ብርቱ ናቸው ጠንካራ ። በስራ የተገነባ አካላቸው ዛሬም ቢሆን ድካም የለውም። የፊታቸው ገጽታ እርጅና የበገረው አይመሰልም። በፈገግታ እንደተሞላ ያለፈውን ውጣውረድ ይመሰክራል ። የአንደበታቸው ቃል ተደምጦ አይጠገብም፣ ተጫዋች ናቸው። አጠገቤ ደርሰው ሰላምታ እንደሰጡኝ ንግግራቸውን በተለየ ምርቃት ጀመሩ።
‹‹አሜን›› እያልኩ በረከታቸውን ተቀበልኩ። ምርቃታቸው ልብ ያሞቃል፣ አቀራረባቸው ያስገርማል። ከዚሁ አድናቆት ሳልወጣ ፣ ስማቸውን ጠየኩ። ቀልጠፍ ብለው ወይዘሮ በለጠች ደበላ እንደሚባሉ ነገሩኝ። በልቤ እውነትም ‹‹በለጠች›› አልኩ ። ኑሮን ታግለው ችግርን በልጠው ማሸነፋቸው እየታየኝ።
ከወይዘሮ በለጠች ጋር ጭውውታችን ጀምሯል። በለጠች ሶዶ ጉራጌ ‹‹አማውቴ›› ከተባለ ስፍራ ነው የተወለዱት። ትውልዳቸው በዚህች ቀበሌ ይሁን እንጂ ዕድገታቸው ‹‹ገሬኖ›› ከሚባል አካባቢ ስለመሆኑ ይናገራሉ። ወላጅ አባታቸውን አያውቁም። እሳቸው እንደተወለዱ መሞታቸውን ሰምተዋል። እናታቸው ባላቸውን በሞት እንዳጡ ለሌላ ባል ተዳሩ። በአካባቢው ባሏ የሞተባት ሴት ብዙ አትቀመጥም፣ እጇን የሚፈልግ ሙያዋን የሚሻ አጠያይቆ ይወስዳታል።
እናት ባል ሲያገቡ በለጡ ለአንዲት አክስታቸው በማደጎ ተሰጡ። አክስት ትንሽዬዋን ልጅ በደስታ ተቀብለው መንከበካብ ያዙ። በቅንጦት ያደጉት በለጡ አንዳች ሳይጎድልባቸውን ልጅነታቸውን በአክስታቸው ዕልፍኝ አሳለፉ።
ዕድሜያቸው ከፍ እንዳለ እንደማንኛወም የአካቢው ሰው እጃቸው በስራ ሊፈተን ፣ ጉልበታቸው በጥንካሬ ሊበረታ ግድ ሆነ ። ለቁፋሮው፣ ለእንሰት ቆረጣው ፣ ለእንጨት ፈለጣው የሚያህላቸው አልተገኘም ። አቅማቸውን ሳይሸሽጉ በታዥነት ከሁሉም ተገኙ ። ወጣትነታቸው ሲያበብ፣ኮረዳነታቸው ከዓይን ሲገባ ደግሞ ትዳር የሚሹ ዓይኖች አረፉባቸው። በወግ ማዕረግ ተድረው ያደጉበትን ቤት በክብር ተሰናቱ ፣ ከደጓ አክስታቸው ጉያም ተለዩ።
በለጡ ትዳር ከያዙ በኋላ ኑሮን ለማሸነፍ ብዙ ታግለዋል። ካቲካላ አውጥተው ጠርሙሱን በሀምሳ ሳንቲም ፣ ጥሩ ጠላ ጠምቀው፤ ጣሳውን በአስር ሳንቲም ሸጠዋል። ባለቤታቸው አብረዋቸው ጥቂት እንደቆዩ አዲስ አበባ በመሄዳቸው ራሳቸውን ለመርዳት የወሰዱት አማራጭ ነበር።
