በእጃቸው የያዙትን የምሳ ዕቃ እንዳጠበቁ በሀሳብ ይናውዛሉ። አስተውሎ ላያቸው ገጽታቸው በእጅጉ ያሳዝናል። የዕድሜ ጅረት ያለፈበት አካላቸው የትናንቱን ውጣውረድ እየመሰከረ ነው። በአዛውንቱ ውስጠት ብዙ ድካም መኖሩ ያስታውቃል።
አንዳች ቃል ሳይተነፍሱ እንኳ ስለማንነታቸው መገመት አይቸግርም። እሳቸው እስከዛሬ በበዛ ችግር ተንገላተዋል። በመከራ ተፈትነዋል። ዛሬም ቢሆን ከዚህ እውነት የራቁ አይደሉም። ከኑሮና ሕይወት ትንቅንቅ ይዘዋል። ለመኖር ሁሌም ይታትራሉ፣ ላለመውደቅ ይታገላሉ። በደከመ አካላቸው፣ በበረታ ማንነታቸው።
የእጃቸው ምሳ ዕቃ ምግብ ብቻ አልያዘም። ከቋጠሮው ጀርባ የሚነገር ታሪክ አለው። በውስጡ ያለው ጸጋ እስትንፋስን ሊቀጥል፣ አካልን ሊያቆም ሀይል ሆኗል። ውስጡ ያለው በረከት ለሌሎች ተኝቶ መነሳትና ውሎ ማደር፣ ቁራጭ ተስፋ ነው። ቋጠሮው ሲፈታ የተራቡ ዓይኖች ይጠግባሉ። ቋጠሮው ለእይታ ቢያንስም ትርጉሙ ሰፊ ነው። የውስጡ ሲሳይ ለሚሹት ሁሉ ዛሬን ያሳድራል፣ ነገን ያሻግራል። ከዚህ እውነት በስተጀርባ የአዛውንቱን ጨምሮ የብዙ ምስኪኖች ታሪክ ይገለጣል። የአብዛኞቹ ሕይወት በመከራ የታሸ፣ በችግር የተፈነ ነው። ያለፉ በማይመስሉ ክፉ ቀናት የተከበበ።
ቅድመ- ታሪክ
ሰበታን አለፍ ብሎ ከሚገኘው ጌቻ ቦረጃ የገጠር ቀበሌ በርከት ያሉ ህጻናት ሲቦርቁ ይውላሉ። ከመስክ ከእርሻው፣ ከወንዝ ከጋራው፣ መሀል ሁሌም ዓለም ሲያልፍ መዋሉ ብርቅ አይደለም። ልጆቹ ከብቶችን እያገዱ፣ ይጫወታሉ፣ ያንጎራጉራሉ። ሲሻቸው እየጨፈሩ፣ ሲላቸው እየዘፈኑ ቀኑን ያጋምሳሉ። እንዲያም ሆኖ እረኝነታቸውን አይዘነጉም። ለአፍታ ዓይኖቻቸው ከከብቶቹ አይነቀልም። ዘወትር ቀልባቸው ከእነሱ ነው። ከላሞቻቸው፣ ከጥጆቻቸው፣ ከበጎችና ፍየሎቻቸው።
ለሜቻ በሬቻ በጌጃ ቦረቻ መስክ ከእኩዮቹ ሲጫወት፣ ሲቦርቅ አድጓል። እረኝነትን፣ አሳምሮ የሚያውቀው ለሜቻ ከብቶቹን ከሜዳ አሰማርቶ፣ ምሽቱን ወደቤት መመለስ የዕለት ተዕለት ስራው ሆኖ ቆይቷል ። ይህን እውነት እሱና እኩያ ባልንጀሮቹ በውዴታ የሚከውኑት የልጅነት ግዴታቸው ነው።
ለሜቻ በልጅነቱ ለእረኝነት ጊዜውን ከፍሎ ራሱን ከሚችልበት ወቅት ደረሰ። ዕድሜው ጨምሯል። አካሉ ጎልብቷል። አሁን እረኝነት ይሉት ዘብ የለም። ከብቶቹን ከአውሬ፣ ከሌባ ለመታደግ ሲሳቀቅ፣ ሲጠነቀቅ አይውልም። በትጋት መልካም ገበሬ ሆኖ ከእርሻው፣ ከማሳው እየዋለ ነው።
