አዲስ አበባ፡- ከቀን ወደ ቀን በአዋሳኝ ቦታዎች እየተከሰተ በመጣው የጸጥታ ችግር ላይ ህዝብና መንግሥት ተቀናጅተው የህግ የበላይነት እንዲከበር የየበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የምስራቅ ወለጋ ዞን ገለጸ፡፡
የዞኑ የአስተዳደርና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታከለ ቶሎሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ከአራት ቀን በፊት በዞኑ ሊሙ ወረዳ አርቁምቤ አካባቢ ለ11 የጸጥታ አካላት ህይወት ማለፍ ምክንያት የሆነ የጸጥታ ችግር ተፈጥሯል፡፡
ይህንንም ችግር በመፍጠር ላይ የሚገኙት አሁን ያለውን አገራዊ ለውጥ የማይደግፉና ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ናቸው፡፡ የኦሮሚያም ሆነ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግሥታት ተነጋግረው ችግሩን በጋራ መፍታት አለባቸው ወይም ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ የሚገባበት ሁኔታ ተፈጥሮ ችግሩ ካልተፈታ እየባሰ ይሄዳል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
«የአካባቢው ኅብረተሰቡ በየጊዜው ቅሬታውን በማሰማት ላይ ይገኛል» ያሉት አቶ ታከለ፣በተለይ ከቀናት በፊት ያጋጠመው ችግር ኅብረተሰቡ በአርቁምቤ መንደር በሰላም እየኖረ ባለበት የጸጥታ ኃይል ፣ በኅብረተሰቡ ንብረት እና በመንግሥት ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በተለይ የቀበሌዋ ጤና ጣቢያ ላይ እና በብዙዎች መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ታከለ ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት እንደሚታ ወቀው ኅብረተሰቡ ሰብሉን የሚሰበስብበት ወቅት እንጂ ጦርነት የሚፈልግበት አጀንዳ የለውም፡፡ ይህን ተልዕኮ ይዞ የሚንቀሳቀሰው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ህዝብ ሳይሆን ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ናቸው፡፡ ይህን አካሄድ ደግሞ መንግሥትና ህዝቡ በጋራ በመሆን ከምንጩ ማድረቅ ካልተቻለ ችግር ነው፡፡
«ህዝቡ የሚፈልገው ሰላም ነው››ያሉት ኃላፊው፣ ጉዳዩ በዞን አሊያም በክልል ብቻ የሚፈታ እንዳልሆነም ጠቅሰው፤ የሰላም ባለቤት ህዝቡ ስለሆነ ሰላሙን የሚያደፈርሰውን ኃይል በትክክል አውቆ የመለየትና ያንን ኃይል ለህግ የሚቀርብበት ሥራ መስራት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ ‹‹በመንግሥት ላይ ብቻ ቅሬታ ማቅረብ ሳይሆን ኅብረተሰቡ ራሱ ሰላሙን ከማስጠበቅ አኳያ መስራት አለበት›› ሲሉ አመልክተዋል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤ ክስተቱ የብሄረሰብ ግጭት አይደለም፡፡ የራሱ የሆነ ተልዕኮ ባነገበ ኃይል የተካሄደ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት በእነዚህ አካላት ላይ እርምጃ በመውሰድ ፈር ማስያዝ ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም ጉዳት አድራሹ ኃይል በቂ ስልጠናና ትጥቅ ያለው የተደራጀ ነው፡፡
በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ውድቀት ያደረሰ ይኸው ኪራይ ሰብሳቢ ኃይል መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው የቤኒሻንጉል ጉምዝን ክልል ህዝብ የሚወክል አይደለም ብለዋል። ይሁንና እነሱን በማስመሰልና ሌላ ሸር በማሰብ ለተልዕኮው ማስፈጸሚያ የሚጠቀሙበት እንጂ የሁሉቱንም ክልሎች ህዝብ የሚወክል ድርጊት እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡
ስብሰባውን እያካሄደ ያለው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሚወስነውን ውሳኔ የሚቀበሉ መሆናቸውን አቶ ታከለ ጠቅሰው፤ የክልሉ መንግሥት ህዝቡን የሚመራ ከህዝቡ አብራክ የወጣ መንግሥት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ክልል መንግሥትነቱ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግሥት ጋር ተነጋግሮ ለመስራት የሄደባቸው ርቀቶች አሉ፡፡ ችግሩ ሲፈታ የሚጠቅመው የኦሮሞን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያንንም ጭምር መሆኑ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2011
በአስቴር ኤልያስ