አዲሱን ዓመት 2015ን ተቀብለን የመጀመሪያውን ወር እያገባደድን እንገኛለን። ግን አዲሱ ዓመት እንዴት ነው። ሁላችንም አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር “አዲስ ነገር” እንመኛለን፣ ምኞት ብቻ ሳይሆን በአዲሱ ዓመት የምንሠራቸውን ሥራዎች እቅድም አዘጋጅተን ዓመቱን እንቀበላለን። በእርግጥ አዲስ ነገር መፈለግ ያለብን 365 ቀን ጠብቀን አዲስ ዓመት ሲመጣ ብቻ መሆን ባይኖርበትም አዲስ ዓመት ሲመጣ በአዲስ መንፈስ አዲስ ነገር ለማግኘት መመኘትና ማቀዳችን ስህተት የለውም። ማንም ሰው በባህሪው ሁሌም አዲስ ነገር ቢያገኝ አይጠላምና። እናም የቻለ አዲስ ዓመት ጠብቆ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ጊዜ አዲስ ነገርን ሊፈጥር ይችላል። ይሁን እንጂ አዲስ ዓመትን ጠብቆ ለለውጥ፣ ለአዲስ ህይወት፣ ለአዲስ ስኬት መነሳሳትም ነውር ነው ብየ አላስብም።
በበኩሌ “አዲስ ዓመት የሚባል ነገር የለም” ከሚሉ ሰዎች ጋር አልስማማም። ምክንያቱም 356 ሌሊቶችንና ቀኖችን አምሽቶና አንግቶ፣ ሃምሳ ሁለት ሳምንታትን ሰንብቶ፣ አስራ ሁለት ወራትን ቆጥሮ፣ ወደ አዲስ የህይወት መቁጠሪያ “አውደ ዓመት” መሸጋገር ዕውነትም አዲስ ነውና። ይህም ሕይወትን እንደ አዲስ እንደመጀመር ነውና በአዲስ ዓመት አዲስ ነገር ለማግኘት መመኘትና ማቀድ ተፈጥሯዊ ነው።
ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒው ሁሉም ነገር የሚሆነው በጊዜው ነው፣ ጊዜው ካልደረሰ የሚፈጠር ምንም ነገር የለም… በሚል እሳቤ ሁሉንም ነገር ለነገ እየገፉ በጊዜ እያሳበቡ መኖር እጅጉን የተሳሳተ ልማድ መሆኑን አጥብቄ እሞግታለሁ። የዚህ ጽሑፌ ዋነኛ ተጠየቅም ይህንኑ የተሳሳተ ማህበረሰባዊ ልማድ በአመክንዮ አስደግፎ ማሳየት ነው። በእኛ አገር “ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚችለው ጊዜ ነው” የሚል በከፍተኛ ደረጃ የሚታመንበት፣ ለዘመናት የቆየ፣ ስር የሰደደ የአስተሳሰብ ልማድ አለ።
“ጊዜ የጣለውን ጊዜ ያነሳዋል”፣ “ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል”፣ “የቀን እንጅ የሰው ጀግና የለውም”፣ “ቀን እስኪያልፍ የአባትህ ባሪያ ይግዛህ”፣ “የእኔም ጊዜ ይመጣል”…የሚሉ አባባሎቻችንም ይህ አስተሳሰብ ምን ያህል በህብረተሰቡ ውስጥ ሰርፆ የገባ መሆኑን በደንብ የሚያሳዩ ምስክሮች ናቸው። ከፈጣሪ በላይ ጊዜ ይመለካል ቢባል ብዙም የሚጋነን አይሆንም። የአንድ ሕብረተሰብ ሁለንተናዊ መገለጫ የሆኑት የጥበብ ውጤቶቻችንም በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የጊዜን አድራጊ ፈጣሪነት ሳይሰብኩ የማያልፉ ናቸው። ለአብነት “ጊዜ ጌታ፣ ጊዜ ንጉስ” የሚል ዜማ በሚደመጥበት ሃገር ከፈጣሪ በላይ ጊዜ ይመለካል ቢባል ማጋነን አይሆንም።
የሙዚቃ ነገር ከተነሳማ የቱ ተነግሮ የትኛው ይቀራል። “አቤት ጊዜ”፣ “ወይ ጊዜ”፣ “በጊዜ”፣ “አይሻለሁ በጊዜ” …። “የምን ሃሳብ የምን ትካዜ፣ ሁሉ ሊሆን በጊዜ” የሚለውን ብቻ ቃላቱ ሳይለወጥ በሦስት ታዋቂ ድምጻውያን ዘፈኖች ውስጥ ማዳመጤን አስታውሳለሁ። ስለጊዜ ኃያልነት የማይቀነቀንበት የዘፈን ሥራ የለም ማለት ይቀላል። በሥነ ጽሁፎቻችንና በፊልሞቻችን ያለውም ከዚህ የተለየ አይደለም። ብቻ በእኛ ሃገር ጊዜ ያልሆነው ነገር ምንም የለም?
