የዝናብ ወቅትን በመጠበቅ በዓመት አንዴ የሚከናወን የግብርና ሥራ ከድህነት የሚያወጣና ኢኮኖሚያዊ እድገትን እያስገኘ አይደለም። ምርታማነትን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ የመስኖ ልማት ወሳኝ የሆነበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። በኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ ለመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል። በተለይም ከአገራዊ ለውጡ (ሪፎርም) ወዲህ ባሉት ዓመታት የዝናብ እጥረት በሚታይባቸው ቆላማ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ በልዩ ትኩረት የመስኖ ልማት በመገንባት የማስፋፋት ስራ ተጠናክሯል። እየተገነቡ የሚገኙት የመስኖ ፕሮጀክቶች በቆላማ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የድርቅ ተጋላጭነትን በመቀነስ የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።
በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች እየተገነቡ ካሉ ትላልቅ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ወልመል የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ይጠቀሳል። ወልመል የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በኢፌዲሪ መስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ባለቤትነት በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት ግንባታቸውን ካስጀመራቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በምዕራብ ባሌ ዞን ደሎመና ወረዳ ውስጥ ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል።
በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደሚያብራሩት፤ ከአገራዊ ሪፎርሙ በኋላ በመስኖ ዘርፍ የአምስት ዓመትና የአስር ዓመት ሰትራቴጂክ ዕቅድ ታቅዷል። በዕቅዱ መሰረት የመጀመሪያው የትኩረት አቅጣጫ በቆላማ አካባቢዎች፣ ህዝብ በብዛት ባልሰፈረባቸው አካባቢዎች፣ በቀላሉ ሊለሙ የሚችሉና ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ያላቸው ቦታዎች መለየት ነው። በዚህ ረገድም ቦታዎችን የመለየት ስራ ተሰርቷል። ከተለዩት አካባቢዎች መካከልም አንዱ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ ውስጥ የሚገኘው ወልመል ወንዝ ነው።
ወልመል መስኖ ልማት ፕሮጀክት ወንዝን በመቀልበስ የመስኖ ልማት ስራ የሚሰራበት ዘዴ የሚተገበርበት ነው። ወንዝ በመቀልበስ የሚከናወን የመስኖ ልማት፣ ውሃ በማጠራቀምና ግድብ በመገደብ ሳይሆን፣ አነስተኛ የመቀልበስ ሥራ በማከናወን የሚሰራ የመስኖ ልማት ስራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ብዙነህ፤ ይህ የመስኖ ልማት ስራ ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ እንደሆነ፣ ወንዞችን በመጥለፍ የመስኖ ልማት ማከናወን ዘዴ በኢትዮጵያ አለመለመዱን ተናግረዋል። ተቀልብሰው ለልማት መዋል የሚችሉ ወንዞችን በአግባቡ መንከባከብ ከተቻለ ዘላቂ የሆነ የልማት ሥራ መስራት እንደሚቻል አስረድተዋል።
እንደ አቶ ብዙነህ ማብራሪያ የወልመል የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በሁለት ሎቶች ተከፋፍሎ በመገንባት ላይ ይገኛል። እነዚህም ሎት አንድ እና ሎት ሁለት ተብለው ይጠራሉ። ሎት አንድ፣ አንድ ነጥብ 72 ቢሊዮን ብር፣ ሎት-ሁለት ደግሞ አንድ ነጥብ 88 ቢሊዮን ብር በሆነ ወጭ ነው በመገንባት ላይ የሚገኙት። የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ ሶስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ነው።
