አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ ለማድረግ ከሚሰሩ ስራዎች መካከል አንዱ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ በበቂ ሁኔታ እንዲኖራት ማድረግ ነው። መንገድ ይወስዳል፤ ይመልሳል። የሚወስድና የሚመልስ መንገድ ታዲያ ለሕዝብ ምቹ የሆነ ለአይን ማራኪና ሳቢ እንዲሁም የትራፊክ መጨናነቅን አስቀርቶ ምቹ እንቅስቃሴ እንዲኖር የሚያደርግ መሆን አለበት። ከዚህ አንጻር በመዲናችን ምን አይነት መንገዶች ተሰርተዋል? ምንስ አይነት ችግሮች ይስተዋላሉ ? እንዴትስ እየታረሙ ነው? የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ከአቶ እያሱ ሰለሞን ጋር ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ባለፈው ትልቅ በጀት መድቦ ወደስራ መግባቱ ይታወሳል በበጀት ዓመቱ ምን ምን ስራ አከናወነ ? ከሚለው ቃለመጠይቃችንን እንጀምር።
አቶ ኢያሱ፡- የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በአጠቃላይ ወደ ስምንት መቶ ሃምሳ ሰባት ኪሎ ሜትር የሚደርስ የመንገድ ግንባታና ጥገና ስራዎች ለማከናወን በበጀት ዓመቱ አቅዶ ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም በርካታ ስኬቶች ተገኝተዋል። ይህ ሲባል ወደ 891 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የመንገድ ግንባታና ጥገናዎችን ማከናወን ችሏል። ይህም ከእቅዱ አንፃር ሲታይ 104 በመቶ አካባቢ ነው።
በዚህ ስኬት ውስጥ አንደኛ በግንባታ ሂደት ላይ የነበሩ በርካታ መንገዶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል። ወደ 14 የሚደርሱ የመንገድ ግንባታና ተያያዥ ፕሮጀክቶች በ 2014 ዓ.ም የካቲት ወር አካባቢ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል። የፑሽኪን-ጎተራ የአስፓልት መንገድ ግንባታ የተጠናቀቀው ባሳለፍነው በጀት ዓመት ነው። ከዚህም በተጨማሪ በርካታ መንገዶች በግንባታ ሂደት ላይ እያሉም ለትራፊክ ክፍት እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ስራ ተሰርቷል።
የአዲስ አበባ መንገዶች በተለያዩ ጊዜያት ተገንብተው ወደ መንገድ ኔትወርክ የገቡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የአገልግሎት ጊዜያቸውም እንደዚሁ የተራራቀ ነው። ይህ በመሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ ለብልሽት የሚጋለጡባቸው ሁኔታዎች አሉ። ከዚህም አንፃር በየጊዜው ጥገና ሊደረግላቸው ይገባል። ባለፈው በጀት ዓመት ወደ 10 ነጥብ 36 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ጥገና ተከናውኗል።
ለመንገዶች ዋነኛ የብልሽት ምክንያት የሆነው የፍሳሽ መውረጃ ቱቦ መበላሸት ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ የጎርፍ ማውረጃ ቱቦዎች 311 ኪሎ ሜትር ፅዳትና ጥገና ተከናውኗል። የእግረኛ መንገድ መልሶ ግንባታ በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከተመረቁ መንገዶች ጋር እንደዚሁ በቂርቆስ ፤ በልደታ ክፍለ ከተሞችና ሌሎች ጋር ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ የተጠናቀቁ መንገዶች እንዳሉት ሁሉ በጣም የተጓተቱ ሕብረተሰቡም የተማረረባቸው እንደ ካራ ኮተቤ፣ ቃሊቲ – ቱሉዲምቱ የመሳሰሉት መንገዶችን ማጠናቀቅ ያልተቻለው ለምንድን ነው?
