ከስምንት የቤተሰብ አባላት ውስጥ እርሳቸው ሶስተኛ ልጅ ናቸው። እንደ እድሜ እኩዮቻቸው ትምህርት ቤት ቢገቡም ስድስተኛ ክፍል ሲደርሱ አዲስ የህይወት መንገድ ተጋረጠባቸው። ገና በአስራ አራት ዓመታቸው ለቤተሰብ ኃላፊነት ታጭተው በትዳር መታሰር ግድ ሆነባቸው። ለጊዜው ትምህርቱ ቢቋረጥም ለትምህርት ካላቸው ብርቱ ፍላጎት የተነሳ ከትዳር በኋላም በማታው ክፍለ ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን መማር ችለዋል። በኋላም የቤት ውስጥ ስራውን እና ልጆች ማሳደጉን እየከወኑ ዲፕሎማ እና ዲግሪያቸውን ይዘዋል። ወይዘሮ ሙሉ አንለይ ይባላሉ። ውልደት እና እድገታቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድባጤ አባባቢ ነው።
አሁን ላይ ለእጃቸው ልስላሴ ሳስተው ከስራ ወደኋላ አላሉም። በርበሬ እና ቅርንፉዱን አሊያም ቁንዶ በርበሬውን እየቀነጣጠሱ በወጉ አበጃጅተው ለውጭ ገበያ ጭምር ያቀርባሉ። የስራ ህይወታቸው የጀመረው ከማጀት ቢሆንም ፍኖተ ሰላም ከተማ ማዘጋጃ ቤት በጽዳት ስራ በመቀጠር የመንግሥት ስራን ተቀላቅለዋል። በወቅቱ ስራ ማፈላለጊያ ይሆናል በሚል የማዘጋጃ ቤቱን ወለሎች እና የተለያዩ ክፍሎች ሲያጸዱ በዛው እንደማይቆዩ ውስጣቸውን ይነግራቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን ህልማቸውን ለማሳካት የሚያግዛቸውን ዕውቀት ለመገብየት በማታው ትምህርት ክፍለ ጊዜ ኮሌጅ ገብተው ከመማር ያገዳቸው አልነበረም። እውቀታቸው ሲጨምር ከጽዳት የጀመረው የስራ መደብ ወደ መዝገብ ቤት ሰራተኛነት ተሻገረ። ሰፊ ጊዜያቸውን ማዘጋጃ ቤት ስለሚያውሉ ልጆች የመንከባከቡን ስራ በትዳር አጋራቸው ድጋፍ አልፈውታል።
በኋላም ከመዝገብ ቤት ስራ በማዘጋጃ ቤቱ ለሚታዩ ፊልሞች ወደ ትኬት ቆራጭነት ተሸጋገሩ። ትምህርታቸውንም በአካውንቲንግ ዲፕሎማ ተመርቀዋልና ወደ ፋይናንስ አስተዳደር ክፍል እድገት አግኝተው ተረጋግተው መስራት ቀጥለዋል። ልጅ ወልዶ መሳሙ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚያው ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። አሁን ህይወት ወደ ደብረማርቆስ መርታቸዋለች። በደብረማርቆስ ከተማ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያ ሴክሬታሪያት በኦዲተርነት ተቀጥረው ሰርተዋል። የኦዲተርነት ስራው ግን ሒሳብ ጎድሏል አልጎደለም እየተባባሉ ከሰዎች ጋር መስራቱ ስለማይቀር ብዙም አልወደዱትም። ከሰው ጋር የሚያጋጭ የስራ አይነት ነው ብለው ስላሰቡም ስራውን ለቀው በግላቸው ለመንቀሳቀስ ልባቸው ፈልጓል። ይሁንና ደብረማርቆስ ላይ ንግድ ከመጀመር ይልቅ አዲስ አበባ ላይ ቢሆን ምርጫቸው ነበር። እናም ወደ አዲስ አበባ የስራ ዝውውር ጠይቀው ቤተሰባቸውን ጠቅልለው ወደ አዲስ አበባ ገቡ።
