ለአርሶ አደሩ የግብርና ሳንካዎች የሆኑትን ኋላ ቀር ስልቶች ለማስቀረትና ዘመናዊውን የግብርና ሂደት ለመከተል በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የግብርና ምርምር ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ለማዳረስ እየተከናወኑ ያሉ እንቅስቃሴዎች እንደቀጠሉ ናቸው።የኦሮሚያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በምርምር የሚያፈልቃቸውንና የሚያላምዳቸውን የተሻሻሉ የሰብል፣ የእንሰሳት፣ የተፈጥሮ ሃብትና ሌሎችም ቴክኖሎጂዎችን በተለያዩ አካባቢዎች ለማዳረስ እየሰራ ይገኛል።
ተግባራዊውን ሥራ እያከናወኑ ካሉት ማዕከላት ውስጥ ደግሞ የመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል አንዱ ነው፡፡ የመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የግብርና ምህንድስና የስራ ሂደት ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት አቶ መሠረት አበበ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የተለያዩ የቅድመ ምርትና ድህረ ምርት ማከናወኛ የግብርና ማሽነሪዎችን (የበቆሎ ማስፈልፈያ፣ የወተት መናጫ፣ ሁለገብ የእህል መውቂያ መሳሪያ፣ ቀላል ገልባጭ ማረሻ፣ ዘመናዊ የእህል ጎተራና የቲማቲም ዘር መለያ) በማምረትና ውጤታማነታቸውን በመፈተሽ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንዲባዙ በማድረግ ለተጠቃሚዎች የማዳረስ ስራን በማከናወን ላይ ይገኛል።
ማዕከሉ ለአካባቢው አርሶ አደሮች በቴክኖሎጂዎቹ አጠቃቀም ዙሪያ የሰርቶ ማሳያ (Demonstration) ስራ አካሂዷል።ይህንን ተሞክሮም በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ለማስፋት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ማዕከሉ ለአርሶ አደሩ የሚያገልግሉ በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ያሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን የማላመድ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል የሚሉት ተመራማሪው፤ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ካዘጋጃቸው ቴክኖሎጂዎች ውስጥ ዘመናዊ ጎተራ አንደኛው መሆኑንና እየሰጠ ያለውን አገልግሎት እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡
‹‹ዘመናዊ ጎተራን ጠቀሜታ ላይ ማዋል ያስፈለገበት ምክንያት፤ በድኅረ ምርት አያያዝ አብዛኛውን ጊዜ ምርቱ ከተመረተ በኋላ ጥቅም ላይ እስከሚውል ድረስ ባለው ጊዜ እስከ 30 በመቶ የሚሆን ብክነት አለ ተብሎ ይታሰባል።በዋነኛነት ብክነቱ ከሚደርስባቸው ምክንያቶች አንዱ እህሉ ከተመረተ በኋላ በሚቀመጥበት ወቅት ቤት ውስጥ ባሉ ነፍሳት የሚደርስ ጥቃት ነው።በዚህ መንገድ እህልን የማስቀመጡ ዘዴ የእህሉን ጥራት ይቀንሳል።በቀላሉ ለዝርፊያምሊዳርግ ይችላል።በመሆኑም እንዲህ አይነቶቹን ችግሮች ለማስቀረት የመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በአፍሪካ አገራት በስፋት ጥቅም ላይ የዋለውንና ውጤታማነቱ የተረጋገጠውን ማሳያ አገር ውስጥ በማላመድ እዚሁ ተመርቶ አርሶ አደሮች እንዲጠቀሙበት እያደረገ ነው›› ሲሉ ተመራማሪው አስረድተዋል፡፡