በእነሱ ዘመን ሴት ልጅ ከአማቷ እንጂ ከአባቷ ሀብት አንዳች የመውረስ መብት አልነበራትም። ትዳር ይዛ ወደ ባሏ ስትሄድ ባዶ እጇን እንድትገባ ትገደዳለች። በለጡ ትዳር ይዘው ጎጆን ባቀኑበት ዓመታት ከባለቤታቸው ጋር በእኩል ለፍተዋል። ጥቂት ቆይተው አማቻቸው ባረፉ ጊዜ ባለቤታቸውና እሳቸው ከቤተሰቡ ሀብት ንብረት የመውረሰ መብቱ እንደነበራቸው ያውቃሉ ።
ባል ግን በመብታቸው አልተጠቀሙም። ሀብቱን ሌሎች ሲጠቀሙበት እያዩ በዝምታ አለፉ። ወንድማቸው በእኩል ሲካፈሉ እሳቸው በዝምታ ዕድላቸውን አሳለፉት ። ይህኔ ከሁለት ያጣ የሆኑት በለጡ በሁኔታው በእጅጉ አዘኑ። የባለቤታቸው ግዴለሽነት ከልብ አበሳጫቸው። ከአባትም ከአማትም ቤት ያላገኙትን በረከት እያሰቡ ዕድላቸውን ረገሙ፣ባላቸውን ኮነኑ። ይህን ቅያሜ መነሻ አድርገው ልባቸው የሸፈተው በለጡ በአገራቸው መኖር፣ መቀመጥ አስጠላቸው። ጊዜ ወስደው አርቀው አለሙ ፣ ብዙ ተመኙ ፣ ያሰቡትን ሊያደርጉት፣ሊፈጽሙት ቆረጡ።
በለጡ የመጀመሪያ ልጃቸውን ታቅፈዋል። ባል ከጎናቸው ባይኖሩም ትዳራቸው አዲስና የሚያጓጓ ነው ። እንዲያም ቢሆን ከፍቷቸዋል። ጠዋት ማታ መንገድ ያሰበው ልባቸው አርፎ አልተቀመጠም ። ከዕለታት በአንዱ ቀን የሀሳባቸውን ሊሞሉ መኪና ተሳፍረው አዲስ አበባ ደረሱ።
የገጠሯ ወይዘሮ
ወቅቱ የአጼ ኀይለ ሰላሴ ዘመን ነው። እንደአሁኑ ከተማ ባይሰፋም ፣ ከገጠር ለመጡት ወይዘሮ ሁሉም አዲስና አስገራሚ ነበር ። በለጡ አዲስአበባ ሲገቡ በዕድሜ ወጣት ናቸው ። ለአገሩ ባዳ፣ ለሰዉ እንግዳ ቢሆኑም በወቅቱ የንጉሱን ሚስትና የልጃቸውን ሀዘን ታድመዋል። የዛኔ የእነሱን ሞት ተከትሎ በየቦታው የነበረ ለቅሶ ከዛሬው ይለያል። በገጠር፤ በከተማ፣ በገበያ በመንደሩ ህዝቡ ሀዘኑን በምሬት ይገልጻል ። እሳቸው በጊዜው የነበረው የለቅሶ ስርዓት ደንብና ወግን የተከተለ እንደነበር አይዘነጉም ። ይህ ሁሉ እውነት የበለጡ የልጅነት ትዝታ ነው።
አሁን ወይዘሮዋ አስቀድመው ከተማ ከመጡት ባላቸው ጋር ኑሮን ዳግም ጀምረዋል ። ከተማ እንደ ገጠር አይደለም። አኗኗሩ ይለያል ። መኖሪያና በቂ ገንዘብ ማግኘት የግድ ነው ። ከሰዎች ፣ ከአካባቢው መግባበት፣ መላመድን ይጠይቃል ። ባል ከገቡበት ሥራ በሳምንት ስድስት ብር ይከፈላቸዋል።