አቶ ኢያሱ፡- እውነት ነው በተወሰኑ ፕሮጀክቶች ላይ የመጓተት ሁኔታዎች ነበር። ለአብነት ያህልም የካራ ኮተቤ መንገድ የግንባታ ፕሮጀክት ማንሳት ይቻላል። ይህ መንገድ ቀደም ሲል በተክለብርሃን አምባዬ ድርጅት የግንባታ ስራ ተይዞ የነበረ ሲሆን የመንገዱን ስራ በሚፈለገው ልክ ማከናወን ባለመቻሉ ውሉ ተሰርዟል። ከዛም የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ተረክቦት ወደ ግንባታ ከገባ በኋላ ስራውን በፍጥነት እንዳይከናወን ሕብረተሰቡ አካባቢ የተወሰኑ ጥያቄዎች ነበሩ። ያንን ለመመለስም ጊዜ ወስዷል። ከሕብረተሰቡ ጋር ውይይቶችን በማድረግ ያነሱትን ጥያቄ የሚመልስ ማሻሻያ ይደረግ ስለነበር ይሄ በተወሰነ ደረጃ የግንባታ ጊዜው እንዲዘገይ አድርጎታል። ነገር ግን ችግሮች ከተፈቱ በኋላ ክረምት ሳይገባ ለማጠናቀቅ ጥረት የተደረገ ቢሆንም ሳይሳካ ክረምት ገብቷል። ስለዚህ የቀሩ ስራዎች የክረምት ወር ማብቃትን ተከትሎ መስከረም መጨረሻ ላይ እንዲጠናቀቅ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- ለመንገድ ስራው መጓተት አሁንም የሚነሳው ምክንያት ሕብረተሰቡ ዲዛይኑን ያለመቀበል ነው። መታጠፊያዎች ወይም የመኪና መግቢያ መውጫዎች ይኑሩ የሚል ነበር። ይሄን የሕብረተሰቡን ጥያቄ በአግባቡ መልሳችኋል? ሌላው የማነሳው ደግሞ በዲዛይን ላይ ነዋሪ አልተስማማም ተብሎ ግንባታን የማቆም ልምድ አለ ወይስ በካራ – ኮተቤው ላይ ብቻ ነው ይህ የተተገበረው?
አቶ ኢያሱ፤- ግንባታ ሕብረተሰቡ ስላልተስማማ አይቆምም። ዋናው መታሰብ ያለበት የመንገድ ግንባታ ስራ የሚከናወነው ደህንነቱ የተረጋገጠ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ከማድረግ አንፃር ታይቶ ነው። ሕብረተሰቡ ካቀረባቸው ጥያቄዎች ውስጥ በዋናነት መስሪያ ቤቱ የማይቀበላቸው ጥያቀዎች አሉ። ቦታው ዳገታማ በመሆኑ የዳገቱ መውጫ ላይ መታጠፈያ መንገድ እንዲኖር የሚፈልጉ አሉ። ይህንን መቀበል ከሚያስከትለው የትራፊከ አደጋ አንፃር የማይሞከር ነው። የታችኛው አካባቢ ነዋሪዎችም ቅሬታ ያቀርባሉ። ሌላው በአጭር ርቀት መታጠፈያ ይኑር የሚል ጥያቄ ነበር፤ ይህም በትራፊክ እንቅስቃሴው ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል። መንገዱ የታለመለትን ግብ እንዳይመታ ያደርጋል።
መንገድ ስራዎች ሲሰሩ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ብቻ የሚያከናውናቸው አይደሉም። ለምሳሌ በራስ ሃይል የመንገድ ስራው ሲከናወን አማካሪ ድርጅት ከውጭ ይቀጠራል። ቴክኒካል ስራውን አይቶ ስለሚሰራ የሕብረተሰቡ ጥያቄ እንደ አግባብነት ይመለሳል እንጂ ሕብረተሰቡ ስላለ ብቻ የሚሆን ነገር የለም።
ሌላው የመዘግየት ስራዎች ካጋጠሟቸው መንገዶች አንዱ የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ መንገድ ነው። ይህ መንገድ የግንባታ ሂደቱ ከተጀመረ ረዘም ያለ ጊዜ ሆኖታል። ለመዘግየቱም ሁለት ዋና ዋና ችግሮች እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ። አንደኛው ከፍተኛ የሆነ የወሰን ማስከበር ችግር ነበረበት ። በብዛት የሚነሱ ቤቶችና መስረተ ልማቶች ከመኖራቸውም በላይ በብዛት የከርሰ ምድር ውሃ ለሶስት ክፍለ ከተሞች የውሃ ሽፋን የሚሰጠው መስመር መነሳት ነበረበት። ይሄ ትልቁ የወሰን ማስከበር ችግር ነበር።
ሌላው ችግር ከፋይናንስ ጋር የተያያዘ ነበር። መንገዱ ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድር የተጀመረ ነበር።
ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ በነበሩት ሁኔታዎች እነዚህ ድርጅቶችም ክፍያ የመፈፀም ሁኔታ ላይ እጃቸውን ሰብስብ አድርው ስለነበር ለከተማው አስተዳደርም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱ እንዲያውቁት ተደርጓል ። ስራውም በመንግሥት አቅም እንዲከናወን የሚደረግበት ሁኔታ ተመቻችቶ የፋይናንስ ዝውውር እንዲኖር ተደርጓል። ከዚህ በኋላ ከኮንትራክተሮች ጋር የውል ማሻሻያዎች ተደርገው በቀጣይ ቀሪ ስራዎችን ለማስቀጠል ታቅዷል። እስካሁን ባለው የግንባታ ሂደት ወደ 55 በመቶ የመንገዱ ክፍል ተሰርቷል። ቃሊቲ ማሰልጠኛ አካባቢ 140 ሜትር ርዝመት ያለው የተሽከርካሪ ድልድይ ግንባታ፤ ወደ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል መዳረሻ አካባቢ 90 ሜትር የሆነ የመሻገሪያ ድልድይ፤ ወደ ጋሪ ድልድይ አካባቢ 50 ከሎ ሜትር መሻገሪያ ድልድይ ግንባታ ተከናውኗል። የመንገዱ የቀኝ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ አስፓልት ለብሶ አገልግሎት እንዲሰጥም ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡- የቃሊቲ – ቱሉ ዲምቱ መንገድ ግንባታ ከቻይናው ኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድር ሲከናወን የግንባታ ባለሙያዎቹ ከቻይና የመጡ ኮንትራክተሮች ይሆናሉ። አሁን በራስ ሃይል መሰራት ሲጀምር በቀደመው የጥራት ደረጃ ልክ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል ?
አቶ ኢያሱ፦ የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ መንገድ አሁንም ስራውን በጀመረው ተቋራጭ እንዲሰራ ነው ጥረት እየተደረገ ያለው። ግንባታዎች በዘገየ ቁጥር ባለው የግንባታ እቃዎች ዋጋ ንረት ምክንያት ብዙ ተጨማሪ ነገሮችን ያስወጣል። ያንን ከኮንትራክተሩ ጋር በመስማማት ስራውን ለመጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ግንኙነት ስራዎች ተጀምራል። ይሄ አንድ ምእራፍ ላይ ሲደርስ ቀድመን በማሳወቅ ስራ እንዲጀመር ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- የመንገድ ግንባታዎች ሲከናወኑ የተለዋጭ መንገዶች ጉዳይ ብዙም ትኩረት አይሰጥበትም። ለምሳሌ የካራ ኮተቤ መንገድ ስራ ላይ ተለዋጭ መንገድ ባለመኖሩ በውስጥ ለውስጥ ኮብልእስቶን መንገዶች ላይ ጫና እንዲፈጠር ሆኗል፤ ሕብረተሰቡም ላልተፈለገ ወጪ ተዳርጓል ። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ኢያሱ፡– ከኮተቤ ካራ ያለው አካባቢ ላይ በርካታ የህብረተሰብ ክፍል የሰፈረበት በኣብዛኛውም አሰፋፈሩ በዘፈቀደ አይነት በመሆኑ አማራጭ መንገድ ለመስጠት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ነበሩ። ያም ሆኖ ግን የውስጥ ለውስጥ አማራጭ መንገዶችን ለመጠቆም በየጊዜው መረጃ ለህብረተሰቡ የሚሰጡበት ሁኔታዎችም ነበሩ። ከአካባቢው ሁኔታ ከኮበልስቶን ንጣፍ መንገዶች አማራጭ በስተቀር ምንም ማድረግ አልተቻለም። ይሄንን ችግር ለመፍታት ግን ትልቁና ዋነኛው መፍትሄ መንገዱን በፍጥነት አጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአዲስ አበባ ከተማ ሶሰት ዘመናዊ መንገዶች እንደሚሰሩ ይፋ አድርጋችሁ ነበር። ስለእነዚህ መንገዶች ቢያብራሩልን?
አቶ ኢያሱ፡- እነዚህ መንገዶች ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ የግንባታ ወጪ ያላቸው፤ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍኑ፣ ከ15 እስከ 30 ሜትር የጎን ስፋት ያላቸው መንገዶች ናቸው። እነዚህ መንገዶች አንደኛው ከአፍሪካ ጎዳና ተነስቶ በኤድናሞል በኩል ወደ 22 ማዞረያ አድርጎ እንግሊዝ ኤምባሲ የሚሄድ የአስፋልት መንገድ ነው። ይህ መንገድ የ Intelligent Transport system (ITS ) መረጃዎችን ጭምር ያካተተና የትራፊክ ፍሰትን ያዘምናል የተባለለት መንገድ ነው።
ሁለተኛው ከአየር ጤና ወለቴ የሚወስደው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ነው። የአካባቢው ማሕበረስብ ለረጅም ጊዜ የሚጠይቀው የመንገድ ማስፋፊያ ጥያቄን ይመልሳል ተብሎ ይጠበቃል። አሁን ላይ ያለውን የትራፊክ እንቅስቃሴ ሊሸከም የሚችል በቀጣይ ደግሞ የፈጣን አውቶብስን ሊሸከም የሚችል ሲሆን 5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 30 ሜትር የጎን ስፋት አለው። ከፍተኛውን በጀት የሚይዘው ይህ መንገድ ሲሆን ወደ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚፈጅ የመንገድ ግንባታ ነው። ሌላው የአቃቂ ድልድይ ግንባታ ሲሆን ይህም 61 ነጥብ 2 ሜትር ርዝመትና 25 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ነው።
አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ የትራፊክ መጨናነቅ ይታያል ለዚህም እንደ ምክንያት የሚነሳው የመኪናውና የመንገዶች አለመመጣጠን ነው፤ የትራፊክ ፍሰቱ ተጣጥሞ እንድሄድ ምን ታስቧል? ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ጋር ተናቦ መስራት ምን ይመስላል ?
አቶ ኢያሱ፦ በከተማችን ውስጥ ያለውን የትራፊክ ፍሰት ቀለል ለማድረግ መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው። የከተማዋን የመንገድ ኔትወርክ እርስ በእርስ የማስተሳሰርና አማራጭ መንገዶች እንዲፈጠሩ ማድረግ በትኩረት የሚሰራባቸው ጉዳዮች ናቸው። ባለፉት ሁለትና ሶሰት ዓመታት የተመረቁት መንገዶች አብዛኛዎቹ የከተማይቱ መንገዶች በዚህ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያላቸው ናቸው።
አሁን በአገልግሎት ላይ ያሉ መንገዶች ደረጃቸውን የማሻሻል ስራ መስራት የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀንስ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል። ቀደም ሲል የከተማዋ ዳርቻ ተብሎ የቀለበት መንገድ የተሰራውና ከተማ ውስጥ ያለው አብዛኛው የቀለበት መንገድም የዚህ አይነት ጫናዎች ያለበት ነው። በመሆኑም በቀለበት መንገዱ መጋጠሚያ ቦታዎች ያለውን የትራፊክ ጫና ለመቀነስ ማዘለያ ድልድዮች እየተገነቡ ነው። ለምሳሌ በተለምዶ ገርጂ ኤምፔሪያል አካባቢ እየተሰራ ያለውን አይነት መንገድ ማለት ነው። በተመሰሳይም ለቡ ፤ ቦሌ አካባቢ እየተሰራ ነው፤ ይሄ በ2015 ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ይገባሉ። አሁን የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የማይናቅ አስተዋፅኦ የሚያደርግ በመሆኑ ወደ ፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
