የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶችን ሲያካሂድ ቆይቷል። ዓባይ እና ኪነ ጥበብ ምን እንደሆኑ ለብዙዎቻችን ግልጽ ነው። ዓባይ እንደ ዛሬው የኃይል ምንጭ ከመሆኑ በፊት የጥበብ ምንጭ ነበር። ዛሬ ግን የኃይልም የጥበብም ምንጭ ሆኗል።
ስለዓባይ ብዙ አልዘመርንለትም እየተባለ ይታማል፤ ከግብፆች አንፃር መሆኑ ነው። ግብፅ ውስጥ ዓባይ ከመዋዕለ ሕጻናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ ከኪነ ጥበብ እስከ ሳይንሳዊ ምርምር ጉዳያቸው ነው። እነርሱ ይህን ያህል ጉዳይ ሲያደርጉት እኛ ባለቤቶቹ ታዲያ ለምን የየዕለት ጉዳያችን አይሆንም ያሰኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ ባለፈው ዓመት ሲያካሂደው የቆየው የሥነ ጽሑፍ ምሽት አለ። የሥነ ጽሑፍ ምሽቱ የዘንድሮውን ዓመት ደግሞ በዚህ በመስከረም ወር ጀምሯል። ቅዳሜ መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም በሀገር ፍቅር ቴአትር የዚህ ዓመት የመጀመሪያው ዙር ተካሂዷል። የሥነ ጽሑፍ ምሽቱ ወርሃዊ ሲሆን በአንዳንድ ምክንያቶች ግን ወር ሲዘል ይታያል። ሆኖም ግን ታስቦበት መዘጋጀቱም የከተማ አስተዳደሩን ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ያስመሰግነዋል።
የ2015 ዓ.ም የሥነ ጽሑፍ ምሽቱ የተጀመረው ‹‹አሻራችን ቀንዲላችን ማዕዳችን›› በሚል መሪ ቃል ነው። በመክፈቻው ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሰርጸ ፍሬስብሐት እንደገለጹት፤ እስከ አሁን ድረስ በተሰራው ሥራ ብዙ አማተሮችን ወደ ጥበብ ዘርፉ ማምጣት ተችሏል፤ የክዋኔ ልምምዶች እንዲደረጉ ዕድል ፈጥሯል። እንደ አገር ደግሞ በኪነ ጥበብ ሥራዎች መልዕክት ማስተላለፍ ተችሏል።
እንደ ሰርጸ ገለጻ፤ የዘንድሮው መድረክ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውጤቱ በታየበት ማግስት የሚደረግ ስለሆነ የጥበብ ሥራዎችም ውጤት ያሳዩበት ይሆናል። ዓባይ ግድብ እንዲሆን ሥነ ጥበብ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፤ ስለሆነም የጥበብ ዘርፉ አቅሙን ያሳየበትም ጭምር ነው። የኪነ ጥበብ ዘርፉ በዓባይ ገዳይ ሲቆጭበትም፣ ሲያለቅስበትም ሲደሰትበትም ኖሯል፤ አሁን ደግሞ ውጤቱን እያየ ነው።
‹‹በ1993 ዓ.ም እጅጋየሁ ሽባባው ‹ዓባይ›› ብላ ያወጣችው ሙዚቃ ዛሬም ቁጭ ብላችሁ የምትሰሙት ነው›› ያለው ሰርጸ፤ ዓባይ ምን አይነት ፖለቲካዊ ውስብስብነት እንዳለው በሚገባ ገልጻዋለች ብሏል። እኛ ጋ ሲንደረደር የምናየው ዓባይ ግብጾች ጋ ሄዶ ግን ብዙ ነገራቸው መሆኑን ነግራናለች። የሕይወታችን መሰረት ሁሉ ዓባይ ውስጥ እንደሚገኝ ትነግረናለች።