በወቅቱ ገንዘቡ ጥሩ ዋጋ ነበረው ። የሚገኘው ገቢ ተጠራቅሞ የወር ቀለብ ይሸምታል፣የቤት ኪራይ ይከፍላል። የጎደለውን ሞልቶ ስለነገው ይቆጠባል። እንዲያም ሆኖ በለጠች ቁጭ አላሉም ። ጎጇቸውን ለማቅናት ቤታቸውን ለመሟላት ከአረቄ፣ ከጠላው ይሉ ነበር ። አረቄና ጠላቸውን የሚወዱ ደንበኞች የእጃቸውን ሙያ እየሻቱ ይጎበኟቸዋል። ወይዘሮዋ ከጣሳ ጠላው አስርሳንቲም፣ ከጠርሙስ አረቄው ሀምሳ ሳንቲም ይቀበላሉ።
አሁን በለጡና የአዲስ አበባ ህይወት በወጉ ተላምደዋል። የልጅነት ባለቸው ከጎናቸው ሆነው ያግዟቸዋል። በለሙያዋ ወይዘሮ ኑሮን ለማሸነፍ ህይወትን ለማሳመር ሌት ተቀን ይለፋሉ። ውሎ እያደር የቤተሰብ ቁጥር መጨመር ይዟል። አንድ የነበረው ልጅ በእህት ወንድም ተከቧል ።
በየጊዜው ቤተሰቡ ሲጨምር ፍላጎት ያይላል፣ የሚበላው ፣ የሚለብሰው ይበዛል፣ የሚፈልግ የሚጠይቅ ይበረክታል። ሆድን ሞልቶ ኑሮን ለማሸነፍ ደግሞ ልጆች ለሆድ እንጂ ለስራ አልደረሱም። በላይ በላይ የሚወለዱት ህጻናት የወላጆችን እገዛ ይሻሉ። ለሚበሉት፣ ለሚለብሱት፣ ለሚኖሩበት ሁሉ ግዴታው በእናት አባት ትከሻ ወድቋል።
የአስራ አንድ ልጆች እናት- በለጠች
አሁን ወይዘሮ በለጠች በልጆች ተከበዋል። አንድ ብለው የጀመሩት መውለድ ተበራክቶ ከአስራ አንድ ልጆች እናት አድርጓቸዋል። ኑሮ ልፋት እየጠየቀ፣ ህይወት በፈተና እየተሞላ ነው። ልጆች ማደግ ሲጀምሩ ፍላጎታቸው በርክቷል። በለጠችና ባለቤታቸው ኑሮን ለማሸነፍ በሩጫ ላይ ናቸው። አንዳንዴ ባሰቡት መዋል አይገኝም፡፤ ይሆናል ያሉት ተለውጦ ካልታሰበው ይጥላል። ይበጃል ይሉት ተቀይሮ ቤት በፈተና ይሞላል ። በበለጠች ህይወት ያለፈው እውነትም ይኼው ነው።
ከወለዷቸው አስራአንድ ልጆች አምስቱን በየጊዜው በሞት አጥተዋል። በየሰበቡ የልጅ ሞት ቢያጠቃቸው በሆነው ሁሉ ማዘናቸው አልቀረም ። ዛሬ ላይ ሲያስቡት ግን ፈቃዱን ሁሉ ለፈጣሪያቸወ ያሳልፋሉ። በተቀሩት ፍሬዎች ተጽናንተውም ነገን በተስፋ ያስባሉ። በለጠች ቤተሰባቸውን ለማኖር ያልሞከሩት የለም። በቀን ሰራተኝነት የአናጺ ረዳት ሆነዋል። በጽዳት ስራ ህንጻዎችን ዞረው ጠርገዋል።