ከተማዋ ውስጥ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ሁኔታ ለመቀነስ የመንገዶቹን ደረጃ ማሻሻል ዋነኛ ተግባር ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ማህበረሰቡ መንገዶችን የሚጠቀምበት መንገድ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይህ ሲባል መንገዶችን የመኪና ፓርኪንግ ማድረግ መንገዶች ለመጨናነቃቸው ምክንያት ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ደረጃቸውን የጠበቁ የመኪና ማቆሚያዎች በከተማዋ እየተሰሩ ነው። ለአብነት መስቀል አደባባይ ስር የተገነባው በጣም በርካታ መኪኖች የሚቆሙበት ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው። አድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክትም በጣም ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ አብሮ እየተሰራበት ያለ ነው። የፓርኪንግ ቦታዎችን በስፋት ማልማት ችግሩን ይቀርፈዋል ተብሎ ይታሰባል።
ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ጋር በቅርበት እየሰራን ነው። ምክንያቱም ስራችን ተያያዥ በመሆኑ ከላይ የተጠቀሱ ነገሮች ከተሟሉ ችግሮች ይቀነሳሉ ተብሎ ይታሰባል።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ አካፋይ መንገዶች ላይ የሚሰሩ የልማት ስራዎች መንገድን በመከለል አደጋዎች እንዲደርሱ እያደረጉ ነው የሚል ወቀሳ አለ ይሄንን እንዴት አያችሁት?
አቶ ኢያሱ፡– በርካታ ትራፊክ ፍሰቱ ላይ ችግር የሚፈጥሩ ነገሮችን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እንመለከታለን። አስፓልት መንገድ ሲገነባ በአካባቢው ላይ የተወሰነ ሙቀት መጨመር የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን ጥናቶች ያሳያሉ። ስለዚህ እፅዋት በመንገድ ዳርና በመንገድ አካፋይ ላይ መተከላቸው ውበት፤ ጥላን ከማምጣቱም በሻገር የአየር ሚዛንን ከመጠበቅ አኳያም የራሱ አስተዋፅኦ አለው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምናያቸው የልማት ስራዎች የትራፊክ እይታን በሚጋርድ መልኩ ናቸው ። ይህን ደግሞ ከአካባቢው ጋር ተመጠጣኝ የሆነን የልማት ስራን በመስራት መቅረፍ ይቻላል።
ሌላው ተገንብቶ በተጠናቀቁ ቦታዎች ላይና የመሀል አካፋይ ለወደፊት መሰረት ልማት ማስፋፊያ ቦታ ይውላሉ ተብለው የተተው ስፍራዎች ላይ የተለያዩ አልሚዎች የግንባታ ተረፈ ምርቶችን በመድፋት የትራፊክ እንቅስቃሴውን እያስተጓጎሉት ይገኛሉ። አንዳንድ ቦታዎቸ ላይ ደግሞ ለስራ እድል ፈጠራ ተብሎ አትክልት መሸጫ ቦታዎች ስለሚሰጡ እና ለተለያየ ተግባር እየዋሉ በመሆኑ የትራፊክ እይታን በመጋረድ የትራፊክ ፍሰቱ ላይ ጫና ሊፈጥር የሚችል መሆኑን በመገንዘብ በማስተዋል ቢሰራ መልካም ነወ።
አዲስ ዘመን፦ በርካታ መንገዶች ተሰርተው ተጠናቀው ለአገልግሎት ከዋሉ በኋላ በፍሳሽ መውረጃ ችግር የተነሳ በክረምት ትንንሽ ሀይቆች ሆነው ይታያሉ። ይህ ከምን የመጣ ነው? አንድ ቦታ ክፍተቱ ከታየ ሌላ መንገድ ሲሰራ እርምት ለምን አይወሰድበትም?
