ከ‹‹ኦሮማራ›› መንደር ሲያደብርና ዋዩ ወረዳ እንገኛለን። ልዩ ስሟ ደግሞ ሲያደብር ይባላል። በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ትገኛለች። በዕለተ ቅዳሜ ነበር ወደ ሥፍራው ያቀናነው፤ ለዚያውም ሲያደብር በሞቀ ገበያ ውስጥ ሆና። ቅዳሜ ገበያ ቆለኛ እና ደገኛ የሚከትምባት፤ ኦሮሞ እና አማራው የቋንቋ ልዩነት ሳይገድበው ተገበያይቶ የሚመራረቅበት ማራኪ አካባቢ ናት። የአካባቢው ሰው እራሱን የኦሮሞና አማራ ወዳጅነት ‹‹ኦሮማራ›› እንደ እኛ የተገበረውና ለዘመናት የኖረው የለም ይላሉ።
ሰፈሩ በቁልቋል አጥር እምር ያለ ነው። አገሩ ለም፤ ሰው ሠላም ነው። ከገጠር ድባብ ወጥታ የከተማ መንፈስ ለመላበስ በምትውተረተረው ሲያደብር ቀበሌ የአንድ ሰዓት ቆይታ አደረግን። በአካባቢው የሲያደብር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከዋናው መንገድ አጠገብ ይገኛል። ይህ ትምህርት ቤት በርካታ ስመጥር ሰዎችን ስለማፍራቱ ሰማን። አብነት ፍለጋም ከመንደሩ ወደ አንዱ ቤት አመራን።
በገጠር ኑሮ ስምንት ልጆቻቸውን በከፍተኛ ማዕረግ አስመርቀው አሁን ብቻቸውን ስለሚኖሩ ባለትዳርና የማያቆመው የለውጥ ትግላቸውን ዳሰን በአዲስ ዘመን ቅዳሜ ጋዜጣ እንዲህም ይኖራል አምዳችን እንግዳ ልናደርጋቸውና አኗኗራቸውን በብዕር ልንዳስስ ወደድን። ወይዘሮ የሺ ታዬ እና አቶ አጎናፍር አበበ ይባላሉ። ወይዘሮ የሺ ታየ በ60ዎቹ አቶ አጎናፍር ደግሞ በ80ዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ። ወደ አካባቢው ስንደርስ የወይዘሮ የሺ የቅርብ ቤተሰባቸው ሞቶ ሐዘን ላይ እንደሆኑ ሰማን። ምንም እንኳን በሀዘን ስሜት ውስጥ ቢሆኑም ተሞክሯቸውን እና አኗኗራቸውን ለማካፈል ይሁንታቸውን አልነፈጉንም።
ሴትየዋ ጠንካራ ናቸው፤ ጥርሳቸው ፈገግ ሲል የውበት እመቤት ናቸው። ሲቆጡም እንደ አራስ ነበር ያደርጋቸዋል፤ ሥራም ከአንጀት ሲሆን ያስደስታቸዋል። የማይፈፅሙት ካልሆነ መጀመር አይወዱም። አቶ አጎናፍርም ለችግር እጅ የማይሰጡ፣ ነገን አሻግረው የሚመለከቱ እንደ አንበሳ ልባም፤ በአካባቢያቸው የተመሰገኑ ታታሪ አርሶአደር ናቸው። ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከቆ ላደጋ ረግ ጠዋል፤ ሌት ከቀን ከኑሮ ጋር ተፋልመዋል። ፀሐይና ቁር ተፈራርቆባቸዋል፤ ችግር ክንዱን አበርትቶባቸዋል።
ግን ችግር ክንዱን ባፈረጠመ ቁጥር እርሳቸው ወኔያቸው እየበረታ፤ ነገ የቤተሰባቸው ሕይወት የሰመረ እንዲሆን ፈግተዋል። አቶ አጎናፍር እና ወይዘሮ የሺ ኑሮ ወደፈለገው መስመር ሲገፋቸው አልገፋ ብለው ጫናውን ተቋቁመው የስኬትን መንገድ ለራሳቸውም ለልጆቻቸውም አሳይተዋል። በተለይም ለትምህርት ያላቸው ፍቅር ወደር የለውም። እነዚህ ባል እና ሚስት ለራሳቸው ከፊደል ጋር ሳይተዋወቁ ልጆቻቸውን በሙሉ በዘመናዊ አስኳላ አዘምንዋል።
