በምልክት በተነገረን አቅጣጫ ከአስፓልቱ ወጥተን ጎርበጥባጣውን መንገድ ይዘን መድረሻችንን እየፈለግን ነው:: በቆርቆሮ አጥር በታጠሩ አንዳንድ ቤቶች ደጃፍ ያገለገሉ የታሸገ ውሃ ኮዳዎች ተከማችተዋል:: የኮዳዎቹ ምልክት አካባቢው ከመኖሪያ መንደርነት ይልቅ የሥራ አካባቢ እንደሆነ ይጠቁማል::
መዳረሻችንም እንዲህ ካሉ የፕላስቲክ የውሃ ኮዳዎችና ከፕላስቲክ ተረፈ ምርቶች የተለያዩ ምርቶች ከሚመረቱበት ድርጅት ስለነበር ቅኝታችንን እያረግን ከምንፈልገው ቦታ ደረስን::
ከቆርቆሮው አጥር ላይ አነስ ባለ ጽሁፍ የተጻፈውን የድርጅቱን ስም አልተለመከትነውም ነበርና ድርጅቱን አልፈነው ሄደናል፤ በኃላ ላይ ግን አጠያይቀን ተመልስን:: ለካስ አጥሩ ላይ የተለጠፈውን ‹‹ ኖቭል›› የሚል ጽሁፍ አልተመለከትነውም ነበር:: የቆርቆሮውን አጥር በር ገፍተን ወደ ውስጥ ዘለቅን:: ወደ ውስጥ ስንገባ ያልጠበቅነውን ነገር ተመለከትን በአግራሞች አፋችንን ያዝን::
ለቤት፣ ለበረንዳና ለመንገድ ዳር ችግኝ መትከያ የሚሆኑ ምርቶች ፣ ሞተረኞች ከኃላ የሚያስገጥሙት ሳጥን፣ ተቋማት ድርጅታቸውን ለማስተዋወቅ የሚጠቀሙበት ሰሌዳ (ቢልቦርድ)፣ የመሳሰሉት ቅርጽ ሲወጣላቸው፣ የተጠናቀቁት በቀለም ሲዋቡ ተመለከትን:: በተለያየ ቀለማትና መጠን ውብ ሆነው ለገበያ ዝግጁ የተደረጉት ደግሞ በመደርደሪያ ላይ በአንድ ረድፍ ተደርገዋል:: ከምርቶቹ መደርደሪያ ላይ ተቋማት በአርማቸው ወይንም በምልክታቸው በትእዛዝ ያሰሯቸው የአበባ መትከያዎችንም ተመልክትን፤ በኖቭል ድርጅት ግቢ ውስጥ::
ምርቶቹ የእጅ ጥበብ ሥራ ውጤት መሆናቸው ደግሞ ይበልጥ አስደነቀን:: ምርትና ማርታማነትን ለመጨመርና ጊዜ ለመቆጠብ ሲባል ዘመናዊ መሳሪያዎችን መጠቀም የሚመረጥ ቢሆንም፣ የእጅ ጥበብ ውጤቶች በደንበኞች በእጅጉ ተፈላጊ መሆናቸው ይታወቃል:: የእጅ ጥበብ ውጤቶች በዋጋም ውድ እንደሆኑ ይነገራል::
ለነገሩ ኢትዮጵያውያን የሚታወቁት በእጅ ጥበብ ሥራቸውም አይደል:: ለእዚህም የሸክላ ውጤት የሽመና ሥራው ይጠቀሳል:: የእጅ ጥበብ ስራ ትእግሥትን ይጠይቃል:: ወጣት ካለው የትኩስነት ባህሪ ጋር ተያይዞ እንዲህ ባለው ሥራ ላይ ተሰማርቶ ለውጤት ይበቃል ተብሎ ላይጠበቅ ይችላል::
እኛ ያየነው ግን በተቃራኒ ነው:: ሰራተኞቹም አሰሪዎቹም በሥራ ያልደከሙ ትኩስ ኃይሎች ናቸው:: ሥራውን ለመሥራት ፍላጎት ብቻ ነው የሚያስፈልገው ክህሎቱን እርስበርስ በመማማር ያዳበሩት መሆናቸውን ሥራቸውንና አሰራራቸውን ተዘዋውረን ባየንበት ወቅት አረጋግጠናል:: በሙያው ላይ የሚገኙት ወጣቶች በተለያየ የትምህርት ደረጃና ኑሮ ላይ የነበሩ ናቸው::
ስራው በተለያየ አጋጣሚ በተዋወቁ ሶስት ወጣቶች ነው የተጀመረው፤ ከብዙ ውጣ ውረድና ልፋት በኃላ ነው ሰርቶ የመለወጥ ፍላጎት ያላቸውን ወጣት ሠራተኞች በማሳተፍ ጥሩ መስመር በመያዝ ላይ የሚገኘውን ኖቭል ድርጅት በሁለት እግሩ ማቆም የተቻለው::
