ታዳጊ አብነት አለማየሁን ያገኘነው ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅራቢያ ካለው መንገድ ዳርቻ ክብደትን በሚለካ የሚዛን ሥራ ላይ ተሰማርቶ ነው። ከአንድ ስፍራ ቁጭ ብሎ አላፊ አግዳሚው ክብደቱን እንዲመዘን ይወተውታል። ቦታው ላይ የተቀመጠው ማልዶ ነው። ካለበት ወደ ሌላው ፈቀቅ እያለ ሥራውን ሲሰራ ያመሻል።
የ12 ዓመቱ ታዳጊ ፀሐይና ብርዱ ሲፈራረቅበት ይውላል። የዕድሜ እኩዮቹ ሰርክ ትምህርት ቤት ሲሄዱና ሲመጡ ቢያይም እሱ እንደነሱ ለመማር አልቻለም። እንዳጫወተን ከሆነ ትምህርቱን ከአራተኛ ክፍል አቋርጧል። ለዚህ ምክንያቱ ለሚዛን ሥራ ከወላይታ ሶዶ ገሱባ ወረዳ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱ ነው።
የዛሬ ሁለት ዓመት አዲስ አበባ ሲመጣ መዋያው በአንበሳ ጊቢ አካባቢ ጀብሎና ሊስትሮ ከሚሰራው ወንድሙ ዘንድ ነበር። ወንድሙና ሊስትሮ ባልንጀሮቹ ሽሮ ሜዳ አካባቢ በተከራዩት ቤት ወለል ላይ በሕብረት ያድራሉ። ወንድምዬው በሚዛን ስራ በቀን ከ150 እስከ 200 ብር ያገኛል። አብነት ስራ ከጀመረ በኋላ ሁሌ ማታ ማታ ወንድሙ ብሩን ይቀበለዋል። ገንዘቡን አጠራቅሞም እቁብ ይጥልለታል።
አብነት እቁቡ ሲደርሰው ሀገሩ ሄዶ ያቋረጠውን ትምህርት መቀጠል ይፈልጋል። በቀረው ገንዘብም ለወላጆቹና ለእሱ ልብስ መግዛትና ከእጁ የሚተርፈውን ሊያበረክትላቸው አስቧል። ወንድሙ ይሄን ሃሳቡን ለመስቀል በዓል እንደሚከውንለት ቃል ገብቶለት ነበር። ይሁን እንጂ እሱ ለመስቀል አገር ቤት ሄዶ አልተመለሰም። እሱም ዘንድሮ ያቋረጠውን ትምህርት ያለመቀጠሉና አገር ቤት ባለመሄዱ ተከፍቷል።
በመዲናችን አዲስ አበባ የዕለት ከዕለት ሕይወታቸውን በዚህ መንገድ የሚገፉ በርካታ ታዳጊ ሕፃናትን በየጎዳናዎቹ መመልከት የተለመደ ነው። ብዙም ሳንርቅ አራት ኪሎ ዳግማዊ ምኒሊክ መሰናዶ ትምህርት ቤት ከመንገዱ ዳርቻ ያገኘናት ታዳጊ ሕፃን እየሩሳሌም ማርቆስ አንዷ ማሳያችን ናት። እንደ ታዳጊ አብነት ሁሉ የእለት ከዕለት ሕይወቷን የምትገፋውና በዚሁ የሚዛን ሥራ የተሰማራችው እየሩስሳሌም በዕድሜዋ ገና ሕጻን ናት። ትኩረት ሰጥቶ ላስተዋላት ደግሞ ሚዛኑን ይዛ መቀመጧ ለጨዋታ እንጂ ለሥራ እንደሆነ አይገምትም።
እየሩስ እንደነገረችን ዕድሜዋን በውል አታውቀውም። ሽሮ ሜዳ አካባቢ ከወንድሟና ከሌሎች ጋር ከወለል ላይ ታድራለች። ከወላይታ ሶዶ ያመጣትና የሚዛን ስራውን ያስለመዳት በሊስትሮና በጀብሎ ሥራ የሚተዳደረው ታላቅ ወንድሟ ነው። ማታ ላይ የሰራችበትን ገንዘብ በሙሉ ትሰጠዋለች።
ወላይታ ሶዶ የወንድሟ ጎረቤት የሆነውና በአካባቢው በሊስትሮ ሥራ የተሰማራው አንድ ወጣት እንደገለፀልን እየሩስ ዕድሜዋ ዘጠኝ ዓመት ነው። ሀገርቤት አንድ ልጅ ከፍ ሲል እንጂ በዚህ ዕድሜው ትምህርት ቤት ማስገባት የተለመደ አይደለም ። እሷንም ቢሆን ወደፊት ከፍ ስትል ያስተምሯታል ብሎ ይገም ታል።
የስድስት ዓመቱን ቶማስ ማዳን ያገኘነው በሳሪስ መስመር መንገድ ዳርቻ ነው። ቶማስ ከደቡብ ክልል እንደመጣ ይናገራል። ወደ አዲስ አበባ የመጣው የዛሬ ሦስት ዓመት ነበር። ‹‹አስተምረዋለሁ›› ብሎ ያመጣው አጎቱ ሲሆን ከመምጣቱ ትንሽ ቆይታ በኋላ የሚዛኑን ሥራ አለማምዶት መሥራት ጀመረ። አሁንም ውሎው ከሚዛን ጋር ነው።
