መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም – በፀረ-ፋሺስት ትግሉ ወቅት መተኪያ የማይገኝለት የነፃነት ተጋድሎ ያደረጉት ጀግናው ሌተናል ጀኔራል ጃገማ ኬሎ አረፉ። ጃገማ ለቤተሰባቸው የመጨረሻ ልጅ ቢሆኑም ከሁሉም ጎበዝና ብርቱ ነበሩና አባታቸው የቤተሰቡ አለቃ አደረጓቸው። አባታቸው ‹‹ልጃችንን ስሙን ጃገማ ብየዋለሁ›› አሉ።‹‹ጃገማ›› የአባታቸው የፈረስ ሥም ሲሆን በኦሮምኛ ‹‹ኃይለኛ›› ማለት ነው። አባታቸው ጃገማ እስኪወለዱ ድረስ የፈረሳቸውን ሥም የሚሰጡት ሁነኛ ልጅ አላገኙም ነበር።
የጣልያን ጦር ዓድዋ ላይ ሽንፈቱን ሊበቀል ጦሩን እጅግ አግዝፎ ከ40 ዓመታት በኋላ በ1928 ዓ.ም በድጋሚ ኢትዮጵያን ወርሮ ሕዝብ ሲፈጅ፤ ሀገሩን ሊታደግ ሁሉም በየፊናው ሲራወጥ ጃገማም ገና በ15 ዓመት ዕድሜያቸው የአባቶቻቸውን ጀግንነት ሊደግሙ ዘምተው ጠላትን አርበድብደዋል። በዚህም ‹‹የበጋው መብረቅ›› የሚል ስም ተሰጥቷቸዋል። ሌተናል ጀኔራል ጃገማ ለአምስት ዓመታት ከፋሺስት ጣሊያን ጦር ጋር ሲዋጉ አንድም ቀን ተሸንፈው አያውቁም። ጥይት ሲያልቅባቸው ብቻ ቦታቸውን ለቅቀው ይሄዳሉ።
ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከእንግሊዝ ተመልሠው ዙፋናቸው ላይ ቢቀመጡም ጎንደርና ጅማ ከጠላት ጦር ሙሉ በሙሉ አልተላቀቁም ነበር። በዚህ ጊዜ ጀግናው አርበኛ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ የጃገማን ጀግንነት ያውቁ ነበርና ለንጉሰ ነገሥቱ ‹‹ለጃገማ ትዕዛዝ ቢሰጡልኝ በአምቦ መንገድ ሄዶ በኋላ በኩል ይቆርጥልኛል›› በማለታቸው ጃገማ ከደጃዝማች ገረሱ ጋር እንዲዘምቱ ታዘዙ።
ታዋቂዋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌም ለንጉሰ ነገሥቱ ‹‹ጃንሆይ ይህ ልጅ ገና ሕፃንና የሚያምር ልጅ ነው፤ እንዴት ከሞት ወደ ሞት ይልኩታል? ጦሩን ቢያዩለትም መልካም ነው›› ብለው ስለተናገሩ ጃንሆይም ‹‹እናይለታለን›› አሉ። ንጉሰ ነገሥቱም የጀግናውን ጦር ጎብኝተው ከጃገማ ጋር ምሳ በሉ። ከዚያም ጃገማ ከጃንሆይ ሽልማት ተቀበሉ። በኋላም ከደጃዝማች ገረሱ ጋር ዘምተው ወደ አጋሮ ወርደው የለመዱትን ጀብድ ፈፅመው ዋናውን አዛዥ ጨምሮ የፋሺስትን የጦር መኮንኖች ማረኩ፤ ጦርነቱንም በድል ፈጸሙ። ከፋሺስት ጦር መባረር በኋላም በኢትዮጵያ ጦር ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተመድበው አገራቸውን አገልግለዋል። እኒህ ታላቅ የሀገር ባለውለታ ጀግና መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም አረፉ። ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ ‹‹ጃገማ ኬሎ የበጋው መብረቅ›› በሚል የሕይወት ታሪካቸውን የያዘ መጽሐፍ ጽፎላቸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2011
አንተነህ ቸሬ