አሸባሪው ትሕነግ የትግራይን ሕዝብ ከጭቆና ነፃ ለማውጣት በሚል ሽፋን ደደቢት በረሃ ከገባ በኋላ በወቅቱ ኢትዮጵያን ይመራ ከነበረው የደርግ መንግሥት ጋር ለአስራ ሰባት ዓመታት ተዋግቷል።የደርግ መንግሥትን የማስወገድ ዓላማ ያላቸው የውጭ ኃይሎች እጅ ተጨምሮበት በነጻ አውጪነት ሽፋን ማካሄድ የፈለገው ድብቁና እውነተኛው ሥልጣን ላይ የመውጣት ህልሙ ተሳክቶለትም የደርግ መንግሥት ወድቆ ኢትዮጵያን ለሃያ ሰባት ዓመታት በፈላጭ ቆራጭነት መግዛት ችሎም ነበር።
ነጻ እናወጣሃለን ላሉት የትግራይ ሕዝብ ግን በስሙ ከመነገድ በቀር አንዳችም የፈየዱለት ነገር አልነበረም።ይልቁንም ሕዝቡን ለከፋ መከራና ስቃይ ዳረጉት እንጂ።ትግራይና አካባቢዋ ዛሬም የጦር ሜዳ ሆና ቀጥላለችና።በአሸባሪው ትሕነግ እብሪት የተነሳ ዛሬም የጦር ቀጠና ሆና የቀጠለችው የትግራይ ምድር አንደበት ቢኖራትና ቃል አውጥታ የምትናገር ቢሆን ኖሮ ሕወሓት ይሰቀል ትል ነበር።ዛሬም ወጣቶችና ታዳጊዎችም ነፍጠኞች፣ ጠባቦችና ትምክህተኞች ሊወጉዋችሁ ነው እየተባሉ፤ ተገደው ለውጊያ እየተመለመሉ ዓላማ ለሌለው ለማያተርፍ ጦርነት እየተማገዱ ነውና።
አሸባሪው ሕወሓት ሥልጣኑን በሕዝባዊ ተቃውሞ ለቅቆ መከረኛው የትግራይ ሕዝብ ጉያ ከተደበቀ ወዲህ በሕዝብ ከተመረጠ መንግሥት ጋር ለሦስተኛ ዙር ጦርነት እያደረገ ይገኛል።ይህንን የሚያደርገውም ያለጦርነት መኖር ስለማይችል በጦርነት ዕድሜውን ለማራዘም ነው።አሸባሪው ሕወሓት ‹ጭር ሲል አልወድም› በሚል እሳቤ የታጠረ ነው።እናም ‹‹ጭር ካለ ዕድሜዬ አጠረ ማለት ነው›› ብሎ ስለሚደናገጥ ሁከት በመፍጠርና ጦር በመወርወር ዕድሜውን ለማራዘም ዛሬም በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ላይ ወረራና ጦርነት እየፈጸመ ይገኛል።
ሦስተኛውን ዙር ወረራና ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በኢፌዴሪ መንግሥት ፈቃድ፤ በትግራይ ሕዝብ ስም የምግብ እርዳታ ተቀብሎ ነበር።ሆኖም ለምግብ እርዳታ ማቅረቢያ ተሽከርካሪ የተዘጋጀውን ነዳጅ በአደባባይ ሰርቆ ለጦርነት ሲያውለው እጅ ከፍንጅ ተይዟል።ለትግራይ ሕዝብ የተቀበለውን የእርዳታ ምግብም ዘርፎና በየቦታው አከማችቶ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚዋጉለትን የራሱን ተዋጊዎች ሲቀልብበት ተገኝቷል።
ይሄም ምስኪኑ የትግራ ይሕዝብ በስሙ እየተነገደበት ለመሆኑ ተጨባጭ ማሳያ ነው።በጦርነቱ ሕወሓት የትግራይን ወጣት እየመለመለ የጥይት እራት እያደረጋቸው ነው።ባሁኑ ውጊያ ደግሞ ወጣቱ አልቆ ታዳጊውን እያስገደደ ወደጦርነት እየማገደ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።አንዳንዶቹ እንኳን ጦር ለመያዝ ብዕር ለመያዝ የበቁ አይመስሉም።ከቁመታቸው ይልቅ የያዙት ነፍጥ በቁመት ይልቃል።ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን ታዳጊዎችን ለጦርነት መማገድ ዓለም አቀፍ ወንጀል ቢሆንም ሕወሓትን ለማውገዝ ድምፅ ያጠረው ይመስላል።ያው አንድ ፊቱን የወደቀ ቀን ግን በዓለም አቀፍ ወንጀል እንደሚከሱት አሳልፈውም እንደሚሰጡት አያጠራጥርም።
መንግሥት ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ከአሸባሪው ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እደራደራለሁ ሲል አሸባሪው ግን አሻፈረኝ አለ ።‹‹…ሒሳብ እናወራርዳለን ፣ድርድር አያስፈልግም አሁን አዲስ አበባ በጥቂት ጊዜ ውስጥ እንገባለን…›› እያለ ሲፎክር ነበረ።ፉከራውና ቀረርቶው ግን ህልም ሆኖ ቀረ።አሸባሪውም በለስ ሳይቀናው ቀረና መከላከያ ሠራዊቱ ማጥቃት ሲጀመር እና ሲጠቃቀኝ ወደኋላ ዞር ብሎ ‹‹እንደራደር›› የሚል ጥያቄ ማቅረብ ጀመረ።መንግሥት በተደጋጋሚ ለመደራደር ፍቃደኛ ነበር፣ ነገር ግን ማን ይችለናል በሚል ትምክህት አሻፈረኝ ያለው አሸባሪው በጦርነቱ ሲቀጠቀጥ በአፍሪካ ሕብረት በኩል ለመደራደር ፈቃደኛ ነኝ ማለቱ ‹‹ሲስሟት ቀርቶ ሲስቧት›› እንደሚባለው ተረት ይመስላል።
