የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በተለያዩ ከተሞች ‹‹ስለኢትዮጵያ›› የተሰኘ መድረክ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ በመድረኮቹ በተለያዩ አገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ በነዚህ መድረኮች ለውይይት በሚቀርቡ ርዕሰ ጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ትልልቅ ሰዎችም የውይይት መነሻ ሀሳቦች ይቀርባሉ፡፡ በመድረኩ ሲነሱ ከቆዩ በርካታ ጉዳዮች መካከል ኪነ ጥበባዊ ይዘት ባለው መልኩ በግጥም የተላለፉ ሃሳቦችም ይገኙበታል። እኛም በዛሬው የዘመን ጥበብ ዓምዳችን ቅርበት ያለውን እና በአንድ መድረክ ላይ የቀረበውን የአቶ መስቀሉ ባልቻን ግጥሞች እንደሚከተለው ሙሉውን አቅርበነዋል፡፡
ከዋሻ መሽጎ ከምግባር መንኖ
እየዋለ ሲያድር ሰውኛ ጠፍቶበት
ሥነ-ምግባር ከድቶት
ሥም አውጪ ስም ሰጠው በግብር አስተካክሎ
“የተንቤኑ ተኩላ” በሰው አስመሥሎ
ጉድ አሰኘን እኮ ከሰው ተራ ውሎ
ለአዛውንት አይነገር በእምነት አይዘከር
ተለምኖ አያውቅ ክብር በርሱ አይኖር
ሰው ጤፉ ተባለ አጋንንት ሰፍኖበት
ሰው ነን ያሉ ሁሉ አብረው በአንድነት
ያገር ሽማግሌ ወጥቶ መከረበት
ሲያወጡ ሲያወርዱ በጣም ተቸግረው
ሄዱ ከመሠረት ማንነት ሊያጠኑ
ግድ ሆኖባቸው እናትን ጠየቁ
እናት በምላሿ ‹‹ልጅማ ልጄ ነው እኔም ቸግሮኝ ነው››
ዘመድ ወዳጆቼ ምን ይሆን ማርከሻው?
ጥያቄ ጠየቁ
አባት ጣልቃ ገቡ
‹‹ኧረ እንዲህ አይደለም የዚህ ልጅ ችግሩ
ከባዕድ ማበሩ ከባዕድ ማደሩ
ከኔ ነው ችግሩ›› ብለው መሰከሩ፡፡
ባይሆን ባይሆን ከዋሻ ሲገባ
የዋሻው አጋንንት መክሮት ይሆን ደባ?
ኧረ እንዲህ አልነበር የዚህ ልጅ ነገሩ
ከሰው ተራ ወጥቶ ከክፋት ማበሩ
ኑሮን ማማረሩ
ከኔው ነው ነገሩ ብለውት ጀመሩ።
የአንድ ጐረምሳ ዕድሜ ከዋሻው መኖሬ
ተፈጥሮን ከድቼ ከባህል ተጣልቼ
ከተንቤን ጥልቅ ዋሻ አይኖር ገብቼ
የተበዳይ አጋር ሐቅ አፋላጊ ሆኜ
ላነጋ ላወጋ እውነት ተከትዬ
መሰልኩ አስመስዬ ፍጥረት አማልዬ
አለሁ ከጐናችሁ ከቅንነት እሴት ጠባጠብ ተክዬ››
ብለው ሌላ አከሉበት
ሀብዬ ስጀምር አሥርቱን ትዕዛዛት
በአሉታ መንፈስ አሳየኝ ምልክት
‹‹ተው ተው ይህ ነገር
ምንም አትናገር
በዚህ በኛ ሰፈር
በዚህ በኛ ምድር
ሟችም አይታወቅ ገዳይም አይናገር
ካህን ጥምጣም የለ
መሠዋት ነው ታግሎ
አገር ማኅበረሰብ እራስን ነው መክዳት
ላልሰማው ማሰማት አይገቡ ውስጥ መግባት
የተንቤኑ ተኩላ ሕግ የለው አይገደድ
የያዘው ይዞ ከዱር መንጎዳጎድ
መሰዋት መማገድ
“ለምን” አይጠየቅ
ምንም አይታወቅ
ሂድ ሲሉህ መሄድ ነው
ሲያዝህም መታዘዝ
አሉ በመተከዝ
ተንቤን የጉድ ሠፈር
አለን ልዩ ምስጢር
አለማንገራገር አለመነጋገር
ፊትና ኋላህ ላይ እሳት ቢንጠረጠር
ጋንጃህን አሽትተህ ለመግባት መንደርደር
ይኸው የተንቤን ጉድ
የተንቤኑ ተኩላ አገር ላገር ሲሄድ
እራሱ ሲማግድ ነፃነትን ሲያነድ
ምነው ማለት የለ
እንዴት አይጠየቅ
ጋኔን ለክፎት ነው ከመሸገው ዋሻ
ሲወራ ሲያድር ከምሽጉ ጥሻ
የተንቤኑ ተኩላ በሰው ተመስሎ
ቢስሚላሂ የለ በስመአብ አይባል
የኛንም አይወስድ የለም የሱ ባህል
እናት ሴት መሆኗን
በአገር መመሰሏን
አያምን አያሳምን
ጠፍቶበት ሰው መሆን
የተንቤኑ ተኩላ ከሰው ተመስሎ
መስሎ አስመስሎ
በእንግድነት ገብቶ ለሆድ አስገድዶ
ቤተሰብ አግቶ ለስሜቱ ማግዶ
ልጅን ከአባቷ ፊት አስገድዶ ደፍሮ
ይህ አልበቃ ብሎት በደቦ ተዛዝሎ
አይሆነውን ሆኖ
ደግሞ ይባስ ብሎ
በያዘው ጠብመንጃ ገድሎ አስገድሎ
የተንቤኑ ተኩላ በሰው ተመስሎ
ጉድ አሰኘን እኮ ከሰው ተራ ውሎ
ነፃ አውጪ ነኝ አለ
ታጋይ ተጋደላይ ነኝ በማለትም ማለ
ቀርበን ስናያቸው
የሰው ቅርጽ እንጂ የሰው ግብር የላቸው፡፡
እልል ብለን ነበር ቀን እንደሚያወጡ
ከዋሻው ሲወጡ
ነገር ተገልብጦ ሲሰነባበቱ
ተኩላ ይሁን እፉኚት ጠፍቶን መለየቱ
ከዱር አራዊቱ ብሰው ተከሠቱ
ቢስሚላሂ የለ በስመአብን አያውቁ
ከጠብመንጃው በላይ ቂምን የታጠቁ፡፡
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
በሐረር ለተካሄደው
የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ
ከሽሽጉ አድማሱ አርሲ ሄ ጦሳ ወረዳ
2014 ዓ.ም
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም