በዚህ ሳምንት የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሙዚየም ተመርቋል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቢሮ መሀል ላይ የተሰየመው ይሄ አዲስ ህንጻ በጣም ግዙፍ እና ውብ ነው። በእውነቱ እነዚህን ሁለት ነገሮች ማለትም ውበት እና ግዝፈትን አንድ ላይ አስተባብሮ መያዝ ቀላል አይደለምና ገንቢዎቹን ማድነቅ ተገቢ ነው። አይታችሁታል ከውጭ እንኳን እንዴት እንደሚያምር። አንድ ትልቅ የአውሮፓ ስቴድየም እኮ ነው የሚመስለው። በእውነቱ ይህን የመሰለ ውበት በአጥር እንዲከለል ባለማድረጋቸው የግንባታው ባለቤቶች ምስጋና ይገባቸዋል። አስቡት እስኪ ይህን የመሰለ ግንባታ ላይ ትልቅ የኮንክሪት ግድግዳ ገድግደውበት ሳናየው ቢቀር…በጣም አሳዛኝ ነበር የሚሆነው። አሁን ግን ግቡብኝ ግቡብኝ የሚል ተቋም ሆኗል።
ለማንኛውም ዛሬ ስለዚህ ሙዚየም አንዳንድ ነገሮች ልል እወዳለሁ። የመጀመሪያው የህንጻውን ውበት በተመለከተ ነው። አስተውላችሁ እንደሆነ የእኛ አገር ግንባታዎች ዲዛይን እና ግንባታው ጭራሽ አይመሳሰልም። አንዳንዴ እንደውም የእኛ አገር ግንባታ ከአንዳንድ ሰዎች የማህበራዊ ሚዲያ ገጽታ ጋር ይመሳሰላል። ሁላችንም እንደምናውቀው ብዙ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለጥፉትን ፎቶ ከብዙ ፎቶዎቻቸው መሀከል መርጠው እና ብዙ አርትኦት አድርገውበት ነው። በዚህም የተነሳ ብዙ ሰዎች ፎቶ ላይ ሲታዩ ሞዴል ይመስላሉ። በአካል ሲታዩ ግን ፉንጋም ባይባሉ እንኳ ፎቶው ላይ ካሳዩን ገጽታቸው የተለዩ እንደሆነ እናውቃለን። ብዙ ህንጻዎቻችንም እንደዚያው ናቸው። ከግንባታው በፊት ንድፋቸውን ስናይ ውበታቸው እጅን በአፍ የሚያስጭን ነው። የህንጻው ማማር፤ የአረንጓዴ ስፍራው ልምላሜ፤ የመኪና ማቆሚያው ስፋት፤ ያለው መጸዳጃ ቤት ብዛት ምናምን ሲታይ የሚፈጥረው ጉጉት የትየለሌ ነው። ህንጻው ሲያልቅ ግን አንድ ትልቅ የኮንክሪት ክምር ይሆንና ወይ ውበት ወይ ጥቅም የሌለው አሰልቺ ነገር ይሆናል። የሳይንስ ሙዚየሙ ግን ከዚህ የተለየ ነው። አሁን ከተመረቀ በኋላ የተነሱት ፎቶዎች ራሱ ደንበኛ ዲዛይን ነው የሚመስሉት። ግዝፈቱ ውበቱን አልቀማውም። ሁለቱንም አቻችሎ የያዘ ግሩም ህንጻ ሆኖ ተጠናቅቋል። ወደፊት ደግሞ አገልግሎቱ እንደ ግንባታው ያማረ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን።
ሁለተኛው ጉዳይ ግንባታው መመረቁን አስመልክቶ የሚሰጡ አንዳንድ አስተያየቶች ጉዳይ ነው። አገሪቱ በጦርነት ተወጥራ፤ የኑሮ ውድነት ሰማይ ነክቶ፤ በአንዳንድ ቦታዎች ድርቅ እያጠቃን የሳይንስ ሙዚየም መስራት ምን ያደርግልናል የሚል ትችት በዚህም በዚያም ይሰማል። እውነት ነው አገሪቱ አሁን በታሪኳ ከተፈተነችባቸው ጊዜያት ከባዱ ላይ ነው ያለችው። ጦርነቱም፤ ረሀቡም፤ የኑሮ ውድነቱም ሌላውም አለ። ነገር ግን ይህ ስላለ ሌሎች መሰራት ያለባቸው ነገሮች መቆም አለባቸው ወይ ነው ዋናው ጥያቄ።