ሥራው በሶስት ወጣቶች ቢጀመርም፣ ሀሳብ ከማፍለቅ ጀምሮ ድርጅቱን ለስኬት ለማብቃት በኃላፊነት እየተጋ ያለውና በኢንቨስትመንት ደረጃ ለማሳደግ እንደ ታላቅ ወንድምም እንደመሪም አጥፊውን እየገሰፀ፣ እየተቆጣ፣ በወጣትነት ከሚስተዋለው ችኩልነት ሰከን ብለው፣የነገን ጣፋጭ ፍሬ ለመብላት ሩቅ አልመው እንዲሰሩ በማድረግ የአንበሳውን ድርሻ የያዘው ወጣት ዮናስ ጌቱ ይባላል::
ሁለቱ የሥራ አጋሮቹ ወጣት ዮናስ መረጃውን እንዲሰጠን መርጠውታልና ቆይታችን ከወጣት ዮናስ ጋር ሆነ:: ወጣት ዮናስ የተወለደውና እድገቱ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል ጌዲኦ ዞን ዲላ ከተማ ሲሆን፣ ለወላጆቹ ሁለተኛ ልጅ ነው:: የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን እስኪያጠናቅቅ ብቻ ነው በዲላ የኖረው::
በሸቀጣሸቀጥ ንግድ ሥራ የሚተዳደሩት ቤተሰቦቹ ኑሮአቸውን በአዲስ አበባ ከተማ በማድረጋቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ከተማ ፀሐይጮራ ተብሎ በሚጠራው ትምህርትቤት ነው የተከታተለው:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኃላ በአንድ የግል ትምህርትቤት ኮምፒውተር ሳይንስ ተምሮ 2002ዓምበዲፕሎማ ተመርቋል::
ወጣቱ በተማረበት የትምህርት መስክም ሆነ የተገኘውን ሥራ ለመሥራት የተለያየ ጥረት ቢያደርግም የልቡ አልሞላለትም:: ቤተሰቡ ይተዳደርበት በነበረው የንግድ ሥራ መስመር ውስጥ ለመግባት መንገዱ ቀላል ቢሆንም፣ በፈጠራ ሥራ የራሱን ሥራ መሥራት ፍላጎት ነበረው::
ያን ወቅት በአሁኑ እድሜው ላይ ሆኖ ሲያስበው ፈጠራን በታዳጊነት እድሜው ነው ያዳበረው:: ታዳጊ ሆኖ ቤት ውስጥ የተበላሹ የቁም ሳጥንና የተለያዩ ሳጥኖችን መጠገን፣እየፈቱ ማሰር፣ የኤሌክትሪክ ሥራዎችን መሞከር ከሚያደርጋቸው ጥረቶች መካከል ይጠቀሳሉ:: ጥረቶቹም ይሳኩለት ስለነበር ቤተሰቦቹ ለሚያጋጥሙ አንዳንድ ብልሽቶች ለባለሙያ የሚያወጡትን አስቀርቶላቸው እንደነበር ያስታውሳል::
ጉርምስናው ሲመጣ ደግሞ አንዳንዶች በውጭ ሀገር የተሻለ ኑሮ ይገኛል ብለው እንደሚያስቡት እርሱም ወደ ውጭ መሰደድን ተመኘ:: በአሜሪካ የሚኖሩ ዘመዶቹ ግፊት ደግሞ የበለጠ ለስደት እንዲነሳሳ አደረገው:: በኬንያ በኩል አድርጎ ወደ አሜሪካ ለመሄድ ኬኒያ ሄደ:: በዚያም ከሁለት ወራት በላይ አልቆየም::
የስደትን አስከፊነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በማየቱና ገና ‹ላም አለኝ በሰማይ› እንደሚባለው አይነት የአሜሪካ ጉዞው መቼ እንደሚሳካ እርግጠኛ ባልሆነበት፣ ሌሎች አምስትና አስርት አመታት በስደት እንደቆዩት በኬኒያ ሆኖ መጠበቁን ጊዜ ማባከን እንደሆነ ተገንዝቦ ወደ ሀገሩ ተመለሰ::
መለወጥና በኢኮኖሚ ማደግ ሀገር በመቀያየር ሳይሆን፣ሰርቶ በመለወጥ መሆኑን ማመኑ እንደጠቀመው የሚናገረው ወጣት ዮናስ፣ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኃላ በታዳጊነት እድሜው ይሞካክራቸው የነበሩ የጥገናና የኤሌክትሪክ ሥራዎችን ማጠናከር ፈለገ:: ለእዚህም አጫጭር ስልጠናዎችን ወሰደ::
የኤሌክትሪክ የሙያ ክህሎቱን በማጎልበት ከኤሌክትሪክ ሥራ ጋር የተያያዘ ሥራ ለመሥራት የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጫ አነስተኛ ድርጅት ከፈተ:: ሙያው ከግንባታ ዘርፍ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ በዘርፉ ላይ ከሚገኙ አንዳንድ ከሚያውቃቸው ሰዎች ጋር በመሆን በሙያው መሥራት ጀመረ:: በኤሌክትሪክ ሥራ አጋጣሚም ከግንባታው ጋር የተያያዙ ሌሎች ሙያዎችን ለመቅሰም ዕድሉን ከማግኘቱ በተጨማሪ ሥራም እየሰራ ገቢ እያገኘ ኑሮውን መምራት ቻለ:: ይህ ስራው ከፍተኛ የገንዘብ ትርፍ ባያገኝበትም፣ የተለያየ ሙያ የማወቅ እድል ከፍቶለታል::
ለአሁኑ ሥራው መነሻዎቹ በዚህ በግንባታው ዘርፍ ላይ የቆየባቻው ጥቂት ጊዜያቶች ናቸው:: በተለይ ደግሞ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በተነሳሽነት የጀመሩት አረንጓዴ አሻራና ፓርኮችን የማስዋብ ሥራ ሀገራዊ ንቅናቄ እንዲፈጠር በማድረጉ የአበባ መትከያዎችን ሰርቶ ለገበያ ማቅረብ አዋጭ እንደሆነ በአእምሮው የመጣለትን ሀሳብ ሳይውል ሳያደር ወደ ተግባር ለማዋል ወሰነ::
ሀሳቡንም በተለያየ አጋጣሚ ለተዋወቃቸው ሴትና ወንድ ጓደኞቹ አጋራቸው:: ሶስቱም በአንድ ላይ ሆነው ለመሥራት ሲወስኑም፣ ለሥራ መነሻ የሚሆናቸው ብድርና የመሥሪያ ቦታ የሚያገኙበትን መንገድ በመምከር ነው ወደ ሥራ የገቡት::
በኦሮሚያ ክልል የሰበታ ከተማ አስተዳደር የሥራ ቦታ በመስጠት ያደረገላቸው ድጋፍ ለሀሳባቸው እውን መሆን ትልቅ እገዛ አደረገላቸው:: ለሥራ መነሻ የሚሆን ብድርም ዋልኮ ከሚባል ድርጅት አገኙ:: ቦታውንም እንደ ተረከቡ ጊዜ ሳያጠፉ በጋራ ሆነው አንድም ሁለትም የአበባ መትከያ ሰርተው ለገበያ ማቅረብ ጀመሩ::
መጀመሪያ የተሰራው የአበባ መትከያ በመጠን አነስተኛ ነው፤ በቀጣይም ለአበባ መትከያ የሚሆን ግብአት ለመግዛት አንድ ሺ ብር ወጭ አድርጉ:: የአበባ መተኪያ አንድ ሺ ስምንት መቶ ብር ተሸጦ ስምንት መቶ ብር ትርፍ አስገኘላቸው:: በዚህም ተደሰቱ፤ የተፈጠረው የደስታ ስሜትም በቃላት የሚገለጽ አልነበረም:: ሁኔታው በተለይ የመጀመሪያዋን የአበባ መትከያ ለብቻው ለሰራው ወጣት ዮናስ የተለየ ደስታ የፈጠረ ነበር:: ሀሳቡን ከማፍለቅ ጀምሮ ለውጤት በማድረስ ያደረገውን ጥረትና ውጣ ውረድ የሚያውቀው እርሱ ብቻ በመሆኑ ነው ከሌሎቹ ስሜቱ የተለየው::
መቸም ደስታ ነው:: ጋብዙኝ የሚል ጓደኛም ስለማይጠፋ መጀመሪያ የተገኘውን ገንዘብ ለዚህ ተግባር አውላችሁት ይሆን ስል ወጣቱን ጠየቅሁት:: ‹‹በፍጹም›› የሚል ነበር ምላሹ:: እድገት የሚመጣው አንድ ተብሎ በመሆኑ አስፈላጊ ከሆኑ ወጭዎች ውጭ ለግል እንዳላዋሉት ነው አጫወተን::
የሥራ መነሻው ዓላማ መለወጥና ማደግ ነው፤ የግል ፍላጎት ይደርሳል የሚል የጋራ አቋም እሱና አጋሮቹ እንዳላቸው ወጣት ዮናስ ያስረዳል:: እዚህ ላይ ስለእርሱ ጠንካራ መሪነትም ወጣቱ ይናገራል::
እነ ወጣት ዮናስ ምርታቸውን በመጨመር ገበያውንም በማስፋት በተለይም ትእዛዞችን ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭም በመቀበል፣ የፈጠራ ክህሎታቸውንም በማሳደግ የተለያዩ ምርቶችን በመጨመር፣ የራሳቸውን ዲዛይን (ንድፍ) ይዘው የሚመጡ ደንበኞችንም ሀሳብ መሠረት አድርገው ሥራቸውን አሰፉ::
በየጊዜው ለውጦችን ማምጣት እንደቻሉና ተቋማትና ግለሰብ ደንበኞችን ማፍራት መቻላቸውን የገለጸው ወጣት ዮናስ፣ የመጀመሪያ የሥራ ውጤታቸውን ከመቀበል ጀምሮ እስካሁን በደንበኝነት አብሮአቸው የዘለቀውን የተለያዩ የማስዋቢያና የዛፍ ችግኞችን በመሸጥ የሚተዳደረውን ወጣት ጅላሎ መኩሪያን ውለታም አልዘነጋውም::
ገበያ ላይ ተፈላጊ ሆኖ የደንበኖች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ አጋዥ ሠራተኞችን በቅጥር ማሰራት የግድ ነበርና የተወሰኑ ሠራተኞችን ቀጠሩ:: ሥራቸው እያደገ መጥቶ ከ60 በላይ ሠራተኞችን መያዝ ቻለ:: በረዳትነት ሥራ የጀመሩ አንዳንድ ሠራተኞችም የሙያ ክህሎታቸውን ማሳደግ (ፕሮፌሽናል መሆን) ችለዋል::
የመሥሪያ ቦታቸውንም በአጥር በመከለልና ምቹ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸው አንዱ ማሳያ ከቢሮ አደረጃጀት ጀምሮ እያንዳንዱ የሥራ ክፍል ምቹ መደረጉ ነው:: ለቢሮ ያዋሏቸው መቀመጫዎችም በድርጅታቸው የተሰሩ ናቸው:: ምርቶቹ ወደ ገበያ ቢወጡም አዋጭ እንደሆኑም እኛም ተቀምጠንባቸው አይተናቸዋል::
የእነርሱን ፈለግ የተከተሉ ሌሎች ደርጅቶችን መፍጠር እንደቻሉም ወጣት ዮናስ ይጠቅሳል:: በድርጅታቸው ምርት ለውጭ ገበያም ሊቀርብ የሚችል እንደሆነ በእርግጠኝነት ይናገራል:: እነ ወጣት ዮናስ ከውጭ ከሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶች ጋር በማወዳደር ራሳቸውን በመፈተሸ ነው በሥራ ውጤታቸው መተማመንን የፈጠሩት:: ምርቱን በሀገር ውስጥ የመተካት አቅም እንደተፈጠረም ይገልጻል::
ደንበኞች በዋጋ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት በሀገር ውስጥ ተመርቶ ሲቀርብ እንደሆነም ያስረዳል:: እርሱ እንዳለው፤ ምርቶቻቸው ከ700 ብር እስከ 15ሺ ብር የሚያወጡ ናቸው::
ድርጅታቸውን አሁን ከሚገኝበት መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ከሚባለው ደረጃ ወደ ከፍተኛ መሸጋገር የእርሱና የአጋሮቹ ፍላጎት ነው:: ድርጅታቸው የሚቀበለውን ትእዛዝ ሌት ከቀን ሰርቶ በጊዜው የማድረስና በመደበኛ የማምረት ጊዜውም በመጠቀም አቅም ከመፍጠሩ በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭም የምርት ማስተዋወቂያ በመክፈት የሚያደርገው ጥረት ለኢንቨስትመንት የሚያበቃው መሆኑን ነው ወጣት ዮናስ የሚናገረው:: መንግሥት ወደ እድገት የሚያሸጋግራቸውን ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥርላቸው ይፈልጋል::
