ቀኑ መስከረም አምስት ዕለተ ሐሙስ ሲሆን ያገኘኋቸው መሀል መገናኛ ነው።እጅግ ሰብዓዊነት በጎደለውና በሚያሳዝን ሁኔታ የአሮጌ ማዳበሪያ ቅዳጅ በተነጠፈበት መሬት ላይ በግንባራቸው ተደፍተዋል። ድምፃቸው ይሰማ እንጂ የፊታቸው ገጽታ አይታይም። እግሮቻቸው፣ እጆቻቸውና ወገባቸው ከተፈጥሮ አቀማመጥ ውጪ በመሆናቸው የበርካታ አካል ጉዳተኝነት ተጠቂ ናቸው::
“ስለ አቦዬ በሽተኛ ፤ያላችሁን ጣል ጣል አድሩልኝ” ሲሉ የሚያወጡት የልመና ድምጽ በለሆሳስ ይሰማል::ለእግዜር ያለም ኪሱን እየፈተሸ ያለውን እየጣለ ይሄዳል::እኔም ቦርሳዬን ፈትሼ ጥቂት ብሮችን ጣል ካደረግኩ በኋላ ጎንበስ ብዩ፦
‹‹ እባኮትን አባቴ ላናግሮት ፈልጌ ነበር››
በጥርጣሬ እና በመደናገር ስሜት ከተመለከቱኝ በኋላ በደከመ ድምጽ
‹‹ ምን ፈልገሽ ነው ?›› በማለት ሽቅብ እየተመለከቱ ጠየቁኝ
‹‹በአሁኑ ወቅት ልመና በአዲስ አበባ እየተስፋፋ መጥቷል:: ለዚህ ደግሞ አንዳንድ ግለሰቦች ሰዎችን እያታለሉ ወደ ልመና እንዲገቡ እያደረጉ ነው የሚል መረጃ ስላለ የሚያውቁትን እንዲነግሩኝ ነው›› የሚል ጥያቄ አቀረብኩ::እርሳቸውም ፊታቸው በድንገት ተቀያይሮ‹‹ ታዲያ እኔ ምን አውቃለሁ፤የሚመለከተውን ሰው ሄደሽ ጠይቂ እንጂ ››ብለው አንባረቁብኝ:: እርሳቸውን እንዳናግር የጠቆመኝን በመገናኛ አካባቢ ሱቅ በደረቴ ከሚሰራ ወጣት ጋር በመሆን ማግባባት ያዝን:: ከብዙ ሙግትና ማግባባት በኋላ የሚያውቁትን አጫወቱኝ::
ስማቸው ሰማ ሴብሮ እንደሚባል ነገሩን።የአካል ጉዳቱ ሲወለዱ የነበረ ነው።የአካል ጉዳተኝነታቸውን የተመለከተ ሰው አዲስ አበባ ብትሄድ ትጠቀማለህ ስላላቸው ከማያውቁት ሰው ወደ አዲስ አበባ መጡ:: ለከተማዋ አዲስ በመሆናቸው የት እንደሚያርፉ እንኳን አያውቁም:: ሆኖም ይዟቸው የመጣው ሰው ለአንድ ሰው አስረከባቸው::የተረከባቸው ሰውም መጠለያ ሰጣቸው::ከጥቂት ቀናት በኋላም በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች ላይ እየወሰዳቸው ያስለምናቸው ጀመረ::
በሌሊት እያስነሳቸው ወደ ተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በመውሰድ ሲያስለምናቸው ይውልና ሲመሽ እንደገና መጥቶ የለመኑትን ገንዘብ ቆጥሮ ይረከባቸዋል:: አንዳንድ ጊዜም ገንዘቡ ጠርቀም ሲል በሰዎች ምሽትን ሳይጠብቅ ሰብስቦ ይወስዳል::
ሆኖም አቶ ሰማ ሴብሮ ይህ ሕይወት አላስከፋቸውም:: ቢያንስ በተወለዱበት አካባቢ የእለት ጉርሳቸውን ለመሸፍን ይቸገሩ ነበር::እጅና እግራቸውም ስለማይታዘዙላቸው የሚያበላቸውና የሚያንቀሳቅሳቸው ሰው ማግኘት ችግር ነው::አሁን ግን የተረከባቸው ሰው ቢያንስ ጧትና ማታ ከማደሪያቸው እያንቀሳቀሰ በመኪና የሚለምኑበት ቦታ ያደርሳቸዋል:: እራታቸውንም አንድ ዳቦ ይሰጣቸዋል:: አንዳንዴ የሚያስለምናቸው ሰውዬ ሳይመጣ ይውላል። ሆኖም ምንም ቢመጣ አመሻሽ ላይ ሳይመጣ አይውልም::
ሆኖም በመገናኛ አካባቢ በአቶ ሰማ ሴብሮ ላይ የሚፈጸመውን ህገ ወጥ ድርጊት የተመለከቱ ወጣቶች ግለሰቡን በፖሊስ ለማስዝ በመሞከራቸው ሰውዬው ፈርቶ ከአካባቢው ተሰወረ::እርሳቸውም የአካባቢው ወጣቶች በመከሩዋቸው መሰረት ግለሰቡ ሊጠጋቸው ሲፈልግ ለፖሊስ እናገራለሁ ብለው በማስፈራራታቸው አሁን ነጻ ወጥተዋል::ከሰውዬው መራቅ ስለፈለጉም ማርያም ወንዝ አካባቢ ከመሰሎቻቸው ጋር የላስቲክ ቤት ተከራይተው ህይወታቸውን መግፋት ቀጥለዋል::አሁን በልመና የሚያገኙትን ገንዘብ የሚቀማቸው ሰው ባለመኖሩ ደስተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ::