ትራንስፖርቱ ከዛሬው ሲታይ ወጪው ትንሽ ይመስላል። የዛኔ የእለቱን ማግኘት ግን ቀላል አልነበረም። በለጠች ካሰቡት ለመድረሰ ረዥሙን መንገድ በእግራቸው አቋርጠዋል ። ሲያገኙ በታክሲ ቢሞክሩም አብዛኛው ጉዞ የጉልበታቸው ነው ። ቤታቸው ሲገቡ ሰውነታቸው ይዝላል፣ አቅማቸው በድካም ይፈተናል። እንዲያም ሆኖ ለራሳቸው ስንፍናን አያሳዩም። ስራ ካሏቸው ባገኙበት ገብተው እንጀራቸው ያደርጉታል።
የትዳር- ወለምታ
የበለጠችና ባለቤታቸው ትዳር የሚጀምረው ከልጅነት ዕድሜ ነው። ደጋግመው እንደሚናገሩት ከእሳቸው ውጭ ሌላ ሰው አያውቁም ። ክፉ ደጉን፣ ሀዘን ደስታውን ያለፉበት ጎጆ አስራ አንድ ልጆችን አፍርቷል። ሁለቱም ባተሌ ሆነው ቤት አቅንተዋል፣ ልጆችን በእኩል አሳድገዋል። ባለቤታቸው ከልጅነት እስከ ዕውቀት ከጎናቸው አልራቁም። ጥንዶቹ ከገጠር ወጥተው ከተማን በመረጡ ጊዜ በሀሳብ አንድ ሆነው ዘልቀዋል።
አንዳንዴ የአባወራው የስራ ባህርይ ከቤት ያርቃል። የመስራት ዕድሉን ባገኙ ጊዜ እንጀራ ፈላጊው አባት ቤተሰቦቻቸውን ትተው ከሌላ ቦታ ይከርማሉ። አስፈላጊ ከሆነ ወራት የሚያሰቆጥር ቆይታ ይኖራቸዋል። ይህ ልማድ በእሳቸውና በቤተሰቡ ዘንድ ሲመላለስ የኖረ እውነት ነው።
በአንድወቅት አባወራው ከቤት ከአካባቢ የሚያርቅ ስራ ተገኘላቸው። ይህን ዕድል ማለፍ ያልፈለጉት ሰው እንደልማዳቸው ቤተሰቡን ተሰናብተው ወደታሰበው ስፍራ አቀኑ። አባወራው ካሉበት ስራውን ጀምረው ወራት አስቆጠሩ ። ቦታው የተስማማቸው ይመስላል። በቶሎ ሳይመጡ ጊዚያት ተቆጠሩ። ለስራ መሄዳቸውን የሚያውቁት በለጠችና ልጆቻቸው መመለሳቸውን እየናፈቁ ጠበቋቸው ። እንደታሰበው አባወራው አልመጡም ። ጥቂት ቆይቶ ከቤተሰቡ ጆሮ አንድ ወሬ ደረሰ። አባወራው ከሌላ ሴት ጋር ኑሮ መያዛቸው ታወቀ።
ይህን እውነት የሰሙት ልጆች አባታቸውን አጥብቀው ተቃወሙ። ከዚህ ዕድሜ በኋላ ከሌላ ጎጆ ትዳር መያዛቸውን ሲያውቁ ከልብ አዘኑ። ይህ ቆይታ እምብዛም አልቀጠለም። አባወራው ያደረባቸው ህመም አልጋ አስያዛቸው። ክፉኛ መታመማቸውን ሲያውቁ ወደ ቤት ሊመለሱ ግድ ሆነ ። በለጠች የልጅነት ባለቸውን የልጆቻቸውን አባት ባዩ ጊዜ አልጨከኑም። ከነችግራቸው ተቀብለው ማስታመም፣ መንከባከብ ያዙ።