ወደ እውቀት ገበታ
ወይዘሮ የሺ እና አቶ አጎናፍር አለመማራቸው ውርስ ሆኖ ለልጆቻቸው መሸጋገር እንደሌለበት ለራሳቸው ቃል ገብተዋል። ከምዳጃው ዳር እሳት እየሞቁ መክረዋል። እንጨቱ በእሳት መስዕዋት ሆኖ ሙቀት ሲሰጣቸው፣ እነርሱም በኑሮ ውጣ ውረድ በእሳት ተፈትነው ልጆቻቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ወስነዋል። አቶ አጎናፍር እና ወይዘሮ የሺ ባለመማራቸው ብዙ ፈተና ደርሶባቸዋል ችግሮችን አሳልፈዋል። የጨለማ ሕይወት እንዲገፉ አንፈልግም የሚለው የጋራ ሃሳባቸው ነው። እናም የመጀመሪያ ልጃቸውን ወደ ትምህርት ቤት ላኩት። በእርግጥ መጀመሪያ ላይ የነበራቸው ሃሳብ እስከሚያድጉ ድረስ ፊደል ይቁጠሩ ብለው እንጂ በማዕረግ ተመርቀው ወደ ሥራ ዓለም ይገባሉ ብለው አልነበረም። በተለይም መጀመሪያዎቹ ሁለት ወንዶችጉልበታቸውን መጠቀም ፈልገው ነበር። ብቻ አንዱን ልጅ ትምህርት አስጀመሩት። ግን አንዱን ልጅ ብቻ እያስተማሩ ሌላውን ማስቀረት የአድላዊነት ስሜት ፈጠረባቸው። «ከልጅ ልጅ ቢለዩ አመትም አይቆዩ» ሆነባቸውና ሁለቱንም ወንዶች አንደኛ እና ሁለተኛ ክፍል ፊትና ኋላ ሆነው ትምህርታቸውን ጀመሩ። ወንዶች በትምህርታቸው እሳት ሆኑ። የእነርሱ መጎበዝ ስድስት ተከታይ ሴቶች እንዲማሩ በር ከፈተ። ልጅ እንዳር አማችም ይኑረን የሚለው ሃሳብ ተሰረዘ። በእርግጥ ‹‹ልጅህን ለልጄ›› በሚል የገጠር ብሂል ለሴቶቹ ልጆች ባሎች ይመጡ ነበር። ግን ከትምህርታቸው የሚበልጥ አልነበረምና ይሁንታን ያገኙ አልነበሩም። በእርግጥ አንድ ጊዜ እንደ ብረት አጥር የጠነከረ አማች ፍለጋ ሞክረው ነበር። በመጀመሪያ ልጃቸው የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለች አግብታለች። የኋላ ኋላ ግን ትዳር ውስጥ ሆና የሚደርስባትን ፈተና ሲመለከቱ አማች በአፍንጫችን ይውጣ፤ ይልቁንም ተምረው ራሳቸውን ያሸንፉ አሉ። እኛ ለልጆቻችን ባል ወይንም ሚስት መምረጥ ሳይሆን እነርሱ ይምረጡ ሲሉ ወሰኑ። ወይዘሮ የሺ ሁኔታውን ሲያስታውሱት «ሎጋው ሽቦ ብለን ልጆቻችን መዳር እንችል ነበር። የብረት መዝጊያ የሆነ አማች ቢያስፈልገን በዚህ ገጠር ውስጥ ጥዋትና ማታ ባል እንደ ጉንዳን ይርመሰመስ ነበር›› ይላሉ። ግን የልጆቻችን የነገ ዕጣ ፋንታ በራሳቸው እንዲወስኑ ማሰብና ዕድሉን መስጠት ስለነበረብን አላደረግነውም።
ትዳርን ያቃናች ስልጠና