25 ዓመታትን በመንግሥት ቤት ከሰሩ በኋላ የትኛው የንግድ ሙያ ያዋጣኛል? ብለው ማጥናት ጀመሩ። ተዝቆ የማያልቀውን የአካባቢያቸውን ሀብት ቅቤና ማር ንግድ መጀመር እንዳለባቸው ወስነዋል። አዲስ አበባ ቄራ ጎፋ ገብርኤል አካባቢ ከሰባት ዓመት በፊት በአንድ ሺ ስምንት መቶ ብር በተከራዩት አነስተኛ ንግድ ቤት ገበያውን ጀመሩት። ወንድማቸው የተወሰነ ገንዘብ አበደሯቸውና እርሳቸውም ቀድሞ በአማራ ክልል ሲሰሩ የሚያውቋቸውን ንፁህ ቅቤ እና ማር እንዲልኩላቸው ጠይቀው አስመጡ። በመጀመሪያው ቀን ሽያጫቸው ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ።
በዕለቱ አንድ ወይም ሁለት ሰው መጥቶ ሊጠይቀኝ ይችላል ብለው የገመቱት ገበያ የሁለት ሺ ብር ሽያጭ አስመዘገቡ። ይህም ስለንግዱ አዋጭነት የነበራቸውን ግምት በእጅጉ እንዲንር አደረገላቸው። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የኦዲተርነት ስራቸውን አልለቀቁም ነበር። ይልቁንም ንግዱ ካላዋጣኝ እመለሳለሁ ብለው የሶስት ወር ፍቃድ ጠይቀው ነበር የወጡት። ንግዱ አዋጭ መሆኑ ያበረታታቸው ወይዘሮ ታዲያ ማር እና ቅቤውን ከአገር ቤት እያስመጡ በየሆቴሎች እና ቤት ለቤት እየዞሩ ማስተዋወቁን ተያያዙት። ምርት አስመጪም ሻጭም እራሳቸው ሆነው የጀመሩት ንግድ ከኦዲተርነት ስራቸው የበለጠ ገቢ እንደሚያስገኝ በተግባር በመረዳታቸው የቅጥር ስራውን ከነጭራሹ ተውት። በተጨማሪ በሚያስመጡት ማር ጠጅ እየጣሉ ለሰርግና ለድግስ ማቅረብ ጀመሩ።
እራሳቸው በበርሜል የጣሉትን ጠጅ ለበዓል ወቅት በሱቃቸው በሊትርና በግማሽ ሊትር እየቀናነሱ መሸጡንም ተለማምደዋል። «አንድ ጊዜ ንግድ ውስጥ የገባ ሰው የምርት አይነቱን እያሰፋ ገቢውን ስለመጨመር እንጂ የወር ገቢውን እያሰበ አይጠብቅም» የሚሉት ወይዘሮ ሙሉ፤ ይልቁንም ተቀጥረው የሰሩበትን ያለፈ ጊዜ በቁጭት እያሰቡ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ሀቀኛ አማራጮችን ስለመጠቀም ያስባሉ። ከቅቤ እና ማር ንግዱ በተጨማሪ የቅመማ ቅመም፤ የበርበሬና ሽሮ በአጠቃላይ የባልትና ውጤቶችን ለገበያ ቢያቀርቡ የተሻለ እንደሚሆን ተረድተዋል።
ቀድሞ ንግድ እየሰሩ ቢሆን በአነስተኛ ንግድ ተደራጅተው ቀበሌያቸውን ቦታ ይጠይቁ ነበርና ተሳክቶላቸው አንድ ዓመት ከሰሩ በኋላ መስሪያ ቦታ ተሰጣቸው። አሁን ቀረፋው፣ጤና አዳሙ፣ ኮረሪማው፣ እርዱ፣ በርበሬውን እና ሽሮውን እንዲሁም የተለያዩ የቅመማ ቅመሞችን ያካተተ የባልትና ውጤቶችን ማምረት የሚያስችል ቦታ አገኙ። የባልትና ውጤቶች ንግዱ እየተስፋፋ ሲመጣ ግን በእርሳቸው ጥረት ብቻ የሚሸፈን አለመሆኑን ተረዱ። በመሆኑም ከስድስቱ ልጆቻቸው መካከል ሶስቱን ለማሳተፍ በመወሰን የንግድ ሁኔታቸውን አስረዷቸው። አንደኛው ልጃቸው በፋርማሲ ሙያ፣ ሁለተኛው ደግሞ በጋዜጠኝነት ሶስተኛው በፎቶግራፍ ሙያ ተመርቀዋል።