አባወራው ከደጓ ባለቤታቸው እጅ ወድቀው የህመም ጊዜያቸውን ገፉ። አስታማሚዋ በለጠች በሆነው ሁሉ ሳይከፉ ፣ ባፈጸሙት በደል ቂም ሳይዙ ባላቸውን ደገፉ። እንደልፋታቸው አልሆነም። ባል ከሞት አላመለጡም ። አንድ ማለዳ ህይወታቸው ማለፉ ተሰማ ። ወይዘሮዋ በደላቸውን ሳያስቡ፣ መካዳቸውን ሳይቆጥሩ አባወራቸውን በክብር ሸኑ።
ኑሮን ከልጆች ጋር
ከሞት የተረፉት ሰድስቱ የበለጡ ልጆች በራሳቸው ዓለም ይኖራሉ። ሁሉም የግል ህይወት ሲያሮጣቸው ይውላል። በለጠች የማረፊያ ዕድሜ ላይ ቢገኙም የልጅ እጅን አልናፍቁም። አሁን ባሉበት አቅም ሮጠው፣ ደክመው ማደርን ይሻሉ። በእርግጥ ከድካም የሚያሳርፍ ፣ ‹‹አለሁሽ›› የሚል ልጅ ቢኖራቸው አይጠሉም። ልጆቹ ግን ይህን ያስቡ አይመስልም። የእሳቸው ጥንካሬም ለዚህ አይነቱ እገዛ የሚጋብዝ አልሆነም። ሁሌም ከልጆቻቸው ፊት ቀድመው መገኘት ልማዳቸው ሆኗል።
ከልጃቸው መሀል አንደኛዋ በክፉ ደግ ከጎናቸው አትርቅም። ሰርታ ካገኘችው ሁሉ የእጇን ታቃምሳቸዋለች፣ አንዳንዴ እናትና ልጅ ባለመግባባት ይጋጫሉ። ጠብ ኩርፊያቸው ግን ዕድሜ አይፈጅም ። ትንሽ እንደሚያማት የሚያውቁት በለጠች ሁሉን በትዕግስት ችለው ያልፋሉ ። በእሳቸው የማትጨክነው ልጅም መልካም በዋለች ቁጥር የእናት ምርቃት ይደርሳታል ።
ካሉት ወንዶች ልጆች አንደኛው በውትድርና እንደዘመተ አልተመለሰም። ይሙት ይኑር ያላወቁት እናት ለዓመታት ደጁን ሲናፍቁ ኖረዋል። እሱን ሲያስቡ አለ ብለው አይደሰቱም፣ ሞቷል ሲሉም ተስፋ አይቆርጡም። በተጋጨ ስሜት ሲዋልሉ ኖረዋል ።
ቀሪዎቹ ሁለት ወንዶችም እናታቸውን ሊጦሩ አልታደሉም ። በተለይ አንደኛው ጥሩ የእጅ ሙያ ከእሱ ጋር ነው። ስራ የተባለውን አሳምሮ ለመጨረስም የሚያህለው የለም። በሚያገኘው ገንዘብ ግን ለእናቱም ሆነ ለራሱ አይበጅም ። ገቢውን ለካቲካላ አውሎ በስካር ሲንገዳገድ ይገባል። ሌሎቹም ራሳቸውን ከመርዳት ባለፈ ለእናታቸው ጓዳ የሚተርፍ አቅም የላቸውም ።
እንዲህ መሆኑ እናት በለጠችን ፈጽሞ አያስከፋም ። ልጆቹ ራሳቸውን ችለው ማደራቸው ብቻ በቂ መሆኑን አምነው ፈጣሪን ያመሰግናሉ። ‹‹ዳሳሼ›› የሚሏት ሌላዋ ሴት ልጃቸው የልጅ ልጆች አሳይታቸዋለች። አንዳንዴም ብቅ እያለች ጓዳቸውን ትጎበኛለች ፣ ጎናቸውን ትዳብሳለች ። በለጠች በዚህ ደስ ይላቸዋል።
በለጠችን በዘንድሮ