አቶ ኢያሱ፡- ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የፍሳሽ መውረጃ ቱቦ በአጠቃላይ ከመንገድ ልማት ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው። አራት ኪሎ አካባቢ ያለው መንገድ የተገነባበት ዘመንና ከዚህ ቀጥሎ የተገነቡበት ጊዜ እንደ አገልግሎት ዘመናቸው የፍሳሽ መውረጃ ቱቦዎች የተለያየ መጠን አላቸው። የዲያሜትራቸው ያለመመጣጠንም ችግሩን ሰፊ ያደርገዋል። በፊት መንገዶቹ ሲገነቡ ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ የነበሩት መንገዶች ከተማዋ ስትሰፋ ውሃውን የሚያሰርጉ አካባቢዎች በኮንክሪት ተሰርተው ውሃውን ማስረግ ሲሳናቸው ከቱቦዎቹ ጋር ተመጣጣኝ ያልሆነ ፍሳሽ እንዲኖር ያደርገዋል። ይህም በራሱ ከባድ ጫና ከመፍጠሩም ባሻገር በበጋ አካባቢ የሚጣሉ ደረቅ ቆሻሻዎች ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል።
ይህን ችግር ለመፍታት 311 ኪሎ ሜትር የውሃ ቱቦ ጥገናና ፅዳት ከመደረጉም ባሻገር በዓለም ባንክ ጋር የከተማዋን ድሬንኤጅ ማስተር ፕላን እየተጠና ነው። ጥናቱ ሲጠናቀቅና ፀደቆ ወደ ትግበራ ሲገባ ብዙ ነገር የሚቀየርበት ሁኔታ ይኖራል።
አዲስ ዘመን፡- ከተማዋ ውስጥ ነዋሪው በማይረዳው ምክንያት የእግረኛ መንገዶች ፈርሰው ይሰራሉ ተብሎ ሲጠበቀ በዛው የሚቀሩበት፤ አፋቸውን የከፈቱ ትልልቅ ጉድጓዶች የሚታይበት አካባቢ በብዛት ይገኛል ይህ ከምን የተነሳ ነው?
አቶ ኢያሱ፡- የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የሚሰራባቸው ሶሰት ዋና ዋና ክፍሎች አሉ፤ አንደኛው ከመንገድ ግንባታ ጋር የተያያዘ ስራዎችን ማከናወን ነው። ሌላው የመንገድ ጥገና ስራዎችን የሚያከናውን ሲሆን ሶሰተኛው ደግሞ የመንገድ ሀብቱን የሚያስተዳድር ነው። ትልቁ የዚህ ተቋም ፈተና የግንባታ ስራ የሚያከናውኑ አካላት የግንባታ እቃዎችንና ተረፈ ምርቶችን መንገድ ላይ አድርጎ የመገንባት ጉዳይ ነው። ተቋሙ ክተትል በማድረግ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል። ነገር ግን መልሰው ያንኑ ሲፈፅሙ ይታያል።
ሌላው ፈተና በስራ እድል ፈጠራ መንገዶች ላይ ንግድ የሚነገዱበት ቦታ የመንገዱን ሀብቱን በሚጎዳ መልኩ ሲሆን ይታያል። ሌላው ደግሞ በስርቆት የመንገድ ሀብት የሚወድምበት ሁኔታ ነው። የመንገድ ፌሮዎቸ፤ ብረቶች፤ አንፀባራቂዎች ሲዘረፉ ይታያል። ችግሮቹ ብዙ ቢሆኑም መስሪያ ቤቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ባሻገር ከከተማዋ ነዋሪ አንስቶ ሁሉም ባለድርሻ አካል ተረባርቦ ችግሮችን መፍታት ይገባዋል።
ቴሌ አገልግሎት ለመዘርጋት፤ ውሃን ለመጠገን ብሎም ለመዝርጋት መንገድ ሲቆፋፈር ይታያል። ይህ ሲሆን ለመንገዶቹ ካሳ ከፍለው በመሰራታቸው የተነሳ የተቆፈሩትን በአግባቡ እንደመመለስ አለባብሶ የመሄድ ሁኔታዎች ችግሮችን ያባብሳሉ። ከቅንጀት ጋር ያለው ጉዳይ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም የበለጠ የተሻለ ስራ በመስራት ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ የአካል ጉዳተኛውም የሌላውም ከተማ እንደመሆና እነዚህን የሕብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ ስራ ይሰራል ወይ? የተሰራውም በተለያዩ ሁኔታዎች ተቆፍሮ በአግባቡ አለመመለሱስ ለአካል ጉዳተኞች አስቸጋሪ ሁኔታን አይፈጥርም ይላሉ?
