“መተከዣ”፤
“ልብ ከሀገር ይሰፋል” ይላሉ፤ ደግ ነው። ችግሩ ሀገር ከልብ የሰፋ እንደሆነ ነው። ከሀገር የሰፋ ልብ ፍልስፍናው ሁሉ “ከራስ በላይ ነፋስ” የሚሉት ብጤ ነው። እነከሌ ብለን ባንዳፈራቸውም፤ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሀገራት ዋነኛው መርሃቸው፣ ሕልማቸውም ሆነ ቅዠታቸው “ገናና ነን! ሀብታም ነን! ሁሉ በእጃችን ሁሉ በእጃችን!” በሚሉ የትምክህት መገለጫዎች የተቃኘ ነው።
በራሳቸው የዕለት ተዕለት ጉዳይ መመጻደቃቸው ብቻም ሳይሆን በዓለም ካርታ ላይ ሳይቀር ሀገራችን “በጽጌሬዳ ቀለማት ካልደመቀልን” በማለት “በጠብ ያለሽ በዳቦ ፉከራ!” ግብግብ እስከ መፍጠርም ሊደርሱ ይችላሉ። በስንዴ ልገሳ ሰበብ እጅ እጃቸውን የሚያዩአቸውን ሀገራት ሉዓላዊነት እንደምን ሲዳፈሩ እንደኖሩ በማስረጃ ማሳየት ይችላል። “እኛ ብቻ እንድመቅ! እኛ ብቻ እንግነን! እኛ ብቻ ዓለምን አንቀጥቅጠን እንግዛ! ሌሎች ይንበርከኩልን!” ጉጉታቸውና የሴራ ቅንብራቸውም ይህንኑ ተልዕኳቸውን ለማሳካት እንደሆነ ከእኛም ሆነ ከእነ እከሌ ሌሎች ሀገራት ታሪክና ዐውድ እያጣቀስን ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ እንችላለን።
በአንጻሩ የልባቸውን አድማስ ከሀገር ይልቅ በጣሙን ለጥጠው የሚያሰፉ ሀገራት እምነታቸው፣ የዲፕሎማሲ ጥበባቸውም ሆነ የፖለቲካዊና መንግሥታዊ አቋማቸው “አንካ በእንካ – win win” መርህ ላይ የተመሠረተ ስለሚሆን ስትራቴጂያቸውን የሚያጠብቁት በመከባበርና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በመመሥረት ነው። ሀገሬ ይህንን ዓይነቱን “የልብ ስፋት” መርህ አጥብቃ ስለምትከተል ባደንቃትና ባደምቃት ይገባት ይመስለኛል።
ችግሩ የእኛ የምንላት ሀገር የታሪኳን ርዝመትና ገናናነት ያህል ቁልቁል ስታንስ እንጂ ሽቅብ ለመንጠራራት ያለመቻሏን ሳስብ በውስጤ ቅይም እልባታለሁ። ከፈጣሪ ዘንድ የተሰጣትን የምድር በረከት ታቅፋና በማህጸኗ ሰውራ እንደ ንፉግ እናት ልጆቿ በርሃብና በችግር ሲጠቁ እያየች ቀድማ ባለመባነንም “ከጉስቁልና፣ ከርሃብና ከድህነት ጋር” አቆራኝታን ለዘመናት ማኖሯ ሲታወሰኝም “ከማኅጸኗ እንደ ወጣ ልጅ” ፊቴን አጥቁሬ ብገስጻት፣ ወይንም መከፋቴ ሲበዛ ብወቅሳት ለምን ብላ ልትሞግተኝም ሆነ ልታስሞግተኝ አይገባም።
እርግጥ ነው የሀገሬ ታሪኳም ሆነ ውሎ አምሽቶዋ “ያልታደልሽ እንዴት አደርሽ!” እንዲሉ ያለፈችባቸው የመከራዎቿ ዘመናትና ዓመታት ሲጻፉ የኖሩት ጥቋቁር ፈተናዎቿ እየተገጣጠሙ እንደሆነ አይጠፋንም። “ለእኔ እናት ምን በጃት፤ ያም ድንጋይ ያም አፈር ያም ኮተት ጫነባት” እንዲሉ፤ በእሾህ በሚመሰሉ የቅርብ ጎረቤቶቿና የሩቅ ጠላቶቿ እየተጎነታተለች ዘመኗን በሙሉ አሳሯን ስትበላ መኖሯ አይሰወርብንም።