ሰርጸ እንደሚለው፤ እጅጋየሁ ሽባባው ስለዓባይ ባቀነቀነች በ10ኛው ዓመት 2003 ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሊጀመር የመሰረት ድንጋይ ተጣለ። ኪነ ጥበብ በምናብ ነገሮችን እንደሚያሳይ አሳየች፤ እጅጋየሁ ነብይ ሆነች።
እነሆ ግድቡ ከተጀመረ በኋላ ደግሞ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በየሙያቸው ዘርፍ አሻራቸውን ሲያሳርፉበት ቆይተዋል። እንደ ሰርጸ ሃሳብ፤ የአሁኑ የኪነ ጥበብ እንቅስቃሴ ደግሞ የተለየ መልክ ያለው ነው፤ ይሄውም የቁጭት ሳይሆን የደስታ ነው። ወደ ቀንዲልነት ሄዷል፣ ቀንዲል የማብሰር ምሳሌ ነው። ውሃ ደግሞ የሥልጣኔ መነሻ ነው። ብዙ የሥልጣኔ መነሻዎች ቢኖሩም ሌሎቹ ግን የመሸራረፍ ባህሪ አላቸው፤ የውሃ ሥልጣኔ ግን የመሸራረፍ ባህሪ የለውም። ይህ በዓለም ላይ የሚታይ ሀቅ ነው። ኪነ ጥበብ ደግሞ የእነዚህ ሁሉ መነሻ ነው።
‹‹ዓባይን የሚያክል የጥበብ ሥራ የለም›› የሚለው ሰርጸ፤ ከዚህ በኋላ ‹‹ያበጠው ይፈንዳ›› የሚል ዘፈን አያስፈልግም፤ ይህ እስከ አሁን ሲዘፈን ቆይቷል። ዓባይ ተገድቦ ውጤት እያሳየ ያለበት ወቅት ነው፤ ስለዚህ የኪነ ጥበብ ምሽት ፕሮግራሙ በዓባይ ተስፋ ላይ እንደሚያተኩር ተናግሯል።
እንዲህ አይነት የጥበብ ምሽቶች መኖራቸው ለአማተር ባለሙያዎች ዕድል ይፈጥራል። ዓባይም ዛሬም እንደ ትናንቱ የጥበብ ምንጭ ይሆናል። የጥበብ ምንጭ ሲባል ዘፈን እና ግጥም ብቻ አይደለም፤ ብዙ ፈጠራ ውጤቶች የሚታዩበት ነው፤ ፍልስፍናዎች የሚፈጠሩበት ነው።
ዓባይ እንዲህ በቁጥጥራችን ሥር ከመዋሉ በፊት በአስፈሪነቱ፣ በወሳጅነቱ፣ በአይደፈሩነቱ ሲሞገስ ኖሯል፤ ከዚህ በኋላ ደግሞ በአገልግሎቱ ይወደሳል ማለት ነው።
እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር ልብ እንበል። ምንም እንኳን ግብጾች ለዓባይ ትልቅ ትኩረት መስጠታቸው ሀቅ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ለዓባይ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠንም የሚለው ግን አያሳምንም። ምናልባት ለመጠቀም ዘግይተን ይሆናል እንጂ ኢትዮጵያውያን ለዓባይ ያላቸው ቅርበት ግን ጥንታዊና የነበረ ነው። የብዙ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ነው። ለዚህ ደግሞ በቂ ማሳያው ሕይወታችን ሁሉ ከዓባይ ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው።