በመሆኑም ሁሉንም ከሙያቸው ይልቅ ንግዱ አዋጭ መሆኑን በማሳመን ከእርሳቸው ጋር እንዲሰሩ እያደረጉ ነው። ልጆቻቸው የተቀላቀሉበት የቅመማ ቅመም ስራ የገበያ አድማሱን አስፍቷል። በ«ሙሉ ባልትና» ስም እየታሸጉ የሚሸጡ የቅመማቅመም ምርቶች ከኢትዮጵያም አልፈው ወደውጭ አገራት የሚሸጡበትም መንገድ ተፈጥሯል። በአንድ አጋጣሚ የወይዘሮ ሙሉ ጓደኛ ደቡብ አፍሪካ ከሚነግዱ ሰዎች ጋር ለምን አላስተዋውቅሽም የሚል ሃሳብ ያነሳሉ። በሁኔታው ይስማሙና ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎቹ ከደቡብ አፍሪካ ሲመጡ ከወይዘሮ ሙሉ ጋር ይተዋወቃሉ። ከዚያም የተለያዩ የቅመማቅመሞችን ደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ ደንበኞች ለማቅረብ ስምምነት አድርገው ይለያያሉ። በዚህ ስምምነት መሰረት ወይዘሮዋ ምርታቸውን በአንድ አንድ ኪሎ አሽገው በካርቶን እያደረጉ የድርጅታቸውን ስምና አርማ ለጥፈው በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መላክ ጀመሩ።
ተቀባዮቹም የምርቶቹ ጥራት ስላስደሰታቸው እና ገበያውም ስላዋጣቸው በየጊዜው እንዲልኩላቸው እየጠየቁ ደንበኝነታቸውን አሳደጉ። ወይዘሮ ሙሉ በሶስት ወር ውስጥ እስከ አምስት ሺ ኪሎ የታሸጉ የባልትና ውጤቶችን በአውሮፕላን ወደ ደቡብ አፍሪካ መላኩን ተያይዘውታል። ከደቡብ አፍሪካ ተሻግረውም ወደ አውሮፓ ምርታቸውን ለማሸጋገር አልተቸገሩም። የምርቱን ጥራት ቀምሰው የተረዱት ኤርትራዊ ነጋዴ ወይዘሮ ሙሉን ይተዋወቃሉ። ኤርትራዊቷ ስዊድን አገር ነጋዴ ናቸውና የእርሳቸውን ምርቶች መሸጥ እንደሚፈልጉ ይገልጹላቸዋል። ስራ ፈጣሪዋም በጥራት የተዘጋጁ ምርቶችን ተቀባይ ወዳገኙባት ወደ ስካንዴኒቪያ አገር መላክ ጀምረዋል። በየጊዜው አዳዲስ የውጪ አገራት ደንበኞችን እያፈሩ ነው።
ለዚህም ደግሞ የምርት ጥራታቸው ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ ይናገራሉ። እስከአሁን በቅመማ ቅመምና ከባልትና ምርቶች የወጪ ንግድ 52 ሺ የአሜሪካን ዶላር ለአገራቸው አስገኝተዋል። በዚህ ስራቸውም ከሁለት ዓመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተዘጋጀ የሽልማት ስነስርዓት በታታሪነታቸው የሶስተኛ ደረጃ ተሸላሚ ነበሩ። የበርበሬ ባልትና የውጪ ንግዳቸው ላይ ግን የአፍላቶክሲን ምርመራ የሁልጊዜ ስጋት ሆኖባቸዋል።