ተመራማሪው እንደሚሉት፤ የዚህ አይነት ቴክኖሎጂ በሜክሲኮና ስፔን በስፋት አገልግሎት ላይ የዋለ ሲሆን፤ በአሁን ወቅትም የአፍሪካ አገራት እየተገለገሉበት ይገኛሉ።ለብዙ ዓመታት ተጠቅመውበት ውጤታማነቱ የተረጋገጠና በቀላል ወጭ ሊሰራ የሚችል፤ የተለየ ክህሎት የማይጠይቅ ቴክኖሎጂ ነው።መሳሪያው ሳይበላሽ ከ15 እስከ 20 ዓመታትን ማገልገል ይችላል።ዋጋው 7ሺ 500 ብር ድረስ ይደርሳል።
ቴክኖሎጂውን በመጠቀም እህልን ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ ማቆየት ይቻላል።አርሶ አደሩ ያመረተውን እህል አቆይቶ ጥሩ ዋጋ በሚያወጣበት ወቅት በመሸጥ ጥሩ የኢኮኖሚ አማራጭ ማግኘት ይችላል። ዘመናዊ ጎተራው እንደ አርሶ አደሩ አቅም ከሶስት እስከ አስር ኩንታል መያዝ የሚችል መሆኑን፤ ስሪቱ ዝገት እንዳያጠቃው ተደርጎ እንደተዘጋጀና፤ እህልን ሊያጠቁ የሚችሉ ነፍሳትን አየር በማሳጣት በህይወት እንዳይኖሩ እንደሚያደርግ ነው ተመራማሪው የገለጹት።ከዚህ በተጨማሪ ‹‹እህሉ በጎተራው ገብቶ ለመከማቸት በእርጥበት መለኪያዎች አማካኝነት በደንብ መድረቁ ይረጋገጣል።
ይህንንም በባህላዊ መንገድ ለማረጋገጥ ደረቅ በሆነ የለስላሳ ጠርሙስ ውስጥ ደቃቅ ጨው በመነስነስ ማወዛወዝ፤ በዚህ ወቅት እህሉ እርጥበት ካለው ጨው እህሉ ላይ ያለውን እርጥበት ስለሚወስድ የለስላሳ ጠርሙስ ውስጠኛው ግድግዳ ላይ እህሉ ተለጥፎ ይቀራል።ይህም እህሉ በጎተራው ውስጥ ለመቀመጥ ዝግጁ አለመሆኑን ማሳያ ነው›› ሲሉ ተመራማሪው የአጠቃቀሙን ሂደት ያብራራሉ። ሌላኛው ግብርናን ያዘምናሉ ተብለው ከታሰቡትና ማዕከሉ እያላመደው ካሉት መሳሪያዎች ውስጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነው በደረት የሚታዘል የጤፍ መዝሪያ መሳሪያ ነው።ጤፍ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል በአብዛኞቹ አርሶ አደሮች በተለያየ የአፈር ዓይነትና የአየር ጸባይ የሚመረት ሰብል ሲሆን፤ በዋናነት የጤፍ ምርት መቀነስ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ ጤፍን በመስመር አለመዝራት ነው።
ይህንን ክግምት ውስጥ በማስገባት የመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ከሚጠቀማቸው ቴክኖሎጂዎች መካከል በደረት የሚታዘል የጤፍ መዝሪያ መሳሪያን ማስታወቅ እንደቻለም ተመራማሪው ገልጸዋል። እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ መሳሪያውን በመጠቀም ጤፍ የሚዘራው ሰው በፊት ለፊቱ ያለውን ነገር በአግባቡ እየተቆጣጠረ እንዲሄድ ማድረጉ መሳሪያውን ተመራጭ ያደርገዋል።መሳሪያው እንደ ጀሪካን ከመሳሰሉ በየአካባቢው ላይ ከሚገኙ ቁሶች የሚዘጋጅ ሲሆን፤ ክብደቱም ቀላል ነው።
በእደጥበብ ባለሙያዎችም ሊዘጋጅ ይችላል።በማንገቻው ደረት ላይ በማሰርና በአንድ እጅ በማሽከርከር ጤፉ በመስመር እንዲዘራ የሚያደርግ አካል አለው።በአንድ ዙር ስድስት መስመሮችን መዝራትም ያስችላል።እንደ ጤፉ የዘር መጠን መሳሪያውን አስተካክሎ በብዛት አሊያም አሳንሶ እንዲዘራ ማድረግ ይቻላል።ክብደቱ ቀላል ሲሆን፤ ሴቶች፣ አረጋዊያንና ህጻናትም ሊሰሩበት ይችላሉ።በጥቂት ሰዓት ውስጥ ብዙ ሄክታር መሬትም መዝራት ያስችላል።በባህላዊ መንገድ አንድ ሰው አንድ ሄክተር ለመዝራት እስከ 20 ኪሎ ሜትር መሄድ ይጠበቅበታል።ይህ በዘመናዊ ዘዴ ሲሆን ግን እስከ 30 ዕጥፍ ድረስ ይቀንሳል፡፡
የመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የግብርና ምህንድስና የስራ ሂደት ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ጋር በመተባበር መሳሪያዎች አርሶ አደሮቹ ጋር እንዲደርሱ ጥረት መደረጉን፣ ለአብነትም በግብርና እድገት ፕሮግራም የጤፍ መዝሪያ መሳሪያውን የጤፍ አብቃይ አካባቢዎች እንደ አደዓ፤ ሉሜና ምንጃር ያሉ አከባባቢዎችን በመድረስ አርሶ አደሮችን ያሳተፈ ግምገማ እየተደረገ አገልግሎት ላይ እየዋለ መሆኑን ተመራማሪው ጠቅሰዋል።ዘመናዊ ጎተራውም እንደሚመረተው የሰብል አይነት በተመረጡ ወረዳዎች ላይ ሥልጠና በመስጠትና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ አርሶ አደሮቹ እንዲጠቀሙበት እየተሰራ መሆኑን፤ የቴክኖሎጂዎቹ ፍላጎት ሲኖር ደግሞ በሁሉም ክልሎች ባሉ ወረዳዎች ላይ አምራቾችን በማሰልጠን እንዲጠቀሙበት ለማድረግ ማዕከሉ በጥረት ላይ ስለመሆኑ አስታውቀዋል።
ተመራማሪው ‹‹የምርት ብክነትን ከመቀነስ፣ ጉልበትንና ወጭን ከመጠቆጠብ አንጻር እንዲህ አይነት ቴክኖሎጂዎች ትልቅ ፋይዳ አላቸው።ምርትን በአግባቡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሳይበላሽ ለማንቀሳቀስም ጠቀሜታቸው የጎላ ነው።ማንኛውም አርሶ አደር የተለየ ቴክኒካል እውቀት ሳይጠቀም መገልገል ይችላል።ይህም ኑሮውን በማዘመን ምርቱን በማሳደግ ተወዳደሪ ለመሆን ያስችለዋል›› ብለዋል፡፡ በአሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ምህንድስና ዳይሬክተር አቶ ካሚል አህመድ በበኩላቸው፤ የተሻሻሉ የስራመሳሪያዎችን ሳይጠቀሙ ግብርናን ማዘመን እንደማይቻል በመጠቆም፤ የሰውን ልጅ ጉልበት ቆጥቦ ምርታማነት እንዲጨምር ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንዳለበትና፤ ከመሬት ዝግጅት እርሻን እስከ መንከባከብ እንዲሁም በድኅረ ምርት ወቅት ድረስ ያሉ ሂደቶችን በሙሉ ማዘመን እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
የግብርና ኢንስቲትዩቱም ይህን ታሳቢ ያደረገ ሥራ እያከናወነ መሆኑን፤ ይህም የጥራጥሬ እህሎችን ጨምሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ላይ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ያካተተ አሰራር መሆኑን ጠቅሰዋል።ለእንስሳት ሀብቱም ቢሆን ምግብን ማድቀቅ የሚችሉ መሳሪያዎችን በዘመናዊ መንገድ ለአገልግሎት ማቅረብ መቻሉን ጠቁመዋል። እነዚህን ሂደቶች ወደ ተግባር ለመለወጥ በርካታ ችግሮች አጋጥመዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ሥር ያሉ አራት ማዕከላት አሰላ፣ ባኮ፣ ጅማና ሐረር ላይ ያሉት አብዛኞቹ ከ60ዓመት በላይ ቢሆናቸውም ግብርና በሚፈለገው ደረጃ ማዘመን አለመቻላቸውን፤ በወቅቱ የነበሩት መሳሪያዎችም ከፊሎቹ ተሰባብረው ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸውን፤ ከጥቅም ውጭ የሆኑትን ለመተካትም የፋይናንስ እጥረት እንዳለ ገልጸዋል።
እንደ ብረታ ብረትና ሞተር የመሳሰሉትን መሳሪያዎች ከውጭ ለማስገባት ትልቅ አቅም እንደሚጠይቅና መንግስት ትኩረት ሰጥቶት ቢያንስ ከቀረጥ ነጻ የሚገቡበትን መንገድ ሊያመቻች ይገባል ብለዋል። ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ማዕከሉ መሳሪ ያዎችን ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ሰፊውን የህብ ረተሰብ ክፍል ማዳረስ ይኖርበታል።በተለይ የእርሻ መሳሪያዎች የአርሶ አደሩን አቅም ባገናዘበ መልኩ እየተመረቱ በመሆናቸው በአሁኑ ወቅትም መግዛት የማይችሉ ተከራይተው እንዲገለገሉበት እየተደረገ ይገኛል።በግብርና እድገት ፕሮግራም የተሻለ በጀት እንዲመደብ በማድረግ ሥራ አጥ ወጣቶችን በማሳተፍ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ ተማሪዎች ተደራጅተው እንዲገለገሉበት እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2011
አዲሱ ገረመው