አቶ አጎናፍር እና ወይዘሮ የሺ «ለውጥን የማይቀበል ሰው፤ ሕይወቱ አይለወጥም» የሚል እምነት አላቸው። እናም ከለውጥ ሲመጣ ለመለወጥ መዘጋጀት የሕይወትን መስመር ያቀናል ይላሉ። ወይዘሮ የሺ ስብሰባ የሚባል ነገር አያውቁም ነበር። ግን በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ለአምስት ቀናት በቤተሰብ አያያዝ፣ በማህበራዊ ሕይወትና ለውጥን ተቀብሎ መተግበር በሚል ርዕስ ለአምስት ቀናት የወሰዱት ስልጠና ሕይወታቸውን እንዳቃናው ይናገራሉ። በተለይም በስብሰባው ላይ ሴት ልጅ እንዴት ማስተማር እንደሚቻል፣ ማህበራዊ ሕይወት እንዴት እንደሚመራ ተምረዋል። አዳዲስ ሃሳቦችንም ስለመቀበል እውቀት ገብይተውበታል።እርሳቸው ፊደል ባይቆጥሩም፤ ሁሉን ነገር በጭንቅላታቸው ከትበው ይይዙታል። ስልጠናው ለመፍረስ ቋፍ ላይ ነየበረ ትዳራቸውን እንደታደገም ያስታውሳሉ።
እንዴት አስተማሩ?
አብዛኞቹ ልጆቻቸውን ሲያስተምሩ ጫማ አያምራቸው፤ጌጥ አይናፍቃቸውም። ወይዘሮ የሺ አራስ ቤት ሆነው ስለልጆቻቸው ያስባሉ። ትምህር በሰዓት ስለመሄዳቸው ምግብ ስለመመገባቸው ይጨነቃሉ። ሥራው ሳይሆን ትምህርታቸው ያጓጓቸዋል። ታዲያ ልጆቹም የዋዛ አልነበሩም። ከቤተሰቦቻቸው ጋር በዓይን ጥቅሻ የሚግባቡ፤ በልብ ትርታ የሚናበቡ ናቸው። እያንዳንዷ ስራም በእቅድ ነበር የሚሰሩት። እነዚህ ቤተሰቦች በሚሆነውና እና እየሆነ ባለው ነገር ይወያያሉ። ለሥራም መርሐ ግብር ያወጣሉ።የሳምንቱ የሥራ ክፍፍልና የስምንቱም ልጆች ስም በግርግዳ ላይ ይለጥፋሉ። አንደኛው ወጥ ሲሠራ፤ ሌላኛው ውሃ ይቀዳል። አንደኛው ከብት ሲጠብቅ ሌላኛው የከብት መኖ ይሰበስባል። የጥናት መርሐ ግብሩም እንዲሁ በግርግዳ ላይ የተለጠፈ ነው።
የማህበራዊ ሕይወት መስተጋብሩም የጠነከረና በመርሀ ግብር የሚመራ ነው። ከዚህ በዘለለ ግን አንድም ሰው ሌላውን ማዘዝ አይችልም። በዚህ ቤት ሰዓት ይከበራል፤ ህግ ይተገበራል። ወለም ዘለም የለም። ለቤቱ ህግና ደንብ መገዛት ግድ ነው። ይህም በመሆኑ ጊዜን አክብረው ጊዜም በተራው መልሶ አክብሯቸዋል። ንጉስ የተባለው ልጃቸው ከቤቱ የመጀመሪያው ተመራቂ ነበር። ታዲያ ወይዘሮ የሺ እና ባለቤታቸው ያንን ቀን ሲያስታውሱ ‹‹ዳግም የተወለድን ያክል ተሰምቶናል›› ይላሉ።
ያች ቀን ለቤተሰቡ መልካም መንገድ የተከፈተበት ቀን እንደሆነ ሲያስቡ በደስታ ይፍከነከናሉ። ከቤቱ የንጉስ መመረቅ ለታናናሾቹ መሰረት ጣለ፤ የመለወጥ ጉጉትም ተከለ። ታናሾቹም የእርሱን ፈለግ ተከትለው ለመውጣት ጥረታቸው ጨመረ። ንጉስም ታናናሾቹን በማገዝ ላይ ተጠመደ። ከቤቱ መጀመሪያው ተመራቂ ሆኖ ከበታቹ ለሚገኙት ሰባት ልጆች ኃላፊነት ወሰደ። መጨረሻ ተመራቂ ልጃቸው ትዕግስት ናት። የቤቱን ስኬት በንጉስ ጀምረው በትዕግስት አጠናቀዋል።
ገጠመኝ
