ፍጹም ፀጥታ የሰፈነበት ነው። በግድግዳ ላይ ከተሰቀለው የምስል ማሳያ (ተንቀሳቃሽ ምስል) ላይ እየተቀያየሩ የሚታዩት ምስሎች ክፍሉ በብርሃን እንዲሞላ አድርጎታል። በክፍሉ ውስጥ ያለው መብራት ደግሞ ይበልጥ ድምቀቱን በመጨመር በውስጡ ያሉትን ሀብቶች ጎልተው እንዲታዩ አግዟል። ለሰስ ብሎ በጆሮ የሚንቆረቆረው በሙዚቃ መሣሪያ የተቀነባበረው ሙዚቃ(ክላሲካል) በክፍሉ ውስጥ ለመቆየት ይጋብዛል። ፀጥ እረጭ ባለውና በብርሃን ተሞልቶ በሙዚቃ በታጀበው ክፍል ውስጥ ውድና ብርቅ የሆኑ፣ በዋጋቸው ውድ፣በህብረ ቀለማቸው የሚያምሩ የሚደመሙባቸውና የሚደነቁባቸው ሀብቶች ይገኛሉ።ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ዋልታና ማገር ሊሆኑ የሚችሉ ወርቅና የከበሩ ማዕድናት፣ ለኢንዱስትሪና ለግንባታ ግብአቶች የሚውሉ የማዕድን ሀብቶች ስብስብ ናቸው። እይታን በሚስብ መልኩ የኢትዮጵያን የማዕድን ሀብት እንዲህ በአንድ ቦታ በማሰባሰብ ለተመራማሪዎች የምርምር ሥራ ምቹ ማድረግ፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ዜጎችም በአገራቸው ውስጥ ስለሚገኘው የማዕድን ሀብት እውቀቱ እንዲኖራቸው ለማስቻል ዘርፉን የሚመራው የማዕድን ሚኒስቴር ባለፈው አመት የከፈተው የማዕድን ማሳያ (ጋለሪ) ነው።
እንዳልኳችሁ የክፍሉ ፀጥታ ቀልብን ሰብሰብ አድርጎ እያንዳንዱን የማዕድን አይነት፣ በየትኛው የአገሪቱ ክፍል እንደሚገኝ፣ ሊሰጥ የሚችለውን አገልግሎት፣ አጠቃላይ የሆነ መረጃ ለማግኘት በአንክሮ ለማየትና ለመረዳት ዕድል ይሰጣል። የማዕድን ሀብቱ በፎቶግራፍ(በምስል)፣ በተንቀሳቃሽ ምስልና በመግለጫ ጽሁፍ የተደገፈ ከመሆኑ በተጨማሪ በማዕድን ማሳያው (ጋለሪ) ውስጥ በሚገኙ አስጎብኝ ባለሙያዎች ተጨማሪ ገለጻ ስለሚደረግልዎት ሰፋ ያለ ግንዛቤ ያገኛሉ።ጋለሪው ለአገልግሎት ከበቃ የአመት እድሜ ያስቆጠረ ባለመሆኑ የማየት ዕድሉን ያገኙት ጥቂት እንደሚሆኑ እገምታለሁ። ስለ ማዕድን ማሳያው (ጋለሪ) መከፈትና በውስጡ ስላለው ሀብትም መረጃው የሌላቸውም ይኖራሉ።
እስኪ በጋለሪው ውስጥ በሚገኙ ባለሙያዎች በተደረገልኝ ገለፃ ተዘዋውሬ ያየኋቸውን የማዕድን ሀብቶች በጥቂቱ ላስቃኛችሁ እና ጋለሪው ከተቋቋመበት ዓላማ አኳያ በአጭር ጊዜ ውስጥም ቢሆን ስለተከናወኑ ተግባራት ከባለሙያዎቹ ያገኘሁትን መረጃ አስከትላለሁ።ጋለሪው ውስጥ የሚገኙት የማዕድን ሀብቶች የኢንደስትሪ፣ የግንባታ፣ ኬሚካል፣ ጌጣጌጥ፣ብረታብረት ነክ፣ ኢነርጂ፣ የማዕድን መገኛ ካርታ፣ በሚል ተከፋፍለው በመልክ በመልኩ ለጎብኚው ምቹ በሆነ ሁኔታ ነው የተደራጀው።
በጉብኝቴ ወቅት ትኩረቴን ከሳበው ውስጥ ጥቂቶቹን ላንሳላችሁ። እንደ ፎስፌት ያሉ ለግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ የሚውል የማዕድን ሀብት እያለ ለማዳበሪያ ግዥ በአመት ከሶስት ነጥብ ስምንት ቢሊየን ብር ያላነሰ ወጪ ይወጣል። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሰቆጣ አካባቢ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊየን ቶን የሚገመት የብረት ማዕድን እያለ ለግንባታና ለተለያየ አገልግሎት የሚውል የብረት ግብአት ከውጭ በግዥ ወደ አገር ይገባል። በዓለም ላይ እጅግ ተፈላጊ፣ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተሸጠው ለአገር የኢኮኖሚ ዕድገት ጥቅም የሚያስገኙ እንደ ፀሐይ ኮከብ የሚያበራ ህብረ ቀለም ያላቸው ቀልብን የሚይዙ የከበረና በከፊል የከበረ ተብለው ተለይተዋል። እንደ ኦፓል፣ ኢመራልድ፣ ሳፋየር የተባሉ የማዕድን አይነቶች እሴት ተጨምሮባቸው ለገበያ ቢውሉ ደግሞ ከፍ ያለ ጥቅም የሚያስገኙ መሆናቸው በአስጎብኚው ሲገለጽ፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ ምን ያህል እምቅ ሀብት እንዳላት ያሳያል። እሴት ጨምሮ ለገበያ የማቅረብ ተሞክሮ ቢኖርም በአብዛኛው ግን ጥሬ ሀብቱ ለገበያ እንደሚውል ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ላይ በአንድ በኩል የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖርና ኢንቨስትመንት የሚፈልግ መሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ግዥውን የሚፈልጉት አካላት ጥሬ ሀብቱን መግዛት ተጠቃሚ ስለሚያደርጋቸው እንደሆነ ይነገራል። አማራጭ ገበያዎችን በመፈለግ ተጠቃሚነት ላይ ማተኮር ግድ የሚባልበት ጊዜ ላይ እንደምንገኝ መዘንጋት የለበትም። ለዚህም ነው በዘርፉ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንዲህ ያለው የማዕድን ጋለሪ ያስፈለገው።
በኢነርጂ ዞን ውስጥ ካየሁት ደግሞ፤ ዓለም አቀፍ የመለኪያ ነዳጅ መሆኑን የሚያሳይ የነዳጅ መጠቀሚያዎች፣ እንዲሁም ሶማሌ ክልል ኦጋዴን ውስጥ የተገኘ ድፍድፍ ነዳጅ፣ የነዳጅ ተረፈ ምርት ደግሞ ለአስፓልት መንገድ ሥራ መዋል እንደሚችልም ጋለሪው ግንዛቤ ያስጨብጣል። ነዳጅ በጠጣር፣ በፈሳሽና በጋዝ መልክ ይገኛል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የነዳጅ ዋጋ ያሻቀበ ነው። በአሁኑ ጊዜ በተለያየ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ጫና እየተፈጠረባት ላለችው ኢትዮጵያ ደግሞ የነዳጅ ዋጋ መጨመር አዳጋች ይሆናል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ምድር የሰጣትን ሀብት ወደ ጥቅም መለወጥ ላይ ነገ ዛሬ የሚባል መሆን እንደሌለበት ይታመናል። ማዕድን ሚኒስቴር አዲስ ባስጠናው ጥናት በሶማሌ ክልል በኦጋዴን አካባቢ 7 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ ማውጣት የሚችል የተፈጥሮ ጋዝ መኖሩ፣ የአሜሪካ ኩባንያ የሆነው ኤልሲኤአይ (LCAI) የጥናትና ውጤቱን የሚያረጋግጥ ሰርተፍኬት ርክክብ ማድረጋቸውን ባለፈው ማስነበባችን ይታወሳል።
በጋለሪው በነበረኝ የጉብኝት ቆይታ በማዕድን መገኛ ካርታ ላይ ሀብቶቹ የሚገኙባቸው አካባቢዎች ሰፍረዋል። ለአብነትም በደቡብ ክልል ወርቅ፣ ኤመራልድ፣ ሩቢ፣ ታንታለም፣ኦፓል፣ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል ላይምስቶን፣ ጨው ነዳጅ፣ በሰሜን ምሥራቅ አፋር ብረት፣ ጨው፣ ፖታሽ፣ ድኝ(ሰልፈር)፣ ቤንቶናይት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ማርብል(እምነበረድ)፣ ኦፓል ላይምስቶን፣ ወርቅ፣ ብረት፣ ምእራብ ኢትዮጵያ ጋምቤላ ኤመራልድ፣ ወርቅ፤ ኦሮሚያ ጉጂ አካባቢ ለኤሌክትሪክ እቃዎች የሚውሉ የማዕድን ሀብቶች በስፋት ይገኛሉ።
በማዕድን ዘርፍ በተለያዩ ሰዎች ከሚነሱ ትችቶች ኢትዮጵያ እምቅ የማዕድን ሀብት እንዳላት በቃል ከሚነገረው በላይ በተደራጀ ሁኔታ ስላላት የሀብት አይነትና ሀብቱ የሚገኝባቸው አካባቢዎችና መጠን በቂ መረጃ አለመኖሩ ነው። የማዕድን ጋለሪው መከፈት እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል እድል ይሰጣል። ከዚህ አንጻር በአጭር ጊዜ ውስጥም ቢሆን ያስገኘው ጥቅም ይኖር እንደሆን በማዕድን ሚኒስቴር የጂኦሳይንስ ባለሙያ ጂኦሎጂስት አበራ ድሪባ እንደሚከተለው ማብራሪያ ሰጥተዋል። እርሳቸው እንዳሉት የሳይንስ ባለሙያዎችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋለሪውን እየጎበኙ ይገኛሉ። ከጎብኚዎች የሚሰጠው አስተያየትም የተለያየ ነው። ስለማዕድን የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው ብዙ ማብራሪያ አይፈልጉም። ጎብኚ ተማሪዎች ግን ብዙ ነገር ለማወቅ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ በጉብኝታቸው ባዩት የማዕድን ሀብት በመደነቅ እስከ ዛሬ በዚህ መልኩ ለእይታ አለመቅረቡ፣ የማዕድን ዘርፉን አልምቶ ወደ ክፍለ ኢኮኖሚው መቀየር ያልተቻለው አገሪቷ የገንዘብ አቅም ስለሌላት ወይንስ ሥራዎች ባለመሰራታቸው ነው? ወደፊትስ ምን ታስቧል? በአጠቃላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የዘርፉን ልማት ለማፋጠን ስላለው እቅድ የማወቅ ፍላጎት? ጥቂቶቹ ናቸው። ‹‹ኢትዮጵያ እንዲህ ያለ ሀብት እያላት ለምን ደሃ አገር ሆነች›› የሚል ቁጭትም አላቸው።በተማሪዎችም ሆነ በአንዳንድ ጎብኚዎች የተለያዩ ሀሳቦች እንዲነሱ ምክንያት የሆነው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ማዕድናትን የያዘ ጋለሪ በመክፈቱ እንደሆነ ባለሙያው አቶ አበራ ይገልጻሉ።
እንደርሳቸው ማብራሪያ የማዕድን ጋለሪው ሲከፈት የተለያዩ ዓላማዎችን ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም፣ ወደፊት በአገራቸው የኢኮኖሚ እድገት ላይ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው በተለያየ የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች የአገራቸውን ሀብት ከማወቅ ባለፈ፤ ባዩት ነገር መደሰታቸው፣ መቆጨታቸውና የተለያየ ጥያቄም ማቅረባቸው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣትና መሥራት እንዳለባቸው ከወዲሁ እንዲገነዘቡ ያስችላቸዋል። ጂኦሎጂስት አበራ ጋለሪው በመከፈቱ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጥቷል ለማለት ባይደፍሩም፤ በማዕድን ዘርፉ በተለይም በድንጋይ ከሰል ልማት ላይ ለመሰማራት ባለፈው አመት ከሚኒስቴሩ ጋር የውል ስምምነት በመፈጸም እንቅስቃሴ የጀመሩ ኩባንያዎች መኖራቸውን አንስተዋል። የጋለሪው መኖር ግን ባለሀብቱን ለመሳብ ድርሻው ከፍ ያለ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ሌላው የማዕድን ጋለሪ ባለሙያ አቶ አወቀ ተስፋው ተጨማሪ ሀሳብ ሰጥተዋል። እርሳቸውም እንደገለጹት በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር የሚኖሩ ባለሀብቶችም ጎብኝተዋል። አብዛኞቹ በጋለሪው ውስጥ ባዩዋቸው ይደነቃሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያየ የማዕድን አይነት ይኖራል ብለው አለመጠበቃቸውንም አስተያየት ይሰጣሉ። በዘርፉ ለመሰማራት ወይም ለማልማት ቃል የሚገቡም አጋጥመዋል። ማዕድን ሚኒስቴር ለእያንዳንዱ የማዕድን አይነት ዝርዝር ሙሉ መረጃ የያዘ የማስተዋወቂያ ሰነድ(ዲኩዩመንት) በማዘጋጀቱ፣ በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ያለው ባለሀብት ሰነዱን በግዥ መውሰድ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ጎብኚው ባለሀብት ባየው ሁሉ ቢሳብም ለግንባታ እና ለኢንደስትሪ ዘርፍ በሚውሉ ማዕድናት ላይ ትኩረቱ ከፍ ያለ መሆኑን አስጎብኚዎቹ ለመታዘብ ችለዋል። በቀን በአማካይ እስከ አንድ ሺ ሰዎች የሚጎበኙ ሲሆን፣ ይህ መረጃ እስከተገኘበት ድረስ እስከ 70 ሺ የሚሆኑ ሰዎች እንደጎበኙት ይገመታል። የማዕድን ጋለሪው በሂደት ውጤት እንደሚያስገኝ የሚጠበቅ ቢሆንም በእስካሁኑ እንቅስቃሴው ከጎብኚዎች የተገኘው የጋለሪው መኖር መነቃቃትን መፍጠሩን ከባለሙያዎቹ መገንዘብ ይቻላል።