ወጣት ዮናስ እንደማነቆ ያነሳው የጥሬ ዕቃ ግብአት አቅርቦት ዋጋ ውድ መሆንን ነው:: እነሱ ከአስመጪዎች በመግዛት ነው የሚያመርቱት:: ለምርቱ ወደ አምስት አይነት የሚሆኑ ግብአቶች ያስፈልጋሉ:: ቀጥታ ግብአቱን ማስገባት የሚችሉበት መንገድ በመንግሥት ቢመቻች ትርፋማነታቸው እንደሚጨምርም ይገልጻል:: ይህ ሲሆን ተጠቃሚውም ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ያስችለዋል ይላል::
በሌላ በኩል እነ ወጣት ዮናስ በአንዳንድ አዲስ ጀማሪ ድርጅቶች ሰራተኞችን በማስኮብለልና በተለያየ መንገድ ገበያቸውን ለመጣል የሚደረገው ጥረት የሚያሳዝን ሆኖ ቢያገኙትም፣ የበለጠ እንዲተጉ እንዳደረጋቸው ያስረዳል:: በዚህ ‹‹ተስፋ ልቆርጥ አልችልም:: ወደፊትም ተስፋ አልቆርጥም:: ተጋፍጬ ለማደግ ነው ጥረት የማደርገው›› ይላል:: የሥራ አጋሮቼ አቋምም ይሄው መሆኑን ይገልጻል::
በአንዳንድ ሀገራት ባለሀብቶች እንደነርሱ ያሉ ጀማሪ አምራቾችን ምርት በመቀበልና ገበያ እንዲያገኙ በማድረግ ያበረታቷቸዋል ያለው ወጣት ዮናስ፣ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችም እንዲህ ያለውን ተሞክሮ እንዲጋሩ ሀሳብ አቅርቧል::
ኖቭል ድርጅት የመጀመሪያ ምርቱን ከመግዝት ጀምሮ እስካሁን በደንበኝነቱ አብሯቸው የዘለቀው የማስዋቢያና የዛፍ ችግኞችን በመሸጥ የሚተዳደረው ወጣት ጅላሎ መኩሪያ፣ የአበባ መትከያ አቅራቢ ደንበኞች አሉት፤ የኖቭልን ምርት መግዛት ከጀመረ ወዲህ ደንበኝነቱን ከኖቭሎች ጋር አጠናክሯል:: ምርቱ በደንበኞቹ ተፈላጊ ሆኖ ስላገኘውም ደንበኝነቱን አጠናክሮ የቀጠለው::
ደንበኝነቱ የወጣቶቹን ጥረት በተለይም የዮናስን ትጋት የማየት ዕድል እንዲያገኝ እንዳረገው ገልጾ፣ የዮናስን ትጋት እንደሚያደንቀውም ነው የተናገረው:: ‹‹ እነ ዮናስ በየጊዜውም በፈጠራና ሥራቸውን በማሻሻል እያደጉ የመጡ ናቸው:: የገበያ ውድድርንም አሸንፈው ነው የወጡት:: የሥራ ዕድል በመፍጠርም ቢሆን ብዙ ሚና ተወጥተዋል›› ሲል ገልጾ፣ ገበያው እነርሱ ጋ ብቻ እንደማይቆምም እየሰፋ አንደሚሄድም ነው የጠቆመው::
ወጣት ጅላሎ በአልባሌ ቦታ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ወጣቶች ከእነርሱ እንዲማሩም ምክሩን ሰጥቷል:: አንድ ውጤት ላይ ለመድረስ ጥረትና ተስፋ አለመቁረጥ እንደሚያስፈልግም ከኖቭል አሰሪዎችና ሠራተኞች ተሞክሮ ማግኘኑንም ተናግሯል::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2015 ዓ.ም