ባሉት በሬዎች መሬቱን እያረሰ ምርቱን ያፍሳል። በላብ በጉልበቱ ድካም የዓመቱን ፍሬ ሲያገኝ ደግሞ ስለከርሞው ያስባል። ከአሁን የተሻለውን፣ ከምርቱ ከፍ ያለውን ለመከመር አሻግሮ እየወጠነ ነገውን ያቅዳል ።
በድንገት…
ጠንካራው ገበሬ ለሜቻ መሬቱን እያለማ ምርት ለማፈስ ሁሌም በሬዎቹ ምክንያት ናቸው። ያለእነሱ ሕይወት የለውም። ያለእነሱ ክንዱ አይበረታም፤ ጉልበቱ አይጠረቃም። ጠዋት ጠምዶ ማታ እስኪፈታቸው ሀይል ሆነውት ይውላሉ። ከእሱ ተዛምደው፣ ከመሬቱ ተዋደው ምርት ሊያሳፍሱት፣ የላቡን ሊለግሱት ዘወትር አብረውት ናቸው። ለሜቻ በበሬዎቹ መኖር ሕይወቱ ይለመልማል፣ ዕድሜው ይጨምራል፤ ዕቅድ ሀሳቡ ይሰምራል።
ለሜቻና የበሬዎቹ ተዛምዶ በአብሮነት ቀጥሏል። እሱ ሕይወቱን፣ የመጪ ጊዜ ህልሙን በእነሱ እየፈታ ነው። ከልፋቱ ጀርባ የሚጠብቀው መልካም ፍሬ በእጁ እስኪገባም ቀኑን ሊያይ ይጓጓል። ይህ እውነት የብርቱ ገበሬዎች ትልም ነው። ከድካም በኋላ የዘራውን ለማጨድ፣ ያፈሰውን ለመከመር የማይጓጓ አራሽ የለም።
ለሜቻ ግን ይህ አይነት ህልሙ ሳይቋጭ ከቀናት በአንዱ ክፉ ጉዳይ ገጠመው። በድንገት የሰማው መጥፎ ዜና ልቡን ሰበረ። ሀሳብ ዕቅዱን አደናቀፈ። ከብቶቹ መዘረፋቸውን ባወቀ ጊዜ መላቅጡ ጠፋው፣ ቀኑ
ጨለመበት። ከብቶቹ ለእሱ ሕይወቱ ናቸው። ለመኖር ዋስትናው እንደሆኑ አብረውት ዘልቀዋል። አሁን ከለሜቻ እጅ የቀረው ባዶ መሬት ብቻ ሆኗል። መሬት ደግሞ ከልምዱ ውሎ ምርት ፍሬ ካላሳየ፣ ምርት ካላሳፈሰ፣ ለብቻው ትርጉም የለውም ።
ገበሬው ለሜቻ የሆነበትን ባመነ ጊዜ ሌላ ሀሳብ መጣለት። ከቀዬው ተቀምጦ ከመቆዘም ራቅ ብሎ ቢሰራ እንደሚበጅ ገባው። ከአእምሮው ደጋግሞ መከረ፤ ከውስጡ ተስማማ ፣ ከቤቱ ወጥቶ ከቀዬው ራቀ። ራሱን አዲስ አበባ ባገኘው ጊዜ ከተሜ ለመሆን ስፍራውን መሰለ። መተዳደሪያውን ለማግኘት፣ እንጀራውን ለማብሰል ማተረ። ለእሱ የሚሆን ሥራ አላጣም።
አዲስ አበባ 1953 ዓ.ም
ወጣቱ ለሜቻ አሁን የአዲስ አበባ ሰው ሆኗል። ጌጃንና አካባቢውን ርቆ መሀል አገር በገባ ጊዜ የመጀመሪያ መተዳደሪያ እንጀራው የቀን ስራ ሆነ። ውሎ አድሮ በአንድ የውጭ አገር ተራድኦ ድርጅት በቋሚነት ተቀጠረ። የስራ መደቡ ከጉልበት ስራ አላለፈም።