አቶ ኢያሱ፡– መንገዶች ሲሰሩ አካል ጉዳተኛውን ታሳቢ አያደርጉም የሚባለውን ሃሳብ አልደግፈውም። በተለይም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በእግረኛ መንገዶች ላይ፤ መሻገሪያዎች ላይ ሁሉንም የህብረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ ጥረቶች ተደርገዋል። በዚህ ዓመት የእግረኛ መንገዶቸ መልሶ ግንባታ ሲደረግ እንኳን ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ያማከለ እንዲሆን ጥረት ይደረጋል። ነገር ግን እነዚህ መሰረተ ልማቶች በሚፈለገው ልክ ተጠብቀው አገልግሎት እየሰጡ ነው የሚለው ላይ ግን ክፍተቶች አሉ። ለምሳሌ ለእግረኞች ተብለው የተሰሩ መንገዶች ላይ ችግኞች ተተክለው አጥር ሲደረግባቸው ይታያል። ይህም ለአካል ጉዳተኞች እንቅስቃሴ አደጋች ነው። ይህ የልማት ስራ ግን ከተቋሙ እውቅና ወጪ ነው። ለዚህም የተለያዩ የእርምት እርምጃዎች ይወሰዳሉ።
ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የመንገድ ግንባታውን አከናውኖ ከጨረሰ በኋላ ሌላ የመሰረተ ልማት አልሚ ደግሞ የሚቆፈርበት ሁኔታ አለ። ምንም እንኳን ካሳ ቢከፈል ሌሎች ቦታዎች በእቅድ የሚሰሩ ስራዎችን አቁሞ ወደ ጥገና ለመመለስ ያለው የሀብት ውስንነት እንቅፋት ሆኗል። በተቻለ መጠን በመናበብ ለመስራትና ለሁሉም ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የፈጣን አውቶብሶች መስመር ግንባታ እንደሚካሄድ ተነግሮ ነበር ። ይሄ በምን ሂደት ላይ ነው? ግንባታው የሚካሄደውስ በማን ነው?