ጨቋኞችና አምባገነኖች ጊዜያቸው ካልደረሰ ከስልጣናቸው ነቅነቅ አይሉም፣ ሕዝቡም የቱንም ያህል ግፍና በደል ቢበዛበት፣ በጭቆና መዳፍ ሥር ሆኖ በባርነት ቀንበር ቢማቅቅ፣ በፍትህና በዕውነት ጥማት ቢሰቃይ ጊዜውን ይጠባበቃል እንጅ ታግየ ነጻነቴን ላስከብር አይልም። ምክንያቱም ጊዜው ካልፈቀደ ምንም ነገር አይሆንም ብሎ ያምናልና። እናም አምባገነኖች ከስልጣን የሚወርዱት በጊዜ ነው። ፍትህና ነጻነትም የሚገኘው በጊዜ ነው። ጀግና የሚኮነነውም በጊዜ ነው፤ ጀግና ራሱ ጊዜ ነው። “የጊዜ እንጅ የሰው ጀግና የለውም” አይደል የምንለው!
ድህነት ቢበዛ፣ ችጋር ቢበረታ በጊዜው ካልሆነ ከድህነት መውጣት አይቻልም። ምክንያቱም ጊዜው ካልፈቀደ ከድህነት ለመላቀቅ ጠንክሮ መስራት በከንቱ መልፋት ይሆናል፤ ሃብት የሚገኘው በጊዜ ነዋ¡ ስኬታማ ለመሆን ጊዜ ያስፈልጋል። ደስተኛ ለመሆን ራሱ ጊዜው መፍቀድ አለበት። ዛሬ ቀኑ ደብሮኛል ብለው ቀኑን ሙሉ ሲቆዝሙ የሚውሉ ሰዎች አጋጥመዋችሁ አያውቁም? እኔ ግን “ዛሬስ ቀኑ ረዘመብኝ በጣም ደብሮኛል”፣ “ዛሬስ ምን ሆኜ ነው? ቀኑ በጣም አጠረብኝ!”፣ “የዛሬው ቀንስ ርዝመቱ፣ ተገትሮ ዋለ እኮ ሲያስጠላ!” የሚሉ አስተሳሰባቸውና ኑሯቸው በቀን ቁጥጥር ሥር የዋለ መዓት ሰዎችን አውቃለሁ።
ይህም ያለንበት የኑሮ ሁኔታና እኛ ለነገሮች ያለን አመለካከት እንጅ “እንዴት ቀን በራሱ ሊያጥርና ሊረዝም ይችላል?” የሚል ጥያቄንና ግርምትን ይፈጥርብኛል። እዚህ ጋር ማሳየት የፈለኩት ዋናው ቁም ነገር አስተሳሰባችንና ነገሮችን የምንመለከትበት የህሊና መነጽር እንጅ ጊዜን ጨምሮ ማንኛውም ውጫዊ ኑባሬ የእኛን ዕጣ ፋንታ የመወሰን አቅም የለውም የሚለውን እንጅ ጊዜ የራሱ የሆነ ዋጋ ያለው መሆኑን አጥቼው አይደለም። እንደዚያ ቢሆን ኖሯማ ከሃብትና ከባለጸግነት ይልቅ ጥበብን በመምረጡ ከሁሉም በላይ ጥበብ የተሰጠው አራት ዓይናው ጠቢብ ንጉስ ሰለሞንም “ለሁሉም ጊዜ አለው” ባላለ ነበር።
በእርግጥም በህይወት ጎዳና ላይ ማንኛውም የዕድሜ ክልል የራሱ የሆኑ አወንታዊና አሉታዊ ገጽታዎች አሉት። “ልጅነቴ፣ ልጅነቴ ማርና ወተቴ” የምትለዋን መዝሙር ደግመን ደጋግመን ዘምረን ብናድግም በወጣትነት የእድሜ ክልል ላይ ስንደርስ በሚሰማን ትኩስ የህይወት ኃይልና የአሸናፊነት መንፈስ ያለምንም ፍርሃትና ማቅማማት የፈለግነውን ነገር ሁሉ በድፍረት ስናደርግና አንዳንዴም ተሳክቶልን ጀብዱ ስንፈፅም በወጣትነታችን ከልብ መደሰታችን አይቀርም።