ቶማስ የሚቀመጥበት ቦታ ሰው የሚበዛበትና የተለያየ ቢሆንም ከሳሪስ አካባቢ አይርቅም። አንዳንዴ የመንገድ መብራት ባለባቸው ቦታዎች እስከ አራትና አምስት ሰዓት ሲሰራ ያመሻል። ሁልጊዜም ማታ ማታ የሰራበትን ለአጎቱ ይሰጠዋል ። የሚያድረውም ከእሱ ጋር ነው። አንዳንዴ አምሽቶ አምስት ሰዓት አካባቢ ይገባል። ሳንቲሙን ሲቆጥሩና ስለ ስራው ሲጠያየቁ ከሰባት ሰዓት በኋላ የሚተኛበት ጊዜ አለ። ለሊቱ ለዕንቅልፍ አይበቃውም። ወዲያው ይነጋና 12 ሰዓት ሲሆን ከመኝታው ይቀሰቀሳል። ዓይኖቹን እያሸ ሚዛኑን ተሸክሞ ይወጣል።
አጎት በግማሽ ቀን እየሰራህ ግማሹን ቀን ትማራለህ ቢለውም ለመስቀል አገሩ እንደሄደ አልተመለሰም። ትምህርት አለመጀመሩ የሚያስከፋው ቶማስ እንደ ሕፃን አብነት ሁሉ ደስታ ርቆት ዓይኖቹ እንባ ያቀራሉ።
መስቀል አደባባይ ባሉ ተቋማት በአንዱ በጥበቃ ሥራ ላይ የሚገኙት አቶ ዋሲሁን ካሳው መኖርያ ቤታቸው ሳሪስ አቦ አካባቢ ነው። ዋሲሁን በስፍራው ሲመላለሱ ስለነዚህ ሕፃናት ብዙ ነገሮችን እንደሚታዘቡ አጫውተውናል። አብዛኞቹ ሕጻናት የሚኖሩት በሳሪስ መስመር ነው። በተለይ አጎና ሲኒማ አካባቢ በርከት ይላሉ። ልጆቹ ሚዛናቸውን እያዘሉ ከያሉበት ወጥተው በመዲናዋ ሁሉም አካባቢዎች የሚሰማሩት ማልደው እንደሆነ ይናገራሉ። ከሳሪስ አቦ፤ እስከ መስቀል፤ አደባባይ፣ ፒያሳ፤ አራት ኪሎና ስድስት ኪሎ ፣ እንዲሁም ወደተለያዩ ቦታዎች ያለ ትራንስፖርት በእግራቸው ይጓዛሉ።
ልጆቹ ውርጭና ፀሐዩ ሲፈራረቅባቸው ይውላል። አብዛኞቹ ከደቡብ ክልል የመጡ ናቸው። የሚያመጧቸው በአብዛኛው የሩቅና ቅርብ ዘመዶች ቢሆኑም አሁን ላይ ሥራው ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ በመሆኑ ሌሎችም ሕፃናቱን እያመጡ ሚዛን በማሰራት የገንዘብ ማግኛ እያደረጓቸው ነው። ሕፃናቱ ጉልበታቸው ይበዘበዛል። ትምህርት አያስተምሯቸውም ። በቂ ምግብና ንፁህ ማደሪያም የላቸውም። ሁሉም በተለይ ሴት ሕፃናት ለተለያዩ ጾታዊ ችግሮች የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው።
አቶ ዋሲሁን ሴቶቹ እስከ መደፈር፣ መታለል የሚያደርስ ጥቃት ሊደርስባቸው ሲል ደርሰው ያስጣሉበት አጋጣሚ አለ። እሳቸው መንግሥት እነዚህ ሕፃናት ትምህርት በነፃ እንዲያገኙ የማድረግ ግዴታ እንደሚኖርበት ያምናሉ።
እንዲህ ዓይነቱን አስቸጋሪና ፈታኝ ሕይወት የሚገፉ ሕፃናት በመዲናችን አብዝተው መስተዋላቸውን የሚያወሱት በዚሁ ዙርያ ያነጋገርናቸውና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ሕፃናትና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማሕበራዊ ጥበቃ ማስተባበርያና መከታተያ ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ከማል ናቸው።
አቶ መሀመድ ሕፃናቱ ለጉልበት ብዝበዛ እንዳይጋለጡ ትምህርት የማግኘት መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን ያነሳሉ። ዜጎች ትምህርት እንዲያገኙ የማድረግ ግዴታ መንግሥትን ጨምሮ የወላጅንና የሕብረተሰቡን ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ያስገነዝባሉ። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሕፃናቱ ከሚመጡበት አካባቢ በቅንጅት መሥራቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የሕግ ማዕቀፍ ማውጣቱ አስፈላጊና የግድ መሆኑንም ይናገራሉ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2015