አቶ ኢያሱ፡- በከተማዋ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ከመፍታት አንፃር ትልቁና ዋነኛው ነገር የትራንስፖርት አገልግሎትን መሸከም የሚችሉ የመንገድ ልማት ነው። ቀደም ሲል በፈረንሳይ ካምፓኒ ስራውን ለማስራት ውል ተገብቶ ነበር። ድርጅቱ ውሉን ለመቀጠል ባለመፈለጉ ምክንያት ስራው ሳይጀመር ቆሟል። ይህ ሲሆን ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ዝም ብሎ አልተቀመጠም።
15 የሚደርሱ የፈጣን አውቶብስ መተላለፊያ ኮሪደሮችን ለማልማት ሃሳብ አለ። ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ከጀሞ ሁለት ተነስቶ አምስት ክፍለ ከተሞችን አቆራርጦ ወደ ጀነራል ዊንጌት የሚደርስ ጅምር ስራዎች አሉ። ከጀሞ ሁለት ወደ ጀሞ ሚካኤል አደባባይ የሚወስደውን የፈጣን አውቶብስ መተላለፊያ መንገድ በራስ ሃይል የማልማት ስራ ጀምሯል። ይሄ ብቻ ሳይሆን የፈጣን አውቶብስ መተላለፊያ ኮሪደሮች ከማልማት አንፃር እየተገነቡ ባሉ መንገዶች ላይ ፈጣን አወቶብስ በሚደርስባቸው መስመሮች አብሮ ግንባታዎች እንዲሰሩ ጥረት እየተደረገ ነው።
ለምሳሌ ፑሽኪን ጎዳና ላይ፤ የአራራት ኮተቤ ካራ መንገድ ላይም ወደ ፊት ማልማት ሲያስፈልግ በቀጥታ ማገናኘት እንዲቻል ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። መንገዶቹ መካከል ላይ ደሴት የሚመስሉ ነገር መኖሩ ለትራፊክ እንቅስቃሴው አስቸጋሪ አይሆንም የሚሉ አስተያየቶች ቢሰሙም ወለል ላይ የሚታዩት ደሴቶች ባስ ብቻ በሚተላለፍባቸው መስመሮች ላይ ፌርማታ የሚሆን ቦታ ነው። በቅርቡ ግንባታው የሚጀመርው ከአየር ጤና ወለቴ መንገድ ላይ በተመሳሳይ የፈጣን አውቶብስ መተላለፊያ መንገድ ግንባታ አብሮ እንዲካተት ታቅዶ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የ2015 የተቋሙ እቅድ ምንድነው?
አቶ ኢያሱ፡- በአዲሱ በጀት ዓመት ከላይ ያነሳናቸውን አዳዲስ መንገዶችና በግንባታ ላይ ያሉትን መንገዶች በማጠናቀቅ ለትራፊክ ክፍት የማድረግ እቅድ አለ። ሌሎቹንም መድረስ ያለባቸው ደረጃ ለማድረስ ጥረት ይደረጋል። በመቶ ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠሩ የጥገና ስራዎችን ማከናወን፤ የኮብል አስቶን መንገዶችንም ሆነ የጠጠር መንገዶችን በስፋት የመገንባት ስራ ይሰራል። የፍሳሽ መውረጃ ቱቦዎችን የማፅዳት ስራም በአመቱ ከተያዘው እቅድ መካከል ነው።
ዘንድሮ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ስለሚያከብር በበዓል ዝግጅት ብቻ ሳይሆን በመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ አሻራቸውን ለማስቀመጥ የሚያስችል ስራ ለመስራት ታቅዷል።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የሚያሰተላልፉት መልእክት ካለ እድሉን ልስጥዎት፤
አቶ ኢያሱ፡- የመንገድ መሰረት ልማት ማልማት ሰፊ በጀት የሚጠይቅ፤ ጉልበት፣ ገንዘብና ጊዜን የሚፈጅ መሰረት ልማት ነው። ነገር ግን መገንባቱ ብቻ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው ሊባል አይችልም። ትልቅ ስኬት የሚሆነው የመንገድ ሀብቱን በአግባቡ የመጠቀም፤ የመንከባከብና፤ የመጠበቅ ልምድ ሲዳብር ነው። ክረምት ሲመጣ በመንገዶች ላይ ከሕብረተሰቡም ከመገናኛ ብዙሃንም ከሁሉም አካላት ቅሬታዎች ሲሰሙ ይታያል። ይህ ግን በበጋ ሁላችንም ያጠፋነው ጥፋት ድምር ውጤት ነው።
ስለዚህ የመንገድ ሀብትን እንደ ግል ንብረት የመንገድ ሀብቱን በመንከባከብ የሀገርን በጀት ያለአግባብ እንዳይባክን ሁሉም በጋራ ሊመለከተው የሚገባው ጉዳይ ነው። ማሕበረሰቡ መንገዶችን እንዲለሙለት ከመፈለጉ እኩል ለጥበቃና ለእንክብካቤው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ውድ ጊዜዎን ሰውተው ለጥያቄያችን መልስ ስለሰጡን እናመሰግናለን።
አቶ ኢያሱ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2015