በመዲናችን አዲስ አበባ ዋና ዋና ቦታዎች እንዲህ ዓይነቱን ትእይንት ማየት እየተለመደ መምጣቱን አንዳንድ ሰዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ:: አካል ጉዳተኞችንና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቅመው ልመናን የገቢ ምንጭ ያደረጉ አንዳንድ ራስ ወዳድ ግለሰቦች በጠራራ ፀሐይ እየፈፀሙት ያለ ሕገወጥ ተግባር ነው። በዚሁ ዙሪያ ያነጋገርናቸውና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ጥበቃ ማስተባበሪያና መከታተያ ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ከማል ችግሩ መኖሩን ያረጋግጣሉ።
በመዲናዋ በአንዳንድ የሕብረተሰብ ክፍሎች ልመና እንደ ንግድ ሥራ የተቆጠረበት ሁኔታ ይስተዋላል።ሰው ቤት ተቀጥረው ወይም ሌላ የጉልበት ሥራ መሥራት የሚችሉት ወደ ልመና ይወጣሉ እንጂ አይሰሩም።መንገድ ላይ ህፃናት እየተለመነባቸው ነው። የአካል ጉዳተኞችም ሲለመንባቸው ይታያል።በተለይም የአካል ጉዳተኝነት ያለባቸውን ግለሰቦች አድኖ በመፈለግ እና ከተለያዩ ክልሎች በማስመጣት ለልመና ማሰማራትና ገቢ ማግኘት የተለመደ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል::
የኔ ቢጤዎችን ለልመና የሚያሰማሩ ግለሰቦች መኪና ያላቸው ሀብታሞች ናቸው።አካል ጉዳተኞቹ አደባባይ መጥተው መቀመጥ የሚችሉ ባይሆኑም አምጥተው አስቀምጠዋቸው ይሄዳሉ። ማታም መጥተው ሲሰበስቡ የዋሉትን ገንዘብ ይወስዱባቸዋል።ለእነሱ ሽርፍራፊ ዳቦና የመጠለያ አገልግሎት እየሰጧቸው በቀን በርካታ ገንዘብ ሲሰበስቡ የሚውሉ ግለሰቦች እንዳሉ አቶ መሃመድ አልሸሸጉም::
ብዙዎቹ በልመና ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ግለሰቦች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ሳይሆኑ በራሳቸው በሰዎች አማካኝነት ከክልል የመጡ ናቸው። በተደረገ ጥናት መሰረት ከነዚህ በልመና ከሚተዳደሩት የሕብረተሰብ ክፍሎች ችግረኞች ያልሆኑ እንዳሉ በጥናት ተለይቷል።በመሆኑም ወደፊት ችግሩን በሕግ ማዕቀፍ የመፍታት ሀሳብ መኖሩንም ያወሳሉ።
አቶ መሐመድ እንደሚያብራሩት፤ ቢሮው የአካል ጉዳተኞችና የተለያዩ የከተማዋ ነዋሪዎች የዕለት ጉርስ በማጣትና በተለያየ ችግር ምክንያት ወደ ልመና እንዳይወጡ ይሰራል።የገቡትም ከልመና እንዲወጡና ተሳትፏቸውንም በተለያየ መንገድ እያጠናከረም ይገኛል። የሴፍቲኔት መርሐ ግብር አንዱ ነው። በመርሐ ግብሩ መሥራት የማይችሉት በቀጥታ ድጋፍ ይረዱበታል።በሂሳብ ቁጥራቸው ብር ይገባላቸዋል።በአንድ ሰው 300 ብር ያገኛሉ።መሥራት የሚችሉት ደግሞ የሚጠቀሙበት መርሐ ግብር አላቸው።በሳምንት የተወሰነ ቀን ይሰራሉ። በሰሩት ሥራ ልክ ብር ያገኛሉ።
ሆኖም በሰዎች አማካኝነት ከተለያዩ ክልሎች እየመጡ በልመና ተግባር ውስጥ የሚሰማሩ ሰዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው ስራቸውን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ይናገራሉ::በዚህም ላይ በመዲናችን የኩላሊት በሽተኛ ያልሆነ የኩላሊት በሽተኛ ነው እየተባለ በመኪና በማዞር የሚለመንበትም እንዳለ ሁሉ የኩላሊት በሽተኞችን በመፈለግ ጭምር ትርፍ የጋራ የሚሰሩ ሰዎች እንዳሉም አረጋግጠዋል::
በአጠቃላይ በልመና የተለየ ጥቅም ለማግኘት የሚጥሩ ሰዎችን በመከታተል ለህግ ለማቅረብ ከጸጥታ አካላት ጋር ስራዎች ተጀምረዋል::ሰዎች ከልመና ይልቅ በላባቸው ሰርተው እንዲኖሩ ግንዛቤ መፍጠር ስራም እየተከናወነ ነው::ሆኖም ችግሩ ውስብስብ በመሆኑና የህግ ድጋፍም የሚያስፈልገው በመሆኑ አስተማሪ ቅጣት ማሳረፍ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ ለማድረግ ስራዎች ተጀምረዋል::
ከዚህ ባሻገር ግን ችግረኛ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የማህበረሰብ አቀፍ ክብካቤ ጥምረት የተሰኘ ፕሮጀክት በቀጣዩ ጥቅምት ወር ይቋቋማል። በጀትም ተመድቦለታል።ጥምረቱ ችግሩን ይቀርፋል ተብሎ ይታሰባል ሲሉ አቶ መሐመድ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም