ሁልጊዜ አብረው የሚታዩ ጓደኛሞች ናቸው። በተለይም የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ላይ ኳስ ሲጫወቱ፤ ሲላፉ ከሚውሉት የሰፈሩ ታዳጊዎች መካከል በፍጹም እነርሱ አይጠፉም፤ አራቱ ጓደኛሞች። በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ የተለየ ቦታ የተሰጣቸው፤ በየራሳቸው ቀለም የተለዩ፤ በአብሮነታቸው ደግሞ የቡድን መልክ ያላቸው።
የአራቱ ጓዳኞሞች ህብረት በፍቅር ብቻም ሳይሆን በጥል ጊዜም ትኩረትን የሚስብ ነው። ከአራቱ ሁለቱ ሲጣሉ፤ ሌሎች ሁለቱ አስታራቂ ሆነው ይቀርባሉ። ከአራቱ አንዱ ሲታመም ሌሎች ሦስቶቹም የታመሙ ሆነው ይቆጠራሉ። የሚጣሉ አብረው የሚሄዱ አራት ጓደኛሞች።
እንደ ቡድን አንድ ሆነው፤ እንደ ግለሰብ ባላቸው አተያይ የሚለያዩበት መንገድ ያላቸው ሆነው የሚገኙ። አንደኛው ታዳጊ ነገሮችን በቁጥር ወይንም በአሃዝ መግለጽ የሚወድ ነው። እዚህ መንደር ውስጥ ይህን ያህል ወንድ አለ፤ ይህን ያህል ሴቶች አሉ፤ ይህን ያህል ከውትድርና የተመለሱ አሉ፤ ይህን ያህል አከራይ አለ፤ ይህን ያህል ተፈናቃይ አለ፤ ይህን ያህል ወዘተ እያለ በንግግሩ ውስጥ መጥቀስ የሚቀናው አሃዙ የሚል ቅጽል ስም የወጣለት ታዳጊ። የሰፈሩ ነዋሪዎች ይህን ታዳጊ የኢትዮጵያን ሙሁራን ይመስላል ይሉታል። ለኢትዮጵያ ምሁራን ይህን ያህል እውነትን ብሎ አሃዝ መጥቀስ የማወቅ ጥግ ይመስላቸዋል የሚል አስተያየትን መነሻ በማድረግ።
ሁለተኛው ታዳጊ አሃዝን ወደ መረጃ በመቀየር የሚታወቅ ነው። የያዘውን መረጃ ትርጉም ሰጥቶ ለማቅረብ ጥረት የሚያደርግ። የአስራ ሁለተኛ ፈተና መቼ እንደሚሰጥና ምንያህል ሰው ሊፈተን እንደሚችል መረጃን ማቅረብ የእርሱ ስራ ነው። በአካባቢው የሚገኘው ቤተመጽሐፍትን የማደስ ስራ መቼ ተጀምሮ መቼ እንደሚጠናቀቅና የቤተመጽሐፍቱ አዳዲስ አገልግሎቶች ምን እንደሆኑ መረጃዎችን አነፍንፎ በአካባቢው ውስጥ በማሰራጨት ይታወቃል።
የቀጣይ ቅዳሜና እሁድ የእንግሊዝ ፕሪሜየርሊግ ውድድሮች ማን ከማን ጋር እንደሚያገናኘው በባለፈው ሳምንት ጨዋታ ማን ምንያህል ውጤት አመጣ የሚለው መረጃው ከአፉ ውስጥ በቀላሉ ሲነገር የሚውል ነው። ማን ጎል እንዳገባ፤ ከየት ጋር እንዳገባ፣ በየትኛው ደቂቃ እንዳገባ ወዘተ መረጃው አለው፤ አሃዝን ተጠቅሞ መረጃን መፍጠር ይችላል። ከአካባቢ ጀምሮ እስከ ዓለምአቀፍ ድረስ መረጃን መሰብሰብና ማሰራጨት ዋናው ሥራ ያደረገ ይመስላል። የራዲዮ ጣቢያዎችን የሚያስንቅ የመረጃ መረብ እንደሆነም በስፋት ተመስክሮለታል።
ሦስተኛው ታዳጊ ሁልጊዜ “እንዴት?” ለሚል ጥያቄ መልስ ለመስጠት የሚታትር ነው። በአንድ ቡድን ውስጥ ስላሉ ኮከብ ጎል አስቆጣሪዎች ሳይሆን ‘እንዴት ኮኮብ ጎል አስቆጣሪ መሆን እንደሚቻል’ የሚጠይቅ ነው። በዘንድሮ አገር አቀፍ ፈተና ስንት ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከማወቅ ባሻገር እንዴት በትምህርት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል’ የሚጠይቅ ነው።
በፎርብስ መጽሔት ላይ ስማቸው ስለተዘረዘሩ ኢንቨስተሮች ከማወቅ በላይ ‘እንዴት ገንዘብ ቆጥቦ ወደፊት ትልቅ ኢንቨስትመንት ማከናወን እንደሚቻል’፤ የሚጠይቅ ነው። ለበሽታ ስለሚዳርጉ ጉዳዮች መረጃን ከመያዝ ባሻገር ‘እንዴት ራስን ከበሽታ መከላከል እንደሚቻል’ ወዘተ የሚጠይቅ ለጥያቄው መልስ በማግኘት ረገድ እውቀትን የእርሱ ያደረገ ነው። የእውቀት ሰው ባህሪን የተላበሰ ታዳጊ። የእውቀት ሰው ማለት እንዴት እያለ እየጠየቀ እውቀትን የሚያበዛ ነውና። እንዴት፤ እንዴት፤ …። አራተኛው ታዳጊ ባህሪ ግን ከእውቀት አንድ እርምጃ ወደፊት የተራመደ ነው፤ ወደ ጥበብ።
ከእውቀት አንድ ምእራፍ ከፍ ብሎ መገኘት እንዴትን ከመጠየቅ ባሻገር ‘ለምን?’ ብሎ መጠየቅ መቻልም ነው። ለምን ጎበዝ ተማሪ መሆን እንደሚያስፈልግ ይጠይቅና መልስ አግኝቶ በጥበብ መንገድ ላይ የሚጋዝ። ሰዎች አንድን ነገር ስላደረጉት ወይንም ስለሄዱበት በተመሳሳይ መንገድ ከመሄድ ለምን ብሎ በመጠየቅ ምክንያትን ማግኘት ያስፈልጋል። ለምን ጨዋታ መጫወት እንዳለበት፤ ለምን ቤተሰብ መርዳት እንዳለበት፤ ለምን የጊዜ ሰሌዳ መጠቀም እንዳለበት፤ ለምን ዜጎች ግብር መክፈል እንዳለባቸው፤ ለምን ከጋብቻ በፊት የግብረስጋ ግንኙነት መጀመር እንደሌለበት፤ ለምን እናትና አባቱን ማክበር እንዳለበት፤ ለምን ከፈተና ወቅት የግርግር ጥናት መውጣት እንዳለበት፤ ብዙ ለምን እየጠየቀ መልስ ይፈልጋል። ይህም ዘወትር በጥበብ መንገድ ላይ እንዲገኝና ከአጥፊም ሆነ ጠቃሚ ሆኖ ግን ለጊዜው ከማያስፈልግ እውቀት ይጠበቃል።
አራቱ ታዳጊዎች ውስጥ የሚታየው ባህሪ ወደ ጥበብ የሚደረግን የእድገት ደረጃዎች ያሳዩናል። አንባቢው ራሱን በየትኛው ደረጃ ላይ እንደሆነ ፈትኖ አንድ እርምጃ ወደፊት መራመድ ይችል ዘንድ እንዲረዳ የተጻፈ።
የአሃዝ ሰዎች
በማንኛውም ጉዳይ ላይ ዝርዝር ቁጥሮችን መፍጠር ይቻል ይሆናል። ነገሮች በቁጥር ሲገለጹ መመልከትም ደስ ይላል። በቁጥር የተቀመጠውን ጉዳይ ወደ መረጃ መቀየር መቻል ግን አንድ ምእራፍ ማደግ ነው። ዜና ይዘውልን የሚቀርቡ ሚዲያዎች መረጃቸውን አሳማኝ አድርገው ለማቅረብ በተገቢው ቁጥር እንዲያስደግፉ እንጠብቃለን። የአሃዝ ሰዎች አሉ፤ ቁጥርን በአግባቡ ማቅረብ የሚችሉ። በህይወት ውስጥ የበዘ አሃዝ ግን አንዳች የሚፈይዱት ነገር የለም፤ ወይንም ተጽእኖቸው ትንሽ ነው።
በትላንት ታሪካችን ውስጥ በቁጥር የሚገለጹ አበይት ጉዳዮች ይኖራሉ። ጥቂት የማይባሉት የትላንት ቁጥሮቻችን ራሳችንን በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊነት እንድንመለከት ሊያደርገንም ይችላል። ዛሬ እጃችን የሚገባውን ደሞዝ በቁጥር ደረጃ አይደለም የምናውቀው፤ በኑሮ ውስጥ እንጂ። ደሞዝን በአሃዝ ደረጃ ማወቅና ደሞዝን በኑሮ ውስጥ ባለው ትርጉም ማወቅ ይለያያል። ቁጥሩን ከቁጥር አልፎ የሚሰጠውን ትርጉም ተረድቶ ለምን ለሚል ጥያቄ መልስ መስጠት በመቻል ውስጥ ሲሆን ህይወትን ወደ ተሻለ ምእራፍ የሚያመጣ የጠቢብ ሰው መንገድ ይሆናል።
የአሃዝ ሰዎች በአሃዝ ውስጥ የሚገኙ ከመሆን ወጥቶ አሃዙ ትርጉም ያለው መረጃ ሰጥቶቸው ህይወታቸውን ለማስተካከል ሊጠቀሙበት እንዲችሉ ማሰብ አለባቸው። የእድሜ ቁጥር በአሃዝ ሲቆጠር የሚሰጠው ትርጉም ብቻውን ትርጉም የለውም። እድሜ ከወሰድነው ትምህርት፤ እድሜ ወድቆ ከመነሳት አንጻር፤ እድሜ ለሌሎች መመንዘር የምንችልበትን እድል ከማግኘት አንጻር፤ እድሜ እሴት ጨማሪ ለሆነ የቀጣይ ጉዞ ዝግጅት ወዘተ ከሆነ የሚሰጠው ትርጉም የተለየ ይሆናል። አብርሃም ሊንከን “በመጨረሻ ትርጉም የሚሰጠው የእድሜያችን ቁጥር ሳይሆን በእድሜያችን ዓመታት ውስጥ የኖርነው ኑሮ ነው” እንዳለው ማለት ነው።
ከአሃዝ ወደ መረጃ ስናድግ አሃዝን ተርጉመን ወደ መጠየቅ እንድንሸጋገር የሚያደርግ ይሆናል።
የመረጃ ሰዎች
ቁጥርን ተንትነው መረጃ ማድረግ የሚችሉ ሰዎች ደግሞ አንድ ምእራፍ ከጥሬ የአህዝ አቅራቢዎች ወደፊት የተራመዱ ናቸው። መረጃ ብዙ ነገር ማለት እንደሆነ ባለንበት ዘመን ውስጥ አንረዳለን። ከየአቅጣጫው የሚለቀቀውን መረጃም አስተውለን የመረጃ መጥለቅለቅ እየገጠመንም እንደሆነም እንረዳለን። ትላልቅ አሃዝ እንዴት አድርጎ መያዝ እንደሚቻል እንዴትስ አድርጎ መረጃን በመፍጠር ለህይወት ዋጋ መጨመር እንደሚቻል ራሱን የቻለ ትምህርትም አለው። መሪዎች ዝርዝር አሃዝን ወደ መረጃ በመቀየርና አመራር ለመስጠት ሲጠቀሙበትም እንመለከታለን። በግለሰብ ደረጃ ያለው የቀን ገቢ አቅም፤ በአካባቢ፤ በሙያ፤ በእድሜ፤ በጾታ ወዘተ ተብሎ መረጃ ሆኖ ሲተነተን ወደ ለውጥ የሚደረግ ጉዞን ሊያመላክትም ይችላል።
ያደጉት አገሮች እያንዳንዱን ዝርዝር አሃዝ ወደ መረጃ አሳድጎ ተንትኖ ለውሳኔ ሰጪነት በመጠቀም እና “ለምን” ብሎ በመጠየቅ ውስጥ ለደረሱበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። የሰው ልጅ በምድር ላይ የሚኖረውን ኑሮ አሳድጎ በሌሎች ቦታዎች ላይም እንዲገኝ ያደረገው ከመረጃ ከፍ ባለው የጥበብ ደረጃው ነው። በጥበብ አማካኝነት ወደ ላይ ከፍ ማለት ቻለ፤ በከፍታውም ላይ ዛሬም እየበረረ ይገኛል። እንዴት ብሎ መጠየቅ ወደ እውቀት ደጅ የሚያደርስ ቢሆንም፤ እውቀት ብቻውን በቂ አለመሆኑን በመረዳት ለምን ብሎ በመጠየቅ ወደ ጥበብ መድረስ ይቻላል። ጥበብ ስራዋን የምትሰራበት፤ እውቀት የምትጎድልባቸው ቦታዎች መኖሩን እውቀት አላቸው የሚባሉት ሰዎች የሚፈጥሩት ጥፋት ጥሩ ማሳያ ነው። “እንዴት” ብሎ መጠየቅ ግን ከመቅረት እጅግ የሚያጎድል ሆኖ እናገኘዋለን። እውቀት ትልቅ የለውጥ መሳሪያ ነውና፤ ወደ ጥበብ መድረሻ መንገድ።
በታሪካችን ገጻችን ላይ ብዙ መረጃ አለ። የጦርነት፣ የንግስና፣ የአናጺነት፣ የመምህርነት፣ የህክምና፣ ወዘተ መረጃዎች በታሪክ ማህደራችን ውስጥ በሚገባ ይገኛሉ። በታሪክ ማህደር ውስጥ የሚገኘው ጥቅም ላይ እንዲውል ወደ እውቀት እንዲቀየር ሆኖ መገንባት አለበት። ያለፈውን መቀየር ባንችልም ከባለፈው እውቀት መውሰድ ግን አስተዋይነት ስለሆነ።
በጦርነት ውስጥ በብዙ አስከፊ መንገድ ውስጥ ያለፉት የአውሮፓ አገራት ዛሬ አብረው ተሰልፈው ለህዝባቸው መፍትሔ ለመሆን የሚያደርጉት ጥረት ትላንትን ወደ እውቀት ትምህርት ቤት መቀየር እንደሚቻል ማሳያ ናቸው። በዘር ምክንያት የተጠፋፉት ሩዋንዳውያን ትላንት እውቀት አድርገው ይገኛሉ። እውቀት እንዴት ለሚለው ጥያቄ ምላሽ እየሰጠን ከእውቀት ያደርሰናልና ለእውቀት ቦታን እንስጥ።
የእውቀት ሰዎች፤
አስቀድመን እንዳልን የእውቀት ሰዎች “እንዴት” እያሉ በመጠየቅ የሚራመዱ ናቸው። የቀን ገቢያችን ይህን ያህል ነው ብሎ በቁጥር አውቆ ከመቀመጥ እንዴት ድህነትን ማሸነፍ ይቻላል ብለው የጠየቁት ራሳቸውን ለጥያቄያቸው ምላሽ የሚሰጥ መንገድ ላይ እንዲገኙ ስላደረጋቸው አይራቡም። የእውቀት መንገድ ከመራብ እንዲወጡ አድርጓቸዋልና። የእውቀት መንገድ ሊያሳካ የሚችለው ችግርን በእውቀት በመፍታት ወደ መፍትሔ መድረስ ነውና።
የእውቀት ሰዎች የገባቻቸውን እውቀት ወደ ተግባር ለመቀየር በተራመዱ ቁጥር ከመፍትሔው መስመር ውስጥ ይገኛሉ። ብዙ እውቀት ይዞ ትንሿን የተገበረና፤ ትንሿን እውቀት በሚገባ የተገበረ መካከል ልዩነት የለውም። እውቀት ከተግባር ሰውናት ጋር ሲቀናጭ ውጤቱ ያማረ ነው። የግብርናው ሆነ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለውጥ የእውቀት ሰዎች የተግባር እንቅስቃሴ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ሊሆን ይገባል። ታላቁ እስክንድር “ሙከራን ለሚያደርጉ ሰዎች ምንም የማይቻል ነገር የለም” ማለቱ ለሁሉም ግልጽ ነው።
ዛሬ የአገራችንን ችግር በእውቀት መፍታት የምንችልበት ደረጃ ላይ እንድንመጣ እውቀት ላይ መስራቱ አስፈላጊ ነው። እውቀት ላይ የሚሰራው ስራ ከቀን ወደ ቀን ፍሬ አፍርቶ ትላንት ያለፍንበትን የድህነት፤ የእርዛት፤ የጦርነት እንዲሁም ዛሬም በተመሳሳይ ሁኔታ ከምንገኝበት መውጣት ያስችለናል። የጥበብ መንገድ ግን ከእውቀት ባሻገር ባለው ከፍታ ላይ መድረስ ያስችላል።
ከአጸደ ህጻናት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ እውቀትን በመፍጠርና በማስተዳደር በመደበኛነት የተሰማሩት ዘርፎች ለማህበረሰባችን የፈየዱትን ፋይዳ ማስፋት አንድ ነገር ነው፤ ከእውቀት የሚጠቀም ሆኖ መገኘት ደግሞ ሌላ። እውቀት በመጠቀም ውስጥ የጥበብ ሰው ሆኖ መገኘት ግድ ይላል። ጠቢብ ከሁሉም ይማራልና።
የጥበብ ሰዎች፤
የጥበብ መጀመሪያ ፈጣሪን መፍራት ሆኖ በሃይማኖቶች ትምህርት ይሰጣል። እያንዳንዱን ነገር በጥያቄ ውስጥ አስገብተን የምንደርስበት መዳረሻ ሁሉም ስለ ሰው መሆኑን እንረዳለን። ሁሉም ስለ ሰው መሆኑን ለመረዳት ግን ለምን ብሎ መረዳት ያስፈልጋል። ለምን ገንዘብ እንደሚያስፈልገን ካልተረዳን ሰውን በመግደል ውስጥ ገንዘብ ማግኘት ትክክል ሆኖም ይገባናል። ሥራ ለምን እንደምንሰራ ካልተረዳን በሥራ ሰዎችን ማገልገል መሆኑን እንስተውና ሰኞና እሁድ ቀን የሚኖራቸው እለታዊ ትርጉም አንዱ ደስ የማይል ሌላው መዝናኛ ይሆናል።