ወይዘሮዋና የዘንድሮ ኑሮ ውድነት በግንባር ተፋጠዋል። ዛሬ ምንም ነገር በቀላል ዋጋ የሚገኝ አልሆነም። ገበያ ወጥተው ባዶ አጃቸውን የሚመለሱበት ጊዜ ይበረክታል። እሳቸው ካገኙ በልተው፣ ካልሆነም ‹‹ተመስገን›› ብለው ማደርን ለምደዋል። ብዙ ቤተሰብ ያላቸውን ባዩ ጊዜ ግን ልባቸው ከልቡ ይሰበራል ።
በለጠች አብዝተው ቡና ይወዳሉ። ቀድሞ በቀን ሶስቴ አፍልተው መጠጣት ልምዳቸው ነበር ። አሁን ይህን ቢተውም አንዳንዴ ከእጃቸው ማጣት የዕለቱ ልምድ ሊቀርባቸው ይችላል። እንዲህ ሲገጥማቸው የቀድሞ ጎረቤቶቻቸውን ያሳታውሳሉ። እነሱ ዛሬ ከጎናቸው የሉም። ሁሉንም በሞት አጥተዋል። ይህ ክፉ አጋጣሚ ዛሬን ብቸኛ አድርጎ በትናንት ትዝታ ያመላልሳቸዋል።
አሁን እንደቀድሞው በጉርብትና የሚቀርቡት የለም። በአጋጣሚው ከሌሎች ቢገናኙም ኑሯቸው ከእነሱ ስለማይመስል አብሮነትን አይመርጡም። እንዲህ መሆኑ ገለልተኛ አድርጎ ለብቻ አኑሯቸዋል። በአጼው ዘመን ያገኙት መኖሪያ ቤት ‹‹የቀበሌ›› የሚል ስያሜ ተችሮት በዝቅተኛ ክፍያ እየኖሩበት ነው። በዓመት ስልሳብር ይከፍሉበታል። በቤታቸው ዓለም ደስተኛ ናቸው። ወይዘሮዋ ዕድሜያቸው ቢገፋም ስራ ካሏቸው ወደኋላ አይሉም። ዛሬም ቢሆን ሰርተው ማደር፣ ሮጠው ማረፍን ይመርጣሉ።
በለጠች አመስጋኝ ሴት ናቸው። ዛሬም ከአንደበታቸው ‹‹ተመስገን›› ይሉት ቃል ተደጋግሞ ይሰማል። የጌጃ ሰፈሯ ወይዘሮ በዕድሜያቸው ማምሻ የሰው እጅ ላለማየት ፣ ከራስ ጋር ትግል ጀምረዋል። አስራአንድ ልጆች ወልደው ሰድስቱ በህይወት ቢኖሩም ከራሳቸው በላይ ለራሳቸው የቅርብ ደራሽ አላገኙም። በልጆቻቸው አለመጦር ፣ አለመደገፋቸው ፈጽሞ አያሳዝናቸውም። ሁሉም ለራሱ እንጂ ለሰው አልተፈጠረም የሚል ዕምነት አላቸው ።
እሳቸው በሆነባቸው ሁሉ ተጨንቀው አያውቁም። ዛሬን በምስጋና እየተሻገሩ የነገዋን ጸሀይ ዳግም ለማየት በንቃት ይነሳሉ። ህይወት ማለት፡- ለእመት በለጠች ራስን አሸንፎ መታየት ነው። ህይወት ማለት፡- ለብርቱዋ ሴት ዛሬን በትጋት መስራት ነው። ህይወት ለእሳቸው በልፋት ድካም የሚቀድሙት፣ የሚያሸንፉት ትግል ነው ። ለበለጠች፣ ለክንደ ብርቱዋ ዕድሜ ጠገብ ወይዘሮ።
መልካም ሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2015 ዓ.ም