ማዕድን ጋለሪውን ሲጎበኙ ያገኘኋቸው ወይዘሮ አይናለም አዱኛንና አቶ ኢብራሂም መሐመድንም ስሜታቸውን እንዲያካፍሉኝ ጠይቄያቸው፤ በተለይም ወይዘሮ አይናለም በሰጡት አስተያየት በትምህርት ከሚያውቁት ውጭ ከዚህ ቀደም በአንድ ሥፍራ የተለያየ የማዕድን ሀብት የማየት ዕድሉ አላጋጠማቸውም። ኢትዮጵያ የዚህ ሁሉ ሀብት ባለቤት መሆኗንም መገንዘብ የቻሉት የማዕድን ጋለሪውን ከጎበኙ በኋላ ነው። ባዩትም ነገር ተደስተዋል። መንግሥት የሚሰራ ኃይል በማሰማራት ሀብቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ቢያደርግ ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሚገኝበት ከጉብኝቱ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ነው ያስረዱት።
‹‹ለማዳበሪያ ግብአት የሚሆኑ፣ የተፈጥሮ ጋዝና ሌሎች ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ ተስፋ የሚያሳድሩ የምድር ውስጥ ሀብቶች ባለቤት ሆነን ግን እንደሌለን አለመጠቀማችን ቁጭት ያሳድራል›› በማለት ሀሳባቸውን የሰጡት አቶ ኢብራሂም አሁንም አለመርፈዱንና ሀብቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ተግቶ መሥራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። የማዕድን ጋለሪውን ሁሉም ሰው ሊጎበኘው እንደሚገባና አገሩ ውስጥ ስላለው ሀብት ቢያውቅ ተንከባክቦ ለመጠበቅም ሆነ ሀብቱ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚጠበቅበትን ድርሻ ለመወጣት እንደሚያስችለው ሀሳብ ሰጥተዋል።
የማዕድን ሚኒስቴር ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከዚህ ቀደም ‹‹ኢትዮጵያ በማዕድን ሀብት የታደለች አገር ብትሆንም በሀብት ላይ መቀመጥ ብቻውን ሀብታም አያደርግም›› ማለታቸው ይታወሳል። ከምድር በታች የሚገኘውን ሀብት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ እና የባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት ሀብቱን ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም ገልጸዋል።ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከኢትዮጵያ ማእድን ሀብትና ከዘርፉ ጋር የተጣጣሙ እንዲሁም በማእድን ዘርፍ በከፍተኛነት የተለዩ የእውቀት ዘርፎችን በመለየት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኩል ስርዓተ ትምህርት እንዲዘጋጅላቸው እና ለባለሙያዎች እንዲሰጡ የሚያስችል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የውል ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅት ነው።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2015