«በርካታ ላኪዎች በኮንቴይነር ጭነው የላኩት የባልትና ምርት አፍላቶክሲን መጠኑ ከፍተኛ ነው ተብለው በኮንቴይነሩ እንደተመለሰባቸው አውቃለሁ» የሚሉት ወይዘሮ ሙሉ እርሳቸውም ላይ ይህ ችግር እንዳይፈጠር ስጋት ውስጥ ናቸው። አፍላቶክሲን የተባለው ንጥረ ነገር ከመጠን በላይ በምግቦች ውስጥ መገኘት ለካንሰርና መሰል በሽታዎች እንደሚያጋልጥ ባለሙያዎች ስለሚገልጹ ተቀባዮቹ የላብራቶሪ ምርመራ ውጤቱ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ያደርጋሉ። አብዛኛውን ጊዜ በርበሬ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች ደግሞ ሚዛን እንዲያነሳላቸው ውሃ ስለሚያስነኩት የአፍላቶክሲን መጠኑን ይጨምረዋል። «እኔ ግን ይህን ችግር ስለማውቅ ከጎጃም አምራች ገበሬዎች ዘንድ በርበሬውን ተቀብዬ ነው የማዘጋጀው»ይላሉ።
በመሆኑም የህገወጥ ነጋዴዎች ተግባር ካልተገታ የባልትና ውጤቶችን በውጭ ገበያ ያላቸው ተቀባይነት ይቀንሰዋልና መንግስትም ትኩረት እንዲያደርግበት ይጠቁማሉ። አሁን ላይ በጥንቃቄ ከአምራች ወስደው በሚያዘጋጁት ባልትና የደንበኛ ቅሬታ ቀርቦባቸው አያውቅም። ነገር ግን የመብራት መጥፋት እና መቆራረጥ ለእርሳቸው ስራ ፈተና ሆኖ ቆይቷል። በተለይ ስራውን በጀመሩ ሰሞን በርበሬ ሲያስፈጩ መብራት በመቆራረጡ ሁለት ኩንታል ሙሉ በተቃጠለባቸው ወቅት ስራው ላይ ኪሳራ እንደፈጠረባቸው አይረሱትም። ንዴታቸውን ዋጥ፣ ወገባቸው ጠበቅ አድርገው ሰርተው ኪሳራቸውን መልሰውታል።
አሁን ላይ የቅመማ ቅመም ምርቶችን ለማዘጋጀት የሚያስችል ወፍጮ ማሽን ለመትከል ወጥነዋል። ሶስት ልጆቻቸውን ጨምሮ ስድስት ሰራተኞች ያላቸው ወይዘሮ ሙሉ፤ትዕዛዝ ከመጣላቸው በፍጥነት እስከ ሁለት ሺ ኪሎግራም የባልትና ውጤቶች የማምረት አቅም እንዳላቸው ይናገራሉ። እዚህ ደረጃ የደረሱት ደፍረው ንግዱን በመጀመር እና ጥራት ያለው ምርት በማቅረባቸው ነው።
በዚህም አዲስ አበባ ውስጥ ከኪራይ ቤት ወጥተው ቦታ ገዝተዋል። ቦታው ላይ ባለሶስት ወለል ዘመናዊ ቤት ገንብተው ጥሪት አፍርተዋል። በተጨማሪ ለምርት ማመላለሻ የሚሆን አንድ የቤት መኪና እና ለቀጣይ ንግዳቸው የሚሆን በቂ ገንዘብ አላቸው። ቀጣይ እቅዳቸው ሰፊ ቦታ ላይ የቅመማ ቅመም ምርቶችን በማዘጋጀት ለተለያዩ የውጭ አገራት ገበያዎች ማቅረብ ነው። «ከተሰራ መለወጥ ይቻላል፣ ሀቀኛ ነጋዴ ገበያውን ማምጣት ባይችል እንኳን የምርትና አገልግሎቱን ጥራት የሚያዩ ደንበኞች ራሳቸው ይቀርቡታል» የሚል እምነት አላቸው።«የምግብ ምርቶችን ለማዘጋጀት ያሰቡ ካሉ ስለጥራቱ እና ስለጣዕሙ ተጨንቀው ከሰሩ ትርፍ መኖሩ አይቀሬ ነው» የሚለው ማጠቃለያ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2011
ጌትነት ተስፋማርያም