በወቅቱ ድርጅቱ በሚያሰራው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ላይ እየዋለ ደመወዝ ማግኘት ጀመረ። በወር ሃያ ስድስት ብር ይከፈለዋል። የዛኔ የገንዘቡ ዋጋ ቀላል አልነበረም። በአስራ ስድስት ብር ኩንታል ጤፍ ተገዝቶ፣ የተረፈው ለቤት ኪራይ፣ ለልብስና ጫማ ይውላል።
ለሜቻ ከቀን ስራ በወር የሚያገኘው ገቢ በቂው ነው። የቀድሞ ህልሙ መልካም ገበሬ ሆኖ ምርት ማፈስ ነበር። እንዲያም ሆኖ ባለበት ሕይወት አልተከፋም። ጉልበቱን ከፍሎ በላቡ ወዝ ያድራል። ወር እስከ ወር ለፍቶ የድካሙን ያገኛል።
አስር ዓመታትን በሰራበት ድርጅት ደመወዝ እያገኘ የልቡን ሲሞላ የቆየው ወጣት ከከተማው ተላምዷል። በርካቶችን አውቆም መውጫ መግቢያውን ለይቷል። ለሜቻ አሁን የከተማ ሕይወት እየከበደው አይደለም። አንዳንዴ ገጠር ትውስ ሲለው የጠፉበት ከብቶቹን ያስታውሳል። የእነሱ አለመኖር ሰበብ ሆኖ ከተማ መምጣቱ ትዝታው ቢሆንም ያለበትን ሕይወት አያማርርም። ቀን በምስጋና ውሎ ማለዳ በምስጋና ይነሳል።
የመንግስት ለውጥና ዕጣ ፈንታ
ለሜቻ ከአስር ዓመታት በላይ በቆየባት አዲስ አበባ እንጀራውን አግኝቷል። መስራቱን ተከትሎም በወር የሚከፈለው ደመወዝ ለመተዳደሪያው ተርፏል። አሁን ወቅቱ በአገሪቱ የመንግስት ለውጥ የተከሰተበት ነው። ይህ ጊዜ የንጉሱን ሰርዓት ገርሰሶ በቦታው ወታደራዊ
መንግስትን ተክቷል። የስርዓቱን መውደቅ ተከትሎ የመጣው ለውጥም ባልተሰበ አቅጣጫ የብዘዎችን ሕይወት እየቀየረ ነው።
ወታደራዊው መንግስት መሬትን ለአራሹ ሰጥቶ በርካቶችን የቤትና ቦታ ባለቤት አድርጓል። ከዚሁ ጎን ለጎንም ብዙሃንን ለእስር አሳልፎም ጥቂት የማይባሉትን ለስደት ዳርጓል። በለውጡ አንዳንድ የውጭ አገራት ተቋማት ተዘግተው ሰራተኞቻቸው ተበትነዋል። የአንዱ መጥፋት ለሌላው ሲሳይ፣ እየሆነ የለውጥ ሰደዱ ተቀጣጥሏል ።
ድንገቴውን አብዮት ተከትሎ በአገሪቱ የመጣው ለውጥ የነለሜቻን እንጀራ መንካቱ አልቀረም። እነሱ የሚሰሩበት የተራድኦ ድርጅት የለውጥ መስመሩ ሳይነካው አላለፈም። ድርጅቱ የመዘጋት ዕድል አጋጥሞታል። ይህ ክፉ አጋጣሚም የሰራተኞችን ዕጣ ፈንታ አዛብቷል። በተለይ እነ ለሜቻን የመሰሉ የቀን ሰራተኞች ከድርጅቱ መዘጋት በኋላ ሕይወታቸው ሊፈተን፣ ስራ አጥ ሊሆኑ ግድ ብሏል። ፡