የፕሮጀክቱ ግንባታ የሚያካትተው የ34 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የዋና ቦይ ግንባታ፣ የወንዝ መቀልበሻ ግንባታ (3 ሜትር ከፍታና 50 ሜትር ርዝመት)፣18 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ፣ በግራና በቀኝ የሚከፈል 58 ነጥብ 48 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የሁለተኛ ቦይ ግንባታ፣ 72 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር 3ኛ ቦይ እና 4ኛ ቦይ 350 ኪሎ ሜትር የሚሆኑ ልዩ ልዩ የመስኖ ልማት መዋቅሮች ግንባታ ይኖሩታል። ይህ የመስኖ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ 11 ሺህ 40 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 22 ሺህ በላይ አርሶአደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ ይችላል።
ከፍ ያለ ጥቅም ያስገኛል ተብሎ ተስፋ ያሳደረው የወልመል የመስኖ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በደሎመና ወረዳ በሚገኙ አራት ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ 22ሺህ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል። አርሶአደሮቹ በቆሎ፣ ሰሊጥ፣ ማሽላ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማልማትና በማምረት በዓመት ውስጥ ከሁለት እስከ ሦስት ጊዜ ምርት በማምረት ተጠቃሚ ይሆናሉ። በዚህ መንገድ የተጠናከረ ሥራ ከተሰራ አርሶ አደሮቹ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይችላሉ።
ፕሮጀክቱ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከሚኖረው ፋይዳ ባሻገር የስራ እድል በመፍጠርም ሚናው ከፍ ያለ ነው። በአሁኑ ወቅት ወደ 1 ሺህ 377 ወንድ እና ወደ 363 ሴቶች በድምሩ ወደ 1 ሺህ 760 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ ስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል። አሁን ከተፈጠረው የሥራ እድል በተጨማሪ ለሌችም ሥራ መፍጠር የሚችል ፕሮጀከት ነው።
ከሚኒስቴሩ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ የወልመል መስኖ ፕሮጀክት በአገር ደረጃ ትኩረት ከተሰጣቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሆን፣ በአገር ደረጃም በሶስት መስፈርቶች እንደ ስትራቴጂክ ተይዞ ትኩረት ተሰጥቷል። አንዱ የትኩረት አቅጣጫ የመስኖ ግድብ የሚካሄድባቸው የአካባቢዎች የአየር ፀባይ ቆላማ መሆን፣ ሌላው ብዙ ነዋሪዎች በአካባቢው አለመኖራቸው፣ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ የአካባቢው ምርታማነት ግምት ውስጥ ገብቷል። እንዲህ ያሉ አካባቢዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሰፊ የመስኖ ልማት ዝርጋታዎች እንዲከናወንባቸው ነው በስትራቴጂው የተቀመጠው። ከዚህ አንጻር የወልመል መስኖ ልማት የሚከናወንበት ደሎ መና ወረዳ የህዝብ ብዛት አነስተኛ በመሆኑ እና ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዘ ችግርም አያጋጥምም በሚል እሳቤ ወደ ሥራ ፈጥኖ ለመግባትና በተቀመጠው ዕቅድ በጊዜው ሥራውን ለማጠናቀቅ ያግዛል በሚል ለወልመል መስኖ ልማት ለፕሮጀክት ቅድሚያ ሊሰጠው ችሏል።
በፕሮጀክቱ ግንባታ ሁለት አገር በቀል ተቋራጭ ድርጅቶች እየተሳተፉ ሲሆን፣ አንደኛው ተቋራጭ ድርጅት የወንዝ መቀልበሻ እና መጋቢ የውሃ ቦይ ግንባታ ሥራውን ሲያከናውን ሁለተኛው ተቋራጭ ድርጅት ደግሞ የመስኖ አውታር ግንባታ ሥራውን የሚያከናውን ይሆናል። በዚሁ መሰረት የመስኖ ልማት ፕሮጀክት የውሃ መቀልበሻውን ዓለማየሁ ከተማ ጀነራል የተባለ የግል ድርጅት፣ ወደ እርሻው ውሃ ለማድረስ የሚያግዘውን መጋቢ ግድብ ወይም ፋርም ግንባታ ሥራ ደግሞ የኦሮሚያ ውሃ ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ እየሰሩት ነው።
ፕሮጀክቱን አራት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተቀምጦ ነው ወደ ስራ የተገባው። የፕሮጀክቱ ግንባታ ታህሳስ 2012 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፣ ሰኔ 2015 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ ታስቦ እንደነበር የሚያነሱት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ፤ ሆኖም ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ በነበሩ ክፍተቶች ምክንያት ፕሮጀክቱ በታቀደው መሰረት እንዳልሄደ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ሁለት ሎት ያለው ሲሆን፤ ሎት አንድ የወንዝ ውሃ መቀልበሻ እና ሌሎች ተያያዥ ስራዎችን የሚያጠቃልል ነው። የሎት አንድ ግንባታ ስራ 62 ነጥብ 7 በመቶ ገደማ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ሎት ሁለት ደግሞ የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎችን የሚያካትት ነው። የሎት ሁለት ግንባታ ስራ ደግሞ 39 ነጥብ 37 በመቶ መጠናቀቀቁን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ብዙነህ ማብራሪያ፤ ፕሮጀክቱ በታቀደለት እቅድ መሰረት እንዳይከናወን ካደረጉ ምክንያች አንዱ ሲሚንቶን ጨምሮ ለግንባታ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ግብዓቶች እጥረትና የዋጋ መናር፣ ግንበኛና አናጺ የመሳሳሉ ባለሙያዎች አለመገኘት፤ የሚመለከተው አካል የካሳ ክፍያውን ቶሎ ሰርቶ አለማቅረብ እንዲሁም የተቋራጭ በተለይም የሎት ሁለት የስራ ተቋራጭ የአቅም ውስንነት ያለበት መሆኑ ለግድቡ ግንባታ መጓተት ዋና ዋና ምክንያቶች ነበሩ።
በዚህ ዓመት ግንባታው መፍጠን አለበት ተብሎ ስለታነመነበት ከፍተኛ ርብርብ እየተሰራ ነው። እንደ ሲሚንቶ ያለ የግንባታ ግብአት ለማግኘት ሚኒስቴሩ ለሚመለከተው አካል የድጋፍ ደብዳቤ በመጻፍ ትብብር ጠይቋል። የግብአት አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ የጀመረውን ጥረት ያጠናክራል።
የግንበኛ እና የአናጺ ባለሙያዎች እጥረት ለመቅረፍ ከአካባቢው ውጭ ባለሙያዎችን እንዲያስመጣ ለግንባታ ተቋራጩ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያቀረበውን ምክረ ሀሳብ ተግባራዊ በማድረግ ተቋራጩ የግንበኛና የአናፂ እጥረት ይቀርፋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ከወረዳ፣ ከዞን፣ እና ከክልል መንግስት ጋር በጋራ በመስራት ለማቃቀለል ጥረት እየተደረገ መሆኑን በመጥቀስ በዚህ ረገድ መሻሻሎች እየታየ መሆኑን ነው ያብራሩት። ከዚህ በላይ በቅንጅት መስራት ከተቻለ የበለጠ መሻሻል ማምጣት እንዳሚቻልም ጠቁመዋል።
የስራ ተቋራጮች አቅም ውስንነት ችግሮችን ቀርፈው ለግንባታ የሚያስፈልገውን ግብዓቶች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ድጋፍ አድርጎላቸው በ2015 ፕሮጀክቱን መጠናቀቅ እንዳለበት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር ተደርጎ መስማማት ላይ መደረሱን አቶ ብዙነህ አብራርተዋል።
በፕሮጀክቱ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ግንባታውን ለማፋጠን እየተደረገ ካለው ርብርብ ጎን ለጎን አርሶ አደሩ እና አገሪቱ ከመስኖ ፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ስራዎችን ከወዲሁ ማከናወን ያስፈልጋል። ፕሮጀክቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በአፋጣኝ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበትንም ሁኔታ የሚመለከታቸው አካላት ከአሁኑ ሊያስቡበት ይገባል። ከፍተኛ በጀት ተመድቦላቸው የሚከናወኑ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ሥራዎች ከግንባታ ባለፈ ለታለመላቸው ዓላማ ውለው ለውጤት በማብቃት ላይ ቀደም ባሉ ጊዜያት በተደጋጋሚ ቅሬታዎች ሲነሱ ነበር።
አገሪቱ ከፍተኛ ወጪ አውጥታ የገነባችው ይህ ፕሮጀክት በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል የልማቱ ተጠቃሚ አርሶ አደር በቂ ድጋፍና ክትትል የሚያገኝበት ሁኔታ እንዲኖር ማድረግ እና ከግንባታው ጎን ለጎን ወደ ልማቱ ለመግባት የሚያስችሉ ሥራዎች ሊሰሩ ይገባል። ምክንያቱም አገሪቱ በከፍተኛ ወጪ ከምትገነባቸው የመስኖ ፕሮጀክቶች ምርት ካልተመረተና አርሶ አደሩ ካልተጠቀመ፣ እንደ አገርም ዕድገት ካልተመዘገበ ለአገሪቱ የሚያስገኘው ምንም ጥቅም አይኖርም። ከዚህ ጎን ለጎን አርሶ አደሮች ስለመስኖ ልማት ያላቸውን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ በትኩረት ሊሰራ ይገባል። የአርሶ አደሮችን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ ለመስኖ ልማት ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ ከምንም በላይ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2015