መቸም በገጠሪቱ አገሪቱ ክፍል እበት መዛቅ፣እንስሳት መመገብ፣ ማሠማራቱ ብቻ ከክረምት እስከ በጋ እረፍት አልባ ደደርጋል። ‹‹አርሶ አደር የአገር ማገር›› የሚለውስ ከዚህ የመነጨ አይደለምን? በአንድ ወቅት ወይዘሮ የሺ ወፍጮ ቤት እህል አስፈጭተው ሲመለሱ ለጠላ የሚሆን አሻሮ በጀርባቸው ተሸክመው ነበር። ይሁንና ድካሙ በጣም ሲጫጫናቸው በሰፈራቸው አቅራቢያ ሲደርሱ ‹ተመልሼ እወስዳለሁ› ብለው ከአንዱ አጥር ጥግ አስቀምጠውት ወደ ቤት ይገባሉ። ከአህዮቹ ጀርባ ላይ ያለውን ዱቄት ካሳረፉ በኋላ ወዲያኑ ሌላ ሥራ ይጀምራሉ። ታዲያ ዱቄቱ ከአጥራቸው ጥግ የተመለከቱት ሰው ነገሩን በበጎ አልተመለከቱትም ነበር። ይህ ሆን ተብሎ ለ‹‹ሟርት›› የተደረገ ነው ሲሉ በየሰፈሩ ዞረው አውጫጪኝ፣ እውነቱ ይታወቅልኝ አሉ።
ነገሩ ከወይዘሮ የሺ ጆሮ ደረሰ። ‹‹እረ የእኔ ነው፤ ትናንት ከወፍጮ ቤት ስመጣ ደክሞኝ አስቀምጨው ሥራ ሲበዛብኝ ተመልሼ ሳልወስደው የረሳሁት ነው›› ብለው ነገሩን አቀዘቀዙት። ነገር ግን ክስተቱ በክፋት መታሰቡ ክፉኛ እንዳሳዘናቸውና ስቅስቅ ብለው ማልቀሳቸውን ያስታውሳሉ። ድካሙም ስለነበር ውጭ ያስቀመጡትን እህል ረስተውት በማግስቱ መውሰዳቸውን ሁሌም ያስታውሱታል።
ጎረቤት ምን ይላል?
አንድ የልጅ ልጅ አስተምረው አስመርቀዋል። ጎረቤት የእነርሱን ጥንካሬ ተመልክተው ልጆቻቸውን ከእረኝነት ወደ ትምህርት ቤት ሰደዋል። ካለማወቅ ወደ ማወቅ ዓለም አስገብተዋል። የሰፈሩ ሰው በሙሉ፤ በታታሪነታቸው፣ ታዛዥነታቸው እና ሰው አክባሪነታቸው ያውቋቸዋል። በአስተሳሰባቸው ምጡቅ፤ ክፉ ላለመናገርም ጥንቁቅ የሆኑ ናቸው ሲሉ ይመሰክሩላቸዋል።፡ እኛም እነርሱን አይተን ልጆቻችን አስተምርን ለቁምነገር አድርሰናል። ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለእኛም ባለውለታ ሆነዋል ሲሉ፤ መነሳሳት እንደፈጠሩላቸው ይመሰክራሉ። ወደፊት ምን ያስባሉ? ከቤቱ የመጀመሪያው ምሩቅ የመጀመሪያ ዲግሪውን በቋንቋ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ እና ማስተርሱን ደግሞ በሶሾሎጂ በከፍተኛ ውጤት አጠናቋል።
ባልከው የተሰኘው ሁለተኛ ልጃቸው ደግሞ በሜዲካል ዶክትሬት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ያጠናቀቀ ሲሆን በሰርጅን ስፔሻላይዝ አድርጎ በደብረ ብረሃን ሆስፒታል እያገለገለ ይገኛል። ሦስተኛ ልጃቸው በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት ተመርቃለች። አራተኛዋ ልጃቸውም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በፊዚክስ በከፍተኛ ውጤት ተመርቃለች። አምስተኛ ልጃቸው በጤና መኮንንነት ከደብረብርሃን ዩኒቨርሰቲ በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቃ በአሁኑ ወቅት በዲላ ዩኒቨርሰቲ የሚዲሲን ትምህርት ለማጠናቀቅ ተቃርባለች።