አንዳንድ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች እንደሚናገሩት አሸባሪው በከፈተው በጦርነት በለስ አልቀናውም። ያለው አማራጭ እንደራደር የሚል ጥያቄ ማንሳት ነበር። እንደራደር ያለው ጊዜ ለመግዛትና ለማዘናጋት እንጂ ሰላምን ፈልጎ አይደለም። ለምዕራባውያንም ይኸው ሰላምን ፈልጌ እንቢ አሉኝ የሚል አሉባልታውን ለማሠራጨት እንዲመቸው ነው።
አሸባሪው ድርጅት በጦርነት ተወልዶ በጦርነት ያደገ ስለሆነ ጦርነትን እንደ ዕድሜ ማራዘሚያ ይፈልገዋል።ሰላም ከሆነ የትግራይ ሕዝብም ይጠይቀኛል ብሎ ይሰጋል።ከትግራይ እናቶች ጉያ ሥር ታዳጊዎችን እየቀማ ነፍጠኞች (አሁን ደግሞ ፋሽስቱ መንግሥት ማለት ጀምሯል) ሊወሩን ሊገድሉን ነው ብሎ፤ የጥይት ራት እያደረጋቸውነው።
አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችም በዚህ ሀሃሳብ ይስማማሉ።ኢዜማ ባወጣው መግለጫ ‹‹ሕወሓት ለሰላማዊ ድርድር ተስማምቼ ያለሁ ብሎ ጥያቄ ማቅረቡ መጥፎ ባይሆንም በተለመደ ባህሪው የሰላም ድርድሩን እንደ ጊዜ መግዣ ወስዶ ቀጣይ ጥቃት ለመክፈትና ለጥፋት ዝግጅት እንዳይጠቀምበት እንሰጋለን” ብሏል።
አሸባሪው ቀደም ባሉት ሁለት ጦርነቶች በአፋርና በአማራ ሕዝብ ባደረሰው ጥቃት፤ ንብረት በማውደም ሀብት ንብረት በመዝረፍ ፣ ኢሰብአዊ ጥቃት በማድረስ ሽማግሌዎችን እና ልጆችን በመግደል እናቶችንና ልጃገረዶችን እንዲሁም ሕፃናትን አስገድዶ በመድፈር ጭካኔውን አሳይቷል።
በኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቆም ጦረኝነትና ጎጠኝነት የተጠናወተው ሕውሓት እትብቱ በተቀበረበት ደደቢት በረሃ አስከሬኑ መቀበር አለበት።ያን ጊዜ ጥይት እንደበረዶ የሚወርድበት የትግራይና የአጎራባቹ ሕዝብ ነዋሪዎች የሰላምን ችቦ ይለኩሳሉ።ያሻውም በደደቢት መቃብር ላይ አበባ ያስቀምጣል።ይወድም የነበረው ሀብት ንብረት ይለማል።ልጆችዋ ከጉያዋ እየተቀሙ የጥይት ራት የሚሆኑባት የትግራይ እናት ሰላም አግኝታ እፎይ ትላለች።
እየተነገደበት ያለው የትግራይ ሕዝብ ዘላቂ ሰላም ለማግኘት ሕውሓት ገለል እንዲልለት ወጣቱ መታገል አለበት።
ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት በትግራይ ምድር በደርግ ዘመን የነበረው ጦርነት ፣ በትረ መንግሥቱን ከጨበጠ በኋላ ከኤርትራ ጋር የነበረው ጦርነት ፣ሥልጣኑን ሲለቅ በየጊዜው ጦርነት እየከፈተ እያለቀ ያለው የትግራይ ሕዝብ በቃህ ሊለው ይገባል።በትግራይ ሕዝብ ጉያ ውስጥ ተሸጎጦ፤ ትግራይን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያን እደማት አንጂ አላለማትም። እና በትግራይ ሕዝብ ስም መቆመርና ማጭበር በር ይብቃ። የትግራይ ወጣቶችና ሴቶች ሕወሓትን በቃህ! ብለው ይነሱበት።
አሸባሪ ሕውሓት በዛቻና ጥላቻ የተሞላ ነፍጥ አንግቦ ይዋጣልን በሚል ግብዝ አስተሳሰብ የተዋጠ ነው።ቀደሞ በነፃ አውጪነት ስም ሲያጭበረብር ፣ በትረሥልጣኑን ሲጨብጥም፤ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት በመመዝበር ፣ዜጎች በማማረር፣ ዕድሜውን ለማራዘም ሲጥር ነበር።ሕዝቡ እርስ በርስ በጥላቻ፣በሽኩቻ የጎሪጥ እንዲተያይ አድርጓል።
ሰላምን የሚጠላ የለም በአንድ በኩል ግጭት እየለኮሱ በሌላ በኩል ደግሞ ድርድር እየፈለጉ፤ ጦር ሳይፈቱ ለሰላም ዝግጁ ነኝ ማለታቸው መታየት አለበት።በርግጥም ለሰላም ዝግጁ ከሆኑ ጦራቸውን ፈተው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሳውቀው መደራደር የሚችሉ ይመስለኛል።የጦር እሳት ለኩሶ ንፁሃንን ለእልቂት እየዳረጉ ለሰላም ዝግጁ ነኝ ማለት ለሰሚ ምን ማለት እንደሚሆን የሚሰወር አይደለም !።
ይቤ ከደጃች.ውቤ
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2015