ለሜቻ ሲሰራበት የቆየው የግል ድርጅት መዘጋቱን እንዳወቀ ቀጣይ አማራጭ ለመውሰድ ዓይኖቹን ማተረ። ልምዱ የጉልበት ስራ በመሆኑ ያሻውን ለማግኘት በየቦታው መሞከር መሮጥ አለበት። ዕድሉ ሆነና ልምድና ችሎታውን የሚመጥን አንድ ድርጅት ተገኘለት። የህንጻ ኮንስትራክሽን ድርጅት የለሜቻን ልምድ ከግምት አስገብቶ በቋሚ ቅጥር ተቀበለው ።
አዲስ ሕይወት
አሁን ለሜቻ አመታትን በገፋበት የአዲስ አበባ ኑሮ አዲስ ሕይወትን ጀምሯል። አብሮት የቆየው የጉልበት ስራ ልምድ ሆኖትም በአዲስ ስራና መስሪያ ቤት በደመወዝ ተቀጥሯል። ጊዜው እየገፋ ዕድሜ እየጨመረ ነው። የትናንቱ ገበሬ የዛሬ ከተሜ ሆኖ ታሪኩ ተቀይሯል።
ለውጡን ተከትሎ የቆመበት አጋጣሚ ለሕይወቱ ለሌላ ለውጥ ማምጣቱ አልቀረም። ለሜቻ ትዳር ይዞ አይኑን በአይኑ አይቷል። የግራ ጎኑን ካገኘ ወዲህ ብቸኝነቱ ቀርቷል። ለእኔ ማለት ተወግዶ ለእኛ ማለት ይዟል። ልጆች አሳዳጊ ባለቤቱን ወዳድ የሆነው ጎልማሳ ቤቱን ያከብራል። ቀን ከሌት ለጎጆው ሙላት ይለፋል።
ቀድሞ በየሰው ቤት እንጀራ የምትጋግረው ሴት አሁን የለሜቻ ወይዘሮ ሆናለች። የቤት እመቤት ናትና መተዳደሪያዋ የባሏ እጅ ብቻ ነው። በትዳራቸው ሁለት ልጆችን ያፈሩት ጥንዶች ‹‹አንተ ትብስ፣ እኔ›› እየተባባሉ ኑሮን መግፋት ይዘዋል። ለሚኖሩበት የቀበሌ ቤት ብዙ ክፍያ አይጠየቁም። ገቢያቸውን አቻችለው ልጆቻቸውን ያሳድጋሉ።
ለሜቻ የተቀጠረበት ድርጅት ህንጻዎችን ይሰራል፣ መንገድና ድልድይ ይገነባል። የወር ደሞዝተኛው ጎልማሳ በሚከፈለው ገንዘብ ቤቱን ለማስተዳደር አያንስም። ጎጆውን ለመሙላት ባለቤቱን ለማስደሰት፣ ላቡን ያፈሳል፣ ጉልበቱን ይከፍላል።
ከዓመታት በኋላ
በህንጻ ግንባታ ስራዎች ከሰላሳ ዓመታት በላይ የሰራው ለሜቻ አሁን በዕድሜው ገፍቷል፣ በስራ ብዛት ደክሟል። እንደትናንቱ ሮጦ ለማደር፣ ለፍቶ ለማግኘት እየጣረ አይደለም። ድካም እየረታው፣ ዕድሜ እየፈተነው ቤት መዋል ከያዘ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ከገጠር ወጥቶ ስራና ትዳር ይዞ ልጆች ያፈራው ለሜቻ ዛሬ በቀድሞ አቋሙ አይደለም። ከስራው በጡረታ ከተሰናበተ ቆይቷል። እሱና ባለቤቱ ኑሮ እየከበዳቸው ሕይወት እየፈተናቸው ነው። ልጆቻቸው ከጎናቸው አይደሉም። ሁሉም በራሳቸው ዓለም ለራሳቸው ሕይወት እየሮጡ ነው። አዛውንቶቹ ባልና ሚስት ዛሬም በፍቅር ይኖራሉ። የዘንድሮ ኑሮ በአቅማቸው ልክ አልሆን ቢል በችግር ሊያልፉ ግድ ብሏል። ከጡረታ ክፍያ የሚገኘው ገንዘብ ከአንድ ሺህ ብር አይዘልም። ተጨማሪ ገቢ የሌላቸው ጥንዶች ችግር እያንገላታ ድህነት እየፈተናቸው ነው።
የለሜቻ ባለቤት ጤና ካጣች ቆይቷል። ቤት
መዋል ከጀመረች ወዲህ ተስፋና ረዳቷ ባለቤቷ ብቻ ነው። የሁለቱም ዕድሜ ገፍቷል። አቅማቸው ደክሟል። እኔም ከእንግዲህ አቶ ለሜቻን እንደ ቀድሞው ‹‹አንተ›› እያሉ መጥራት አይቻለኝም። በዓይኔ የማረጋግጠው እውነት ሰውየው ያሉበት ዕድሜ ከአንቱታም በላይ በክብር የሚያስጠራቸው መሆኑን ነው።
እናም በአክብሮቴ ልቀጥል ግድ ይለኛል። አሁን ከአቶ ለሜቻ ጋር ጭውውት ይዣለሁ። አዛውንቱ አሳዛኙ ገጽታቸው ልክ እንደኔ የብዙዎችን ስሜት ይፈትናል። ለሜቻን ያገኘኋቸው ልደታ ክፍለ ከተማ ከሚገኘው የምገባ ማዕከል ውስጥ ነበር። አረፍ ብለን ጨዋታ ከመጀመራችን በፊት በእጃቸው አጥብቀው የያዙትን የላስቲክ ቋጠሮ በዓይኖቼ መረመርኩ። አልተሳሳትኩም። በፌስታል የታሰረው ቋጠሮ ምግብ የያዘ የምሳ ዕቃ ነው።
ቦታው የምገባ ማዕከል ነውና በርካታ አቅመ ደካሞች በእልፍኙ ተገኝተው ርሀባቸውን ያስታግሳሉ። ከቀረበው ሲሳይ ጎርሰው ፣ ከተቀዳላቸው ውሀ ተጎንጭተው ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ። በስፍራው ለምሳ የመጡ በርካቶች ከገበታው ቀርበው እየተመገቡ ነው።
የለሜቻ ሁኔታ ግን ከሌሎች ሁሉ ይለያል። እሳቸው እንደሌሎች እንጀራቸውን በትኩስ ወጥ እየጎረሱ፣ ከውሃው ሲጎነጩ አላየሁም። ከወሰዱት ምግብ አንዳች ሳይቀምሱ በምሳ ዕቃ ቋጥረው ከአዳራሹ ለመውጣት ተዘጋጅተዋል። እኔ የመጡበትን በወጉ አለማድረሳቸው አስገርሞኛል። ስለምን እንዲህ ሆነ? ጥያቄው በአእምሮዬ ተመላለሰ። አይቼ ዝም ማለት አልቻልኩም። የውስጤን ሀሳብ ፈጥኜ አወጣሁት። አዛውንቱን ለምን? ስል ጠየኳቸው።
ከለሜቻ ጋር ዓመታትን በትዳር የዘለቁት ባለቤታቸው ከአልጋ መዋል ከያዙ ቆይቷል። በሽታቸው የከፋ ነውና መላ አካላቸው አይታዘዝም። በሽተኛ ሚስታቸውን ከማስታመም ባለፈ የቤቱን ስራ የሚከውኑት ሽማግሌው ናቸው። ብዙ ጊዜ ከቤት የሚላስ የሚቀመስ ሲጠፋ ጥንዶቹ የዘመድ ጎረቤቱን እጅ ሊያዩ ግድ ይላል።
የሚገኘውን አብስሎ ለመብላት ማገዶ አልያም ኤሌክትሪክ ሊኖር ግድ ይላል። ይህን ለመሙላት አቅሙ የሌላቸው ለሜቻ በእጃቸው ከሚገባው የጡረታ ገንዘብ ግማሽ ያህሉን ኩንታል ከሰል ለመግዛት ያውሉታል። በከሰሉ ፍም የሚያገኝዋትን እያበሰሉና፤ ለቀዝቃዛው ቤታቸው ሙቀት እየቸሩ ባለቤታቸውን ያጎርሳሉ፣ ይደግፋሉ። ለሜቻ በዘመነ ኮረና ሕይወት ለእሳቸውና ለሚስታቸው ፈታኝ እንደሆነ አልፏል። ደግነቱ በቀበሌ በኩል ይሰጣቸው በነበረ እርዳታ ያን ክፉ ጊዜ ተሻግረውታል።
ባለቤታቸው በህመም አልጋ ይዘው ቤት ከዋሉ ወዲህ የለሜቻ የዓመታት ግዴታ እሳቸውን መንከባከብና የቤቱን ስራ መሸፈን ሆኗል። አሁን ባሉበት ዕድሜ ጎንበስ ቀና ማለቱ ይከብዳል። ታማሚ ባለቤታቸውን ማንሳት ማስተኛቱ ይፈትናል። የፍላጎታቸውን መሙላትና ማጽናናቱም ቀላል አይደለም። በተለይ ቤት የዋለን፣ በህመም የተሸነፈን ሰው እንደባህሪይው ማሳደር ትዕግስት ይፈትናል።
አመታትን በትዳር ከእሳቸው የዘለቁት ሚስት ከለሜቻ ሌላ ‹‹አለሁ›› ባይ አጋር የላቸውም። ገበና ሸፋኛቸው፣ አልባሽ፣ አጉራሻቸው አዛውንቱ የልጅነት ባላቸው ብቻ ናቸው።
ከለሜቻ ጋር ንግሬን እንደቋጨሁ የምሳ ዕቃዋ ሚስጥር ተገለጠልኝ። አንዳች ሳይቀመስላት የተቋጠረችው የውስጧን በረከት ለባለቤታቸው ለማካፈል ነው። ለሜቻ በምገባ ማዕከሉ የመጠቀም ዕድል ካገኙ ወዲህ የሚሰጣቸውን ምግብ እንደቋጠሩ ከቤት ይወስዳሉ።
በቤታቸው የእሳቸውን እጅ የምትናፍቅ ነፍስ ትጠብቃቸዋለች። ምግቡን አቅርበው ለታማሚ ባለቤታቸው ያጎርሳሉ። ለእሳቸውም ይቀምሳሉ። ይህ ዕውነት የአዛውንቶቹ ባልና ሚስት የዘወትር ልምድ ነው። ጥንዶቹ ልክ እንደጥንቱ ዛሬም ተደጋገፈው ይኖራሉ። ‹‹አንተ ትብስ አንቺ›› ይባባላሉ።
ለሜቻ ዛሬም የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን አልረሱም። የልጅነት ሚስታቸውን አልጣሉም። ችግርና ድህነት ከበሽታ ተዳምሮ ቢፈትናቸውም አሁንም ከውድ ባለቤታቸው ጎን ሆነው አለሁሽ እያሉ ነው።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2015