በሕዝብ ሥነ ቃል ውስጥ ያሉ ትውፊቶችን ልብ እንበል። ትውፊት የሚመጣው ከሕይወት መስተጋብር ነው፤ በመኖር ውስጥ ነው። አባባሎች፣ ተረትና ምሳሌዎች፣ የቃል ግጥሞች የሚፈጠሩት በዕለት ከዕለት ኑሯችን ውስጥ ከምናገናቸው ነገሮች ነው። ስለዚህ ዓባይ ከሕይወታችን ጋር የተሳሰረ ነው ማለት ነው፤ ምክንያቱም ትውፊቶቻችን ዓባይ ላይ ያተኮሩ ናቸው። ዓባይን የተመለከቱ የትየለሌ አባባሎችና የቃል ግጥሞች፣ ተረቶች አሉን። ጥቂቶችን እናስታውስ።
ዓባይ የሚለውን ቃል ትርጉም እናስብ። ለወንዙ እያገለገለ ያለውን መደበኛውን ቃል እንተወውና፤ ብዙ፣ ግዙፍ፣ ጀግና፣ ሰፊ… የሚሉ ተደራቢ ትርጓሜዎችን ተሰጥቶታል። ለዚህም ነው ዓባይ እና ዓባይነሽ የሚሉ የሰው ስሞች የሚወጡት። በዓባይ ስም የተባሉ ምሳሌያዊ አነጋገሮቻችንም እንዲሁ ግዝፈትን፣ ስፋትን፣ ብዛትን የሚገልጹ ናቸው።
ከምሳሌያዊ ንግግሮች፤ ዓባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል፣ ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል፣ ዓባይ ቢሞላ ተሻገር በሌላ፣ ዓባይ አንተ አየኸኝ ከደረት እኔም አየሁህ ከጉልበት፣ ዓባይና ስንቅ እያደር ይቀላል፣ የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው፣ የሰው ቤት ዓባዩ፣ ዓባይን በጭልፋ… የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ።
ለምሳሌ ‹‹ዓባይን በጭልፋ›› የሚለው አባባል ዓባይ ትልቅ ስለሆነ እንደማያልቅ ለመግለጽ ነው። ‹‹የሰው ቤት ዓባዩ›› የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገርም አንድ በራሱ ቤት ንፉግ የሆነን ሰው ለመግለጽ የተባለ ነው። በራሱ ቤት ንፉግ የሆነ ሰው ከሌላ ሰው ቤት ሄዶ ቸርና ለጋሽ ለመሆን ይሞክራል። ‹‹የሰው ቤት ዓባዩ›› የተባለው ከሌላ ሰው ቤት ያለ ንብረት የማያልቅ ስለሚመስለው ነው።
ዓባይ የጥበብ ምንጭ ነው፣ የቅኔ ምንጭ ነው፣ የቋንቋ ምንጭ ነው። ኪነጥበብ ‹‹ዓባይ›› የሚለውን ቃል ልክ እንደ ወንዙ ግዙፍ፣ ሰፊና ብዙ አድርጎታል። የሌላን ነገር ግዝፈትና ጥልቀት እንኳን ለመግለጽ በዓባይ ይመሰላል። ከእረኞች እንጉርጉሮ ጀምሮ እስከ ታላላቅ ባለቅኔዎች ዓባይ የጥበብ ምንጭ ሆኖ ኖሯል።
ኧረ የአንችስ ነገር ይቅርብኝ ይቅርብኝ
ዓባይን በጭልፋ መጠንቀል ሆነብኝ
የሚል የአገር ቤት የሕዝብ ዘፈን አለ። የማያልቅ፣ የማይነካ እና የማይደፈር ነገር ነው የጀመርኩ ማለቱ ነው። የማያገኛትን ልጅ አፍቅሮ እየተሰቃየ ነው። ቀደም ባለው ዘመን የመገናኛ አማራጮች የሉም፤ በዚያ ላይ ወግና ልምዱም ጥብቅ ነው። የወደዳትን ልጅ እንዲህ እንደዛሬው በተለያዩ አማራጮች ማግኘት አይችልም ነበር። ዋናው ጉዳያችን ስለፍቅር መግለጽ ሳይሆን ዓባይን እንዴት ሃሳባቸውን እንደገለጹበት ማሳየት ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ቦታው ድረስ በመሄድ ተቀኝተውለታል፤ አወድሰውታል። በየዓመቱ መጋቢት ወር ደግሞ የኪነጥበብ መድረኮች ተዘጋጅተውለታል። ምንም እንኳን ስለ ዓባይ ማንም በየቤቱ፣ በየትምህርት ቤቱ፣ በየሥራ ቦታው የተሰማውን ስሜት ብዕር ከወረቀት ያገናኘበት ቢሆንም የራሱ መድረኮች መዘጋጀታቸው ደግሞ የስሜት ማጋራትን ይፈጥራል። ከያኒያኑም ስሜታቸውን በአደባባይ እንዲወጡ አድርጓቸዋል። ይህ በየዓመቱ ሲካሄድ የቆየ ነው።
ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ደግሞ ዓባይ በዓመት አንዴ መጋቢት ወርን ተጠብቆ ብቻ የሚዘመርለት አይደለም በሚል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ እነሆ ራሱን የቻለ ወርሃዊ የሥነ ጽሁፍ ምሽት አዘጋጅቶለታል።
አንቺ ወዲያ ማዶ እኔ ወዲህ ማዶ
አንገናኝም ወይ ተራራው ተንዶ?
የሚል የአገር ቤት የሕዝብ ዘፈን አለ። እንግዲህ ተራራ ተብሎ የተገለጸው የዓባይ ውሃ ነው። የያኔው አፍቃሬ ፀሎቱ ሰምሮ እነሆ ዛሬ ተራራው ተንዷል። ከዓባይ ወዲህ ማዶ ያለ አፍቃሪ ከዓባይ ወዲያ ማዶ ያለች ፍቅረኛው እንዲህ ህልም አትሆንበትም። ያ የከለከለው ተራራ በዓባይ ድልድይ ተንዷል። በፈለገው ቀን ሄዶ ፍቅረኛውን ማግኘት ይችላል። እንዲህ በአስፈሪነቱ ብቻ ይዘፈንበት የነበረው ዓባይ ዛሬ ግን ስለሚሰጠው ጥቅም ሊዘፈን ነው ማለት ነው።
የዓባይ ውሃ ክረምቱን ሙሉ ሰውን ያቆራርጥ ነበር። መገናኘት የሚቻለው በበጋ ወቅት ነው። ፍቅሩ ብሶበት የበጋ ወቅት የሚጠባበቀው አፍቃሪ እንዲህ ሲል ተስፋ በቆረጠ አንጀት ይዘፍናል።
ዓባይ ጉደል ብለው አለኝ በታህሣሥ
የማን ሆድ ይችላል እስከዚያ ድረስ?
ታህሳስ የበጋ ወቅት የመጀመሪያው ወር ነው። ይሄን የበጋ ወቅት መጠበቅ ያልቻለ ያለው አማራጭ በዋና መሻገር ነው። በእርግጥ ይህ የሚሆነው ደግሞ ዋና ለሚችል ሰው ነው። ዋና የሚችለው ደግሞ እንዲህ ሲል ይዘፍናል።
እስኪ ልሻገረው ዓባይን በዋና
የጎጃም ልጅ ወዶ ምን እንቅልፍ አለና!
ዛሬ ዓባይን ለመሻገር ሐምሌ ነሐሴ፣ ታህሳስ ጥር ብሎ ነገር የለም። በፈለገው ጊዜ ይሻገራል። ልክ የዓባይ ድልድይ ተሰርቶ መሻገሪያ እንደተገኘው ሁሉ አሁን ደግሞ ግድቡ ተገድቦ አገራችንን ብርሃን ሊያደርጋት ነው። ስለጨለማ የተዘፈኑ ሁሉ ታሪክ ይሆኑና ስለብርሃን ይዘፈናል ማለት ነው። እነሆ የዓባይ ዘመን ጥበብ ብርሃን ይሆናል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2015