ስድስተኛ ልጃቸው በሲቪል ምህድስና ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተምርቃለች። ሰባተኛዋ ደግሞ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል ምህንድስና ተመርቃለች። የመጨረሻዋ ልጅ ደግሞ በአካውንቲንግ ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ድግሪዋን ይዛለች። ሁሉም ልጆቻቸው ለቁም ነገር በቅተው ልክና መልክ ይዘው በአካባቢው ሲደነቁ ሲያዩ ደስ ይላቸዋል። ሁሉም ልጆቻቸው ስኬት ተጎናፅፈው ሲመለከቱ ምነው አሁንም በወለድን እያሉ ያስባሉ። ያኔ ሴት ልጅ ተምራ የት ልትደርስ ነው? እያሉ ይጨቀጭቋቸው የነበሩ ጎረቤቶቻቸውን ሲያስቡትና በወቅቱ አማች አንፈልግም ብለው በወሰኑት ውሳኔ ዛሬ ኩራት ይሰማቸዋል።
በተለይ ጥዋትና ማታ ባል ሲመጣ፤ ልጆቹ «ራሳቸውን በራሳቸው ይዳሩ እንጂ እኛ በሕይወታቸው አንወስንም» ብለው ሁሉን ነገር ለልጆቻቸው ምርጫ መስጠታቸው ዛሬ አኩርቷቸዋል። ጉብዝና ከታላቅ ወደ ታናሽ እየተላለፈ ሁሉም ስኬታማ መሆናቸው አስደስቷቸዋል። ትጋታቸውና ለልጆቻቸው አርአያ መሆናቸው ዛሬ ዋጋ ከፍሏቸዋል። አቶ አጎናፍር እና ወይዘሮ የሺ በማህበራዊ ሕይወትም የተሳካላቸው ናቸው። በእርግጥ ልጆቻቸውን ለማስተማር ሲሉ አስቸጋሪ የሚባሉ ጊዜያትን አልፈዋል።
‹‹ልጆች ማስተማር መሃሉ እሬት፤ መጨረሻው ማር ነው›› የሚሉት ወይዘሮ የሺ የወጡትን አቀበትና የወረዱትን ቁልቁለት መቸም ላይዘነጉት በህሊናቸው ማህደር አትመውታል። «የበረታ ሰው ያልፈዋል፤ ከፍሬውም ይቋደሳል። ለአንዱ እስኪቢርቶ፣ ለሌላው ልብስና እርሳስ ሲባል ሃሳብ ይበታተናል፤ ጉልበት ይዝላል። ግን ከታገሱት የማያልፍ የለምና ሁሉንም አልፍነው፤ ከታሰበው ቦታም ደረሰን» በማለት ነው ያሳለፉት ጊዜ በኩራት የሚያስታውሱት እነዚህ ሁለት ጀግኖች። አሁን ላይ እርጅና እየተጫጫናቸው ነው። ቢሆንም ከመሥራት አልተቆጠቡም፤ ከብት ያጅባሉ፣ እርሻ ያርሳሉ፣ ያርማሉ፣ ይጎለጉላሉ። ሰንበት ደግሞ ከቤት ክርስቲያን ደጅ ደርሰው ሠላምን ይለምናሉ።ከምንም በላይ ስለ አገራቸውና ልጆቻቸው የኢትዮጵያን ሠላም አብዝተው ይሻሉ። ጥዋትና ማታ ስለ አገር ይፀልያሉ፤ ብልፅግናን ይሻሉ። ትናንት በማይረታ ጉልበት፣ ዛሬ በማይረታ ማንነት ነገም ደግሞ በማያልቅ ምኞት ውስጥ ሆነው ይዋኛሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር