪያ ያላቸው ወይም የትዳር አጋራቸው በቂ መተዳደሪያ ያለው ናቸው:: ግን የሴት ልጅ ሕይወት በዚህ መገደብ የለበትም::
አንዳንድ ሰዎች ተማሪ ሆኖ መውለድን እንደ ትልቅ ነውር የሚያዩት አሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ እንደ ትልቅ ስኬት የሚያዩት አሉ:: ስኬትም ነውርም አይሆንም:: ነውር አይደለም ስንል፤ ልጆቹ የሚወልዱት ከትዳር ውጭ ሲወሰልቱ አይደለም፤ በወግና ሥርዓት ያገቡ ናቸው:: ልጅ መውለድም መታደል ነው፣ ፀጋ ነው:: ሌላው ነውር የማይሆንበት ምክንያት ተገደውና ጫና ተደርጎባቸው ስለሚሆን ነው::
ስኬት አይደለም፤ ስንል ደግሞ ተማሪዋ መድረስ ያለባት ደረጃ ላይ እንዳትደርስ ስለሚያደርግ ነው:: የሴት ልጅ ሕይወት ገና በልጅነቷ ልጅ ታቅፋ መኖር አይደለም:: ተመራማሪ የሚያደርግ ደረጃ ላይ መድረስ አለባት:: ልጅ እየወለዱም ይቻላል ይባል ይሆናል፤ ግን ይለያያል:: ልጅ ለመውለድ ቢያንስ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን በሚገባ መጨረስ ያስፈልጋል:: በሰርግ፣ እርግዝና እና በወሊድ ጊዚያት ከትምህርት ርቀው ነው የሚቆዩ፤ ለዚህም ነው አብዛኞቹ የሚያቋርጡት::
አንዳንዶቹን ፎቶ ላይ ስናያቸው ትልልቅ ይመስሉን ይሆናል፤ ግን በተጎሳቆለ እና በገጠር ሕይወት ውስጥ ስለሚኖሩ እንጂ በዕድሜ ትልቅ ሆነው አይደለም:: ስለዚህ የሴቶች ጉዳይ ተቋማት እና የትምህርት ተቋማት ጉዳዩን ሊያጠኑት ይገባል::
ሌላው ልብ ሊባል የሚገባው ነገር በብዙ አካባቢዎች ለትምህርት የሚሰጠው ዋጋ ዝቅተኛ እየሆነ ነው:: በተለይም አንዳንድ ወላጆች ‹‹የእገሌ ልጅ ተምራ የት ደረሰች?›› በማለት ተመርቀው ያልተቀጠሩ ልጆችን ይጠቅሳሉ:: ወይም አገር አቀፍ ፈተና ላይ ውጤት ያልመጣላቸውን ልጆች በመጥቀስ እንደ እነርሱ ከመሆን በሚል እንዲያገቡና ልጅ እንዲወልዱ ያደርጓቸዋል:: እውነታው ግን እነዚያ የአካባቢያቸው ልጆች ውጤት ያልመጣላቸው ለትምህርት በቂ ጊዜ ስላልተሰጣቸውና ክትትል ስላልተደረገላቸው ነው::
ሌላኛው እውነታ በዚህ ዘመን ያልተማረ ምንም መሥራት እንደማይችል አለመታወቁ ነው:: በ20 እና 10 ዓመታት ውስጥ እንኳን ያለውን ልዩነት ልብ እንበል:: ከዛሬ 20 ዓመት በፊት 12ኛ ክፍል መድረስ ትልቅ ደረጃ ነበር:: ዛሬ ግን የመጀመሪያ ዲግሪ ራሱ ምንም ነው:: ምክንያቱም የዓለም ነባራዊ ሁኔታ እየተቀየረ ነው:: ከዛሬ 20 ዓመት በፊት የወረቀት ደብዳቤ የሚያነብ ሰው የተማረ የሚባል ነበር፤ ዛሬ ግን በረቂቅ የቴክኖሎጂ መተግበሪያዎች ነው::
በዚህ ስሌት ከሄድን ከዛሬ 20 ዓመት በኋላ ደግሞ የት ላይ እንደምንሆን አይታወቅም:: ስለዚህ መማር ሥራ ለመቀጠር ብቻ ሳይሆን ለመኖር ራሱ የግድ ይሆናል ማለት ነው:: መማር ለመኖር የግድ መሆኑን ማህበረሰባችን ልብ ያለው አይመስልም:: ለዚህ ነው ልጆች በልጅነታቸው እንዲወልዱና ከትምህርት እንዲያቋርጡ የሚደረገው:: ይህን የትምህርት ተቋማት ሊሰሩበት ይገባል::
የሴቶች መብት ላይ የሚሰሩ ተቋማትም የቀሚስ ማጠር እና መርዘም ላይ ከሚጨቃጨቁ ያለፍላጎታቸው የሚዳሩ ልጆች ላይ ሊሰሩ ይገባል:: መብት የሚባለው ነገር የሚገባቸው መጀመሪያ የትምህርት ዕድል ሲያገኙ ነው:: የሴት ልጅ ዕጣ ፋንታ ሚስት መሆን እና ልጅ ወልዶ ማሳደግ ብቻ እስከሚመስል ድረስ ያለዕድሜያቸው የሚዳሩ ልጆች አሉ::
በአጠቃላይ ሴቶች ልጆች ላይ የሚደረገው ጫና አሁንም አልተቀረፈም:: አገር አቀፍ ፈተናዎች ላይ ለዜና የበቁት ልጆች ማሳያ ናቸው፤ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች (አንደኛ ደረጃ ጨምሮ) የሚከሰት ነው:: የሚከሰተውም ትልልቅ እናቶች ሆነው ሳይሆን በልጅነታቸው እየተዳሩ ነው፤ በፍላጎታቸው ሳይሆን በአካባቢ ጫና ነው:: ስለዚህ መንግሥትም ሆነ የሲቪክ ተቋማት በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2015