በጥበብ መንገድ ውስጥ ፍቅር ትልቅ ቦታ አላት። ከመቀበል ይልቅ መስጠት ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል። ሰዎችን እንዴት መኖር እንዳለባቸው ትልቁን መረዳት ያገኛሉ። በጨለማ ውስጥ ታልፎ ስለሚገኝ ብርሃን መታሰብ ይችላል። ፈላስፋው አርስቶትል እንዳለው በጨለማ ጊዜያችን ላይ ብርሃን ላይ ማተኮር እንችላለን። የጥበብ መንገድ በውስጣችን ለምን እያልን ጠይቀን ማስተካከያ እንድናደርግ ያግዘናል። ከሰዎች ጋር የምትጋጭ ከሆነ ለምን ብለህ ትጠይቃለህ፤ ወደ ውስጥህ ተመልክተህ ማስተካከልም ትችላለህ። በሥራ ቦታህ ውጤታማ ካልሆንክ ለምን ትላለህ፤ ወደ ውጤታማነት የሚያደርስህን መንገድ ታገኝ ዘንድ እድል ይታይሃል። በሰዎች ተጎድቶ ልቦን አክብዶ የሚንቀሳቀስ ሰው ለምን ብሎ በመጠየቅ ከገባበት ውድቀት ይወጣል። ለምን ብሎ መጠየቅ ወደ ጥበብ ይወስዳል፤ እንዴት ብሎ መጠየቅ ወደ እውቀት።
እውቀትም ሆነ ጥበብ የበዙለት ሰው ደግሞ ታምር መፍጠር ይችላል። የሚፈጥረውም ታምር ወደ ውጤት የሚያደርስ ብቻ ሰዎች ሌሎች ወደ ውጤት እንዲደርሱ ምክንያት የሚሆን ነው።
ያለንበት ዘመን በብዙ ጉዳዮች የምንቸገርበት ነው። ልጆችን ማሳደግ ከባድ ሆኖ የሚታይበት፤ ገንዘብ አበድሮ መልሶ ማግኘት ተራራ የሚሆንበት፤ ሰው ቃሉን ጠብቆ መገኘቱ እንዲሁ አስቸጋሪ መስሎ የሚታይበት፤ ለትዳር ታማኝ ሆኖ መገኘትም እንዲሁ። ለምን ብሎ የሚጠይቅ ለህይወት ዋጋ በመስጠት ህይወቱን በአግባቡ መምራት የሚችልበትን እድል ያገኛል። ሰነፉና ጠቢቡ የሚለዩበት ወቅት አለ፤ እርሱም ወቅት ዛሬ ነው። ዛሬን በጥበብ የመራመድና ያለመራመድ።
በመንደርደሪያ ታሪካችን ውስጥ ያሉትን አራት ታዳጊዎች ዳግም በማሰብ ወደ መውጪያው በር እንድረስ። ከአሃዝ ወደ መረጃ እንድንደርስ፤ ከመረጃ ወደ እወቀት፤ ከእውቀት ወደ ጥበብ። የጥበብ መጀመሪያም ሆነ መዳረሻ ለህይወት ትርጉም ስለሚሰጠው ሰው ልንሆን የተገባውን መሆን ነው። ለራሳችን የሚገባውን ቦታ በመስጠት፤ በዙሪያችን ላሉት የሚገባቸውን ቦታ በመስጠት፤ በፍቅር ውስጥ ያለውን ሃይል በተግባር በመኖር፤ ቃላችን ከእርምጃችን ጋር በማገናኘት።
ትላንት ላናገኘው የሸኘነው ነው፤ ትላንት በእውቀት ደረጃ ለዛሬ የሚሰጠን እውቀት ጥበብ ሆኖልን ህይወት በተገቢው መንገድ እንድንመራ ሊያደርገን ይገባል። ትላንት አለመቻል አብዝቶ የተነገረው ዛሬ በጥበብ መንገድ ውስጥ ያለመቻልን መንፈስ አልፎ በመቻል ጎዳና ላይ ራሱን ለማግኘት ለምን ብሎ ይጠይቃል።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2015