ዛሬ ላይ አገሪቱ በብዙ ችግሮች ውስጥም ሆና ሰዎች ትዳር እየመሰረቱ፤ ልጅ እየወለዱ፤ እየተማሩ፤ እየሰሩ፤ እየተዝናኑ ነው። ትክክል ናቸው። ምክንያቱም ጦርነት ስላለ የግል ኑሮ መቆም አይገባውምና ነው። ጦርነት ስላለ አንማርም፤ አንሰራም፤ አናገባም፤ አንወልድም፤ አንዝናናም ብንል ለሰላም መምጣት ከምንከፍለው መስዋእት ይልቅ በራሳችን ላይ የምንፈጥረው ችግር ይበልጣል። ጦርነት አለ ብሎ ስራ ያልሰራ ሰራተኛ፤ ትምህርት ያልተማረ ተማሪ፤ ሁሉንም እቅዶቹን በይደር ያቆመ ማንም ሰው የገዛ ህይወቱን ችግር ውስጥ ከትቶ ለአገርም የሚያበድረው ችግር ይኖረዋል። ስለዚህም የሚዋጋው እየተዋጋ ሌላው ስራውን መቀጠል አለበት።
በተመሳሳይም አገር ጦርነት ውስጥ ስለሆነች መንግስት ሌላ ስራውን ትቶ ጦርነቱን ብቻ ይዋጋ ወይም ረሀቡን ብቻ ይከላከል ወይም የኑሮ ውድነቱን ብቻ መላ ያበጅ ካልን ለነገ የሚተርፍ ስራ አንሰራም ማለት ነው። ይሄ ብልሀት አይደለም። እርግጥ ነው ሰላም ከሁሉ ነገር ቀዳሚው ነው። የሰዎች በሕይወት የመኖር ጉዳይም ከማንኛውም ጉዳይ ይቀድማል። ነገር ግን ዛሬ ሰላም ለማስከበር ጥረን ቢሳካልን ወይም የኑሮ ውድነቱን መግታት ቢሰምርልን እንኳ ዛሬ ያልሰራናቸው የቤት ስራዎች ለነገ ሌላ ችግር ሆነው ይጠብቁናል። ስለዚህም የሳይንስ ሙዚየምም ሆነ ሌሎች ስራዎች አሁን ላይ የሚሰሩ እንጂ ለከርሞው ስራ ስንፈታ እንሰራቸዋለን ብለን የምናስቀምጣቸው ስራዎች አይደሉም።
በነገራችን ላይ ስለ ሰላም የሚያስብ ሰው ለጦርነት መዘጋጀት አለበት ይላሉ ልሂቃን።ለጦርነት ዝግጅት የሚደረገው በጦርነት ውስጥ ሆኖ ሳይሆን በሰላሙ ጊዜ ነው።ለሰላምም ዝግጅት የሚደረገው በሰላም ወቅት ሳይሆን በጦርነት ወቅት ነው። በዚህ መልኩ ነው ጦርነትን ማስቀረት እና ሰላምን ማጽናት የሚቻለው። ስለዚህም ቀጣዩ ጦርነት በየት በኩል እንደሚመጣ የሚያውቅ ሰው ከአሁኑ ለሰላም ዝግጅት ያደርጋል። የዓለም አካሄድ እንደሚያሳየው ቀጣዩ ጦርነት የሚካሄደው በቴክኖሎጂ ነው። አብዛኛው ውጊያ የሳይበር ነው። ይህን የሳይበር ውጊያ መመከት እና ራስን ማስከበር የሚቻለው ደግሞ ጦርነቱ ከተከፈተብን በኋላ አይደለም። በጦርነት ውስጥ ሆነን ተዋጊ ምልመላ እና ስልጠና አናካሂድም። አሁን ላይ ነው አገርን የሚመክት ተዋጊ የምናዘጋጀው። የሳይንስ ሙዚየሙም ቀጣዮቹን የሳይበር አርበኞች የምንመለምልበት እና የምናሰለጥንበት የከተማው ብር ሸለቆ ወይም የሳይንሱ ወታደራዊ ካምፕ ነው ልንል እንችላለን። በተመሳሳይ ረሀብንም ሆነ የኑሮ ውድነትን ወይም ሌላ አይነት ችግር መመከት የምንችለው በዋነኝነት ሳይንስን እንደ ትጥቅ በመያዝ እንጂ የእለት የእለቱን ችግር ብቻ ለመቅረፍ በመንደፋደፍ አይደለም።
ሌላኛው ስለ ሳይንስ ሙዚየም የተመቸኝ ነገር ያረፈበት ቦታ ነው። ሳይንስ ሙዚየም ብቻ ሳይሆን አብርሆት ቤተ መጻህፍት እና ወዳጅነት አደባባይ በከተማው ደላሎች ዐይን ግንባር የሆኑ ቦታዎች ናቸው ተብሎ ለዓመታት በከፍተኛ ንቃት ለሽያጭ ሲጠበቁ የነበሩ ናቸው። አድዋ ሙዚየምንም እዚያው ውስጥ ልንጨምረው እንችላለን። እነዚህ ቦታዎች ለባለሀብት ቢሸጡ ቢበዛ ሊሆኑ የሚችሉት ሆቴል ወይም የገበያ ማእከል ነው። ከዚያ ያለፈ እንደማይሆኑ የከተማው ባህል ያሳያል። ከነዚህ አንጻር የተሰራበትን ነገር ስናይ በጠቀሜታውም ይሁን በውበት ብሎም በፋይዳ በጣም የተሻለ ነው ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል።
በአጠቃላይ ሲታይ የሳይንስ ሙዚየሙ እንደ አገር እጅጉን የሚጠቅመን ምርጥ ነገር ነው ብለን በድፍረት እንናገራለን።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም