ኢትዮጵያ ቡና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁን ወቅት የኢኮኖሚ ዋልታነቱን እያስመሰከረ ይገኛል። ቡናን ከሚያለሙ አርሶ አደሮች ጀምሮ እሴት ጨምረው ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ባለሙያዎች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። በተለይም በዘርፉ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ላኪዎች ታች ካለው አርሶ አደር ደጃፍ ወርደው ቡና በተሻለ ጥራትና በከፍተኛ መጠን እንዲመረት ሲያደርጉ ይስተዋላል። በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ቀጣይነት ማረጋገጥ እንዲቻልም መንግሥት የድርሻውን እየተወጣ ሲሆን፤ በዘርፉ ከተሰማሩ ቁልፍ ተዋናዮች የሚጠበቅ የቤት ሥራ ስለመኖሩም ይነገራል። የዛሬው የስኬት እንግዳችንም ይህንን ሃሳብ ይጋራሉ።
እንግዳችን ‹‹ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር እንደመሆኗ የቡና ሥራ ገና ያልተነካና ወደፊት ብዙ ሊሠራበት የሚችል ዘርፍ ነው፤ ከዚህም ባለፈ ቡና የአገሪቷን ኢኮኖሚ በመደገፍ ዋልታና ማገር መሆን የሚችል ትልቅ ሃብትና የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል ብሩህ ማድረግ የሚችል ነው›› ብለው የሚያምኑና ገና በለጋ ዕድሜያቸው ዘርፉን የተቀላቀሉ ናቸው።
ከልጅነታቸው ጀምሮ ‹‹የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና…›› የሚለው መዝሙር እየሰሙ ያደጉት የያኔው ተማሪ መዝሙሩ የቡናን ጥቅም በስፋት እንዲረዱና እንዲጠቀሙበት መንገዱን ከፍቶላቸዋል። ተማሪ ቤት እያሉም የመመረቂያ ጽሁፋቸውን የጻፉት ቡና ላይ ነበር። ታድያ ለቡና ያላቸውን ቅርበትና በዘርፉ ያካበቱትን ዕውቀት በመጠቀም ላለፉት 20 ዓመታት በቡናው ዘርፍ ውስጥ በሥራ ቆይተዋል።
እንግዳችን አቶ አሸናፊ አርጋው ተቀጥረው ከመሥራት ጀምረው በቡና ንግድ የቆዩ ሲሆን፣ በተለይም በአገረ አሜሪካ የኢትዮጵያን ቡና ከመግዛትና ከመሸጥ ባለፈ በማስተዋወቅ በኩል ሰፊ ሥራ ሠርተዋል። በአሁን ወቅትም የ12 ዓመት የአሜሪካን አገር ቆይታቸውን ገታ በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። በኢትዮጵያም አርደንት ቡና ላኪ የተባለውን ድርጅት ከፍተው ቡናን ወደ ውጭ ገበያ ከመላክ ባለፈ ለዘርፉ ተዋንያኖች የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ሲያጠናቅቁ የመመረቂያ ጽሁፋቸውን በቡና ላይ በማድረግ ስለቡና ይበልጥ የተረዱት አቶ አሸናፊ፤ ቡና ላይ እሠራለሁ የሚል ሃሳብ እንዳልነበራቸው ያስታውሳሉ። ይሁንና በቡና ላይ ጥናት ሲያደርጉ የሚያውቋቸው በቀድሞው ቡናና ሻይ እንዲሁም በግብርና ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የነበሩ ሰዎች በዘርፉ እንዲሰሩ አድርገዋቸዋል። በወቅቱ በኤክስፖርት ማናጀርነት ተቀጥረው ሰርተዋል። በአፍላ ዕድሜያቸውም ወደ ውጭ አገር የመውጣት አጋጣሚ ተፈጥሮላቸው በውጭው ዓለም የኢትዮጵያን ቡና በመሸጥና በመግዛት ብሎም በማስተዋወቅ ጭምር ትልቅ ተሳትፎ ነበራቸው።
መገኛው ኢትጵያዊ የሆነን ቡና በውጭው ዓለም ከመሸጥ ባለፈ አገርን በማስተዋወቅ በወኔ ይሠሩ እንደነበር የሚያነሱት አቶ አሸናፊ፤ አገር እና ቡና አንድ ነው ብለውም ያምናሉ። በመሆኑም ለዘርፉ ያላቸው ቀረቤታና ጥልቅ ፍላጎት ተዳምሮ ዛሬም ድረስ በከፍተኛ ተነሳሽነት በቡና ዘርፉ ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅት ከእርሻ እስከ ኤክስፖርት ያውቁት የነበረውን ቡና በውጭው ዓለም ደግሞ አጠቃላይ የግብይት ሰንሰለቱንና ውድድሩን የማወቅ ዕድል አግኝተዋል።
ኢትዮጵያዊ ሆነው የኢትዮጵያ ቡና ላይ መሥራት መቻላቸው ተደማጭነትን እንዳተረፈላቸው የሚያነሱት አቶ አሸናፊ፤ ከ12 ዓመት የውጭ አገር ቆይታ በኋላ የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ ወደ አገር ቤት ተመልሰው በቡና ላኪነት ለመሥራት ሲሰናዱ ታድያ የከበዳቸው አንድም ነገር እንዳልነበር ነው ያጫወቱን። ለዚህም እርሳቸው በዘርፉ ካካበቱት ልምድና ዕውቀት በተጨማሪ መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ አካላትን ድጋፍና ምክር አግኝተዋል። ገበያውም ቢሆን ጥያቄ አልሆነባቸውም በውጭ ቆይታቸው በርካቶችን ያውቁ ነበርና የገበያ ችግር አልገጠማቸውም።
አርደንት ቡና ላኪ ድርጅትም ዓላማ አድርጎ የተነሳው በዋናነት ከፍተኛ ጥራት ያለውን ቡና በከፍተኛ ዋጋ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሆነ ነው። በተለይም በኢትዮጵያ በጣዕም፣ በዝርያና በጥራት ለየት ያሉትን ፈልጎ በማውጣትና በጥራት በማዘጋጀት ለየት ባሉ የውጭ ገበያዎች ለየት ባለ ዋጋ እያቀረበ ይገኛል። ድርጅቱ ለየት ላለው ገበያ የሚያቀርበው በጥራቱ የተመሰከረለትን ብቻ ነው።
ቡና ከአዘገጃጀቱ ጀምሮ በእርሻ ላይ ሊደረግለት የሚገባውን ጥንቃቄ በማድረግ ለውጭ ገበያ እስከማቅረብ እስካለው ሂደት በዕውቀት የመሥራት ስትራቴጂን ተከትለው የሚሠሩ እንደሆነ ያጫወቱን አቶ አሸናፊ፤ በዘልማድ ከሚሰራው አሰራር ወጣ በማለት ቡናን በተሻለ ዋጋ የመሸጥ ስትራቴጂን አማራጭ አድርጎ የተመሰረተ ድርጅት ነው ይላሉ።
‹‹የቡና ሥራ ዓለማቀፍ ሥራ ነው›› የሚሉት አቶ አሸናፊ፤ የውጭውን ተሞክሮ ይዘው የገቡ እንደመሆናቸው በኢትዮጵያ ደረጃ በዘርፉ ለተሰማሩ የተለያዩ አካላትና ላኪዎች ስልጠናዎችን ይሰጣሉ። ቡናን ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ የተለያዩ አገራት በመኖራቸው፤ ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገራት ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን በዕውቀት ከፍ ማለት የሚገባት እንደሆነና ለዚህም አርደንት ቡና ላኪ ድርጅት የድርሻውን እየተወጣ እንደሆነም አጫውተውናል።
በኢትዮጵያ አሁን ያለው የቡና ግብይት ሥርዓት በተለይም አርሶ አደሩን እና አቅራቢውን የበለጠ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችልና የመደራደር አቅማቸውን ከፍ የሚያደርግ መሆኑን በማንሳትም፤ ከዚህ ቀደም ከነበረው የግብይት ስርዓት ይልቅ አሁን ያለው የተሻለ እንደሆነ ያነሱት አቶ አሸናፊ፤ ቡና ላኪው ታች ወርዶ ቡና ማግኘት መቻሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት ይላሉ። በተዘረጋው የገበያ ትስስር መሰረት በተለይም በሲዳማ፣ በይርጋጨፌ. ጌዲዮ፣ በጉጂና አርሲ ከመሳሰሉት ቦታዎች ቡና በመግዛትና ለውጭ ገበያ በማዘጋጀት በዋጋ ተደራድረው ቡናው የሚገባውን ክፍያ እንዲያገኝ ያደርጋሉ።
ቡና የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እጅግ ሰፊ ሲሆን ያለውን አበርክቶ ቀጣይነት ባለው መንገድ ለማስቀጠልም ከአርሶ አደሩ ጋር የቀረበ ትስስር መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ አብራርተዋል። በዚህም መሰረት አርደንት ቡና ላኪ ደርጅት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ጋር ቤተሰባዊ የሆነ ትስስር ፈጥሯል። ቡናን በገበያ ዋጋ መግዛት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ እገዛና ድጋፎችንም ያደርጋል።
ድርጅቱ እንደ ድርጅት ቡናን ገዝቶ በመሸጥ የሚያቆም ሳይሆን ተመልሶ ገበሬው ጋር በመሄድ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ይሳተፋል የሚሉት አቶ አሸናፊ፤ የአርሶ አደሩ ክፍያ የሚገባውን ዋጋ ከመክፈል ጀምሮ ለሥራ በገቡባቸው አካባቢዎች ሁሉ በቅድሚያ የአርሶ አደሩን ፍላጎት በማሟላት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋሉ። ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻርም ከመደበኛ ሥራቸው እኩል የሚተገብሩት ሥራ ነው። በዚህም መሰረት ይርጋጨፌ፣ ሲዳማ፣ ደንቢና በመሳሰሉት አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን ሰርተው የማስረከብና ጥገና የማድረግ ሥራ ሰርተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በእነዚሁ አካባቢዎች ከ70 የሚልቁ ወላጅ አልባ ህጻናትን ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማሟላት ያግዛሉ።
ከህብረተሰቡ በተለይም ከአርሶ አደሩ ጋር አብሮና ተባብሮ መሥራትን አንዱ ዓላማ አድርጎ የተነሳው አርደንት ቡና ላኪ ለአርሶ አደሮች የመልካም አርሶ አደር የስልጠና ማዕከል በሚል የተለያዩ ስልጠናዎችን ይሰጣል። ድርጅቱ በአሁን ወቅት ለ35 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን፤ በየዓመቱ ደግሞ ከአራት እስከ ስድስት ወር የሚቆዩ 100 ለሚደርሱ ሰራተኞች በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ድርጅት ነው።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና በቢሊዮን የሚጠቀስ ገቢ እያስገባች ስለመሆኑ የጠቀሱት አቶ አሸናፊ፤ ይህም የብዙዎች ድምር ውጤት እንደሆነና በገበያ ስርዓቱ መንግሥት የተዘረጋው አሰራርም ትልቅ ድርሻ አለው። የዋጋ ቁጥጥር በመደረጉም ከፍተኛ ገቢ እንዲገኝ አድርጓል። ባጠቃላይ በአሁን ወቅት መንግሥት ለዘርፉ እየሰጠ ያለው ትኩረት ሊበረታታ የሚገባው እንደሆነ ነው ያስረዱት።
ይሁንና ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር እንደመሆኗ እንዲሁም ተፈጥሮ አብዝታ በሰጠቻት በረከት መጠቀም እንዳልተቻለ የሚያነሱት አቶ አሸናፊ፤ በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ የቡና ሥራ ተጀመረ እንጂ ገና አልተሠራም ይላሉ። አስር ሺ የሚደርሱ የቡና ዝርያዎች ቢኖሩም በአሁን ወቅት ወደ ገበያው የገቡት 42 የሚደርሱት ዝርያዎች ብቻ ናቸው። ይህም ማለት 10 ሺ ብር ያለው ሰው 42 ብሩን ብቻ ሲጠቀም እንደማለት ነው ብለውም በምሳሌ ያሰረዳሉ። ስለዚህ ቡና የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል ብሩህ እንዲሆን ማድረግ የሚችል በመሆኑ ገና ያልተነካው የቡና ዘርፍ በተሻለ ሊሠራበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ላለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት የሲዳማ ቡና የኢትዮጵያ አንደኛ ቡና ሆኖ መመዝገቡን ያስታወሱት አቶ አሸናፊ፤ በአካባቢው የሚበቅል ቡና ባለው ከፍተኛ ጥራትና ጣዕም በዓለም ቀዳሚ ቡና እንደሆነና ተወዳጅ በመሆኑ በዓለም ገበያ በውድ ዋጋ መሸጡንም ነግረውናል። የሲዳማ ቡናን ተመራጭ ካደረጉት ምክንያቶች መካከልም የአካባቢው ለምነትና የአየር ሁኔታውን ጨምሮ ተወዳዳሪ የሆኑ ቡና ላኪዎችና ቡናን ለውጭ ገበያ ሊያዘጋጁ የሚችሉ አዳዲስ ደንበኞች በአካባቢው መግባት መቻላቸውም ተጠቃሽ እንደሆነ አመላክተዋል።
በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በተለይም ከመንግሥት ብዙ የሚጠበቅ እንደሆነ በማንሳት፤ ሊያሰራ የሚችል የአሠራር ስርዓት፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ መቅረጽ ያስፈልጋል። ሊሰሩ የሚችሉ ብቃት ያላቸው በርካታ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖራቸው እነዚህ ሰዎች መሥራት የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር ይገባል። በማለት ለአብነትም የቡና ቀን የማክበርና ዕውቅና የመስጠት ጅማሮ አንዱ እንደሆነና ሊበረታታ የሚገባው ነው ብለዋል።
‹‹ኢትዮጵያ በብዙ ሺዎች የሚቆጠር የቡና አይነትና ዝርያዎች ያሏት በመሆኑ ይህንን ዕምቅ ሃብት አውጥቶ መጠቀም ይገባል›› የሚሉት አቶ አሸናፊ፤ ድርጅታቸው በተለይም ከተለመደው ነገር ወጣ በማለት በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቡና አይነቶችን እና ልዩ ጣዕም ያላቸውን ኢትዮጵያዊ የሆኑ ቡናዎችን በማውጣት ለዓለም ገበያ ማስተዋወቅ ከፍተኛ ዋጋ እንዲያወጡ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ መሆኑን በመግለጽ ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2015