ሁሉንም ነገር በስሜት ከማድረግ፣ ከችኩልነትና ከግብታዊነት ወጥተን ክፉና ደጉን አመዛዝነን ወደ ምንወስንበት ደረጃ ተሸጋግረን፤ ለአቅመ አዳምና አቅመ ሔዋን ደርሰን፣ ለወግ ለማዕረግ በቅተን፤ ተድረንና ተኩለን ከልጅነት አልፈን ልጅ ወልደን ማሳደግ ስንጀምር ደግሞ አብሮ የሚመጣው ድርብርብ ኃላፊነት ቢከብደንም ኃላፊነታችን የምንወጣ፣ አስተዋዮችና አዋቂዎች ለመሆን በመብቃታችን አዲስ ደስታን ይፈጥርልናል። እንደዚሁ የጎልማሳነት ዘመናችንን ጨርሰን ወደ ሽምግልና ደረጃ በምንደርስበት ጊዜ አቅማችን እተዳከመ በመሄዱ ምክንያት እንደ ልባችን ሰርተን የፈለግነውን ነገር በፈለግነው ሰዓት ማግኘት ባለመቻላችንና የልጆቻችን እርዳታ ወደ መጠበቅ በመሸጋገራችን ቅር መሰኘታችን አይቀሬ ይሆናል።
ክፉንም ደጉንም አሳልፈን፣ ሁሉንም አይተን በረጅሙ የዕድሜ ዘመናችን ባካበትነው ሰፊ የህይወት ልምድና ዕውቀት ክብርና ሞገስን አግኝተን፣ መካሪና አስተማሪ፣ ሸምጋይና አስታራቂ ለመሆን በመታደላችን በዚህም እንደሰታለን። በዕድሜያችን ምከንያት ህብረተሰባችን አክብሮን አርዓያና መሪ አድርጎ ሲሾመን እውነትም ዕድሜችን ጸጋችን መሆኑን እንረዳለን። በዚህም ደስ እንሰኛለን።
ይህም በሕይወት ዘመናችን ውስጥ የጊዜ ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳይ ተፈጥሯዊ እውነታ ነው። ይህ የሚያመላክተው ግን ጊዜ የሕይወት መስፈሪያ አውድ በመሆኑ ከሕይወት ጋር ከዕድሜያችን ጋር ያለውን ተፈጥሯዊ ትስስር እንጅ እኛው እንደምናደርገው ባለንበት የጊዜ ክፍል ውስጥ ማድረግ የምንፈልገውን ነገር በማድረግ ፋንታ ሁሉንም ነገር ለጊዜ እየሰጡ በጊዜ ቁጥጥር ሥር የመኖርን አባዜ አይደለም። እናም አዲስ ነገር ለመሥራት አቅደን አዲሱን ዓመት መቀበላችን ነውር የለውም። የመጀመሪያዋን ወር በዚሁ መሠረት እየሠራን ከሆነም ብልሕነት ነው።
ይህን ማድረግ ሲያቅተን “ሁሉም በጊዜው ይሆናል” በሚል አሁንም ለነገ እየገፋናቸው ከሆነ ግን አዲስ ዓመት ስለሆነ ብቻ የተመኘነውን አዲስ ነገር ማግኘት አንችልም። እናም “ሁሉም ጊዜው ሲደርስ ይሆናል” በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ሁሉንም ለነገ እየገፉ ጊዜን መጠበቅ የራስን ስንፍና ለመደበቅ የሚደረግ ከንቱ የጊዜ አምላኪነት አባዜ ነውና ከዚህ ከንቱ ልማድ በመላቀቅ በማንኛውም ሰዓት ማድረግ የሚገባንን በማድረግ የምንመኘውን አዲስ ነገር መፍጠርና ምንፈልገውን አዲስ ሕይወት መኖር ይገባናል።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2015