ከቤት ውላጅ የራሷ ልጆች መካከልም ቢሆን እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ “ባጋቱት ጡቶቿ እንዳንባረክ” የጠቡትን ጡት እየነከሱና መከራዋን እያበዙ እንደሚያስለቅሷት እያስተዋልን ነው። ስለዚህም ነው “ከእሾህ እንደተጠጋ ቁልቋል ዘላለሟን ስታለቅስ” የምትኖረው። ብዙ ሀገራት ከኋላዋ ተነስተው በኢኮኖሚ አቅማቸው እያስከነዷት፣ በእውቀትና በሥልጣኔ ጥበባቸው እያቁለጨለጯት ሲገሰግሱ እርሷ ግን “ከውስጥና ከውጭ መከራዎቿ ጋር እየተፋለመች” በኤሊ ዝግመት ለምን ስትንፏቀቅ እንደኖረችና እንደምትኖር ምክንያቶቹን ደጋግመን እየሰለቅን ስንቆዝም ስለከረምን እንደ አዲስ ለማሰብም ሆነ ለማብሰልሰል መሞከሩ ልብን ያታክታል፤ ጉልበትን ያርዳል፣ ሀሞትንም ያፈሳል።
እንደ ቅንጦት ባያስቆጥርብን፤ ቢያንስ “ያለ ጭንቅና መሸማቀቅ” የዕለት ዳቧችንን ገመና ሸፍነን ብናድር ትልቅ ፀጋ ነበር። የጦርነትና የጦር ወሬ ከመስማት ጆሯችን ጦም መዋል በጀመረ ጊዜም ለፈጣሪ የሚዥጎደጎድለት “ሥዕለት” በቁጥርም ይሁን በመጠን “ይህ ልኩ” ተብሎ ለመዘርዘር የሚያዳግት ይመስለናል።
ሥርዓተ መንግሥታት እየተቀባበሉት ዛሬን የደረሰው ሀገራዊ ዘርፈ ብዙ መከራችን መቼና እንዴት እንደሚቋጭ የሚነግረን ወይንም የሚተነብይልን ጠቢብ ብናገኝና ቁርጡን ብናውቅ፤ እኛ ልጆቿ “ሀገራችን ወዴት እየሄደች ነው?” ብለን ግራ ለተጋባንበት ጥያቄ፤ እርሷም ለራሷ “ወዴት እየሄድኩ ነው?” ብላ ለተቸገረችበት እንቆቅልሽ “እፎይታ” ማግኘት በቻልን ነበር። “ብልጭ ድርግም” የሚለው የዛሬው ሀገራዊ ተስፋችንም በታቀደለት መስመር እየተፋጠነ እንዳይጓዝ እንኳን እየገጠመን ያለው ዘርፈ ብዙ ችግር ከማንም የተሰወረ አይደለም።
“ብልህ ከሌሎች ይማራል”፤
ጸሐፊው ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በሀገሩ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ምሥራቃዊ ሀገራት ኤምባሲዎች ውስጥ ከጥቂት ወዳጆቹ ጋር ለመገኘት ዕድል ገጥሞት ነበር። የመገኘቱ ዋና ዓላማም ከመጻሕፍት ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነበር። አንደኛው በቅርብ ምሥራቋ ሀገር በእስራኤል ኤምባሲ ሲሆን ሰበበ ምክንያቱ ደግሞ በትውልደ ኢትዮጵያዊው ደራሲ በአምሳሉ መሐሪ የተደረሰው “ቤተ-እስራኤል ከትናንት እስከ ዛሬ” የሚለው መጽሐፍ ነበር።
በሁለተኛነት የተገኘነው በሩቅ ምሥራቋ ሀገር በጃፓን ኤምባሲ ሲሆን ለመገናኘታችን ምክንያት የሆነው የዲፕሎማቱ ወዳጄ የደራሲ አሰፋ ማመጫ አርጋው “የጃፓን መንገድ፤ ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ጠላት የለም” የሚለው መጽሐፍ ነው። በእነዚህ ሁለት የኤምባሲ ጽ/ቤቶች በጥቂት ቁጥር የታደምነው እንግዶች አቀባበል የተደረገልን የፕሮቶኮል ይዘቱ በጠነነ አኳኋን ሳይሆን ቤተሰባዊ ወዳጅነቱ ጠንከር ባለበት ዐውድ ነበር። የሁለቱም ኤምባሲ አምባሳደሮች ቁጭ ብድግ እያሉ ስለ ሀገራቸውና ሀገራችን እንድንጨዋወት ድባቡን ያመቻቹልን “ጉርሻው ብቻ ሲቀር” ደማቅ የእራት ገበታ ዘርግተውልን ነበር።
በኢትዮጵያ፣ በብሩንዲ፣ በቻድና በአፍሪካ ኅብረት የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵዊው ክቡር አለልኝ አድማሱ በሚጣፍጠውና በሚራቀቁበት ቋንቋችን ለዛ ባለው ጨዋታ እያዋዙ ያካፈሉን ቁምነገሮች በእጅጉ ተሰምተው የሚጠገቡ አልነበሩም። የኢትዮጵያን ጥንተ ታሪክና አሁናዊ እውነታ ከእስራኤል ታሪክ ጋር እያዛመዱ እንደ “ቤት ልጅ” በቁጭት ይሰጡት የነበረው አስተያየት ስለራሳችን ብዙ እንድንጠይቅ ምክንያት ሆኖናል።
ደራሲ አምሳሉ መሐሪም የተሸመኑበት የኢትዮጵያና የእስራኤል ውብ ባህልና ሕይወት በመጽሐፋቸው ብቻም ሳይሆን ከአንደበታቸው ጭምር እየፈሰሰ ሊያስረዱን የሞከሩበት አቀራረብ ከልብ እንድናመሰግናቸው ግድ ብሎናል። ህልማቸውና ምኞታቸው ሁሉ እትብታቸው የተቀበረበት ቀደምት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ልክ እንደ እስራኤል በልጽጋና ተውባ ማየት እንደሆነ ይናገሩ የነበረው “የድህነታችን እንቆቅልሽ እየመረራቸው፣ የችግሮቻችን ግዝፈት እያስተከዛቸው” ነበር። መጽሐፉን በቋንቋችን ጽፈው ለቀረቡልን ደራሲ አምሳሉ መሃሪ ለሀገራቸው ስላላቸው የላቀ ፍቅር አመስግነን ወደ ጃፓን ኤምባሲ ጎራ እንበል።
ዲፕሎማቱና ደራሲው ወዳጄ አቶ አሰፋ ማመጫ “የጃፓን መንገድ” የሚለውን መጽሐፋቸውን ለመጻፍ መነሻ የሆናቸው የሀገሪቱ በአጭር ጊዜ ሰልጥኖ በኢኮኖሚዋ በዓለም ላይ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የቆመበችበት ምሥጢር ለሀገራችን እንቆቅልሽ እንደ ማነቃቂያና ማንቂያ እንዲሆን በማሰብ እንደሆነ አስረድተውናል። በኤምባሲው የተደረገልን ግብዣ ዋነኛ ዓላማም በቋንቋችን የተዘጋጀውን ይህንን መጽሐፍ ያበረከቱልንን ደራሲ፤ ክብርት አምባሳደሯ በወዳጆቻቸው ፊት በጃፓን መንግሥትና ሕዝብ ስም ለማመስገን ታስቦ እንደሆነ በኢትዮጵያ የጃፓን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ክብርት ኢቶ ታካኮ ገልጸውልናል። በርግጥም ለደራሲው ምሥጋና ሲያንስባቸው ነው። ክብርት አምባሳደርንም ሆነ ደራሲውን የምናመሰግነው ከልብ ነው።
እስራኤልና ጃፓን በቆዳ ስፋታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸሩ በእጅጉ አነስተኛ የሚባሉ ናቸው። ለምሳሌ፡- የጃፓን የቆዳ ስፋት 377,915 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ሲሆን የኢትዮጵያ ደግሞ 1,104,300 ስኩዌር ኪሎ ይሆናል። ይህ ማለት ሀገራችን ጃፓንን 192% ትብልጣለች ማለት ነው። በሕዝብ ቁጥር ሲነጻጸሩ ግን ጃፓን 125.93 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ሲኖራት ኢትዮጵያ በ10 ሚሊዮን ገደማ የሕዝብ ብዛት ከጃፓን ታንሳለች።
ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ነፍስ ወከፍ ምርትን (Per capita GDP) በተመለከተም እ.ኤ.አ የ2022 ትንበያ የሚያመለክተው የእኛዋ ኢትዮጵያ 650.00 ዶላር ሲገመት ጃፓን ደግሞ 36,200.00 ዶላር እንደሚደርስ ይጠበቃል። ዓመታዊ የዜጎችን ገቢ ከማነጻጸር ይልቅ ሹልክ ብሎ በማድበስበስ ማለፉ ይመረጣል። የሕዝብ ቁጥሩን ንጽጽር ለጊዜው አዘግይተን ከእስራኤል ጋር ያለው የኢኮኖሚ እድገት ከጃፓን ጋር ሲተያይ ሁለቱ ሀገራት እጅግ ተቀራራቢዎች ናቸው።
ጃፓን በዓለማችን ላይ ሦስተኛዋ ባለ ግዙፍ የኢኮኖሚ ጌታ ለመሆን የደረሰች ሲሆን በአንጻሩ እስራኤልም የዋዛ እንዳልሆነች በጥናት ላይ የተመሠረቱት መረጃዎች ያረጋግጣሉ። አሁንም የእኛን የኢኮኖሚ ደረጃ በሆድ ይፍጀው እናልፈዋለን።
እጅግ የሚገርመው ጉዳይ ጃፓንም ሆነች እስራኤል ሁለቱም ሀገራት ኢኮኖሚያቸው አገግሞ ዛሬ የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ የቻሉት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አድቅቆና አላሽቆ ከትቢያ ላይ የመነሳት ያህል ማገገም በመቻላቸው ነው። እ.ኤ.አ ሐምሌ 1937 በአሜሪካኖቹ አቶሚክ ቦንብ የጋዩትና ወደ አመድነት የተለወጡት የጃፓኖቹ ሁለት ከተሞች የሂሮሺማና የናጋሳኪ ሰቅጣጭ ታሪክ ዛሬም ሲወራ ለእምባ ይዳርጋል። እስራኤልም ብትሆን ከናዚዎች አሰቃቂ ጭፍጨፋ ተርፋና መንከራተቷ አብቅቶ ነፃነቷን ተጎናጽፋ እንደ መንግሥት የቆመችው እ.ኤ.አ በ1948 መሆኑን ስናሰላ ዛሬ የደረሰችበት ለመድረስ ምን ያህል መራራ ዋጋ እንደከፈለች ለመረዳት አያዳግትም።
በርግጠኝነት ለመናገር የሚቻለው፤ ከማናቸውም ሀገራት ይልቅ እነዚህ ሁለት ሀገራት ለኢትዮጵያውያን ያላቸው ቅርበት የቤተሰብ ያህል የተጠጋጋ ነው። ለምሳሌ፡- የኢትዮጵያን ከተሞች ያጥለቀለቁት የጃፓን ቶዮታ መኪኖች ናቸው። ይህ የመኪና ብራንድ በእኛ ዜጎች በአንደኝነት መመረጥ ብቻም ሳይሆን “በአምልኮት” ደረጃ የሚወደድ ነው። ከቶዮታ ውጪ ሌላ መኪና በዓለም ላይ የተሰራ እስከማይመስል ድረስ ሁሉም ሰው ምርጫው ከእነዚሁ መኪኖች አይዘልም።
እነ ኒሳን፣ ሆንዳ፣ ሱዙኪ፣ ማዝዳ፣ ሚትሱቢሺንና አይሱዙን የመሳሰሉትን በዝርዝሩ ውስጥ እናካት ካልንም የሌሎች ሀገራት ብራንዶች ድርሻ ኢምንት የሚባል እንደሚሆን አያጠራጥርም። ስለዚህም በኢኮኖሚያችን ውስጥ ጃፓን ያላት ቦታ ቀላል እንዳልሆነ ለማመን አይከብድም። በአንጻሩ እስራኤልም ለአብዛኞቹ ኢትዮጵያን ከሃይማኖታዊ፣ ከዕለት ጸሎት፣ ከታሪክና እስከ ደም ውርርስ በሚደርስ መተሳሰር የተጋመድን ስለሆነ ቅርርባችን የቤተሰብ ያህል ነው።
እነዚህን ሁለት ሀገራት የሚያመሳስላቸው የጋራ ታሪክ መከራን ተቋቁሞ የማሸነፍ ብርታታቸውና የሕዝባቸው ጠንካራና አይበገሬ የሥራ ባህል ነው። ጃፓን በውቂያኖስ መካከል የተመሠረተች ሀገር ከመሆኗ አንጻር በየዓመቱ በአደገኛ ዐውሎ ነፋስና በተያያዥ የተፈጥሮ ክስተቶች ሳትጠቃ ኖራ አታውቅም። የፉኩሺማ የኒኩሌር ኃይል ማብላያ ጣቢያዋን ሳይቀር አደጋ ላይ እስከ ማድረስ የደረሰው የሰሞኑ የሱናሚ አደጋ ጉዳቷ እንኳን አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
በአንጻሩ እስራኤል ነጋ ጠባ ስትታገል የምትኖረው ከከበቧት ደመኞቿ ጋር እየተፋለመችና የበረሃ መስፋፋትን ለመግታትና ላለመሸነፍ እየተጋች ነው። የዓለም ሕዝብ የሚሻማበት የጃፋ ብርቱካን የሚበቅለው ከዚያ ከተገራው የምድረ በዳ አሸዋ ውስጥ የመሆኑ ምሥጢር እንኳን ለሩቅ ተመልካቾች ቀርቶ ለእነርሱም ቢሆን ሳይገርማቸው አይቀርም። የሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ግዝፈትና የሕዝቦቻቸው የአእምሮ እውቀት የበለፀገው በዚህን መሰል ተግዳሮች ውስጥ እያለፉ ነው።
“አዬ ጉድ!” እያልን ከእነዚህ ሀገራት ጋር የምንነጻጸረው በመራራ ትዝብት ራሳችንን በራሳችን እየቀጣን ነው። ትዝብቱ በእኛ ብቻ ተውስኖ የሚያበቃ ሳይሆን ተፈጥሮ ራሷና ፈጣሪም ጭምር መስክሩብን ብንል ምን ምላሽ እንደሚሰጡን አይጠፋንም። የተባረከ ምድር ይዘን፣ “የሺህ ዘመናት” ኩራት ተከናንበን፣ “ገናና ነበርን” እያልን ለመተረክ እየጀገንን፤ ስለምን ዳቦ አሮብን “በርሃብና በድርቅ ልምጭ” ስንገረፍ እንደምንኖር ራሳችንን ልንሞግት ይገባል።
“የማይሰለጥን ፖለቲካ ታቅፈን እሹሩሩ” እያልን የምናላዝነውም እስከ መቼ እንደሆነ ግራ ያጋባል። “ፉከራችን ጣሪያ ነክቶ” ተግባራችን ትቢያ ላይ ሲንፈራፈር የሚኖረውም ለምን ያህል ጊዜና ዘመናት እንደሆነ ምሥጢሩ ተሰውሮብናል። ማረሻ ከሚጨብጡ እጆች ይልቅ ስለምን ቃታ ለመሳብ እንደምንሽቀዳደምም እንቆቅልሽ ሆኖብናል።
“ልማድ ውሎ ሲያድር ባህል ይሆናል” እንዲሉ ሥራ ጠልነታችን፣ በላባችን ወዝ ሳይሆን በዘረፋ ለመክበር መቃዠታችን፣ ከመቻቻል ይልቅ መቧቀስ መውደዳችን እነሆ ዛሬ የደረስንበት ደረጃ ላይ አድርሶናል። በዚሁ እንቀጥል ካልንም ነገ ወደየትኛው እንጦሮጦስ ተወርውረን እንደሚለይልን ማናችንም እርግጠኞች አይደለንም።
ሁለቱ የተከበሩ የምሥራቅ አምባሳደሮች በገበታ ጭውውት ወቅት በዋነኛነት የመከሩን ልክ እንደተመካከሩ ሁሉ “እንቆቅልሾቻችሁን ስለምን መፍታት አቃታችሁ?” የሚል ነበር። “ጥያቄ አቅርቤያለሁ መልሱን ብትሰጡኝ” አለ አንጎራጓሪው ድምጻዊ። በወዳጆቻችን መጻሕፍትና ግብዣ ምክንያት ይህን ያህል ከቆዘመን ዘንዳ ነገን መጠበቅ የሚገባን በመሰል ትካዜ ውስጥ ተዘፍቀን ሳይሆን በተነቃቃ ተስፋ ከራሳችን ጋር መሃላ ገብተን መሆን ይገባዋል። ሰላም ይሁን።
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2015 ዓ.ም